Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የራያ ቢራ ፋብሪካ ግንባታ መጠናቀቅና ተምሳሌትነት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአክሲዮን ኩባንያዎች ደረጃ ከባንክና ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውጪ ያሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን በመቀላቀል በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ የገቡ አክሲዮን ኩባንያዎች እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ አክሲዮን በማሰባሰብና በፍጥነት ወደ ሥራ በመግባት ደግሞ እንደ ምሳሌ ከሚጠቀሱ ጥቂት አክሲዮን ኩባንያዎች ውስጥ የቢራ ፋብሪካ ለመገንባት የተቋቋመው ራያ ቢራ አክሲዮን ኩባንያ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል፡፡ በቀድሞ ኢታማዥር ሹም ሌተና ጀኔራል ፃድቃን ገብረተንሳይና የተለያዩ ከፍተኛ የቢዝነስ ተቋማትን በመምራት የሚታወቁ ግለሰቦችን በቦርድ አባልነት በመያዝ የሚመራው ራያ ቢራ አክሲዮን ኩባንያ፣ ከሌሎች አክሲዮን ኩባንያዎች በተለየ በአጭር ጊዜ ግንባታውን ማጠናቀቅ የቻለ ሆኗል፡፡ ኩባንያው ለመገንባት ያቀደውን የቢራ ፋብሪካ በአንድ ዓመት ከሁለት ወር በማጠናቀቅ ወደ ሥራ መግባት መቻሉ በተለየ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ ከ2,241 በላይ ባለአክሲዮኖችን የያዘው ራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ከአዲስ አበባ በ667 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በታሪካዊቷ ማይጨው ከተማ ያስገነባው ይህ ፋብሪካ 710 ሺሕ ሔክቶ ሊትር የማምረት አቅም ሲኖረው፣ የካቲት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመርቆ የአገሪቱን የቢራ ገበያ ይቀላቀላል፡፡ የአክሲዮን ኩባንያው ከፍተኛ የአመራር አባላት አጽንኦት ሰጥተው እንደሚናገሩትም፣ ራያ ቢራ አክሲዮን ኩባንያዎች ከፍተኛ ሊባሉ የሚችሉ ኩባንያዎችን መፍጠር እንደሚቻሉ ለማሳየት ጭምር ጥሩ ምሳሌ ይሆናል፡፡ ፋብሪካው አጠቃላይ ግንባታውን በማጠናቀቅ ወደ ማምረት ሥራ የገባበት ጊዜ ሲታይና በተመሳሳይ ደረጃና የኢንቨስትመንት ወጪ ከተገነቡ ፋብሪካዎች የግንባታ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የራያ ቢራ ፋብሪካ በፍጥነት የተጠናቀቀ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ፈጣን ግንባታ ሒደት በተመለከተ የኩባንያውን የሥራ ኃላፊዎች ሲገልጹ፣ አክሲዮን ኩባንያው ከምሥረታው ጀምሮ እስከ ፋብሪካው ግንባታ መጠናቀቂያ ድረስ ያለው ጉዞ በተያዘለት ዕቅድ መሠረት የተጓዘ በመሆኑ ውጤታማ ነው፡፡ የአክሲዮን ኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አትክልት ኪሮስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የዚህ ፋብሪካ ግንባታ ከተጠበቀውም ጊዜ ቀድሞ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በተለይ የአክሲዮን ኩባንያዎች ሚና ምን ድረስ ሊደርስ እንደሚችል ለማሳየት ጭምር ታስቦ የተካሄደው ሥራ ውጤት አስገኝቷልም ብለዋል፡፡ አክሲዮን ኩባንያዎች ከምሥረታቸው ጀምሮ በተገቢው መንገድ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ አነስተኛ ገንዘብ አሰባስበው ወደ ሥራ በመግባት ከፍተኛ ውጤት ሊያስመዘግቡ እንደሚችሉ ያመላከተናል ብለዋል፡፡ ይህም ልምድ አክሲዮን በማሰባሰብ ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን መግባት እንደሚቻል ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል ሲሉ አክለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር አክሲዮን ማኅበሩ ይዞት የተነሳውን ዓላማ ለማሳካት የቻለ ስለመሆኑ ያስረዱት አቶ አትክልት፣ ኩባንያቸው ለውጤት ሊበቃ የቻለው በዋናነት ከአዋጭነት ጥናቱ ጀምሮ በጥንቃቄ የተሠራ መሆኑ፣ በጀቱን በአግባቡ በመመደብ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረጉ፣ በማሽነሪ ተከላ የተሰማሩ ተቋማትና ሌሎች የሥራው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሠሩ ማድረግ በመቻሉ ነው ብለዋል፡፡ እያንዳንዱን የሥራ ክንውንም በአግባቡ እየተገበረ ስለመሆኑም የቅርብ ቁጥጥር መደረጉ ለግንባታው መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው አስታውሰዋል፡፡ የሥራ ሒደቱንም የአክሲዮን ማኅበሩ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች የተለያዩ የሥራ ዘርፎችን በመከፋፈል፣ የግንባታው ቦታ ድረስ በመምጣት ጭምር በመገምገምና የጠበቀ ቁጥጥር በማድረጋቸው የፋብሪካው ግንባታ በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እንዲጓዝ አስችሏል ተብሏል፡፡ በተለየ የአሠራር ሥልት የተካሄደውን ሥራ ሒደት በማቀላጠፍ ረገድ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም የነበራቸው ሚና ቀላል እንዳልነበር የገለጹት አቶ አትክልት፣ የፕሮጀክቱን መሬት ላይ ለማውረድ አስፈላጊ የነበሩ የመሬት፣ የውኃና የኤሌክትሪክ አቅርቦት በፍጥነት እንዲገኝ የመንግሥት እገዛና ሚና የጎላ ነበር ብለዋል፡፡ ለኢንቨስትመንት የሚሰጠውን ከቀረጥ ነፃ መብት በአግባቡ እንድናገኝና ይህም በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲያልቅ የተደረገው እገዛም፣ ለፋብሪካው ግንባታ በቶሎ መጠናቀቅ የራሱ ድርሻ ነበረው ብለዋል፡፡ አክሲዮን ኩባንያው በእርግጥ ለሌሎች ምሳሌ መሆን ይቻላል የሚለውን እምነት የሚያጠናክረው ሌላው እውነታ ደግሞ ሁሉም ባለአክሲዮኖች የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ በወቅቱ ገቢ ማድረግ በመቻላቸው ነው ተብሏል፡፡ ይህም ፕሮጀክቱ ያለ ችግር እንዲጓዝ አድርጓል ያሉ አቶ አትክልት፣ ምሳሌ ሊሆን የሚችል አክሲዮን ማኅበር መፍጠር አለብን የሚለው የአመራሩን ራዕይ በመቀበልና በመተግበር የአክሲዮን ኩባንያው ሠራተኞች ያበረከቱትም አስተዋጽኦ የሚፈለገው ግብ ላይ ለመድረስ ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የጠየቀው ራያ ቢራ ፋብሪካ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ የአገሪቱን የቢራ ገበያ ለመቀላቀልና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል በሚያስችለው ደረጃ መዘጋጀታቸውን የገለጹት የአክሲዮን ኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች በቀላሉ ገበያ ውስጥ እንገባለንም ይላሉ፡፡ ራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ከፍተኛውን የአክሲዮን ድርሻ እንደያዘ የሚታወቀው ቢጂአይ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ቢጂአይ ኢትዮጵያ በራያ ቢራ አክሲዮን ኩባንያ ውስጥ 42 በመቶ የሚሆነውን የባለቤትነት ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ በዱባይ በተለያዩ ኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩት ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር ደግሞ 25 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ አላቸው፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ለኢቨስትመንቱ ከባለአክሲዮኖች ከሰበሰበው ካፒታል በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ910 ሚሊዮን ብር ብድር አበድሮታል፡፡ የፋብሪካው ግንባታ ላይ የቻይናና የጀርመን ኩባንያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ የጠርሙስና የድራፍት ቢራ ምርቶቹን መጠን ለማሳደግ ተጨማሪ የማስፋፊያ ግንባታ ያካሂዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች