Sunday, June 4, 2023

‹‹ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ኮንቬንሽንን እንድታፀድቅ የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለ››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዶ/ር ታከለ ሰቦቃ ቡልቶ፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብትና የዓለም አቀፍ ሕግ ኤክስፐርት

ዶ/ር ታከለ ሰቦቃ ቡልቶ በአውስትራሊያ በሚገኘው ዌስተርን አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ መቀመጫቸውን ያደረጉ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግና የዓለም አቀፍ ሕግ ኤክስፐርት ናቸው፡፡ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ በምትገኘው አመያ ወረዳ የተወለዱት ዶ/ር ታከለ የመጀመርያና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው አመያ ከተከታተሉ በኋላ፣ የከፍተኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወሊሶና በአዲስ አበባ ተከታትለዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የኤልኤልቢ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ከዚሁ ዩኒቨርሰቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት ዶ/ር ታከለ፣ ከደቡብ አፍሪካው ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ በሰብዓዊ መብት ሌላ ሁለተኛ ዲግሪም ወስደዋል፡፡ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒኤችዲ) ደግሞ ከአውስትራሊያው ሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ዶ/ር ታከለ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሁለት ዓመታት በዳኝነት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአውስትራሊያ በሚገኘው ዌስተርን አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ታከለ በውኃ ሕግ፣ በአካባቢ ጥበቃ ሕግ፣ በሕገ መንግሥት ሕግና በውኃ መብት ላይ የሚያጠነጥኑ የምርምር ሥራዎቻቸውን ታዋቂና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ በቅርቡም ‘‘The Extraterritorial Application of the Human Right to Water In Africa’’ በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሐፍ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ታትሞ ለገበያ ቀርቧል፡፡ ሰለሞን ጎሹ በመጽሐፋቸው ስለዳሰሱት የውኃ መብትና ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ ዶ/ር ታከለን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የውኃ መብት ራሱን ችሎ ለመጠጥና ለንፅህና አገልግሎት የሚያስፈልግ የውኃ መጠን የማግኘት መብትን በማረጋገጥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ ዕውቅና አልተሰጠውም ነበር፡፡ አገሮች ለዚህ መብት በቅርቡ ዕውቅና በመስጠት ይዞታውን ያሻሽላሉ ለማለት በቂ ምክንያቶች አሉ?

ዶ/ር ታከለ፡- የውኃ መብት በአብዛኛዎቹ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች በግልጽ ዕውቅና የተሰጠው አይደለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ብዙና የተለያየ ነው፡፡ የትኛው ምክንያት የበለጠ ትክክል ስለመሆኑ አላውቅም፡፡ አንዳንዶች መብቱ ለሁሉም ሰዎች የተሟላ በመሆኑ ላይ ግምት በመወሰዱ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ ነገር ግን ይኼ ትክክለኛ መከራከሪያ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን ያረቀቁ ሰዎች በየዋህነት እንደዘለሉት አምናለሁ፡፡ እነዚህን ስምምነቶች የማርቀቅ ሒደት ወቅት የውኃ መብት ለውይይት እንዳልቀረበና ውድቅ እንዳልሆነ ግን አውቃለሁ፡፡ እነዚህ ስምምነቶች በግልጽ ዕውቅና አይስጡት እንጂ የውኃ መብት ሕጋዊ መብት ነው፡፡ በእነዚህ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች ውስጥ ያሉ አንቀጾች በውስጣቸው የውኃ መብትን ያቀፉ በመሆናቸው፣ ይህ መብት እንደ አዲስ የምንፈጥረው መብት አይደለም በሚል ነው የተከራከርኩት፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2002 የተመድ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ጉዳይ ኮሚቴ የውኃ መብት የዓለም አቀፉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች ቃል ኪዳን አንቀጽ 11 አካል እንደሆነ አትቷል፡፡ አንቀጹ ስለበቂና ደረጃውን የጠበቀ ኑሮ የሚደነግግ ሲሆን ይህም ምግብ፣ መጠለያና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጐቶችን እንደሚያካትት ይገልጻል፡፡ ደረጃውን ለጠበቀ ኑሮ ምግብና መጠለያ ማሳያ እንጂ ሙሉ ዝርዝር ሆነው ባለመቅረባቸው ሌሎች የቀሩ ዝርዝሮች መኖራቸውን ታሳቢ ማድረጉን ማየት ይቻላል፡፡ ውኃ ከእነዚህ ከቀሩ ዝርዝሮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ኮሚቴው የውኃ መብት በዚሁ ቃል ኪዳን የተደነገገው የአንቀጽ 12 አካል እንደሆነም አትቷል፡፡ አንቀጹ ስለጤና መብት የሚደነግግ ሲሆን፣ ለመጠጥና ለንፅህና አገልግሎት የሚውል በቂ የውኃ መጠን ሳይረጋገጥ የጤና መብትን ማሰብ አይቻልም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 በተመድ 160 አገሮች ተሰብስበው ለውኃ መብት ዕውቅና መስጠት ይገባል አይገባም በሚለው ላይ ተወያይተው ነበር፡፡ 122 አገሮች የውኃ መብት ራሱን የቻለ ልዩ መብት መሆኑን ዕውቅና ሲሰጡ 41 አገሮች ግን ድምፅ ተአቅቦ አድርገዋል፡፡ ተቃውሞ አላቀረቡም፡፡ እርግጠኛ አይደለንም ነው ያሉት፡፡

ሪፖርተር፡- የውኃ ሕግ በዓለም ላይ በአጨቃጫቂነታቸው ከሚታወቁ ሕጐች አንዱ ነው፡፡ በውኃ ሕግ ዋነኛዎቹ ተዋናዮች አገሮች ናቸው፡፡ በውኃ መብት ግን እነዚህ ተዋናዮች በዜጐች ይቀየራሉ፡፡ በተጨማሪም አገሮች ከራሳቸው ዜጐች በተጨማሪ ውኃውን የሚጋሩ ሌሎች አገሮች ዜጐችን መብት የማክበር ድንበር ዘለል ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡ የውኃ ሕግና የውኃ መብትን ማጣጣም ይቻላል?

ዶ/ር ታከለ፡- ይኼ ጥያቄ ወደ አጨቃጫቂው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ የሚወስደን ነው፡፡ በቅርብ ዓመታት ምሁራንና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ችሎቶች በአገሮች ድርጊትና የሚጠበቅባቸውን ባለመፈጸማቸው የተነሳ ለሚደርስ ድንበር ዘለል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ መሆን ይኖርባቸዋል ወይስ አይኖርባቸውም የሚለውን መጠየቅ ጀምረዋል፡፡ በሌላ በኩል ጥያቄአቸው አገሮች በራሳቸው ግዛት ቢፈጽሙት ሕገወጥ የሚሆን ተግባርን በሌላ አገር ላይ መፈጸም ይችላሉ ወይ? የሚል ነው፡፡ መልሱ ደግሞ አይችሉም ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንድ አገር ሲቀበልና ሲያፀድቅ ስምምነቶቹ ያቀፏቸውን መርሆዎችና መለኪያዎች የትም ቢሆን አከብራለሁ ብሎ ነው፡፡ እያንዳንዱ አገር ዋና ኃላፊነቱና ግዴታው የዜጋውን መብት ለማክበር፣ ለመጠበቅና ለማሟላት ነው፡፡ ድንበር ዘለል ኃላፊነት በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ነው፡፡ ለምሳሌ ሱዳን ለሕዝቦቿ የመጠጥ ውኃ ማቅረብ ባትችል ኢትዮጵያ በተወሰነ መልኩ ይኼን የማድረግ ግዴታ ይጣልባታል፡፡ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤትና የአፍሪካ ኮሚሽን አገሮች በራሳቸው ግዛት የመፈጸም ግዴታቸውን ድንበር ዘለውም ሊወጡት እንደሚገባ ወስነዋል፡፡ መርሆዎቹና መለኪያዎቹ የትም ቦታ ተፈጻሚ በመሆናቸው አገሮች ቢያንስ ቢያንስ መሠረታዊ መብቶችን ሊያከብሩ የሚገባቸው በሁሉም ቦታዎች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼን መብት የሚቃወሙ ወገኖች ውኃ እንደ ልብ የሚገኝ ሀብት ባለመሆኑ በውኃ አጠቃቀም ላይ ዜጐች ድምፃቸውን የሚያሰሙበት መድረክ መስጠት አስፈላጊ አይደለም በማለት ይከራከራሉ፡፡ ከዚህ ይልቅ አገሮች በውኃ ጉዳይ ላይ ከሌሎች አገሮች ጋር የመደራደር ብቸኛ ሥልጣናቸው መሠረታዊ የውኃ ጉዳዮችን ከመረዳት ይልቅ፣ ለግል ጥቅማቸው ጥያቄ በሚያነሱ ግለሰቦች ጣልቃ ገብነት ይረበሻል በማለት ይከራከራሉ፡፡ በዚህ ይስማማሉ?

ዶ/ር ታከለ፡- ውኃ የሉዓላዊነት ጥያቄ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ የውኃ ጉዳይ ይገዛ የነበረው በአገሮች የመንግሥት ተቋማት አማካይነት ነው፡፡ አገሮች ከሌሎች አገሮች ጋር በመነጋገር የሚወስኑት ጉዳይ ነው፡፡ ይኼ አሁንም የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ነገር ግን መልስ የሚያሻው አንድ ጥያቄ አለ፡፡ ለምሳሌ ለዓባይ ተፋሰስ 11 አገሮች በድርድር እያንዳንዱ አገር ከውኃው የሚደርሰው ድርሻ ላይ ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ ይህ ውሳኔ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ምን ማለት ነው ብለን ከሰብዓዊ መብት አኳያ እንጠይቃለን፡፡ እንደ ዜጋ የኢትዮጵያ መንግሥት ለእኔ ምን ያህል ይሰጠኛል ነው ጥያቄው፡፡ የኢትዮጵያ ድርሻ በግምት 30 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በዓመት ቢሆን፣ ይኼን ውኃ በፍትሐዊነት ለሁሉም ዜጐች የማከፋፈል ግዴታ መንግሥት የለበትም ወይ ነው ጥያቄው፡፡ ስለዚህ የውኃ መብት ሥልጣኑን ለዜጐች መስጠቱ ዜጐች መንግሥታቸው ዝቅተኛውን የመጠጥና ለንፅህና አገልግሎት የሚውል የውኃ መጠን እንዲያቀርብ ለማስገደድ ያስችላቸዋል፡፡ ይኼ የዘፈቀደ አሠራርን ለመዋጋት ያስችላል፡፡ ይኼን መብት ዕውቅና ካልሰጠን መንግሥታት የመጠጥና ለንፅህና አገልግሎት የሚውል የውኃ መጠን የሚያገኙ ዜጐቻቸውን ጉዳይ ግድ ላይሰጡት ይችላሉ፡፡ የውኃ መብት አገሮች በውኃ ጉዳይ ላይ የሚያደርጉት ዓለም አቀፍ ድርድር ላይ የግለሰቦችን የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ የሚያደርግም ነው፡፡ ይኼ በተመድ የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ኮሚቴም ድጋፍ የተቸረው ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የውኃ መብት ሲነሳ ከፍተኛ ተቃውሞ የሚያቀርቡ ወገኖች ዜጐች መንግሥታቸውን ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል እንዲያደርግ ማስገደዱ ላይ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን መንግሥታት ድንበር ዘለል ኃላፊነት መውሰዳቸውን አይቀበሉም፡፡ ለምሳሌ አንድ የግብፅ ገበሬ የኢትዮጵያን መንግሥት እንዲከስ መፍቀድ ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በእልህ አስጨራሽ ድርድር ያገኘውን ውጤት የሚሸረሽር በመሆኑ ተፈጻሚነቱ ላይም ጥርጣሬ አላቸው፡፡ እነዚህን ትችቶች እንዴት ያዩዋቸዋል?

ዶ/ር ታከለ፡- በእኔ ዕይታ የውኃ መብት ከሌሎች መብቶች የሚለየው ተፈጻሚነቱን ለማረጋገጥ ወሳኝ የሆነው ሀብት የተለያዩ ድንበሮችን የሚያካልል ከመሆኑ ላይ ነው፡፡ የአፍሪካን አኅጉር ብንወስድ ሁሉም አገሮች ማለት ይቻላል የውኃ ሀብታቸውን ከሌላ አገር ጋር ይጋሩታል፡፡ ስለዚህ አፈጻጸሙ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ሁለት አስቸጋሪ ጥያቄዎች አሉ፡፡ አንደኛው የውኃ መብትን ዕውቅና መስጠት አለብን ወይ? የሚል ነው፡፡ ለዚህ መልሴ አለብን የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም የሕይወትና የጤና ጉዳይ በዚህ መብት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ጥያቄ ለመብቱ ዕውቅና የምንሰጥ ከሆነ እንዴት እንፈጽመዋለን? የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም አፈጻጸሙ ከአንድ በላይ ግዛቶችን የሚያሳትፍ በመሆኑ ነው፡፡ የአንድ ሱዳናዊ የውኃ መብት ኢትዮጵያን ጨምሮ በላይኛው ተፋሰስ አገሮች ድርጊትና ማድረግ የሚጠበቅባቸውን በማድረጋቸው ላይ የተንጠላጠለ ነው፡፡ ስለዚህ አፈጻጸሙ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለመብቱ ዕውቅና ከተሰጠ በኋላ የውኃ ሀብቱ የሚገኘው በሌላ ግዛት በመሆኑ ተፈጻሚ የማይሆን ከሆነ እንደ መብት መቁጠሩ ነጥብ የለውም፡፡ ይኼንን ነው በመጽሐፌ ላይ ‹‹የመብት ግሽበት›› (Rights Inflation) ብዬ የጠራሁት፡፡ መብት ይሰጥሃል ነገር ግን ምንም ልትገዛበት አትችልም፡፡ በዓለም ላይ 122 አገሮች ድጋፍ የሰጡትን መብት ተፈጻሚ ለማደረግ መንገድ ሊበጅ ይገባል፡፡ ተፈጻሚነቱን ለማረጋገጥ አንዱ መንገድ ዓለም አቀፍ ትብብርን ማግኘት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የአገሮች ግዴታ ነው፡፡ ሌሎች አገሮች ዕርዳታ የሚሰጡት ባለቤት አገሮች ያላቸውን ሀብት በመጠቀም ተፈጻሚ ለማድረግ ጥረት ካደረጉ በኋላ ነው፡፡ አንድ አገር እንደ ግብርና ላሉ ሌሎች ጉዳዮች ውኃን ከመጠቀሙ በፊት ለዜጐች የመጠጥና ለንፅህና አገልገሎት የሚውል የውኃ መጠን ማቅረቡን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ይኼ ማለት ድንበር ዘለል ኃላፊነት ማለት ለምሳሌ ኢትዮጵያ ለግብፅ ውኃ የማቅረብ ግዴታ ሁሌም አለባት ማለት አይደለም፡፡ ግብፅ ለዜጐቿ ማድረግ ያለባትን ሁሉ ካደረገች በኋላ ነው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ግዴታ የሚነሳው፡፡ ዓለም አቀፍ የድንበር ዘለል ወንዞች ኮንቬንሽን ውኃን ለተለያዩ ጉዳዮች ለመጠቀም ግጭት ከተፈጠረ፣ ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው ለመጠጥና ለንፅህና አገልግሎት ለሚውል የውኃ መጠን እንደሆነ ይደነግጋል፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንዶች የውኃ መብት የላይኛውንና የታችኛውን ተፋሰስ አገሮች እኩል ተጠቃሚ አያደርግም በሚል ይተቻሉ፡፡ የውኃ መብት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የላይኛው ተፋሰስ አገሮችን እንደ ታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ተጠቃሚ ያደርጋል?

ዶ/ር ታከለ፡- ለዚህ ጥያቄ መልሴ አዎና አይደለም ነው፡፡ መልሱ በዕይታ ልዩነት የሚመነጭ ነው፡፡ ከዓባይ ተፋሰስ አንፃር ካየነው አገሮች በእኩልነት እየተጠቀሙ አይደለም፡፡ ግብፅ፣ ሱዳንና ኡጋንዳ ብቻ ናቸው በተሻለ በቂ የሚባል ውኃ ለዜጐቻቸው የሚያቀርቡት፡፡ ኢትዮጵያና ሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ግን ለዜጐቻቸው በቂ የመጠጥና ለንፅህና አገልግሎት የሚውል ውኃ በማቅረብ በኩል ዝቅተኛ ቦታ ላይ ነው የሚገኙት፡፡ የመጠጥ ውኃን በሚመለከት ከዓባይ ወንዝ የተሻለ መጠቀም ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብዛት በመጠቀም የተሻለ የውኃ መጠን ማግኘት ይቻላል፡፡ ይኼ ደግሞ ግብፅ ላይ ጫና ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ግብፅ ከኢትዮጵያ በተሻለ ለዜጐቿ ውኃ ስለምታቀርብ ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ ወደፊት ሊቀየር ይችላል፡፡ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ከላይኛው ተፋሰስ አገሮች የተሻለ የውኃ መጠን የሚጠይቁበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የውኃ ሕግና የውኃ መብት ዋና ተዋናዮች የተለያዩ ቢሆኑም አንዳቸው ለሌላው ድጋፍ የሚሰጡበትን ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል?

ዶ/ር ታከለ፡- አንዳቸው ለሌላው ድጋፍ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ አገሮች ስለውኃ ሲደራደሩ አንዱ መስፈርታቸው የሕዝብ ብዛት ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ኮንቬንሽን ይህንን ያስቀምጣል፡፡ በሌላ በኩል በድርድሩ የተገኘው ውኃ የሚከፋፈለው ለዜጐች ነው፡፡ ስለዚህ አንዳቸው ለሌላው መብት ግብዓት ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ውስጥ በታቀፉ መብቶች አማካይነት መንግሥት ውኃን በፍትሐዊነት ለዜጐቹ እንዲያከፋፍል ማድረግ ስለሚቻል፣ የውኃ መብትን በተናጠል ዕውቅና መስጠት አያስፈልግም በሚል የሚቀርበውን ክርክር እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ታከለ፡- ይኼንን ክርክር በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ ምሁራንና ሥራው ላይ ያሉ ባለሙያዎች የውኃ መብት በምግብ፣ በጤናና በሕይወት የመቆየት መብት ውስጥ ሊካተት እንደሚችል ይከራከራሉ፡፡ ነገር ግን በእነዚህ መብት ውስጥ የተካተተ መብት ጥገኛ መብት መሆኑ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ የውኃ መብትን የጤና መብት አካል ብናደርገው የውኃ መብት ሊነሳ የሚችለው በውኃ እጥረት የተነሳ የጤና እክል ከገጠመህ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የውኃ መብትን እንደ አንድ ራሱን የቻለ መብት ዕውቅና ከሰጠን መብቱን ለማክበር ዝቅተኛው ደረጃ ለእያንዳንዱ ዜጋ በቀን 20 ሊትር ውኃ አቅርቦት እንዲኖረው በማድረግ ነው የሚገለጸው፡፡ ስለዚህ አገሮች 19 ሊትር ውኃ ካቀረቡ የውኃ መብት ጥሰት በተናጠል ተፈጸመ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የጤና እክል እስኪገጥም መጠበቅ አይኖርብህም፡፡ የውኃ መብት እንደ ጥገኛ መብት የሚወሰድ ከሆነ ዝቅ ያለ ጥበቃ ነው የሚሰጠው፡፡

ሪፖርተር፡- የውኃ መብት በዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ኮንቬንሽን ዕውቅና ተሰጥቶታል?

ዶ/ር ታከለ፡- እ.ኤ.አ. በ1997 የተረቀቀው ዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ኮንቬንሽን ምናልባትም ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አስመልክቶ የተፈረመ ብቸኛ ስምምነት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከነሐሴ 17 ቀን 2014 ጀምሮ ተፈጻሚ ሆኗል፡፡ በስምምነቱ የማርቀቅ ሒደት የውኃ መብትን በተናጠል ዕውቅና ስለመስጠት ክርክር ተደርጓል፡፡ ብዙ አገሮች ለግለሰቦች መብት የሚሰጠውን የውኃ መብት ስለአገሮች መብትና ኃላፊነት በዋኛነት በሚደነግግ ስምምነት ውስጥ ማካተት ተገቢ አይደለም ብለው ተከራክረው ነበር፡፡ ነገር ግን አገሮች የዜጐቻቸውን ብቻ ሳይሆን ውኃውን በጋራ የሚጠቀሙ አገሮችን የውኃ መብት ለማክበር ተስማምተዋል፡፡ አገሮች የውኃ ክፍፍል ሲያደርጉ ለተፋሰሱ አገሮች ነዋሪዎች መሠረታዊ ፍላጐቶች ቅድሚያ መስጠትን ግንዛቤ ውስጥ እንዲከቱ ተስማምተዋል፡፡ ይኼ በኮንቬንሽኑ አንቀጽ 10(2) ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ አስቀድሞ በነበሩ የውኃ ክፍፍል ልማዶች የውኃ መብት ዕውቅና አልነበረውም፡፡ ስለዚህ አዲስ ነገር ነበር፡፡ አዲስ መሆኑ የፈጠረው አንዱ ችግር በርካታ አገሮች ስምምነቱን እስካሁን ካለመቀበላቸው የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ አንቀጽ እስካሁንም አስገዳጅ አልሆነም፡፡ ተፅዕኖውም አነስተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኮንቬንሽኑ አባል አይደለችም፡፡

ሪፖርተር፡- የመጽሐፍዎ ትኩረት የአፍሪካ አኅጉር ነው፡፡ በአፍሪካ ያሉት ተጨባጭ ሁኔታዎች በአኅጉሩ የውኃ መብትን ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ናቸው?

ዶ/ር ታከለ፡- የአፍሪካ አኅጉር የውኃ መብትን ለመተግበር እጅግ አስቸጋሪው ቦታ ነው፡፡ ምክንያቱም በአኅጉሩ በርካታ ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ስለሚገኙ ነው፡፡ ውኃውን ከሌላ አገር ጋር የማይጋራ የአፍሪካ አገር የለም፡፡ ይኼ የውኃ መብትን አፈጻጸም ያወሳስባል፡፡ በሌላ በኩል የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብት ቻርተር የውኃ መብትን አላካተተም፡፡ ከአሥር ዓመታት በፊት የውኃ መብት የቻርተሩ አካል መሆን አለበት ብዬ ወደ አፍሪካ ኮሚሽን ጉዳዩን አቅርቤ ነበር፡፡ ጉዳዩ አንጐላን የሚመለከት ነበር፡፡ የአንጐላ መንግሥት ከአሥር ሺሕ በላይ የውጭ ዜጐችን አስሮ ወደየመጡበት አገር እስኪሄዱ ድረስ በጫካ አስቀምጧቸው ነበር፡፡ በወቅቱ የውጭ ዜጐችን ከአንጐላ ማባረር የአገሪቱ ፖሊሲ ነበር፡፡ የታሰሩበት አካባቢ በጣም ሞቃታማ ነበር፡፡ ነገር ግን ለ500 ሰዎች ለመጠጥና ለንፅህና አገልገሎት የሚውል ሁለት ባልዲ ውኃ ብቻ ነበር የሚሰጣቸው፡፡ ይኼ በርካታ የሰብዓዊ መብቶችን የጣሰ ድርጊት ነበር፡፡ ለነፃና ለገለልተኛ የዳኝነት አካላት ጉዳያቸውን ማሰማት አልቻሉም፣ ክብራቸው ተዋርዷል፣ የመሥራት መብታቸው ተጥሷል፣ በአድልኦ ተይዘዋል፣ የውኃ መብታቸው ተጥሷል፡፡ በእነዚያ ታሳሪዎች ስም ለአፍሪካ ኮሚሽን ያቀረብነው አቤቱታ እነዚህን ጥሰቶች ሁሉ የያዘ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ሁሉንም አቤቱታ ተቀብሎ አንጐላን ጥፋተኛ ያለ ሲሆን፣ የውኃ መብትን ግን አልተቀበለም፡፡ ከነጭራሹ አስተያየት እንኳን አልሰጠበትም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው በጉዳዩ ላይ ምርምር ለማድረግ የተነሳሳሁት፡፡ ድንበር ተሻግሮ ተፈጻሚ የሚሆን የውኃ መብት በአፍሪካ ካልተረጋገጠ በቀር በአፍሪካ የውኃ መብትን ማሟላት አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ለተፈጻሚነቱ ተቀዳሚ ተነሳሽነት የወሰደችለት ሁሉን አቀፍ የዓባይ የስምምነት ማዕቀፍ (ሲኤፍኤ) ለውኃ መብት ዕውቅና ይሰጣል?

ዶ/ር ታከለ፡- በሲኤፍኤ የውኃ መብት የተዘነጋ ጉዳይ ነው፡፡ ስምምነቱ በአገሮች መካከል የተፈጸመ ነው፡፡ ለውይይት እንኳን አላቀረቡትም፡፡ ይኼ ማለት ግን አገሮቹ የውኃ መብትን በየግዛታቸው ለመፈጸም ግዴታ የለባቸውም ማለት አይደለም፡፡ ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ከደቡብ ሱዳን በስተቀር የአፍሪካ ቻርተር ፈራሚ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ኮሚሽን አሁን ቻርተሩን ተርጉሞ የውኃ መብት የቻርተሩ አካል እንዲሆን ወስኗል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ኮንጐ የውኃ መብትን ጥሳለች ብሎ ወስኗል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ሱዳን በውኃ ብክለት የውኃ መብትን ጥሳለች ሲል ወስኗል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በተመድ ደረጃ የውኃ መብትን ዕውቅና ለመስጠት በተደረገው ስብሰባ ድምፀ ተአቅቦ ነው ያደረገችው፡፡ ለውኃ መብት ዕውቅና የሚሰጠው የዓለም አቀፉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ኮንቬንሽንን አልተቀበለችም፡፡ ለውኃ መብት ዕውቅና የማይሰጠው ሲኤፍኤ ግን ዋነኛ ተዋናይ ናት፡፡ እነዚህ ፍሬ ነገሮች የኢትዮጵያን አቋም ለመገምገም በቂ ናቸው?

ዶ/ር ታከለ፡- የኢትዮጵያ አቋም ተለዋዋጭ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ የዜጐች ሳይሆን የመንግሥት ሚና ነው የሚል አቋምን በሁሉም መድረኮች አሳይታለች፡፡ በዓለም አቀፉ ኮንቬንሽንም ሆነ በሲኤፍኤው የኢትዮጵያ አቋም ግልጽ ነበር፡፡ በተመድ በተካሄደው ስብሰባ ኢትዮጵያ ድምፀ ተአቅቦ ማድረጓ ተቃውሞ አለማቅረቧን ነው የሚያሳየው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከዓባይ ወንዝ ፍትሐዊና ምክንያታዊ ድርሻዋን ለማግኘት ትግል ላይ ነች፡፡ ኢትዮጵያ የውኃ መብትን ብትቀበል ለታችኛው የተፋሰሱ አገሮች የተሻለ ውኃ መጠን እንድትሰጥ እንደምትገደድ እያሰበች ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ጥንቃቄን መርጣለች፡፡ አንዳንድ ሰዎች የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የብሔራዊ ፖሊሲ መርሆዎችና ዓላማዎች በሚዘረዝረው ክፍል ኢትዮጵያውያን ለመጠጥና ለንፅህና አገልግሎት የሚውል ውኃ የማግኘት መብታቸው የተረጋገጠ ነው ማለቱን በመጥቀስ ኢትዮጵያ የውኃ መብትን ተቀብላለች በማለት ይከራከራሉ፡፡ ነገር ግን ይኼ አንቀጽ በሰብዓዊ መብቶች ዝርዝር ውስጥ ስለሌለ የክርክሩን አሳማኝነት እጠራጠራለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ለውኃ መብት ዕውቅና መስጠት በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ዓይነት ውዝግብ ለመፍታት ምን ሚና ይጫወታል?

ዶ/ር ታከለ፡- በግብፅና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ሁኔታ ቀዝቃዛውን ጦርነት ይመስላል፡፡ ጦርነት የመቀስቀሱ ሁኔታ የማይመስል ቢሆንም ሰላምን ማረጋገጥ ደግሞ የማይቻል ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛት ትልቅ ነው፡፡ ነገር ግን የውኃ አቅርቦት አነስተኛ ነው፡፡ የውኃ መብት የፖለቲካ መብት ሳይሆን የሰብዓዊ መብት ነው፡፡ የሕይወትና የሰዎች ኑሮ ሁኔታ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ስምምነትም ሆነ በልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕጐች ገዥ የሆነው መርህ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም መርህ ነው፡፡ ይህን መርህ ተግባራዊ ስታደርግ ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በእኩልነት ይታያሉ፡፡ አገሮች በአንድ ላይ ተሰባስበው ለመጠጥና ለንፅህና አገልግሎት የሚውል ውኃን ማቅረብ ተቀዳሚ አጀንዳ ካደረጉ፣ በመካከላቸው እምነት ለማሳደር መነሻ ነጥብ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም አገሮች መቼ ውኃን ለግብርና፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለቱሪዝምና ለኢንዱስትሪ መጠቀም እንዳለባቸው እንዲደራደሩ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ የውኃ መብት የሰዎችን ሕይወት የሚመለከት ስለሆነ በድርድሩ ላይ ፖለቲካዊ ውጥረትን ያነሳል፡፡ በአገሮች መካከል የጋራ እምነት በማሳደር ስምምነት ለመፍጠር ያግዛል፡፡ ስለዚህ የውኃ መብት ድርድሩን በማሳለጥ ሰላማዊ የግጭት አፈታት በዓባይ ተፋሰስ ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር በዓባይ ተፋሰስ ድርድሮች በተለይም በሲኤፍኤውና በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር የነበራትንና ያላትን አቀራረብ እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር ታከለ፡- ከሕግ አንፃር ካየነው የኢትዮጵያ አቀራረብ ሁሌም በሕጉ ትክክለኛ ጐን ላይ ያረፈ ነበር፡፡ ግብፅ ከማንኛውም የተፋሰሱ አገሮች በላይ የዓባይ ውኃን ትጠቀማለች፡፡ ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ መብቷን ተጠቅማ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም ተግባራዊ እንዲደረግ ስትገፋ ነበር፡፡ አንድን ወንዝ ከሌላ አገር ጋር ለሚጋራ አገር ሲኤፍኤው ወይም ኮንቬንሽኑ ኖረም አልኖረም ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም ተፈጥሮአዊ መብቱ ነው፡፡ ይኼ ልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ ነው፡፡ ስለዚህ ፈቃደኛ ሆኑም አልሆኑም ይገደዱበታል፡፡ በዓባይ ዙሪያ ለሚደረግ ድርድር የኢትዮጵያ አቋም አስቀድሞ ደረጃውን የጠበቀ አልነበረም፡፡ ባለፉት 10 እና 15 ዓመታት ግን ኢትዮጵያ የመሪነት ሚና እየተጫወተች ነው፡፡ በተግባር የህዳሴ ግድብ የዚህ አንድ አካል ነው፡፡ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ መሠረታዊ ጉዳት እስካላስከተለች ድረስ የገዛ ሀብቶቿን የመጠቀም መብት አላት፡፡ መሠረታዊ ጉዳት በትክክል የሚደርሰውን ጉዳት የሚመለከት ሳይሆን፣ የደረሰው ጉዳት በሕግ የተከለከለው መሆን አለመሆኑን የሚመለከት ጉዳት ነው፡፡ ይህም ማለት አንድ አገር ከተፈቀደለት ፍትሐዊ አጠቃቀም ውጪ ሲሄድ ብቻ የሚከሰት ነው፡፡ አለበለዚያ ጉዳት መከሰቱ አይቀርም፡፡ እያንዳንዱ አገር በተወሰነ ሁኔታ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍልም ሲደረግ ጉዳት ሊከሰት እንደሚችል ሊቀበል ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ድርጊት በሕግ ከተቀመጠው ገደብ የዘለለ ሆኖ አያውቅም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል አንድም የታችኛው ተፋሰስ አገር በዓለም አቀፍ ችሎቶች ፊት ኢትዮጵያ የትኛውንም ሕግ ቢሆን ጥሳለች ብሎ ከሶ የማያውቀው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ኮንቬንሽን አልፈረመችም፡፡ ይህን ስምምነት ኢትዮጵያ እንድትፈርም የሚያደርጉ አሳማኝ ምክንያቶች እንዳሉ መጽሐፍዎ ላይ ተከራክረዋል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ግን የዚህ ስምምነት አካል መሆን የኢትዮጵያና የግብፅ ጉዳይ ወደ ዓለም አቀፍ ችሎቶች እንዲያመራ ያደርጋል፣ ግብፅ ደግሞ የተሻለ ተሰሚነት ስላላት ነገሮች ሊበላሹ ይችላሉ ብለው ይሰጋሉ፡፡ እነዚህን ሥጋቶች እንዴት ያዩዋቸዋል?

ዶ/ር ታከለ፡- ኢትዮጵያ ኮንቬንሽኑ እንድታፀድቅ የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለ፡፡ ስምምነቱ የተመጣጠነ ነው፡፡ ግብፅና ኢትዮጵያ ተመሳሳይ አቋም የያዙት የሚያጡትን ነገር በመቀመር ነው፡፡ ነገር ግን የሚያገኙትም ነገር ይኖራል፡፡ ግብፅ አሁን ያላትን ድርሻ መቀነስ አትፈልግም፡፡ ስምምነቱ ግን የኋላ ተጠቃሚነትንና የወደፊት ፍላጐቶችን ያጣጣመ ነው፡፡ ስለዚህ ስምምነቱ በተወሰነ መልኩ የኢትዮጵያን ይፋዊ አቋም የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ሙግትን በተመለከተ፣ ሙግት የትኛውንም የተፋሰሱን አገር ተጠቃሚ ያደርጋል ብዬ አላስብም፡፡ ሙግት የውድድር ስሜትን ነው የሚፈጥረው፡፡ ይኼ ደግሞ አሸናፊና ተሸናፊን ይፈጥራል፡፡ የጋራ መተማመን አይፈጥርም፡፡ ነገር ግን ድርድር ምርጡ አማራጭ ነው፡፡ ድርድር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትንና መከባበርን የሚያስፋፋ ነው፡፡ የዓባይ ጥያቄን ለመፍታት የጋራ ጥቅሞችን መለየት፣ በእኩልነት ማየት፣ ፍተሐዊነትና የጋራ ትብብር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም የዓባይ ተፋሰስ አገሮች በተለይም ኢትዮጵያና ግብፅ የሲኤፍኤውን ድርድር መቀጠል እንጂ ሙግት አይጠቅማቸውም፡፡ ከሙግት የሚገኘው ጥቅም ከድርድርና ከትብብር ከሚገኘው ጥቅም የተሻለ አይደለም፡፡ በዓባይ የተነሳ ሁሉም አሥራ አንዱም የተፋሰስ አገሮች እርስ በርስ የተጋቡ ስለሆነ ሙግት የትኛውንም አገር አይጠቅምም፡፡                      

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -