የገቢዎችና ጉምሩክ ወንጀል ምርመራ ቡድን የፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለድርሻ በሆኑት በአቶ ፀጉ ብርሃነ ገብረ እግዚአብሔር ላይ ያወጣው የፍርድ ቤት የመያዣና ከአገር እንዳይወጡ የሚያዘው ዕግድ፣ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ፡፡ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ጥር 13 ቀን 2007 ዓ.ም. የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የምሥራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የወንጀል ምርመራ አስተባባሪ ቡድን፣ በአቶ ፀጉ ብርሃነ ላይ ያወጣው የመያዣና የዕግድ ትዕዛዝ ውድቅ ያደረገው በከሳሽና ተከሳሽ መካከል የነበረው ግራና ቀኝ ክርክር ካዳመጠ በኋላ ሲሆን፣ ትዕዛዙ የወጣበትና ፀንቶ የሚቆይበት ምክንያት የለውም በማለት ነው፡፡ የባለሥልጣኑ የወንጀል ምርመራ ቡድን ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ያለደረሰኝ ሽያጭ አከናውኗል በማለት የባለሥልጣኑ ሠራተኞች የድርጅቱን የሒሳብ ሰነዶች በግዳጅ መውሰዳቸውን፣ በንብረቱ ላይ ዕገዳ በመጣልና በድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ባላቸው በአቶ ፀጉ ብርሃነ ላይም ከአገር እንዳይወጡና በተገኙበት እንዲያዙ የሚል ትዕዛዝ እንዲወጣ አድርጎ እንደነበር ክርክር ተደርጎ ነበር፡፡ በሌሉበት የዕግድ ትዕዛዝ የወጣባቸው አቶ ፀጉ ብርሃነ ከነበሩበት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የወጣባቸው የመያዣ ትዕዛዝ በምን የተነሳ እንደሆነ እንዲገለጽላቸው ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ ጠይቀዋል፡፡ የእስርና የዕግድ ትዕዛዙ እንዲወጣ ያደረጉ የባለሥልጣኑ የወንጀል ምርመራ ቡድን አስተባባሪ አቶ ተመስገን ጨዋቃ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ በፍርድ ቤት ቢጠየቁም በተደጋጋሚ ሊቀርቡ አልቻሉም ነበር፡፡ በመሆኑም አቶ ተመስገን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ባለማክበራቸው ለ24 ሰዓት ታስረው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ታስረው አድረው ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ቤት መቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የዕግድ የመያዣ ትዕዛዝ እንዲወጣ ያሉበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በፍርድ ቤት የብርበራ ትዕዛዝ የሒሳብ ሰነዶችን መውሰዳቸውን የተናገሩት አስተባባሪው፣ ለምርመራው መነሻ የሆናቸው አቶ ፀጉ ብርሃነ ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑበት ፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በተጭበረበረ መንገድ ተሽከርካሪ መሸጡንና ከገዢዎቹ 2.3 ሚሊዮን ብር ሲቀበል ደረሰኝ አለመቁረጡ መረጃ ስለደረሳቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ የተጠርጣሪ ጠበቆችም ያለደረሰኝ ተሽከርካሪ ተሽጧል የሚባለው ከእውነት የራቀ እንደሆነ አስረድተው ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም እያለ ባለድርሻ በሆኑት አቶ ፀጉ ብርሃነ ላይ ትኩረት ተደርጎ ዕግድ እንዲወጣባቸው መደረጉ ሕገወጥነት መሆኑን አስረድቷል፡፡ ግራና ቀኙን ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ጥር 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በሰጠው ውሳኔ በተከሳሽ ላይ የወጣውን የመያዣና የዕግድ ትዕዛዝ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ‹‹አመልካች የተጠረጠሩበት መነሻ ያለደረሰኝ ሽያጭ ተከናውኗል የሚል ሲሆን፣ ሽያጩ በተካሄደበት ጊዜ ሥራ አስኪያጅ አልነበሩም፡፡ በተጨማሪም ሽያጩን ያከናወኑ ሰውም አልነበሩም፡፡ እነዚህ ባልተሟሉበት ሁኔታ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ውስጥ ከፍተኛ ባለድርሻ ስለሆኑ ብቻ ተጠርጣሪ ሊሆኑና ሊያዙ የማይገባ ስለሆነ፤›› በማለት በአቶ ፀጉ ብርሃነ ላይ የወጣውን የመያዣና የዕግድ ትዕዛዝ ውድቅ አድርጎታል፡፡ እንዲሁም ‹‹ለመዝገቡ መከፈት ምክንያት የሆነው ያለደረሰኝ ሽያጭ ማከናወን እንጂ የታክስ ስወራ መሰል ወንጀሎችን መሠረት አድርጎ ስላልሆነ፣ ያንን የሚያሳይም የተሠራ የኦዲት ሪፖርትም የሌለ ስለሆነ ከዚህ ቀደም ኅዳር 10 ቀን 2007 የተሰጠው ትዕዛዝ ፀንቶ ሊቆይ የሚችልበት ምክንያት ስለሌለ፣ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን የመያዣ ትዕዛዝና አመልካች ከአገር እንዳይወጡ የሰጠውን የዕግድ ትዕዛዝ እንዲነሳ አዟል፤›› በማለት መዝገቡ እንዲዘጋ አድርጓል፡፡ ጉዳዩ የተነሳው በአቶ ፀጉ ብርሃነና በወ/ሮ ክንድሓፍቲ የባልና ሚስት ክርክር ሲሆን፣ ከሳሽ ወ/ሮ ክንድሓፍቲ ክርክሩ በሒደት ላይ ሳለ በአቶ ፀጉ ብርሃነ ስም የተመዘገቡ ንብረቶች እንዳይሸጡና እንዳይለወጡ ዕግድ እንዲጣልባቸው አመልክተው ነበር፡፡ ከሳሽ እንዲታገዱላቸው ያመለከቱዋቸው ንብረቶች በፀጉ ብርሃነ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም መሆናቸው ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ በድርጅቱ ስም የተመዘገቡትና በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የታገዱ ንብረቶች ሁኔታ ግራ ያጋባቸው የጉምሩክ አስተዳደርና ቁጥጥር የሥራ ሒደት መሪ፣ ለፍርድ ቤት በጻፉት ደብዳቤ ንብረቶቹ የተመዘገቡት በድርጅቱ ስም ሆኖ ሳለ ፍርድ ቤቱ ንብረቶቹ እንዲታገድ የሰጠው ትዕዛዝ ግራ የሚያጋባ በመሆኑ ፍትሐዊ ውሳኔ ማስተላለፍ እንዲቻል በድርጅቱ ስም የተመዘገቡ ንብረቶች ማገድ የሚቻል እንደሆነ እንዲያረጋግጥለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ድርጅቱ ንብረቶቹን ለማስለቀቅ ከፈለገ ሦስት ሚሊዮን ብር በሞዴል 85 አስይዞ እንዲያስለቅቅ፣ አለበለዚያ ግን ንብረቱ እንደታገደ እንዲቆይ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ገልባጭ ተሽከርካሪዎችንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን በማስመጣት የተሰማራው ድርጅቱ፣ በፍርድ ቤት ከተያዘው የባልና ሚስት ክርክር ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው በመግለጽ መከራከሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የንብረት ዕገዳውና እንዲሁም በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኞች የድርጅቱ የሒሳብ ሰነዶች በግዳጅ መወሰዳቸውን በተመለከተ አቤቱታ መቅረቡን፣ የድርጅቱ መሥራችና ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑት አቶ ፀጉ ብርሃነ በሌሉበት እንደነበርም መዘገባቡ አይዘነጋም፡፡