Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ትራኮን ትሬዲንግ በሽርክና ያቋቋመው ኩባንያ 30 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት አገኘ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አገር በቀል ኩባንያ የሆነው ትራኮን ትሬዲንግና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ታዋቂ ከሆነው አልጉርር ግሩፕ ጋር በጋራ ለሚገነቡት አሉሚኒየም ፋብሪካ 30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ፈቀደ፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች በ50 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአሉሙኒየም ፋብሪካ ለማቋቋም ኩባንያ መሥርተዋል፡፡ ኩባንያው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ኢንዱስትሪ ዞን 60 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጠው ከወራት በፊት ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል፡፡ በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራው የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የኩባንያውን ጥያቄ ከመረመረ በኋላ 30,000 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጠው ወስኗል፡፡ የትራኮን ትሬዲንግ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤሊያስ ኡመር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ካቢኔው ፕሮጀክቱ ያለውን ጠቀሜታ በመረዳቱ ቦታውን በፍጥነት ሰጥቷቸዋል፡፡ አስተዳደሩ ፕሮጀክቱ የሚፈልገውን መሬት በሙሉ ለጊዜው ባይፈቅድም በቀጣይነት ለማስፋፊያ ቀሪውን መሬት እንደሚፈቅድ ቃል መግባቱን አቶ ኤሊያስ ጠቁመዋል፡፡ ትራኮን ትሬዲንግ ከሚያካሂዳቸው የንግድ ሥራዎች በተጨማሪ የተለያዩ የአሉሙኒየም ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ይታወቃል፡፡ በዚህ ሥራ ሸሪኩ ከሆነው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬት ግዙፍ ኩባንያ አልጉርር ጋር ላለፉት አሥር ዓመታት ይኼንኑ ሥራ አከናውኗል፡፡ አልጉርር በአሉሙኒየም ምርቶች አምራችነቱ የሚታወቅ ኩባንያ ሲሆን፣ ከትራኮን ጋር በጋራ ኢትዮጵያ ውስጥ የአሉሙኒየም ፋብሪካ ለማቋቋም ተስምምቷል፡፡ የአልጉርር ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ማጅድ ሰይፍ ለዚሁ ሥራ በቅርቡ አዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዲሱ ኩባንያ ከ50 እስከ 60 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ያደርጋል፡፡ የሚገነባውም ፋብሪካ በዓመት ከ25,000 እስከ 30,000 ሜትሪክ ቶን የተለያዩ የአሉሙኒየም ውጤቶችን የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡ አቶ ኤሊያስ እንዳሉት፣ አዲሱ ፋብሪካ ወደ ማምረት ሲገባ ከውጭ አሉሙኒየም ማስገባትን ያስቀራል፡፡ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መቀመጫውን ያደረገው ግዙፉ አልጉርር በስምንት መስኮች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው በዋነኛነት ዱባይ የሚገኝ ግዙፍ የገበያ ማዕከል፣ በፓኬጅ፣ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ እንዲሁም በተለያዩ ኢንቨስትመንት መስኮች ላለፉት 40 ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ተገልጿል፡፡ ትራኮንም እንዲሁ በሰባት ዘርፎች የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በተለይ ቡና ወደ ውጭ በመላክ፣ በሪል ስቴት፣ በአልሙኒየም ሥራና የሕንፃ መሣሪያዎች አስመጥቶ ማከፋፈል፣ በኮንስትራክሽን ማሽኖች ኪራይና በደረቅ ጭነት ማመላለሻ ትራንስፖርት ሥራዎች ይታወቃል፡፡ ትራኮን በአሁኑ ወቅት ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚያስገባውን አቅጣጫ መያዙን አቶ ኤሊያስ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች