Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሐበሻ ሲሚንቶ 49 ሚሊዮን ዶላር ያወጣባቸው ማሽኖች ይገባሉ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አርባ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር የወጣባቸው የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ማሽነሪዎች በሦስት ቀናት ውስጥ ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን አቢ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ እነዚህን ዋና ዋና ማሽነሪዎች ከጂቡቲ ወደብ በማንሳት ፋብሪካው ወደሚገነባበት አካባቢ የማጓጓዙ ሥራ ሰኞ ይጀመራል፡፡ አስፈላጊ የጉምሩክ መሥፈርቶችን የማሟላት ሥራ መጠናቀቁንም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማሽኖቹ ተጨማሪ ክፍሎች በመጪው ሚያዝያ ጂቡቲ ወደብ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢንጂነር መስፍን ጠቁመው፣ አስፈላጊ የግንባታ መሣሪያዎች ግን ግንባታው የሚካሄድበት ሥፍራ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በሆለታ ከተማ አካባቢ በመገንባት ላይ ያለው የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ካፒታል 2.3 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ውስጥ 755 ሚሊዮን ብር በአክሲዮን የተሰበሰበ ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ ከባንክ በብድር የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሐበሻ ሲሚንቶ ከስድስት ዓመታት በላይ የባንክ ብድር ለማግኘት ሲጠባበቅ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በማግኘቱ ፒቲኤ ከተባለው የምሥራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ባንክ 50 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማግኘት ችሏል፡፡ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለሐበሻ ሲሚንቶ 70 በመቶ የፕሮጀክት ፋይናንስ ለማቅረብ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ ኩባንያው የሚጠበቅበትን 30 በመቶ መዋጮ በወቅቱ ሊያሟላ ባለመቻሉ ሳይፈጸም ቀርቷል፡፡ ሆኖም ሐበሻ ሲሚንቶ ከልማት ባንክ ሲጠባበቅ ከነበረው 70 በመቶ ብድር ውስጥ 30 ከመቶው ሲፈቀድለት፣ የተቀረውን ከራሱ በማዋጣትና ከውጭ ባንኮች በማሟላት የፕሮጀክቱን ወጪ ፋይናንስ እንዲያደርግ መገደዱ ይታወሳል፡፡ ሐበሻ ሲሚንቶ ከ16,500 በላይ ባለአክሲየኖችን በማካተት የተመሠረተ ሲሆን፣ የተመዘገበ ካፒታሉ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ሥራ ሲጀምር በዓመት 1.34 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ እንደሚያመርት ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች