Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኤርትራ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከ24 ዓመት በኋላ ከኢትዮጵያ ተለየች

የኤርትራ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከ24 ዓመት በኋላ ከኢትዮጵያ ተለየች

ቀን:

• በባህር ዳር አዲስ መንበረ ጵጵስና ተመሠረተ

የኤርትራ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከአዲስ አበባ ሜትሮፖላዊት መንበረ ሊቀ ጳጳስ ተለይታ ራሷን እንድታስተዳድር የሮም ፖፕ (ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት) ፍራንሲስ ወሰኑ፡፡ የአሥመራ ጳጳሱን ብፁዕ አቡነ መንግሥተአብ ተስፋማርያም ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሲሾሟቸው፣ አሥመራ ከተማም ወደ መንበረ ሊቀ ጳጳስ እንድታድግ ወስነዋል፡፡ ከመንበረ ቫቲካን ፕሬስ ጽሕፈት ቤት ጥር 11 ቀን 2007 ዓ.ም. የወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ሬዲዮ ቫቲካን እንደዘገበው፣ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የተገነጠሉት አራቱ የኤርትራ ኤጳርቆች/አኅጉረ ስብከት (Eparchies) ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የወሰኑት ፖፕ ፍራንሲስ፣ በኤርትራ መዲና አሥመራ ለሚቆመው ሜትሮፖሊታን ጳጳሱን አቡነ መንግሥተአብ ተስፋማርያምን የመጀመርያው ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሟቸዋል፡፡ የአሥመራ ሜትሮፖሊታን ሊቀ ጳጳሳት ከእንግዲህ የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሪ ይሆናል፡፡ በኤርትራ አሥመራ የተመሠረተው አዲሱ መንበረ ሊቀ ጳጳስ አራት ኤጳርቆች (አኅጉረ ስብከት) ሲኖራት እነሱም የአሥመራ፣ የሰገነይቲ፣ የከረንና የባረንቱ ናቸው፡፡ በሦስት ጳጳሳትና በአንድ ሊቀ ጳጳሳት የቆመው የኤርትራ ጳጳሳት ጉባዔ እስካሁን ድረስ ጳጳሳቱ በብፁዕ እምብፁዓን ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል ይመራ በነበረው የኢትዮጵያና የኤርትራ ጳጳሳት ጉባዔ ሥር ነበሩ፡፡ አዲሲቷ ሜትሮፖላዊትና ራሷን በራሷ የምታስተዳድረዋ የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 22ኛዋ የምሥራቃውያን ቤተ ክርስቲያን ስትሆን፣ ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ጋር ቀጥታዊ ግንኙነት እንደሚኖራት ታውቋል፡፡ ኤርትራ ከ24 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ብትገነጠልም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያኗ ግን እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሥር ቆይታለች፡፡ በ1983 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ የተገነጠለችውና ከሁለት ዓመት በኋላ (1985 ዓ.ም.) በውሳኔ ሕዝብ ነፃነቷን የተቀዳጀችው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ላለፉት አሠርታት በውጥረት ውስጥ እንዳለች ይታወቃል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን (1945 – 1953) የቆየችው ኤርትራ ፌዴሬሽኑ ፈርሶ መስከረም 1 ቀን 1953 ዓ.ም. በይፋ ብትዋሀድም፣ ወዲያውኑ የተጀመረው የኤርትራ ጦርነት ለ30 ዓመታት ዘልቆ ያበቃው በ1983 ዓ.ም. ሲሆን፣ ውጤቱም ለነፃነት አብቅቷታል፡፡ ሁለቱ አገሮች ዳግመኛ ከ1990 እስከ 1992 ዓ.ም. ጦርነት ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ኤርትራ ካላት 6.5 ሚሊዮን ሕዝቧ 155,000 ያህሉ በምሥራቅና በግእዝ ሥርዓት የሚመራው የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ ነው፡፡ የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተለየችው የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ 1.5 ሚሊዮን ምዕመናን ያሏትና በኮፕቲክ (ግብፅ) ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት መንበረ ፓትርያርኳን መሥርታ በራሷ ፓትርያርክ የምትመራ ሲሆን፣ በ1990 ዓ.ም. ከኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን መለየቷ ይታወሳል፡፡ በተያያዘ ዜና ፖፕ ፍራንሲስ፣ አዲስ ለተቋቋመው የባህር ዳር – ደሴ ኤጳርቃና (ሀገረ ስብከት) የአዲስ አበባ ሊቀ ጳጳሳት ረዳት ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን ብፁዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቴዎስን በጳጳስነት መሾማቸውን ከቫቲካን የተሠራጨው ዜና አመልክቷል፡፡ መንበሩ በባህር ዳር ከተማ የሆነው አዲሱ ኤጳርቃና፣ እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባ መንበረ ሊቀ ጳጳስ ሥር የነበሩትን የባህር ዳርና ደሴ ከተሞችና አካባቢዎች ሰበካዎችን የሚያጠቃልል መሆኑ ታውቋል፡፡ አዲሱ የባህር ዳር ደሴ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ ማቴዎስ በጉራጌ ዞን በ1952 ዓ.ም. የተወለዱና ማዕረገ ክህነትንም በ1980 ዓ.ም. የተቀበሉ ሲሆን፣ በሮም ቅዱስ ቶማስ አኲኖስ ዩኒቨርሲቲ በሥነ መንፈሳዊ ቲዮሎጊያ ተመርቀዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉት አቡነ ልሳነ ክርስቶስ፣ ጳጳስነትን እስካገኙበት ድረስ ያገለገሉባትን በባህር ዳር ለምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ረዳት ሊቀ ጳጳሳት ሹመትን የሰጧቸው የቀድሞው ፖፕ በነዲክቶስ 16ኛ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ፣ በአዲግራት፣ በሐዋሳ፣ በእምድብር፣ በሐረር፣ በጅማ ቦንጋ፣ በመቂ፣ በነቀምት፣ በጋምቤላና በሶዶ ሆሳዕና ስም የሚጠሩ የተለያዩ አኅጉረ ስብከት እንዳላት ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...