አዲስ አበባ ከተማ ለአደጋ ያላትን ተጋላጭነት የሚያጠና ኮሚቴ ተዋቀረ፡፡ የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን በጥናቱ ውጤት ላይ ተመሥርቶ አዲስ አበባን ከአደጋ ለመታደግ ስትራቴጂ ቀርፆ ለመንግሥት እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡ ይህንን ጥናት የሚያካሂደው ቡድን ከቀይ መስቀል፣ ከአዲስ አበባና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከአሜሪካ ፎረስት ሰርቪስ ድርጅትና ከአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ድርጅት በተወጣጡ የድንገተኛ አደጋ ማኔጅመንት ባለሙያዎች ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር አለነ ገብሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጥናቱ የሚያተኩረው አዲስ አበባ ለአደጋ የተጋለጠችባቸው አደጋዎች ላይ ነው፡፡ በጥናቱ ውስጥ ትኩረት ከሚሰጣቸው መካከል የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የጎርፍ አደጋ፣ ወረርሽኝና የእሳት አደጋዎች ይገኙበታል፡፡ ኮማንደር አለነ ጥናቱ በዚህ የበጀት ዓመት ሰኔ ወር እንደሚጠናቀቅ፣ በጥናቱ ውጤት ላይ ተመሥርቶ ባለሥልጣኑ አደጋውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዕቅድ ይነድፋል ብለዋል፡፡ ባለሥልጣኑ የነደፈው ዕቅድ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ቀርቦ አቅጣጫ እንደሚሰጥበት ኮማንደሩ ጨምረው አብራርተዋል፡፡ ከዚህ መሠረታዊ ለውጥ ከሚያመጣው ጥናት በተጨማሪ የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ድርጅት ከተማውን ከአደጋ ለመታደግ ራሱን በሰው ኃይልና በቁሳቁስ እያደራጀ መሆኑ ታውቋል፡፡ የከተማው አስተዳደር ለባለሥልጣኑ ከፍተኛ በጀት በመመደብ አሥር እሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪዎች ግዥ ፈጽሞ በማጓጓዝ ላይ መሆኑን ሌሎች ተጨማሪ የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት ጨረታ መውጣቱን ኮማንደር አለነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟላ አገልግሎት መስጠት እንችላለን፤›› በማለት ኮማንደር አለነ ባለሥልጣኑ በከፍተኛ ለውጥ ውስጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በከተማው ውስጥ ያሉ የገበያ ሥፍራዎች፣ ሆቴሎች፣ የንግድ ሕንፃዎችና የመሳሰሉ ሥፍራዎች ምን ያህል ለአደጋ ተጋላጭ መሆናቸው በየጊዜው ጥናት እንደሚያካሂዱ ገልጸዋል፡፡ በጥናቱ ውጤት ላይ ተመሥርቶ ባለሥልጣኑ የእርምት ዕርምጃ እንዲወስድ ምክረ ሐሳብ ይሰጣል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣኑ የሚሰጠውን ምክረ ሐሳብ የማይቀበሉ አካላት እንዳሉ የሚናገሩት ኮማንደር አለነ፣ ‹‹ባለሥልጣኑ የሚያስገድድበት መንገድም አልነበረውም፤›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው የእሳት አደጋ መከላከያ መመርያ (ፋየር ኮድ) ባለሥልጣኑ የሚሰጠው ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ እንዲደረግ ማስገደድ እንደሚያስችል ኮማንደር አለነ አክለዋል፡፡