የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዚዳንቱና የሰሜን ቀጣና ኃላፊ አቶ ዘመነ ምህረት፣ ከጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በአስከፊ ሁኔታ በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታወቀ፡፡ ፓርቲው ይህን ያስታወቀው ባለፈው ዓርብ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡ ‹‹የመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት በአሁን ሰዓት አዘዞ በሚገኘው የጦር ካምፕ ገደል ውስጥ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ እየተሰቃዩና ከሰው ልጅ የማይጠበቅ ከፍተኛ ስቃይ ላይ መሆናቸውን በደረሰን ትክክለኛ መረጃ ለማረጋገጥ ችለናል፤›› በማለት መኢአድ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ የፓርቲው አባላት ላይ ከፍተኛ ወከባና እስራት እየተፈጸመ መሆኑን ጠቅሶ፣ ይህ ጉዳይ የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ሰላማዊ ትግል ክፉኛ የሚጎዳ በመሆኑ የፓርቲው አመራሮች እንዲፈቱ በጥብቅ አሳስቧል፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ፓርቲው ስለገባበት ውዝግብም በመግለጫው የተነሳ ሌላኛው ጉዳይ ሲሆን፣ ‹‹ቦርዱ በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ያልተገባ አካሄዱን እንዲያስተካክል አጥብቀን እንጠይቃለን፤›› በማለት ጥያቄውን ለቦርዱም አቅርቧል፡፡ የቦርዱን ያልተገባ ያለውን አካሄድ ከመተቸቱም በተጨማሪ፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ አማካይነት በሚደረገው ጫና ከሰላማዊ ትግል ወደኋላ እንደማንል ቦርዱ ልብ ሊለው ይገባል፤›› ካለ በኋላ፣ ‹‹የቦርዱን ጫና ተቋቁመን መቀጠል እንችላለን፤›› በማለት ያለውን ዝግጁነት ገልጿል፡፡ ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በቦርዱ በተሰጠ ትዕዛዝ መሠረት ፓርቲው የውስጥ ችግሩን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመፍታት፣ ከፓርቲው በልዩነት ከወጡ አባላት ጋር አንድ ላይ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ ማዘዙ ይታወሳል፡፡ ይህን የቦርዱን ውሳኔ የተቃወመው መኢአድ፣ ‹‹ቦርዱ በመኢአድ ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት ካላቆመ እስከ መጨረሻው ድረስ አስፈላጊውን መስዋዕትነት በመክፈል፣ በሰላማዊ መንገድ የምንቋቋመው መሆናችንን ለመላው ሕዝብ እንገልጻለን፤›› በማለት የቦርዱን የተፅዕኖ ውሳኔ ለመወጣት ዝግጁነቱን ገልጿል፡፡