Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ችግር ውስጥ ያለው ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ዕጣ ፈንታውን የሚወስን ጥናት እየተካሄደበት ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ከንግድ ባንክ ጋር ለማዋሀድም ታስቧል

በ1968 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ለማዋሀድ ወይም በባንኩ የወደፊት ዕጣ ላይ ለመወሰን ጥናት መጀመሩ ተሰማ፡፡ ይህንን ለማድረግ የታሰበው የባንኩ አትራፊነት በአስደንጋጭ ሁኔታ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ በመሄዱና አሁን ያለበት ተልዕኮም ምን እንደሆነ ባለመታወቁ ነው ተብሏል፡፡ ሪፖርተር የባንኩን የ2007 ዓ.ም. የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያገኘ ሲሆን፣ ሪፖርቱም የባንኩ የስድስት ወራት ትርፍ ቀድሞ ከነበረበት በማሽቆልቆል 21.3 ሚሊዮን ብር ከታክስ በፊት መድረሱን ለመገንዘብ ችሏል፡፡ ባንኩ በተጠቀሱት የስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ 537.2 ሚሊዮን ብር ገቢ ማለትም ከዕቅዱ 105.1 በመቶ መሰብሰቡን ይገልጻል፡፡ ለዚህም የውጭ ምንዛሪ ተመን መለዋወጥ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ማድረጉን ሪፖርቱ ያስረዳና በስድስት ወራት ውስጥ የባንኩ አጠቃላይ ወጪ ከዕቅዱ በላይ 122.7 በመቶ በመውጣት 515.9 ሚሊዮን ብር መድረሱን ያስረዳል፡፡ ባንኩን ለገጠመው ከፍተኛ ወጪ ከውጭ ምንዛሪ ተመን መለዋወጥ ጋር የተያያዘ ኪሳራ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ የሒሳብ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ ባንኩ በተጠቀሱት ስድስት ወራት ውስጥ የብሔራዊ ባንክ 27 በመቶ የግዴታ ቦንድ ግዥን ጨምሮ 670.3 ሚሊዮን ብር ብድር መልቀቁን ቢገልጽም፣ በዕቅድ ከያዘው 1.43 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር 52.7 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ካበደረው 1.1 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር በ419.7 ሚሊዮን ብር ወይም በ38.2 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡ በዚሁ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ባንኩ 302 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል፡፡ ይህ የብድር ማስመለስ እንቅስቃሴ በዕቅድ ተይዞ ከነበረው 455.3 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር በ152.5 ሚሊዮን ብር አሽቆልቁላል፡፡ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በ35.1 ሚሊዮን ብር ወይም በ13.1 በመቶ ያንሳል፡፡ በመሆኑም በዓመቱ በመጀመሪያው አጋማሽ የባንኩ የታመሙ ብድሮች ወይም መመለስ የማይችሉ ብድሮች መጠን በ13 ሚሊዮን ብር ወይም በ16.5 በመቶ መጨመሩን የሒሳብ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ የዚህ ምክንያቱ 15 ብድሮች በአጠቃላይ ዋጋቸው 23.5 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ሌሎች ሁለት ብድሮች አጠቃላይ መጠናቸው 4.6 ሚሊዮን ብር፣ በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሠረት ወደ ተበላሸ ብድርነት በመዞራቸው መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ በአጠቃላይ ባንኩ በስድስት ወራት ውስጥ በብሔራዊ ባንክ የሚጠበቅበትን የመጠባበቂያ ክምችትና ሌሎች ግዴታዎቹን ቀናንሶ 791.1 ሚሊዮን ብር ብቻ ካሽ እንዳለው በሪፖርቱ አስቀምጧል፡፡ ባስቀመጠውም የመፍትሔ ሐሳብ ይህንን ገንዘብ ለአጭር ጊዜ ብድሮች ማዋል እንደሚገባና ከፍተኛ የቁጠባ ማሰባሰብ ሥራ መሥራት እንዳለበት በመፍትሔነት ተቀምጧል፡፡ ባንኩ እ.ኤ.አ. በ2007/08 ያስመዘገበው ከታክስ በፊት ትርፍ 123 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ እየተሻሻለ መጥቶ እ.ኤ.አ. በ2011/12 የበጀት ዓመት 162.6 ሚሊዮን ብር ደርሶ ነበር፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት የባንኩ ያልተጣራ ትርፍ 148 ሚሊዮን ብር እንደነበረም መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ በባንኩ አጠቃላይ የሚዋዥቅ እንቅስቃሴ ዙሪያ የተጠየቁት የባንኩ የቢዝነስ ልማት የሥራ ሒደት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ታዬ፣ ባንኩን ተወዳዳሪና ውጤታማ ለማድረግ የሥራ ኃላፊዎች በጥረት ላይ ቢሆኑም መንግሥት ሊደግፋቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ባንኩ ተቀማጭ ሒሳብን ለማስፋት ቀድሞ የነበሩትን ቅርንጫፎች ከ35 ወደ 116 እንዲደርሱ መደረጉንና 1.2 ቢሊዮን ብር አካባቢ የነበረውን ተቀማጭ ሒሳብም ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ እንዲደርስ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን የባንኩ ዕጣ ፈንታ ግልጽ አይደለም፤›› የሚሉት የሥራ ኃላፊው፣ ባንኩ የመንግሥት ቢሆንም የተሰጠው ተልዕኮ እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ የባንኩ የቀድሞ አጠቃላይ ብድር የረጅም ጊዜ እንደነበር (ማለትም ከ80 እስከ 90 በመቶ ባንኩ የሰጣቸው ብድሮች የረጅም ጊዜ እንደሆነ)፣ ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ ከአንድ ባንክ አጠቃላይ ብድር ውስጥ 40 በመቶው የአጭር ጊዜ መሆን አለበት በማለቱ የማስተካከል ሥራ መሠራቱን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት የምንሠራው የንግድ ባንክን ዓይነት ሥራ ነው፤›› ብለው፣ ይሁን እንጂ መንግሥት የገንዘብና የፕሮጀክት እንቅስቃሴዎቹን ማለትም እንደ ኮንዶሚንየም ያሉ ፕሮጀክቶቹን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ማድረጉ ባንኩ እንደጐዳው ተናግረዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ለእኛም የተወሰኑ ነገሮችን ቆርሶ ቢሰጠን ጥሩ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን ባንኩ ወደ ግል እንዲዞር (ፕራይቬታይዝ እንዲደረግ) ለመንግሥት የውሳኔ ሐሳብ አቅርበው እንደነበር ከመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከባንኩ የትርፍ ማሽቆልቆል ጋር ተያይዞ ባንኩን ወደ ግል የማዞር ሐሳብ አሁንም ይኖር እንደሆነ የተጠየቁት የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገብሬ ኤርቃሎ፣ ሁለት በጥናት የተያዙ ሐሳቦች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ አንደኛው ባንኩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተመሳሳይ ሥራ እየሠራ በመሆኑ ሁለቱን ማዋሀድ የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው እንደ ቀድሞው በግንባታ ብድር አቅራቢ ባንክነቱ ልዩ የሆነ ተልዕኮ እንዲሰጠው ጥናት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ይህ ጥናት ሲጠናቀቅ ለውሳኔ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡ ለጊዜው ግን በመንግሥት በኩል የተያዘው አቅጣጫ እንደ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓይነት ተልዕኮ ቢኖረውም፣ ለሕዝብ በአማራጭነት ሊያገለግል ይችላል የሚል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ከዕቅዱ በታች ያሽቆለቆለ ትርፍ ያስመዘገበበትን ምክንያትም ኤጀንሲው አጣርቶ ይፋ እንደሚያደርግ፣ እንዲሁም የማስተካከያ መፍትሔ እንደሚያስቀምጥ አቶ ገብሬ ጠቁመዋል፡፡ (ብርሃኑ ፈቃደ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል)

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች