ለአሥራ አራት ዓመታት በሥራ ላይ ያለው የስደተኞች አያያዝ አዋጅ ሊሻሻል መሆኑ ታወቀ፡፡
የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አስተዳደር ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሱሌማን ዓሊ ማክሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከዚህ በፊት ዓለም አቀፉ የአፍሪካ ኅብረት የስደተኞች አያያዝ ሕጎችን መሠረት በማድረግ ወጥቶ የነበረው አዋጅ በቅርቡ ይሻሻላል፡፡
አዲስ በሚሻሻለው አዋጅ ስደተኞች ከዚህ በፊት ከነበራቸው መብት የተሻለ ዕድል የሚፈጥርላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ባሉ 27 የስደተኞች ጣቢያ ከዘጠኝ መቶ ሺሕ በላይ ስደተኞች እንዳሉ የጠቆሙት ኃላፊው፣ የሚሻሻለው አዋጅም ስደተኞች ከዚህ በፊት ያገኙት የነበረውን የትምህርት ዕድል የሚያሰፋ፣ በእርሻ እንዲሰማሩ የሚያደርግ፣ የተማሩት ደግሞ እንደ አገሬው ሕዝብ እኩል ተወዳድረው ሥራ የሚይዙበት፣ ከስደተኛ ካምፕ ወጥተው ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩበትን ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በፊት እነዚህ ዕድሎች እንደነበሩ የጠቆሙት አቶ ሱሌማን፣ ‹‹አዲሱ አዋጅ የበለጠ ነፃነትንና መብትን የሚሰጥ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ስደተኞች በዋናነት ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከኤርትራ፣ ከሱዳንና ከቻድ እንደሚመጡም ተናግረዋል፡፡ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በአገሪቱ ካሉ ስደተኞች ከፍተኛውን ቁጥር እንደያዙ ገልጸዋል፡፡ በሁለተኛና በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የሶማሊያና የኤርትራ ስደተኞች በቅደም ተከተል እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥራቸው እየጨመረ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በጥቅምት ወር ብቻ ሦስት ሺሕ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በኤርትራ ተቀስቅሶ በነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ 28 ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከተቃውሞው በኋላ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡