በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ የማሽን ግዥ ጨረታ ሊወጣ መሆኑ ታወቀ፡፡
የአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አየለ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የአንቦጭ አረም በዘላቂነት ለማስወገድ የማሽን ግዥ ዓለም አቀፍ ጨረታ ሊወጣ ነው፡፡
በክልሉ መንግሥት፣ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና በክልሉ ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የእንቦጭ አረም ከተከሰተ ወዲህ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ ሐይቁን መታደግ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከልና ጣናን ከተጋረጠበት ፈተና ለመታደግ፣ የክልሉ መንግሥት ከለጋሽ ድርጅቶችና ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ማሽኑን ለመግዛት ተወስኗል፡፡
የክልሉ መንግሥት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በጅቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ፣ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው የእንቦጭ መከላከያ ኮሚቴ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የክልሉ መንግሥት ጨረታው እንዲወጣ ለሚመለከተው የፌዴራል መንግሥት ማስተላለፉን ዋና ዳይሬክተሩ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
ነገር ግን ጨረታው መቼ ወጥቶ መቼ እንደሚከፈትና ዝርዝር የጨረታ ሒደቱ እንዴት እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም፡፡