Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ የመሠረተ ልማት ተቋማት በቅንጅት እንዲሠሩ የሚያደርግ ደንብ እየተዘጋጀ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ የመሠረተ ልማት ተቋማት በአዲስ አበባ ከተማ የሚያካሂዱትን የዘፈቀደ ግንባታ እንዲያስቆም ኃላፊነት የተሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሠረተ ልማት ቅንጅት፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የመሠረተ ልማት ተቋማቱን አቀናጅቶ የሚመራበትን ደንብ እያዘጋጀ መሆኑ ታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ሰኔ 2009 ዓ.ም. ተሰብስቦ የከተማውን የመሠረተ ልማት ቅንጅት፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በአዋጅ አቋቁሟል፡፡ ቀደም ሲል ይህ ተቋም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ይሰኝ የነበረ ሲሆን፣ ተጠሪነቱ ለከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ነበር፡፡ በአዲሱ አደረጃጀት ባለሥልጣኑ አዲስ ለተቋቋመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ 

ኮንስትራክሽን ቢሮ ይህንን ባለሥልጣን መስከረም መጨረሻ ላይ ከመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሙሉ ለሙሉ የተረከበ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ ከሚያካሂደው የዕለት ተዕለት ሥራው ጎን ለጎን የመሠረተ ልማት ተቋማቱን አቀናጅቶ ለመምራት በሚያስችል ደረጃ ራሱን እንደ አዲስ በማደራጀት ላይ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ አያሌው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ በከተማው የሚገኙ የመሠረተ ልማት ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሠሩ ለማድረግ በሚያስችል መዋቅር እየተደራጀ ነው፡፡

‹‹በፌዴራልም ሆነ በአዲስ አበባ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ተቋማት ተቀናጅተው የሚሠሩባቸውን ዝርዝር የአሠራር ሒደቶችን ለመደንገግ ደንብ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ደንብ ተቀናጅተው በማይሠሩት ላይ ቅጣት ጭምር የሚጥል በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ ያልተናበበ ግንባታ በከተማው አይካሄድም፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ዮናስ፣ ‹‹ደንቡ ለካቢኔ ቀርቦ ሲፀድቅ ተግባራዊ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

ባለሥልጣኑ የተቋቋመበት አዋጅ መግቢያ እንደሚያመለክተው፣ የከተማው አስተዳደር ያለውን የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ገጸ ምድራዊ የከተማ ፕላንም ሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ልማት ዕቅድ ለማሳካት እንዲቻል፣ በከተማው በሚንቀሳቀሱ የልማት ኃይሎች መካከል የሚታየውን ያለመቀናጀትና በልማቱ ላይ እየመጡ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት አስፈላጊ በመሆኑ ተቋሙን ማደራጀት አስፈልጓል፡፡

‹‹የመሠረተ ልማትና የሕንፃ ግንባታ የሚያከናወኑ አካላት የግንባታ ልማት የድርጊት መርሐ ግብሮችና አፈጻጸማቸውን የሚያቀናጅ፣ የግንባታ ፈቃድ የሚሰጥና ቁጥጥር የሚያደርግ፣ እንዲሁም ሕንፃው ከተገነባ በኋላ በትክክል መገንባቱን መርምሮ የሕንፃ መጠቀሚያ ፈቃድ የሚሰጥ ተቋም በድጋሚ ማደራጀት አስፈልጓል፤›› ሲል ባለሥልጣኑ የተቋቋመበት አዋጅ ይገልጻል፡፡

በአዲስ አበባ በርካታ ነዋሪዎች በየጊዜው ከሚያነሷቸውና ለዘመናት ሊፈቱ ካልቻሉ ችግሮች መካከል፣ በከተማው የሚገኙ የመሠረተ ልማት ተቋማት የሚያካሂዱት የዘፈቀደ ግንባታ ነው፡፡

በተለይም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የግልና የመንግሥት ሕንፃ ገንቢዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

አንዱ የመሠረተ ልማት ተቋም የገነባውን ሌላኛው እያፈረሰ ከተማዋ በማያቋርጥ ፍርስራሽ ውስጥ እንድትቆይ መደረጉ በርካታ ቅሬታ ሲያስነሳ ከመቆየቱም በላይ፣ ለሰው ሕይወትም አደገኛ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ግንባታዎች በቅንጅት ባለመካሄዳቸው መንግሥትን ላልተፈለገ ወጪ ሲዳርጉ ቆይተዋል፡፡

አቶ ዮናስ ይህ ጉዳይ በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ማግኘቱን ገልጸው፣ ይህንን ለማስቀረት ቢሮአቸውም ሆነ ባለሥልጣኑ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡ በፌዴራል ደረጃ በቅርቡ የፌዴራል መሠረተ ልማት ተቋማት ቅንጅት ኤጀንሲ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች