Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የነፍስ ወከፍ የጤፍ መዝሪያ ማሽኖች ግዥ የሙስና ጥያቄ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች አንዳንዶቹ ከአገር ወጥተዋል

ለሦስት ክልሎች የተከፋፈሉ 30 ሺሕ ያህል የነፍስ ወከፍ የጤፍ መዝሪያ ማሽኖችን በመግዛት ያከፋፈለው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ ከማሽኖቹ ግዥና ሥርጭት ጋር የተያያዘ የሙስና ጥያቄ ተነሳበት፡፡

ከቻይና ተገዝተው እንደገቡ የሚነገርላቸው እነዚህ ማሽኖች ለኦሮሚያ፣ ለአማራና ለደቡብ ክልሎች የተከፋፈሉት እያንዳንዳቸው አሥር ሺሕ ማሽኖችን እንዲወስዱና ለገበሬዎች እንዲያከፋፍሉ፣ ብሎም የመሣሪያዎቹን ዋጋ እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሦስቱም ክልሎች እያንዳንዳቸው አሥር ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዝብ ለማሽኖቹ እንዲከፍሉ ተጠይቀዋል፡፡ ይሁንና ማሽኑ እንዲገዛላቸው እንዳልጠየቁ የገለጹ ክልሎች ማሽኖቹ የተሰጧቸው በአደራ እንዲያስቀምጡ ተጠይቀው እንደነበር ገልጸው፣ ኋላ ላይ ግን ክፍያ ፈጽሙ የሚል ጥያቄ ከአሁኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከቀድሞው ግብርና ሚኒስቴር እንደደረሳቸው አስታውቀዋል፡፡

ከምንጮች በደረሰው ጥቆማ መሠረት ሪፖርተር ጉዳዩን ሲከታተል የኦሮሚያ ክልል በተለይ ይኸው የሚኒስቴሩ ጥያቄ ቀርቦለት ውድቅ ማድረጉን ለመረዳት ተችሏል፡፡ የክልሉን ግብርና ቢሮ ሪፖርተር አነጋግሮ ባገኘው መረጃ መሠረት፣ የነፍስ ወከፍ የጤፍ መዝሪያ ማሽኖቹ (Double Tube Planter for Fertilizer and Seed) ከሚኒስቴሩ ለክልሉ የተላኩት ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ነበር፡፡

በወቅቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ግብርና ቢሮ ኃላፊ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ዘለዓለም ጀማነህ በጻፉት ደብዳቤ መሠረት፣ ማሽኖቹ እንደማይሠሩ ተረጋግጧል፡፡ እንደ አቶ ዘለዓለም ደብዳቤ ከሆነ፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ባለሙያዎች ከክልሉ የዞንና የወረዳ ግብርና ባለሙያዎች ጋር በመሆን መሣሪያው መሥራት አለመሥራቱን ፈትሸው፣ ‹‹መሣሪያው ችግር ያለበትና ጥቅም ላይ መዋል እንደማይችል ገልጸዋል፤›› ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ባለሙያዎች አማካይነት በቀበሌ አርሶ አደር ማሠልጠኛ ማዕከል፣ እንዲሁም በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ተሞክሮ መሣሪያው እንደማይሠራ በተግባር መረጋገጡን፣ በአርሶ አደሮች ዘንድም ተቀባነት ማጣቱን አቶ ዘለዓለም ለሚኒስቴሩ በግልጽ ጽፈው ነበር፡፡

በመሆኑም የጤፍ መዝሪያ መሣሪያዎቹ የተገዙበት አግባብ፣ ‹‹በአርሶ አደሩ ጥያቄና ፍላጎት ላይ ያልተመረኮዘ፣ የመንግሥት የግዥ ሥርዓትና ደንብን ያልተከተለ ከመሆኑም በላይ፣ ያለምንም የውል ስምምነት ወደ  ኦሮሚያ ግብርና ቢሾፍቱ መጋዘን ተልከው ርክክብ ሳይደረግበት በሚኒስቴሩ ባለሙያዎች ፍላጎት …›› በመጋዘን እንደተከማቸ በደብዳቤው ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም የተከማቸው መሣሪያ የቦታ ጥበት ከማስከተል አልፎ፣ በሠራተኞች ላይ እንዳይናድ ሥጋት ከመፍጠሩ ባሻገር ለመሣሪያው ክልሉ ተጠያቂ እንደማይሆን በግልጽ አስታውቆ ነበር፡፡

ከዚህ ደብዳቤ በተጨማሪ የአሁኑ የኦሮሚያ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አሊይ ሁሴንም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ደብዳቤ ለሚኒስቴሩ ጽፈው ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. ክልሉ ለጻፈው ደብዳቤ ምላሽ እንዳልተሰጠው የጠቀሱት አቶ አሊይ፣ በአሥር ሺሕ የሚቆጠረው የጤፍ መዝሪያ መሣሪያ ባለመነሳቱ ምክንያት በቢሾፍቱ መጋዘን የሚሠሩ ሠራተኞች በመሣሪያው ናዳ ጉዳት ይደርስብናል የሚል ሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን አሳስበው ጽፈዋል፡፡ ‹‹ይህንን ችግራችን በመረዳት ከፍተኛ ቦታ ይዞ የተቀመጠውንና ለአሠራር ችግር የፈጠረብን ይህ መዝሪያ እንዲነሳልንና እንድትወስዱ ትብብራችሁን እንጠይቃለን፤›› በማለት ለሚኒስቴሩ አስታውቀዋል፡፡

የመሣሪዎቹን ግዥ በማስመልከት ለክልሉ የቀረበውን አሥር ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የክፍያ ጥያቄ በማገድ ትክክለኛ አካሄድ እንዳልሆነ በማስረዳት ጭምር የተቃወሙት፣ በኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ በምክትል ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የዋና ሥራ ሒደት መሪ የሆኑት አቶ ተረፈ ዲሳሳ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሒደቱን አብራርተዋል፡፡ ለክልሉ የቀረበው የመጀመሪያ ጥያቄ ንብረቱን በአደራ አስቀምጡ የሚል ቢሆንም ኋላ ላይ ክፍያ ፈጽሙ፣ ለገበሬው ሽጡ የሚል ጥያቄ ከሚኒስቴሩ መምጣቱ ትክክለኛ አካሄድ እንዳልነበር አስረድተዋል፡፡

የመሣሪያዎቹ የግዥ ሒደት ይበልጥ ለመረዳት አዳጋች ሆኗል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች ጉዳዩ ሙስና እንደታየበት ይናገራሉ፡፡ በጨረታ የተከናወነ ግዥ እንዳልሆነና ለክልሎቹም በተገቢው ሁኔታ እንዳልተሠራጨ ከኦሮሚያ ክልል የቀረበው አስረጂ ነው፡፡ ስለጉዳዩ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ማብራሪያ እንዲሰጡበት በተደጋጋሚ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ጥያቄው ሲቀርብ በኮሙዩኒኬሽን በኩል አቅርቡ የሚሉ ምላሾች ሲሰጡት የከረመው ሪፖርተር፣ በኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ኃላፊው አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ በኩል ስለጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራም አጥጋቢ አልሆነም፡፡

ሪፖርተር የመሣሪዎቹ ግዥ ሙስና አለበት የሚል መረጃ እንዳለውና ይህንኑ በተቋሙ በኩል እንዲያብራሩ የተጠየቁት አቶ ዓለማየሁ፣ ግዥው እሳቸውና አብዛኞቹ አሁን ያሉት ኃላፊዎች ባልነበሩበት ወቅት የተፈጸመ እንደመሆኑ መጠን መረጃው እንደሌላቸው፣ ሆኖም የሚመለከታቸውን ባለሙያዎች ሪፖርተር እንዲያነጋግር እንደሚያደርጉ ቃል ቢገቡም ይህንን ለማድረግ አልቻሉም፡፡ በተደጋጋሚ ለቀረበው ጥያቄ ቀጠሮ ከመስጠት ባሻገር የሙስና ጉዳይ በሚኒስቴሩ መኖሩን ሪፖርተር ካረጋገጠ፣ ዘገባውን እንደሚደግፉና መሥራት ያለበትን ቢሠራ እንደማይቃወሙ በጽሑፍ መልዕክት ገልጸዋል፡፡

ይህም ሆኖ ሪፖርተር እስከ ቅርብ ጊዜ በነበረው መረጃ መሠረት፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የኦሮሚያ ክልል ላቀረበው አቤቱታም ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልሰጠ፣ የተከማቸው መሣሪያም አለመነሳቱን ከአቶ ተረፈ ማብራሪያ ለመረዳት ችሏል፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉት የሪፖርተር ምንጮች በመሣሪያው ግዥ ሒደት ወቅት ተሳትፎ ከነበራቸው ኃላፊዎች አንዳንዶቹ ከአገር መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች