Friday, March 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለአገር የሚያስፈልጋት የጋራ ኃላፊነት ነው!

ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ከምንም ነገር በላይ የሚያሳስባቸው የአገር ጉዳይ ነው፡፡ የአገር ህልውና የጥቂቶች ጉዳይ ሳይሆን የመላው ሕዝብ ነው፡፡ የጋራ ኃላፊነት የሚመነጨውም በእኩይ ድርጊቶች ሳቢያ የአገር ህልውና እንዳይናጋ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ደንታ የማይሰጣቸው ነውጠኞች ካገኙት ጋር እየተላተሙ አቧራ ሲያስነሱ፣ የአገራቸው ሰላምና ደኅንነት የሚያሳስባቸው ደግሞ በአንድነት በመቆም መከላከል ታሪካዊ ግዴታቸው ነው፡፡ ለልዩነት ሥፍራ የማይሰጡ፣ ተቃራኒ ሐሳብን ለማስተናገድ ቅንነት የሌላቸው፣ ከራስና ከቡድን ጥቅም በላይ አርቀው የማያስቡ፣ የሕዝባችንን መስተጋብር በመናድ የአንድነት ካስማውን ነቅለው ለመጣል የሚሯሯጡ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያንኳስሱና ጨዋነት የጎደላቸው ማኅበራዊ ግሰፃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ምንም እንኳን ነፃነት ማኅበራዊ ኃላፊነትን ያካተተ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፣ በአገርና በሕዝብ ላይ ራሳቸውን ፈተው የለቀቁ መረኖች ግን ይታገሱ ዘንድ የግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚባለው የጨዋነትና የአስተዋይነት የጋራ እሴት መከበር አለበት፡፡ ለዚህም አገራቸውን የሚወዱ ዜጎች የጋራ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ኢትዮጵያ የምትባለው ታሪካዊት አገር ለዘመናት ወረራ የቃጡባትን ባዕዳን አሳፍራ የመለሰችው፣ ከዳር እስከ ዳር ሕዝቧ በከፈለው ወደር የሌለው መስዋዕትነት ነው፡፡ ከአፍሪካውያን አልፋ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች አንፀባራቂ ተምሳሌት መሆን የቻለችው፣ መላው ሕዝቧ ለአገሩ በነበረው ጥልቅና የጋለ ፍቅር ነው፡፡ ከአገሩ በላይ ምንም ባለመኖሩም ውድ ሕይወቱን በተለያዩ ዓውደ ግንባሮች እየሰዋ የጠበቃት ታላቅ አገር አሁንም መጠበቅ ያለባት በመሰል አኩሪ ልጆቿ ነው፡፡ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህልና መሰል ልዩነቶች የማይበግሩት ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ ዘመናትን ተዋልዶና ተጋብቶ የተሸጋገረው ማኅበራዊ መስተጋብሩ ጠንካራ ስለነበረ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተፈራረቁ ገዥዎች ቀንበሩን ቢያከብዱበት እንኳን በአገሩ ጉዳይ ተደራድሮ አያውቅም፡፡ ይህ ለዚህ ትውልድ ትልቁ የጋራ ኃላፊነት ማሳያ ልምድ ነው፡፡ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያው  ቁም ነገር ያላቸው በርካታ ወገኖች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ጠቃሚና ወቅታዊ መልዕክቶችን እንደሚያስተላልፉ ዕሙን ቢሆንም፣ በዚያው ልክ ደግሞ የኢትዮጵያዊነትን የጋራ እሴቶች የሚደረምሱ ይታያሉ፡፡ ታላቁን የኢትዮጵያዊነት ጠንካራ ገመድ የሚገዘግዙና ኅብረ ብሔራዊ የአንድነት ስሜትን የሚያላሽቁ አሉ፡፡ ብሔርተኝነትን ከመጠን በላይ በማራገብ ወጣቱን ትውልድ ለጥፋት የሚያንደረድሩ፣ አስተዋዩን ሕዝብ የሚያደናግሩና ብሩህ ተስፋን የሚያጨልሙ ኃላፊነት የማይሰማቸው ድርጊቶች ይፈጽማሉ፡፡ ሕዝባችን በመከባበር፣ በመተሳሰብና ያለውን ተካፍሎ በመኖር አቻ የሌለው አርዓያነት ባሳየባት አገር ውስጥ ሕዝብን፣ ተቋማትንና ግለሰቦችን ሳይቀር የሚያንቋሽሹ በየጎራው ማቆጥቆጣቸው ምን ያህል ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች እየበዙ መምጣታቸውን ያመላክታል፡፡ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት አስተምህሮ ጋር የሚቃረኑና ባልታረሙ ቃላት የሚነዙ ውዥንብሮች የደካሞች መገለጫ ቢሆኑም፣ ዞሮ ዞሮ ለአገርም ለሕዝብም አይጠቅሙም፡፡ ይህ ትውልድ በነፃነት እያሰበ በነፃነት የሚሞግትበት ሰላማዊ ዓውድ እንዲኖር መታገል ሲገባ፣ የሐሰተኛ ወሬዎችና የአሉባልታ ሰለባ ማድረግ በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ለመግታት ሲባል የጋራ ኃላፊነት ሊኖር ይገባል፡፡

ወጣቱ ትውልድ በትምህርትና በሥነ ምግባር ተኮትኩቶ ማደጉ የሚጠቅመው ለአገር ነው፡፡ ትምህርት ማስተዋል ከጎደለው ከንቱ ነው፡፡ ወጣቱ ዕውቀት እንዲጨብጥ፣ አካባቢውንና ዓለምን በሚገባ እንዲገነዘብ ማድረግ የሚቻለው፣ መንግሥትም ሆነ ማኅበረሰቡ የጋራ ኃላፊነታቸውን በብቃት ሲወጡ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በርካታ ወጣቶች ለሱስና ለአልባሌ ድርጊቶች ተጋልጠውና ተስፋ ቢስ ሆነው የሚታዩት፣ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ስላልቻሉ ነው፡፡ ወጣቶች ተስፋ ሲቆርጡ ከምንም ነገር በላይ የሚታያቸው ጥፋት ነው፡፡ በሌላ በኩል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ተመርቀው የወጡ ወጣቶች፣ የሥራ ዕድል ሳይመቻችላቸው ሲቀርና የቤተሰብ ሸክም ሲሆኑ የበለጠ ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ የሚታያቸው አጥፊነት ብቻ ነው፡፡ በፖለቲካው መስክ ደግሞ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዳልተከበሩላቸው የሚሰማቸው ወጣቶችም ውስጣቸው በአመፃ ይሞላል፡፡ የአድሎአዊነትና የመገለል ስሜት ስለሚሰማቸው ምንም ከማድረግ አይመለሱም፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ባሉበት ጊዜ ኃላፊነት የሚሰማው አካል ያስፈልጋል፡፡ ዋነኛው መንግሥት ሲሆን፣ ቀጥሎ ደግሞ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ናቸው፡፡

የጋራ ኃላፊነት ጉዳይ ሲነሳ የአገር ሰላምና መረጋጋት ትልቁን ሥፍራ ይይዛል፡፡ አገር ሰላም የምትሆነው የመላው ሕዝብ ደኅንነት ሲረጋገጥ ነው፡፡ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ሙሉ ተሳታፊ ሲሆን ነው፡፡ ለአገሩ የሚፈለግበትን የሚያበረክትበት ዕድል ሲያገኝ ነው፡፡ የአገሩን ውሎና አዳር በሚገባ ሲያውቅ ነው፡፡ ግዴታውን እየተወጣ ያለ አንዳች አድልኦ በእኩልነት ሲተዳደርና የሕግ የበላይነት መስፈኑን ሲያረጋግጥ ነው፡፡ ራሳቸውን ከሕዝብ በላይ የሚያደርጉ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ከራሳቸውና ከቢጤዎቻቸው ጥቅም አንፃር ብቻ የሚያስቡ ከሆነ ግን ለአገር ጠንቅ ናቸው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለበት ምኅዋር ውስጥ እየተሽከረከሩ ከሕግ በላይ መሆን ጣጣው ለአገርና ለሕዝብ ነው የሚተርፈው፡፡ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋርም አይሄድም፡፡ በአንድ ወቅት በተገነባ ስምና ዝና ብቻ ተኮፍሶ መቀጠል እንደማይቻል ሁሉ፣ ከአዲስ አስተሳሰብና ዘመኑ ከሚያመጣው ለውጥ ጋር መናበብ የግድ ይላል፡፡  ከለውጥ በተቃራኒ ቆሞ ካገኙት ጋር ከመላተም በፊት፣ ለውጡ ለአገርና ለሕዝብ እንደሚጠቅም አድርጎ መግራት የብስለት ምልክት ነው፡፡ ለውጥን የግርግርና የሽኩቻ ማወራረጃ ለማድረግ መፍጨርጨርም ኃላፊነት የጎደለው ነው፡፡ የጋራ ኃላፊነት የሚያስፈልገው ለዚህ ጭምር ነው፡፡

በኢትዮጵያ ምድር አሁን ዋናው ተፈላጊ ጉዳይ ይህን የተከበረና ጨዋ ሕዝብ ይዞ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ ሥነ ልቦናው ባዕዳንን ሳይቀር ለማመን እስኪያስቸግር ድረስ በጣም ተቀራራቢ ነው፡፡ ሕዝቡ አኗኗሩ በጣም ተመሳሳይ ነው፡፡ እንኳን በብሔር ለመጋጨት ይቅርና ቋንቋ ሳይገድበው፣ ባህል እንቅፋት ሳይሆንበትና እምነት ሳይለያየው በዓይኑ እየተያየ መግባባት የሚችል ተምሳሌታዊ ሕዝብ ነው፡፡ ይህንን የተከበረ ሕዝብ ይዞ ድህነት ውስጥ መኖር ያሳፍራል፡፡ ይህንን አስተዋይ ሕዝብ ይዞ ልዩነትን እያጦዙ መወራረፍና በጥላቻ በተበከሉ አንደበቶች መሰዳደብ ያሳቅቃል፡፡ ይህንን ታጋሽና አርቆ አሳቢ ሕዝብ ይዞ ካብ ለካብ እየተያዩ ዛቻ ውስጥ መዘፈቅ ያሳምማል፡፡ በተለይ ተምሬአለሁ የሚለው የኅብረተሰብ ክፍል ለልዩነት ዕውቅና አለመስጠቱና የቂም በቀል ፖለቲካ ውስጥ ተነክሮ መነታረኩ የሥልጣኔ ሳይሆን የኋላቀርነት ምልክት ነው፡፡ ብሔርተኝነትን ብቻ እያቀነቀኑ ኅብረ ብሔራዊነትን ማንኳሰስ ጤነኝነት አይደለም፡፡ ከዚህ ሁሉ ይልቅ ከአጉል ብሽሽቅና ከድርቅና በመላቀቅ ሕዝብን ማክበር ይገባል፡፡ ሕዝብ የአገሪቱ የመጨረሻው ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ነውና፡፡ ለዚህም ነው አገር የሚያስፈልጋት የጋራ ኃላፊነት ነው የሚባለው!

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል አፍሪካ ጁስ ኩባንያ ላይ ባደረሱት ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ

ከአዲስ አበባ በ175 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአርሲ ዞን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው ሾሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(ዶ/ር) አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...

የዜጎች ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ ጥበቃ ያስፈልገዋል!

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው ዘግናኝና አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢገታም፣ በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የዜጎች ሰቆቃዎች በስፋት ይሰማሉ፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር...