Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም በውጭ ምንዛሪ እጥረት መሥራትም ሆነ ብድር መክፈል አልቻልኩም አለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገሪቱ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተባባሰ በመምጣቱ፣ ለበጀት ዓመቱ ያቀዳቸውን ሥራዎች ማከናወን አለመቻሉን፣ መክፈል የሚገባውን የውጭ ብድሮችን ለመክፈል መቸገሩን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዱዓለም አድማሴ (ዶ/ር) ሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፓርላማው የሳይንስ፣ ኮሙዩኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ  የሩብ ዓመት የዕቅድ ክንዋኔ ሪፖርት አቅርበው ነበር፡፡ በዕለቱም ለተቋሙ ኃላፊዎች ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ከቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች ውስጥ፣ የተቋሙ የካፒታል ወጪ አፈጻጸም በሩብ ዓመቱ ከታቀደው አንፃር 15 በመቶ ብቻ በማከናወኑ የአፈጻጸም ድክመቱን እንዲያስረዱ የሚለው አንዱ ነበር፡፡

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዋናውና ትልቁ የሚባለው ችግር ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ሥራዎችና በከፍተኛ ወጪ ከውጭ የቴክኖሎጂና የመሠረተ ልማት ዕቃዎችን ለመግዛት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡

‹‹የካፒታል ወጪያችንን አፈጻጸም በተመለከተ ዝቅተኛ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዎቹ ግዥዎቻችን በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ተይዘው ነው የተቀመጡት፡፡  ግዥዎቻችን የሚከናወኑት ከውጭ ገበያ ነው፡፡ እነዚህን ዕቃዎች ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ዕቃዎች ግዥዎች ባንክ ውስጥ ሠልፍ ላይ ነው ያሉት፤›› በማለት፣ የዕቃዎችን ዓይነት በመዘርዘር ሌተር ኦፍ ክሬዲት እየጠበቁ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡

እንደ ዩፒኤስ ኮምፒዩተርጄኔሬተር፣ ባትሪና የመሳሰሉት ዕቃዎች ግዥዎች ባንክ ውስጥ ተቀምጠው ሠልፍ እየጠበቁ ነው ብለው፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ በውጭ ምንዛሪ ምክንያት መንቀሳቀስ አልቻልንም፡፡ ከዚህ መረዳት እንደምንችለው በተግባር ግዥ አቁመናል፡፡ በንድፈ ሐሳብ ብቻ ነው ግዥ እያከናወንን የምንገኘው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ለበጀት ዓመቱ ግዥ ይፈጽምባቸዋል ተብለው ከታቀዱት በተጨማሪ፣ ቀደም ብለው ለመግዛት ታስበው የነበሩ ዕቃዎች ከሁለት ዓመታት በላይ ቆይተው እስካሁን ምንዛሪ እስኪለቀቅላቸው በመጠበቅ ላይ ያሉ ስለመኖራቸውም ገልጸዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ከአጠቃላይ አገራዊ ሁኔታ ጋር የተገናኘ በመሆኑ የተቋማቸው ችግር ብቻ አድርገው እንደማያዩት የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ችግሩ በአጭር ጊዜ የማይፈታና የሚቀጥል በመሆኑ፣ ‹‹ዕገዛ እንፈልጋለን፣ ብድራችንንም እየከፈልን አይደለም፤›› ሲሉ ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረዋል፡፡

‹‹እንደ አገር ችግሩ ካልተቀረፈ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ብድሮቻችን እየከፈልን አይደለንም፡፡ የራሳችንንም ሒሳብ እያንቀሳቀስን አይደለም፤› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በዚህ ሒደት የካፒታል ወጪያቸው በሚቀጥለውም ሩብ ዓመት በተመሳሳይ ዝቅተኛ ሊሆን እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡ እስካሁን ያከናወኑትም 15 በመቶ እንኳን የደረሰው ከአገር ውስጥ ገበያ በብር በተገዙ ዕቃዎች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች