Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማስቀጠል ከ700 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንቶች እንደሚያስፈልጉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አስታወቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይገታ ከ700 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንቶች በኤክስፖርት ተኮር ዘርፎች እንደሚያስፈልጉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ገለጹ፡፡

የባንኩ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዳስታወቁት፣ የተጠቀሰውን የገንዘብ መጠን ያህል አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በተለይ ኤክስፖርት ተኮር በሆኑ ዘርፎች ማከናወን ስላልተቻለ የኢኮኖሚው ዕድገት ሊገታ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ባንኩ በቅርቡ የብር የምንዛሪ አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ ያደረገውም፣ የሚፈለጉትን ኢንቨስትመንቶች ለማምጣት እንዲቻል የቀየሰው የገንዘብ ፖሊሲ ሥልት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የፊስካል ፖሊሲ መሣሪያዎችም በመንግሥት ተግባራዊ የሚደረጉ በመሆናቸው፣  በሁለቱ መሣሪያዎች ድምር በከፍተኛ ደረጃ የሰፋውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማነቃቃት ይገባል ብለዋል፡፡

ከሰባት ዓመት በፊት የአገሪቱ አጠቃላይ ምርት (GDP) 370 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደነበር ያስታወሱት የባንኩ ገዥ፣ በአሁኑ ወቅት 1.8 ትሪሊዮን ብር መድረሱን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማስቀጠልም የጂዲፒውን (GDP) ከ35 እስከ 40 በመቶ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች የግድ ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡

በተጠቀሰው መጠን ኢንቨስትመንቶችን ፋይናንስ ለማስደረግ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እንደሚጠይቅ የገለጹት የባንኩ ገዥ፣ ‹‹የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ካልተቻለ ኢኮኖሚው ይቆማል፤›› ብለዋል፡፡

የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የኤክስፖርት ንግድ ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ፣ ይህም በተደጋጋሚ ጊዜ በመንግሥት የሚገለጽ ቢሆንም በተግባር ግን ከኤክስፖርት እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ አገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ እየከተታት መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

‹‹ሌላው ይቅርና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ኤክስፖርቱ በየዓመቱ 36 በመቶ ማደግ እንዳለበትና በዕቅድ ዘመኑ ማገባደጃ በ2012 ዓ.ም. የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ 14 ቢሊዮን ዶላር መድረስ አለበት ብለን አስቀምጠናል፡፡ ነገር ግን ከዕቅድ ዘመኑ መጀመርያ 2007 ዓ.ም. አንስቶ ላለፉት ሦስት ዓመታት የታቀደውን ማሳካት አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ዕቅድ መሠረት ከግብርና ምርቶች ኤክስፖርት በዓመት ሰባት ቢሊዮን ብር፣ ከማኑፋክቸሪንግ ደግሞ አራት ቢሊዮን ብር፣ ቀሪውን ከማዕድን ዘርፍ ለማግኘት ቢታቀድም እንደ ዕቅዱ መሥራት አልተቻለም ብለዋል፡፡

ከዚህ ይልቅ ከውጭ በሐዋላ የሚላክ የውጭ ምንዛሪ፣ ብድር፣ ዕርዳታና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከዕቅዱ ጋር የተጣጣመ ገቢ በማስገኘታቸው ኢኮኖሚው ለሚጠይቀው የዶላር ፍላጎት ደጀን መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከውጭ ሐዋላ በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ 5.5 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡

በ2009 ዓ.ም. ግን የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተጋርጦበት መፈተኑን ገልጸው፣ ‹‹መንግሥት ‹ኤክስፖርትን ማሳደግ የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው› እያለ የሚገኘው ዝም ብሎ መፈክር አይደለም፣ በትክክል የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግብርናው የአገሪቱ መሠረታዊ የኤክስፖርት ዘርፍ በመሆኑ፣ መንግሥት የዚህን ዘርፍ ማነቆዎች በመፍታት የኤክስፖርት ግኝቱን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑንና ከፍተኛ ዘመቻ በኮንትሮባንድ ላይ እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ደግሞ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚሰማሩ እንዲያገኙትና መልሰው የውጭ ምንዛሪ በማስገባት፣ ለኢኮኖሚው መዋቅር ሽግግር መሠረት እንዲጣል ለማድረግ ተቆርጧል ብለዋል፡፡

የገንዘብ ፖሊሲን በመጠቀም የብር ምንዛሪ ተመን አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ የተደረገውም ለዚሁ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን የብር ምንዛሪ ተመን እንዲቀንስ መደረጉ ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት እንደማያመጣ የተናገሩት የባንኩ ገዥ፣ ኤክስፖርት የሚመራው ኢኮኖሚ ለመፍጠር በመንግሥት በኩል የተጀመረው ጥረት ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መንገድና ቁርጠኝነት መፈጸም እንደሚገባው፣ በዚህ ነጥብ ላይም በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ውይይት ተካሂዶ መግባባት የተደረሰበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ መንገድ ከታገዘ የብር ምንዛሪ ተመንን በመቀነስ ተግባራዊ የተደረገው የገንዘብ ፖሊሲ በሁለት በኩል እንደተሳለ ቢላ ሊያገለግል የሚችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ እሳቸው አባባል በአንድ በኩል በኤክስፖርት ተኮር የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚሰማሩ ተዋናዮችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በማጠናከር፣ በብር የተመን ለውጥ ምክንያት በሚያገኙት ትርፍ ላይ ትርጉም ያለው ዕድገት የሚፈጥር መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ከፍጆታ ይልቅ ቁጠባን በማበረታታትና ከውጭ በሐዋላ የሚላከውን መጠን እንዲጨምር፣ እንዲሁም ቱሪስቶች በአገር ውስጥ ቆይታቸው የበለጠ የውጭ ምንዛሪ እንዲያወጡ በማበረታታትና የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ለማድረግ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ ምርቶች እንዲቀንሱና የእነዚህ ምርቶች ምትክ የሆኑ የአገር ውስጥ ምርቶች ገበያ እንዲያገኙ ማድረግ (ኢምፖርት ሰብስቲቲዩሽን)፣ የአገር ውስጥ አምራቾችን የሚያጠናክር እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ የብር ምንዛሪ ተመን ለውጥ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ የምርቶች ዋጋ መናር ቢሆንም፣ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የተወሰነ በመሆኑ የዋጋ ንረት ጫና ሊፈጠር እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

የዋጋ ግሽበት የሚፈጠረው በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል አለመጣጣም ሲኖር እንደሆነ፣ በአቅርቦት በኩል በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ጫና የሚፈጥረው ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶች እጥረት እንደሆነ አክለዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም. ከፍተኛ የግብርና ምርት የሚገኝ በመሆኑና መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጥ የሆኑት ስኳር፣ ዘይትና ስንዴ የመሳሰሉትን መንግሥት ከውጭ እያስገባ ለማሠራጨት መወሰኑን፣ የ700 ሺሕ ቶን ስኳር ግዥ በአሁኑ ወቅት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ ይህ የሚቀጥል በመሆኑ የዋጋ ንረት ጫና ሊመጣ አይችልም፡፡ ነገር ግን የምንዛሪ ተመን ለውጥ በሚደረግበት ወቅት የገበያ መረበሽ የተለመደ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የፍላጎት ጫና 35 በመቶ አካባቢ የዋጋ ንረት ሊያመጣ እንደሚችል የገለጹት የባንኩ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ፣ በዚህ በኩል የዋጋ ንረት ሊመጣ የሚችለው ፍላጎቱን ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ሲመለስ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ፍላጎቱ የሚገለጸው ወጪ በማውጣት በመሆኑ ብሔራዊ ባንክ በዚህ ረገድ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚሠራጨው የገንዘብ መጠን ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ ዋነኛው መንግሥት ዘንድሮ የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን የሚያስፈልገውን ብር በቀጥታ ብድር ከብሔራዊ ባንክ እንዳያገኝ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከብሔራዊ ባንክ የሚገኝ ቀጥታ ብድር ማለት በሌላ አነጋገር ‹‹ብር ማተም›› መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን የሚቻልበት ሥሌት በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከውጭ ብድር የበጀት ጉድለቱን መሸፈን የዋጋ ግሽበት የሚያስከትል መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ የብር ምንዛሪ ተመን እንዲቀንስ ተወስኖ ተግባራዊ መደረግ በጀመረበት ወቅት ይህንን መፍቀድ የሚያስከትለውን የዋጋ ንረት እጥፍ ስለሚያደርገው፣ በዚህ መንገድ የበጀት ጉድለቱ እንደማይሸፈንና በተቻለ አቅም የበጀት ጉድለቱን ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው በመሰብሰብ ለመሸፈን ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ይህንን ዕውን ለማድረግ ተግባራዊ የሚደረገው የሚታወቅ መሣሪያ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም. ተግባራዊ መደረግ የሚጀምረው የሁለተኛ ገበያ የዕዳ ሰነድ ሽያጭ (Secondary Market) ሌላው አኮኖሚው የሚያመነጨውን ገንዘብ ሰብስቦ ለበጀት ጉድለት መሸፈኛ የሚውልበት ሥልት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የ2010 ዓ.ም. የመንግሥት አጠቃላይ በጀት 320.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የበጀት ገድለቱ 53 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ በ2009 ዓ.ም. በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ 18 ቢሊዮን ብር ከኢኮኖሚው የሰበሰበ ሲሆን፣ 27 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለመንግሥት ቀጥተኛ ብድር መስጠቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች