Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልብሔራዊ ቴአትርና ሥነ ጥበባት ኮሌጅ በጥምረት ለመሥራት ተስማሙ

ብሔራዊ ቴአትርና ሥነ ጥበባት ኮሌጅ በጥምረት ለመሥራት ተስማሙ

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ በጥምረት ለመሥራት የሚያስችላቸው የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡ ተቋማቱ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያሳወቁት ጥር 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ካምፓስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሆን፣ ስምምነቱ ጥናትና ምርምር ማካሄድ፣ የልምድ ልውውጥ እንዲሁም ሌሎች ዘርፎችን እንደሚያካትትና ቴአትር ቤቱንና ኮሌጁን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡ ስምምነቱን የተፈራረሙት የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ዲን አቶ ነብዩ ባዬና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሽመልስ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ነብዩ ገለጻ ተቋማቱ በተናጠል ያላቸው አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ በጋራ መሥራታቸው ለኪነ ጥበብ ዕድገት ሁነኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በቅርብ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ በሚል የተጣመሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ትምህርት ክፍል፣ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤትና ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በየዘርፋቸው ከቴአትር ቤቱ ጋር የነበራቸው ግንኙነት አንዳች መስመር ያለው ሳይሆን በጥቂት ሰዎች ትስስር ላይ የተመሠረተ እንደነበር በማስታወስ፣ ስምምነቱ ግንኙነታቸውን ተቋማዊ መስመር እንደሚያስይዝ ዲኑ አብራርተዋል፡፡ አቶ ነብዩ እንደ ምሳሌ የጠቀሱት የኮሌጁ ባለሙያዎችና ተማሪዎች በየቴአትር ቤቱ በመድረክ ቅብ፣ በሙዚቃ፣ በቴአትርና ተመሳሳይ ዘርፎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ነው፡፡ ሥራዎቹ ለቴአትር ቤቶች ግብዓት ሆነው ዓመታት እንዳስቆጠሩና ከስምምነቱ በኋላ በመደበኛ መንገድ እንደሚካሄዱ እንዳብራት ዲኑ አገላለጽ፣ የተቋሙ ዋና ዋና ዓላማዎችና የቴአትር ቤቱ ተልዕኮ ትስስር አላቸው፡፡ ከተቋሙ ዓላማዎች ቀዳሚው በየዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን ማስተማር በመሆኑ በመደበኛ ተቋሙ ከሚያስተምራቸው በተጨማሪ የቴአትር ቤቱ ባለሙያዎችም የሚጠቀሙበት መንገድ ይፈጠራል፡፡ ሌላው የተቋሙ ግብ ማኅበረሰባዊ ግልጋሎት መስጠት ሲሆን፣ ዓላማው ከቴአትር ቤቱ ጋር በቀጥታ የሚያገናኛቸው ነው፡፡ ከተቋሙ ዓላማዎች ውስጥ ለኪነ ጥበብ ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው የተገለጸው ጥናትና ምርምር ነው፡፡ አቶ ነብዬ እንደተናገሩት፣ ጥናቱ ለዘርፉ አስፈላጊ ግብዓቶች የሚገኙበትና ችግሮች የሚቀረፉበትን መንገድ አመላካች ይሆናል፡፡ የተቋማቱ ጥምረት የቴአትር ቤቱ አቅም የሚጐለብትበትና ኮሌጁም የሚጠናከርበት እንደሆነ በአጽንኦት የተናገሩት አቶ ነብዩ፣ ‹‹ስምምነቱ በተናጠል ይሠሩ የነበሩ ትልልቅ የአገሪቱ የጥበብ ተቋሞችን ለጋራ ዓላማ የሚያስተሳስር ነው፡፡ ላለፉት ዓመታት ሦስቱ ትምህርት ክፍሎች በርካታ ባለሙያዎች አፍርተዋል፡፡ ቴአትር ቤቱም እንደ ሰንደቅ ዓላማ ብሔራዊ ነው፡፡ በመሆኑም የሁለቱ ስምምነት አስፈላጊ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ስምምነቱ አንድም ተማሪዎች በቴአትር ቤቱ ልምምድ እንዲያደርጉ መንገድ የሚከፍትና በሌላ በኩል የቴአትር ቤቱን ሥራዎች በጥናትና ምርምር የሚደግፍ ይሆናል፡፡ እሳቸው ትኩረት የሰጡት ከቴአትር ቤቱ ተልዕኮዎች አንዱ የሆነውን ትውፊታዊ ተውኔት ነው፡፡ በተለይም በዩኒቨርሲቲው ቴአትር ትምህርት ክፍል የሚሠሩ ተውኔቶች የቴአትር ቤቱ ትውፊታዊ ትውን ጥበባት ክፍል በጥናትና ምርምር በሚያዘጋጃቸው ተውኔቶች ላይ ይታከላሉ ብለዋል፡፡ ቴአትር ቤቱ ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ ሥራዎች እንደሚያቀርብ በመግለጽ፣ በጥበባዊ ሥራዎቹ የሚነሱት ጉዳዮች መፍትሔ አመላካች እንዲሆኑ ጥናት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ስምምነቱ ተማሪዎች መድረክ የሚረከቡበትን መንገድ ያመቻቻል፡፡ ኮሌጁና ቴአትር ቤቱ ያላቸውን አቅም በጋራ መጠቀሙ አንዳች ለውጥ እንደሚያመጣ አያጠራጥርም፤›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ አብሮነቱ አዲስ አበባን የአፍሪካ የኪነ ጥበብ መዳረሻ ለማድረግ አጋዥ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ቅንጅቱ ለሌሎች ቴአትር ቤቶችም አርአያ እንደሆነ አክለዋል፡፡ በውይይት ከተነሱት ጉዳዮች አንዱ የስምምነቱ ተፈጻሚነት ነው፡፡ አቶ ነብዩና አቶ ተስፋዬ በመግባቢያ ሰነዱ ላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች ተፈጻሚነት የሚከታተል የቴክኒክ ኮሚቴ ከኮሌጁና ቴአትር ቤቱ በተውጣጡ ባለሙያዎች እንደሚዋቀር ገልጸው፣ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡ ስምምነቱ ቴአትር ቤቱ ተማሪዎችንና የተቋሙን ባለሙያዎች እንደ ግብዓት ከመጠቀሙ ባሻገር የሦስቱም ትምህርት ክፍሎች ተማሪዎች ሥራዎች መድረክ እንዲያገኙ ማስቻል እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ ሌላው ጥምረቱ ለተማሪዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ያለው ሚና ነው፡፡ በውይይቱ የተገኙት ተማሪዎች እንደተናገሩት፣ ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ እንደ አዲስ ወደ ቴአትር ቤት ከሚገቡ በለመዱት መድረክ ላይ ቢሠሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ የኮሌጁ ባለሙያዎች በቴአትር ቤት ያለውን ክፍተት እንደሚሞሉ የገለጹት የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተባባሪ ዲን ወ/ሮ የሹምነሽ ታዬ፣ በአሁን ወቅት በርካታ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ምሩቃን በቴአትር ቤቱ ተቀጥረው እንደሚሠሩና ስምምነቱ ነገሮችን ፈር እንደሚያስይዝ ተናግረዋል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ ከብሔራዊ ቴአትር ባለሙያዎች አንዱ አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ እንደተናገረው፣ ስምምነቱ ባለሙያዎች የሚማማሩበትና በልምድ የሚሠሩ ሥራዎች በትምህርት የሚደገፉበት ይሆናል፡፡ በጥምረት መሥራት ሙያዊ ደረጃቸው ከፍ ያለ ሥራዎች እንዲከውኑና የኪነ ጥበብ ሥራዎች መሬት ላይ ወርደው ኅብረተሰቡን እንዲያማክሉ እንደሚያደርግ የገለጹም ነበሩ፡፡ ሁለቱ አካላት የመግባቢያ ሰነድ በተፈራረሙበት ጊዜ፣ በሥነ ጥበባት ኮሌጅ ሥር ያሉት ሦስት የትምህርት ክፍሎች አመራሮች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...