Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

​​​​​​​‹‹ገቢ ቢኖረንም ባይኖረንም ተልዕኳችንን ማጣት አንፈልግም››

ወ/ሮ ሳባ ገብረመድኅን የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር

ወ/ሮ ሳባ ገብረመድኅን የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ በ1993 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አጠናቅቀዋል፡፡ በቅርቡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በጀንደርና ግሎባላይዜሽን አግኝተዋል፡፡ በዓቃቤ ሕግነትና በረዳት ዳኝነት ለዓመታት የሠሩ ሲሆን፣ አሁን የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የቅንጅቱን ረዥም ጉዞና አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ለዓመታት ከመሩት ወይዘሮ ሳባ ጋር ሻሂዳ ሁሴን  ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት አመሠራረት ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ሳባ፡- የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት የተቋቋመው በ2003 ሲሆን፣ እኔ የቀድሞዋ የማኅበሩ ዳይሬክተር በዋናነት አባላትን ማሰባሰብ፣ ፈንድ ማፈላለግ፣ መሥሪያ ቤቱን ማቋቋም፣ ጽሕፈት ቤት ለመክፈትና በሕግ አስመዝግበው ሥራ ማስጀመር ላይ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በአጠቃላይ ማኅበራትን በተመለከተ አዲስ ሕግ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ድርጅቱ እንዲዳብር አድርገዋል፡፡ ቅንጅቱ በወቅቱ 13 አባላትም ነበሩት፡፡ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣ የራስ አገዝ ሴቶች ማኅበር፣ ፋዌ ኢትዮጵያ፣ ላቭ ፎር ችልድረንና ሌሎችም እንደ አዲስ አበባ፣ የትግራይ ሴቶች ማኅበራት ከመሳሰሉት ጋር አብረን እንሠራ ነበር፡፡ በጊዜው ቅንጅቱ ሴቶችና ሕፃናት ላይ ብቻ የሚሠሩ ማኅበራት አባል የሚሆኑበት ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ሌሎችም ድርጅቶች ተጨመሩ፡፡ የሲቪል ማኅበራት ሕጉን ተከትሎ ለሁለት እስክንከፈል ድረስም 42 ደርሰን ነበር፡፡ አባላቶቻችን በአዲስ አበባ ብቻ ያሉ ሳይሆኑ በአፋር፣ በጋምቤላ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚሠሩ ሌሎች ማኅበራትንም አካትተን ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ አዲሱ ሕግ ሲወጣ ለሁለት ተከፈልን፡፡

ሪፖርተር፡- ቅንጅት ለሁለት ከመከፈሉ በፊት በሚሠሩ ሥራዎች ይገጥሙ የነበሩ ተግዳሮቶችም ምን ነበሩ?

ወ/ሮ ሳባ፡- የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት የተቋቋመው የሴቶችን እኩልነት ከፖለቲካ ከማኅበራዊ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንፃር ለማረጋገጥ ነው፡፡ አባል ድርጅቶቹ በቀጥታ ከሴቶች ጋር በመገናኘት ያሉባቸውን የጤና፣ የትምህርት አቅርቦት፣ የመብት ጉዳዮች በእኩልነት እንዲዳረሱ ጥብቅና በመቆምም ይሁን በተለያየ መልክ ይሠራ ነበር፡፡ የማኅበሩ ሚና የተለያዩ ማኅበራትን እንቅስቃሴ ማቀናጀትና የተሻለ የጋራ ድምፅ ማውጣት ነበር፡፡ ነገር ግን የአቅም ችግር ነበረበት፡፡ አዲስ ድርጅት ስለነበር ብዙ ለጋሽ ድርጅቶችን የማግኘት ችግሮች ነበሩ፡፡ ተቀባይነትን ማግኘት ይከብድ ነበር፡፡ ነገር ግን ባገኘነው ትንሽ ገንዘብ ብዙ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ የክትትል ጥናት በማድረግ፣ የጀንደር ቶፕ ፎረም አቋቁመን በየሁለት ወሩ ከመንግሥት ኃላፊዎች፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማትና ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር የሚደረጉ ውይይቶችን በቋሚነት ማዘጋጀት ጀመርን፡፡ በተለያዩ ክልሎችም የሴቶች ፎረሞች ይካሄዱ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ድርጅቱ ተቀባይነት እንዲያገኝ ረዳው፡፡ ከዚያ በኋላ የገንዘብ ፈሰስ አልተቸገርንም፡፡

ሪፖርተር፡- ተቀባይነታችሁ ምን ያህል ነበር?

ወ/ሮ ሳባ፡- በማኅበረሰቡ ቶሎ ተቀባይነት ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ እነማን ናችሁ? ምን ታደርጉልኛላችሁ? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሱ ነበር፡፡ በቀጥታ ግለሰቦችን የምንረዳ ባይሆንም ሊረዱ የሚችሉ ማኅበራትን እናጠናክር ነበር፡፡ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ላይ ሕዝቡ እኛን አያውቀንም ነበር፡፡ ከታወቅን በኋላ ደግሞ ምን ምን አመጣችሁ? ምን ለውጥ ፈጠራችሁ? የሚል ጥያቄ መነሳት ጀመረ፡፡ ያ ጥሩ ነበር፡፡ ተጠያቂነት መኖር አለበት ነገር ግን ግን የምንሠራበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ሲሆን የተፈለገውን ለውጥ በአጭር ጊዜ ለማምጣት ከባድ ነበር፡፡ በአመለካከት፣ የሕግ እንዲለወጥ እንዲሻሻል በሚሠሩ ሥራዎች፣ በአፋጣኝ ለውጥ ማምጣት ይከብዳል፡፡ ለውጡ የሚታየው በጊዜ ሒደት ነው፡፡ ስለዚህ ምን ለውጥ አመጣችሁ የሚለውን ለመመለስ ይከብዳል፡፡ በአንዳንድ የግንዛቤ ማስጨበጫና የግፊት ሥራዎች ላይ ግን የሕዝቡ ተሳትፎ አመርቂ ነበረ፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ለሁለት የተከፈለው እንዴት ነው?

ወ/ሮ ሳባ፡- ማኅበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶችን የሚያስተዳድረው አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ይዘት ማኅበሩን በአንድ ላይ ሊያቆየን የሚችል አልነበረም፡፡ እኛ  ከመቋቋማችን ጀምሮ የእኩልነት፣ የሴቶችን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብት ጥያቄ ይዘን ነበር የምንሠራው በዚህ ረዥም ተጉዘን አዋጁ ሲመጣ ልንቀየር አልቻልንም፡፡ እንደኛ የመሰሉ የጥላ ድርጅቶችን በተመለከተ የወጣው መመሪያ እንደሚለው፣ ሁለት ዓይነት ገፅታ ያላቸው ማኅበራት በአንድ ማኅበር ስር መጠቃለል አይችሉም፡፡ 90 በመቶ ያህሉ የእኛ አባላት ደግሞ የውጭ ገንዘብ እየተቀበሉ በኢኮኖሚና በልማት ሥራዎች የሚሠሩ ሲሆኑ የቀሩት ደግሞ በመብት ላይ ለመሥራት የተመዘገቡ ናቸው፡፡ እነዚህን በአንድ አባልነት መያዝ አትችሉም ተባልን፡፡ ስለዚህ እንዳንበተን የነበረውን መዋቅር ሁለት ቦታ ከፈልነው፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያዊ ማኅበራትን የሚያቅፍ ሲሆን ሁለተኛው የኢትዮጵያ ነዋሪ ማኅበራትን እንዲያቅፍ አደረግን፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያዊ ማኅበር ሆኖ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር ስምንት አባል ማኅበራትን ይዞ ሲመዘገብ ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ማኅበራት ኅብረት በሚል የተቀሩትን 35 የሚሆኑ ማኅበራት አቅፎ ተመዘገበ፡፡ ሐሳቡም እንድንደጋገፍ ነበር፡፡ እኛ መብት ላይ እንሠራለን ገንዘብ አናገኝም፡፡ እነሱ ደግሞ የውጭ ድጎማ ያገኛሉ፡፡ ስለዚህ መመሪያው መጀመሪያ ሲመጣ ቢያስደነግጠንም በኋላ ላይ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ወሰድነው ነገር ግን ነገሮችን እንደታሰቡት አልሆኑም በወቅቱ ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እናገኛለን ብለን ብናምንም ገንዘብ ለማገኘት ከባድ ሆነ፡፡ ስለዚህም አቅማችን ስለማይፈቅድ ሌሎች ፕሮጀክቶቻችንን  አጠፍናቸው፡፡ ምክንያቱም የምናገኘው ገንዘብ የሚያሠራ አልነበረም፡፡ ያሉብንን አንዳንድ ችግሮች ለመቅረፍም መሬት ከመንግሥት በመጠየቅ የሴቶች ማዕከል ለማቋቋም ወሰንን ነገር ግን መሬቱን መንግሥት ተባብሮን ብናገኝም፡፡ ግንባታውን ለመጀመር እየተንከራተትን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- መሬት የጠየቃችሁት መቼ ነበር? ለማዕከሉ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ምን ያህል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል?

ወ/ሮ ሳባ፡- ኢትዮጵያዊ ማኅበር ሆነን ስንቋቋም ነበር ጥያቄውን ያቀረብነው ከሁለት ዓመት በኋላ ሠዓሊተምህረት አካባቢ 1600 ካሬ መሬት ተሰጠን፡፡ ግን ወደ ግንባታ አልገባንም፡፡ የግንባታ ፈቃድ ማውጣት ላይ ትልቅ ውጣ ውረድ ገጥሞን ነበር፡፡ ምክንያቱም እኛ መንግሥታዊ ተቋም ስላልሆንን ካርታ ሊሰጠን አይችልም ነበር፡፡ ስለዚህ ካርታ የተሰጠው በማኅበራዊ ጉዳይ ስም ነበር፡፡ ግንባታ ፈቃድ ለማውጣት ስንሄድ ደግሞ የግንባታ ፈቃድ ግንባታና ካርታ ለአንድ አካል ነው የሚሰጠው ስለዚህም ፈቃዱ የሚሰጣችሁ በውክልና ይሆናል ተባልን፡፡ በመሬት አስተዳደር ቢሮክራሲ እስካሁን ፈቃድ አግኝተን ወደ ሥራ መግባት አልቻልንም፡፡ ግንባታውን ብናካሂድ ቢያንስ ከቢሮ ኪራይ እንላቀቃለን፡፡ የተወሰኑትን በማከራየትም በሚገኘው ገቢ አባላቶቻችንን በገንዘብ እየደገፍን በሴቶች መብት ላይ የሚሠራውን ሥራ እናጠናክር ነበር፡፡ ለማዕከሉ ግንባታ ማስፈጸሚያ ገንዘብ ማሰባሰብም ጀምረን ነበር፡፡ ግን በጣም ከባድ ሆነ፡፡ የእራት ግብዣ አዘጋጅተናል ትኬት  ሸጠናል፡፡ ኤስኤምኤስ የቴሌ መልዕክትም ጀምረን ነበር ከዚያም ባለፈ የተለያዩ ጨረታዎችን በማዘጋጀት ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥረት አድርገናል፡፡ በተደጋጋሚ ገንዘብ ሊሰጡ ከሚችሉ ድርጅቶች ስንሄድ  ለዚህ ጉዳይ ገንዘብ የማውጣት ፍላጎት እንደሌላቸው ተረድተናል፡፡ እንደሚመስለኝ በአጭር ጊዜ የሚታይ ለውጥ ይፈለጋል፡፡ ነገር ግን በመብት ዙሪያ የሚሠራ ሥራ በፍጥነት ለውጥ አያሳይም፡፡ አንዲት ሴት ጥቃት ሲፈፀምባት ሕዝቡ ተሰባስቦ ቁጣውን ይገልጻል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ጥቃቶች ለማስቀረት በሚሠሩ ሥራዎች ተሳትፎ አያደርግም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በጎ ፈቃደኞችን በማግኘት ረገድ አበረታች ነገሮች ይታያሉ፡፡ ብዙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየመጡ በበጎ ፈቃድ ይረዱናል፡፡  ብዙ ሥራዎቻችንን የምንሠራው በበጎ ፈቃደኛ ተማሪዎች ነው፡፡ በእኛ ብቻ ቢሆን ባለን የድርጅት አቅም ውስንነት ድርጅቱ እስከመዘጋት ይደርስ ነበር፡፡ በዘላቂነት የሚታየኝ ነገር ኅብረተሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ በመሆን ያለውን ሀብት ማኅበራዊ ችግሮች ላይ የማዋል ባህሉ እንዲዳብር መሥራት አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የዛሬ አቅምና ሥራችሁ ከቀድሞ ጋር እንዴት ይነፃፀራል?

ወ/ሮ ሳባ፡- በጣም ከባድ ንፅፅር ነው፡፡ ዛሬ ድርጅቱ እንደሌለ ሁሉ ይቆጠራል፡፡ ድሮ የነበረን በጀት 90 በመቶ ነበር አሁን ግን አሥር በመቶ ብቻ ነው፡፡ ቢሆንም ገቢ ቢኖረንም ባይኖረንም ተልዕኳችንን ማጣት አንፈልግም፡፡ በአንድና በሁለት ሠራተኞችም ቢሆን እየሠራ ድርጅቱ መኖር መቀጠል አለበት፡፡ ዛሬ የሽግግር ጊዜ ሊሆን ይችላል፡፡ ኅብረተሰቡ እነዚህን ማኅበራዊ ችግሮች በደንብ ካጤነ የተሻለ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ ማኅበራትም ግዴታ የውጭ ፈንድ ሳይጠብቁ በራሳቸው የሚቆሙበት ዕድል ይኖራል፡፡ በተለይ አሁን ወጣቶቹ ላይ የምናየው ተነሳሽነት ተስፋ ሰጪ  ነው፡፡ በራሳቸው ብዙ ሥራ ሠርተው የእኛን ግዴታ ሁሉ የሚያቃልሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አሁን ግን ነገን ተስፋ አድርገን ነው ያለነው፡፡ ሁኔታው በጣም አዳጋች ነው ግን ባይመችም ቢመችም ድርጅቱ መኖር አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ለወደፊቱ መንግሥትም እነኚህን  ችግሮች እያየ አበረታች መንገዶችን ይፈጠራል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ኅብረተሰቡም የበለጠ ግንዛቤ ኖሮት ድጋፍ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ፡፡ እስከዚያ ግን ማኅበሩ የግድ መኖር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ለመሥራት አቅዳችሁ ነበር? ያሰባችሁትን ያህል ሠርታችኋል?

ወ/ሮ ሳባ፡- በሴቶች ጥቃት ላይ ብዙ ሥራዎች ለመሥራት አቅደን ነበር፡፡ ብዙ ሥራዎች ሠርተናል ግን የዛን ያህል ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ሥራዎች አልተሠሩም፡፡ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በተመለከተ ብዙ መሥራት አቅደን ነበር ግን ካለው የሰው ኃይል እጥረትና ሌሎች ችግሮች አንፃር አልቻልንም፡፡ ነገር ግን በፕሮጀክት ቀርፀን የሎካል ፈንድ አግኝተን የምንሠራበት የዓለም ባንክ ፈንድ አለ የማኅበራዊ ኃላፊነት ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የራሱ የሰው ኃይል ስላለው ብዙ ሠርተናል፡፡ አባል ድርጅቶች ናቸው ሥራውን የሚሠሩት አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ውጤቱ ጥሩ ነበር፡፡  በበጎ ፈቃደኛ ልንሠራቸው ያሰብናቸውን ብዙዎቹን ሥራዎች ግን መሥራት አልቻልንም፡፡ በቀጣይም ከዚህ በላይ መንቀሳቀስ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከሴቶች ጥቃት ጋር በተያያዘ ዛሬና ትናንት እንዴት ይነፃፀራሉ?

ወ/ሮ ሳባ፡- ይህንን ለመመለስ ራሱን የቻለ ጥናት ስላልተሠራ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጥቃት ደረጃ ከፍተኛ የመሆኑ ጉዳይ አሳሳቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በየፍርድ ቤቱ የሚቀርቡ የጥቃት ክሶች በየጊዜው እየጨመሩ ነው፡፡  ከምንሠራው የማስተማርና የሕግ ክትትል አንፃር መቀነስ ነበረበት፡፡ ቁጥሩ በዓመት ገደብ ሲታይ ብዙ ክሶች በዚህ ዓመት ቀርበዋል፡፡ ጥልቅ ጥናት ባይደረግም በአዲስ አበባና በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ ይህን ያመላክታል፡፡ ሌላው አሳሳቢ የሆነው በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙት አዳዲስ የወንጀል ዓይነቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ አሲድ መድፋት፣ ዓይን ማውጣት፣ ጥቃቶች ከቀድሞ በብዛት ይፈፀማሉ፡፡ የችግሮቹ አሳሳቢነት የእኛን ጣልቃ ገብነት መጨመር አለበት፡፡ የመንግሥት እንቅስቃሴና ሕግ አወጣጥ ከዚህ አንፃር መሆን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ከጥቃት ጋር በተያያዘ ቅጣቶች መክበድ አለባቸው የሚሉ አሉ?

ወ/ሮ ሳባ፡- ማኅበራዊ ችግሮችን የምንፈታው በአንድ አቅጣጫ ብቻ አይደለም፡፡ ለውጥ ከፍተኛ ቅጣት በመጣልና ሕግን በማስተማር ብቻ የሚመጣም አይደለም፡፡ ለዚያም ነው ሕግ አስተማሪም፣ ቀጪ ከልካይም ሚባለው፡፡ ደግሞም ማኅበራዊ ቀውስን በሕግ ብቻ የምንከላከለው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ኅብረተሰቡ ራሱ ወንጀል ያስነውራል ሊል ይገባል፡፡ ወንጀለኞችን የማባባልና ለእነሱ የመራራት ነገር አለ፡፡ ይህ የሚመጣው ለተጠቃችው ሴት ካለን አመለካከት አንፃር ነው፡፡  አንዲት ሴት ስትደፈር ወይም ሌላ ጥቃት ሲደርስባት ለምን እንዲህ ለብሳ ወጣች ትባልና ጥፋቱ ተመልሶ ተጠቂዋ ላይ ይወድቃል፡፡ ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ ስለደረሱ ጥቃቶች ብናነሳ በመጀመሪያ ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ይገባና ቀጥሎ ግን እንዲህ አድርጋው ነው የሚል ሰበብ መፍጠር ይጀመራል፡፡ ነገር ግን ሕጉ ከእነዚህ ተለዋዋጭ ወንጀሎች አንፃር ከክብደት ተደጋጋሚነት አንፃር ሊታይ ይገባዋል፡፡ ሕግ ሲወጣ እንዲያስፈራራም ጭምር ነው፡፡ ያለው ሕግ በበቂ ሁኔታ ያስፈራራል ወይ? ሁሉንም ዓይነት ድርጊት አካቶ ተገቢ ቅጣት ተቀምጧል ብንል አልተቀመጠም፡፡ በእርግጥ በዚህ ረገድ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉና የቤተሰብ ሕጉ መሻሻል ትልቅ አንድምታ አለው፡፡ የፆታ ጥቃትን በተመለከተ ራሱን የቻለ ሕግ መውጣት አለበት፡፡ ልክ ለልማት እንደምናወጣው በሴቶችና በሕፃናት ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች መርሀ ግብር ወጥቶ ሁሉም ሰው ሊወያይበት ይገባል፡፡ ኅብረተሰቡ ችግሩን የሚቀርፍና  ወንጀሉን የሚቀጣ ሕግ አለ ብሎ ካላመነ ችግሩ እንዳለ ይቆያል፡፡ ብዙ ሰዎች ቅጣቱን ተመልክተው ሕጉ መላላቱን ይናገራሉ፡፡ ወንጀለኛው የቅጣቱን ማነስ እያሰበ ከወንጀል አይርቅም፡፡ ስለዚህ ሕጉን በዚህ መልኩ ማሻሻል አለብን፡፡ ኅብረተሰቡም ደግሞ አጀንዳው የእኔ ነው ብሎ መሥራት አለበት፡፡ ሁለቱ ሲተባበሩ ብቻ ነው ለችግሮቹ መፍትሔ የሚገኘው፡፡

ሪፖርተር፡- ከወራት በፊት የሴቶች ጥቃትን የሚመለከቱ ሕጎች እንደገና ይፈተሹ በሚል ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ደብዳቤ ለማስገባት በዝግጅት ላይ ነበራችሁ፡፡ ከምን ደርሳችኋል?

ወ/ሮ ሳባ፡- እንቅስቃሴውን የጀመርነው በቡድን የተደፈረችው የሃና ላላንጎን ጉዳይ ለማውገዝ ባዘጋጀነው መድረክ ሲሆን፣ ተጨማሪ ፊርማ አሰባስበን ጨርሰናል፡፡  ደብዳቤውን ለመላክ ከማኅበረሰቡ ከተውጣጡ ግለሰቦች ጋር ተወያይተን ቀጠሮ ጠይቀን ፈቃድ አግኝተን እየተጠባበቅ ነው፡፡ ደብዳቤ መላኩ ብቻ ለውጥ ስለማያመጣ ከፊርማው ባለፈ  ብዙ ሰዎች ባሉበት ውይይት እንዲካሄድ እንጠይቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከመንግሥት የምታገኙት ድጋፍ አለ?

ወ/ሮ ሳባ፡- መንግሥት የሰጠን መሬት ትልቅ ድጋፍ ነው፡፡ መሬት ማግኘታችን ከብዙ ችግሮች ነፃ ስለሚያወጣን ለምንሠራው ነገር ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ አንድ የሴቶች ማዕከል ቢኖር ብዙ ሴት ተማሪዎች፣ ሴት የመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎችም ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ገቢ ማስገኛነቱ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ ባለፈ ብዙ ድጋፍ አላገኘንም፡፡ በክልሎች ለምናደርገው እንቅስቃሴ አንዳንድ የክልል መንግሥታት እገዛ ያደርጉልናል፡፡ ማኅበራት በመብት መከበር ዙሪያ በሚሠሩት ሥራ ላይ የመንግሥት እገዛ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...

‹‹በአሁኑ ሰዓት እየፈተነን ያለው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው›› አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን፣ አይሲዳ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

አይሲዳ አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት በኤችአይቪ ሥርጭት ቁጥጥር ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ አዋቅሮ በተለይ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ...