Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ስለአፍሪካ 50 ዓመታት የሚመከርበት የመሪዎቹ ጉባዔ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሁለት ዓመታት በፊት የአፍሪካ ኅብረት ወይም የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ሃምሳኛ ዓመት ሲከበር፣ ለመጪዎቹ ሃምሳ ዓመታት የአኅጉሪቱ ጉዞ ምን ይምሰል የሚል ረቂቅ ዶሴ ተሰናድቶ ነበር፡፡ ይኸው ዶሴ ዓምና ለዓለም ሁሉ ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች በዚህ ሳምንት ማብቂያ በአዲስ አበባ በሚያካሄዱት 24ኛው መደበኛ ጉባዔ ወቅት በሁሉም አገሮች ዘንድ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አጀንዳ 2063 የሚል መጠሪያ ያለውና በመጪዎቹ 50 ዓመታት ውስጥ አፍሪካ እንድትደርስበት የተተለሙትን ሐሳቦች የያዘው ሰነድ ካካተታቸው ነጥቦች መካከል አፍሪካ በአሳታፊና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገቷ የተነሳ፣ ብልፅግናን የተላበሰች እንድትሆን ይመኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር የተሳሰረች፣ በፓን አፍሪካ አስተሳሰቦች መነሻነት በፖለቲካ የተዋሃደችና ህዳሴን የተላበሰች አኅጉር እንድትፈጠር ታልሟል፡፡ የወደፊቷ የ50 ዓመቷ አፍሪካ፣ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩባት፣ ፍትሕና የሕግ የበላይነት የሰፈኑባት ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአፍሪካ የሃምሳ ዓመት ዶሴ ሌሎችም ያዘላቸው የተስፋይቱን ምድር የሚያስመኙ ዕቅዶች ተካተውበታል፡፡ ሰላማዊና ደኅንነቷ የተጠበቀ አፍሪካ፣ ሕዝቦችን ማዕከል ያደረገ ልማት የሚለመልምባት፣ ወጣቶቿና ሴቶቿ ዕምቅ አቅማቸውን የሚያወጡባት አፍሪካ ትታሰባለች፡፡ ‹‹በመጪው ጊዜ እንድትኖረን የምንፈልጋት አፍሪካ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ዶሴ፣ አፍሪካን ከዚህም በላይ የተባበረች፣ በዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪና የሌሎች አጋር እንድትሆን መታጨቷን ያትታል፡፡ በዚህ መሠረት ድኅነትን ከአፍሪካ በማጥፋት፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን በኩል የጋራ ብልፅግና የሚሰፍንባት የተባበረች አኅጉር ትሆናለች ተብላ የታጨችው አፍሪካ፣ በመቶኛ ዓመቷ ላይ ይህንን ሁሉ አሳክታ ለሕዝቦቿ ትተርፋለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ባለፈው ሳምንት ጀምሮ በአዲስ አበባ ሽር ጉድ ሲሉ የከረሙት የአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት አባላት፣ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለሚመጡት የአፍሪካ መሪዎች የደረሱባቸውን ስምምነቶች አቅርበው ከማፀደቅ በተጨማሪ፣ የአኅጉሪቱን የወደፊት ሃምሳ ዓመት ጉዞ የሚገዛውን ሰነድም መሪዎቹ ያፀድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በፖለቲካ ትዋሃዳለች፣ በኢኮኖሚ ትተሳሰራለች የሚባልላት አፍሪካ፣ የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነትና በማካሄድ የአንድ ኢኮኖሚ አኅጉርነት መንገዷን ትጀምራለች እየተባለ ነው፡፡ ይህንኑ በማስመልከት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበሯ ዶክተር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ከትናንት በስቲያ እንዳስታወቁት፣ በመሪዎቹ ጉባዔ የሚፀድቀው የሃምሳ ዓመት ሰነድን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነበር፡፡ ሊቀመንበሯ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ አካላት ሲመከርበት ቆይቷል ያሉት የአፍሪካ የሃምሳ ዓመት ሰነድ፣ ኮሚሽናቸው ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት የሚመራበትን ዕቅድ ለመሪዎቹ በማቅረብ እንደሚያፀድቅ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የአፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ብዙም አጥጋቢነት እንደማይኖረው ከሚገልጹት መካከል የቻይናው ዕውቅ ኢኮኖሚስት ጀስቲን ሊን አንዱ ናቸው፡፡ ምሁሩ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢኮኖሚ ትስስር ማድረግ አፍሪካን ከመጥቀም ይልቅ ለማያተርፍ የንግድ ግንኙነት እንደሚዳርጋት ማብራራታቸው ይታወሳል፡፡ ፕሮፌሰሩ እንደሚገልጹት የአፍሪካ አገሮች ትልቁን የገበያ ልውውጥ የሚያከናውኑት ከምዕራባውያን ጋር ነው፡፡ በዚያም ላይ አፍሪካውያኑ በአብዛኛው ለገበያ የሚያቀርቧቸው ምርቶች የግብርና ሸቀጦችና የተፈጥሮ ምርቶች በመሆናቸው፣ እርስ በርስ ከመነገድ ይልቅ ለውጭ ገበያ ማቅረቡ ያዋጣቸዋል በማለት ፕሮፌሰር ጀስቲን ሊን አብራርተዋል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በፖለቲካዊ ውሳኔ ሳቢያ እርስ በርስ ይነግዱ ቢባል ደግሞ ለመሠረተ ልማት ግንባታ ቢሊዮን ዶላሮችን በማውጣት፣ መንገዶችን፣ የባቡር መስመሮችንና ወደቦችን መዘርጋት የአፍካውያኑ ግዴታ ይሆናል፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ ከሆነ፣ ለኢትዮጵያ አዋጭ ዕርምጃ የሚሆነው ወደ ጂቡቲ ወደብ ወይም በአቅራቢያ ወደሚገኝ ሌላ ወደብ መንገድና ባቡር መዘርጋቱ ነው፡፡ ይህም አጎራባች ከሆኑ በርካታ አገሮች ጋር የተሽከርካሪ መንገዶችን፣ የባቡር ሐዲዶችንና፣ የመርከብ ወደቦችን ከማስፋፋት ይልቅ ውጤታማ ያደርጋታል ይላሉ፡፡ አብዛኛው የንግድ ትስስሯ ካለበት አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ ጋር ይበልጥ ለመቆራኘት የሚያስችላት የመሠረተ ልማት ወጪ፣ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ለመተሳሰር ከሚያስወጣት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የበዛ እንደሆነ ይተነትናሉ፡፡ አፍሪካውያኑ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ የእርስ በርስ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር የበለፀገች አፍሪካን ተልመዋል፡፡ እንደ ጀስቲን ሊን ያሉ ምሁራን ለሚያነሷቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ አይደመጡም፡፡ ከብዙ አፍሪካ ይልቅ አንድ የተባበረ አፍሪካ ለጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ እንዳለው አበክረው ይገልጻሉ፡፡ በቅርቡ ይፋ የተደረገው የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታን የሚያሳየው ሪፖርት የአፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት (በጠቅላላ አገር ውስጥ ምርት ሲመዘን) ከሌሎች ቀጣናዎች ይልቅ የተሻለ ሆኖ እንደሚቀጥል ይገልጻሉ፡፡ የአሥር ዓመቱ መራሔ ድርጊት ያካትታቸዋል ከተባሉት ወይም ደግሞ አኅጉራዊ ትስስሩ ይንፀባረቅባቸዋል ተብለው ከታሰቡት ሥራዎች መካከል አኅጉራዊ ነፃ ገበያ ምሥረታ፣ አንድ አኅጉራዊ ፓስፖርት፣ አንድ የአቪዬሽን ገበያ፣ ድንበር ተሻጋሪ የፈጣን ባቡር አገልግሎት፣ የትልልቅ ግድቦች ግንባታ፣ የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ፣ የፓን አፍሪካ የኢንተርኔት ኔትወርክ ትስስር ከብዙዎቹ መካከል የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ ወደፊት አንድ የመገበያያ ገንዘብና አንድ የፋይናንስ ተቋም (የአፍሪካ ገንዘብ ድርጅት – አፍሪካ ሞንታሪ ፈንድ) እንደሚመሠረቱ ይታለማል፡፡ የወደፊቱ የአፍሪካ ውህደት ከሚፈጥራቸው ተቋማት መካከል አንዱ ሆኖ የሚጠበቀው የአፍሪካ የገንዘብ ድርጅት (አፍሪካን ሞንታሪ ፈንድ) ብዙ ሲባልለት ከርሟል፡፡ እስካሁን ግን ይህ ነው የሚባል እርምጃ መጓዝ አልቻለም፡፡ የየአገሮቹ የኢኮኖሚ መለያየትና የአቅም ልዩነት ይህንን ድርጅት የመፍጠሩን ሐሳብ ከባድ አድርጎታል፡፡ በኢኮኖሚ ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች በአፍሪካ ሞንታሪ ፈንድ ውስጥ የሚኖራቸው ድምፅ፣ ከድሃ አገሮች አኳያ እንዴት ይታያል፣ ደካማ አገሮች በሉዓላዊነታቸው እኩል ቢሆኑም በድምፅ አሰጣጥ ላይ ለድርጅቱ ከሚያዋጡት የመመሥረቻ ገንዘብና መሰል ቅድመ ሁኔታዎች በመነሳት ይህ ተቋም ዕውን የመሆኛው ጊዜ እንደ ሕልም የራቀ መሆኑን የሚጠቁሙ አሉ፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት ይፋ የተደረገው የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታ አመላካች ሪፖርት፣ ምንም እንኳ የአፍሪካ አገሮች ከዓለም አገሮች የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኙ ቢያትትም፣ ፈታኝ ጋሬጣዎች ዕድገቶቻቸውን ላይ መደንቀራቸውን ይጠቅሳል፡፡ የእርስ በርስ ግጭትና ፖለቲካዊ ትኩሳት ላለፉት ሃምሳ ዓመታት እንደነበሩት ሁሉ አሁንም የአፍሪካ ራስ ምታት ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ምንም እንኳ ከጠቅላላው የአፍሪካ ኢኮኖሚ አኳያ የአንድ ከመቶ ድርሻ ያለው ተፅዕኖ ቢያሳድርም፣ እንደ ኢቦላ ያሉ የበሽታ ወረርኞች ለአፍሪካ የሥጋት ምንጮች ናቸው፡፡ በኋላ ቀር የግብርና አመራረትና ዝቅተኛ ውጤታማነት ላይ የተመሠተው አብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚም ወንዝ የማያሻግር እየተባለለት ይገኛል፡፡ ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ ከአፍሪካ የሚወጣው የገንዘብ መጠን ነው፡፡ በኢንቨስትመንት ሰበብ ከውጭ የመጡ ኢንቨስተሮች እንደ ዶላር ያሉ መገበያያዎች ጠንካራ እየሆኑ በመጡ ቁጥር፣ በአፍሪካ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን ለማሸሽ የሚያደርጉት መቻኮል አፍሪካን ማጥ ውስጥ እየከተተ ይገኛል፡፡ እስካሁን በየዓመቱ 15 ቢሊዮን ዶላር ከአፍሪካ በተለያየ መንገድ እንዲሸሽ እየተደረገ እንደሚገኝ የኢኮኖሚ ሪፖርቱን ይፋ ያደረጉት አዳም ኤልሒራይካ አስታውቀዋል፡፡ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የማክሮ ኢኮኖሚክ ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ኤልሒራይካ ሪፖርቱን ይፋ ሲያደርጉ እንዳብራሩት፣ የአሜሪካ ዶላር የመግዛት አቅም ሲዳብር፣ ለወለድ የሚከፈለው መጠን ስለሚያድግ በአፍሪካ ኢንቨስት ያደረጉ አካላት ገንዘባቸውን በተለያየ አሳሳች ዘዴ ከአኅጉሪቱ ለማስወጣት ይሯሯጣሉ፡፡ የተለያዩ ግብዓቶችን የገዙበትን ዋጋ በማጋነን እያቀረቡ፣ የሸጡትን ምርት ዋጋ እያሳነሱ ያገኙት ገንዘብ አነስተኛ እንደሆነ እያስመሰሉ በዓመት 15 ቢሊዮን ዶላር ከአኅጉሪቱ ማስኮብለላቸውን ቀጥለዋል፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን የአፍሪካ መሪዎች ተስፈኞች ነው፡፡ በዚህ ሳምንት መጨረሻ በአዲስ አበባ ተገናኝተው ስለመጪው ጊዜ ይመክራሉ፡፡ የአፍሪካውያንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ፡፡ አኅጉሪቱ የምትመራበትን የሃምሳ ዓመት የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ ዕቅዶችን ያፀድቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች