አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ የተወሰኑ ወራት በቀሩበት በዚህ ጊዜ፣ የምርጫው ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ጉዳዮች የተነሳ ውዝግብ ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለይ ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)፣ ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ከሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ) ጋር ከረር ያሉ እሰጥ አገባዎች ውስጥ መግባቱን፣ በተለያዩ ጊዜያት የአገሪቱን የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ተቆጣጥሮት ሰንብቷል፡፡ ቦርዱ ለሰማያዊ ፓርቲ በጽሑፍ ይቅርታ እንዲጠይቅ ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ፓርቲው ደግሞ ይቅርታ የሚያስጠይቅ ምንም የፈጸምኩት ስህተት ካለመኖሩም በላይ፣ እንዲህ ዓይነት አሠራርን የሚፈቅድ የሕግ አካሄድ የለም በማለት ይቅርታ እንደማይጠይቅ አስታውቆ ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈ ቦርዱ ለመኢአድና ለአንድነት በውስጣቸው ክፍፍል መፈጠሩን አስታውቆ፣ ልዩነት የፈጠሩት ወገኖች በጋራ ሆነው ጠቅላላ ጉበዔ እንዲጠሩና የውስጥ ችግራቸውን በራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት እንዲፈቱ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ቦርዱ ለሁለቱ ፓርቲዎች የሰጠው የጊዜ ገደብ ማክሰኞ ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ያበቃ ሲሆን፣ በመጪዎቹ ቀናት የመጨረሻ ውሳኔው የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ የቦርዱ ትዕዛዝ ጋር በተገናኘ ሁለቱም ፓርቲዎች ውሳኔውን ክፉኛ በመቃወማቸው፣ የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነትን በተደጋጋሚ ጥያቄ አንስተውበታል፡፡ አንድነት ፓርቲ ይህን የቦርዱን ውሳኔ ከመቃወሙም በተጨማሪ፣ የሚጠራው ምንም ዓይነት ጠቅላላ ጉባዔ እንደማይኖርና አንድነት አንድ ነው በማለት ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህን በመቃወም ለእሑድ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. የሰላማዊ ሠልፍ ፕሮግራም ማዘጋጀቱን አስታውቆ ነበር፡፡ አንድነት ለጠራው ሠልፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዕውቅና ካለመስጠቱም በተጨማሪ፣ ሠልፍ ለማድረግ የሚያስችል ፈቃድ አለመስጠቱን ባለፈው ዓርብ አስታውቆ ነበር፡፡ በአንድነት ፓርቲ ሠልፍ እወጣለሁና በከተማ አስተዳደሩ ዕውቅና አልሰጠሁም ፍጥጫ መሀል ባለፈው እሑድ ረፋድ ላይ በዕቅዱ መሠረት ሠልፍ ለማድረግ ዝግጅቱን በጽሕፈት ቤቱ ማከናወኑን ቀጠለ፡፡ በፓርቲው እሑድ ዕለት ተጠርቶ የነበረው ሠልፍ መነሻውን የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ከሚገኝበት ቀበና አንስቶ፣ በአራት ኪሎ እንዲሁም በፒያሳ በማድረግ መጨረሻውን ኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ወይም ድላችን ሐውልት አካባቢ ለማድረግ ነበር፡፡ የተፈጠረው ቀውስ እሑድ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በፓርቲው ጽሕፈት ቤት ተሰባስበው ሥራ መጀመራቸውንና ለሠልፉ የሚያገለግሉ መፈክሮችንና ሌሎች ነገሮችን ሲያሟሉ እንደነበር ያስታወሱት፣ የፓርቲው ተጠባባቂ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሥራት አብርሃ ናቸው፡፡ በአቶ አሥራት ማብራሪያ መሠረት ፓርቲው ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ለጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ሠልፍ ጠርቷል፡፡ ‹‹ነገር ግን ሠልፉ ሕገወጥ ነው በማለት በአንድነት አመራሮችና አባላት ላይ ፖሊስ ያደረሰው አሰቃቂ ድብደባ ወደር የማይገኝለት ነው፤›› በማለት በዕለቱ ስለተፈጠረው ሁኔታ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰገድ ጌታቸው በበኩላቸው፣ ‹‹የፓርቲው አመራር አባላት ደብዳቤ አምጥተው ጥለው ነው የሄዱት፡፡ መሙላት የሚገባቸውን ፎርም እንኳን በአግባቡ አልሞሉም፡፡ ስለሆነም ሠልፉ ሕገወጥ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለዚህ አስተያየት ምላሽ የሚሰጡት አቶ አብርሃም በበኩላቸው ደግሞ፣ ‹‹የሚሞላውን ፎርም በተመለከተ ኃላፊነት ያለባቸው እነሱ ናቸው፡፡ ኃላፊነት ወስደው ይህን ሙሉ ይህን አድርጉ ማለት ያለባቸው ራሳቸው መሆን ሲገባቸው፣ እነሱ ግን እኛን አላስሞሉም፡፡ እኛ ደግሞ በግድ ቀምተን የምንሞላው ፎርም አይኖርም፤›› በማለት መነሻውን አስረድተዋል፡፡ ፓርቲውና የከተማ አስተዳደሩ ምርጫን በተመለከተ እየተወዛገቡበት የሚገኘው ጉዳይ ‹‹ፎርም ሙሉ ወይም አንሞላም›› ከሚለው በተጨማሪ፣ አንድነት ፓርቲ ይህን ሠልፍ እንዳያደርግ የሚያግደው አንዳችም መደበኛ በሆነ መንገድ የደረሰ ደብዳቤ የለም ይላል፡፡ ፓርቲው ስለጉዳዩ የሰማው በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት እንሆነ አቶ አሥራት አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ዓርብ ማታ አንድ ሰዓት ወይም አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ ከአስተዳደሩ ሰዎች መጥተው የሆነ ነገር አለ ተቀበሉን ማለታቸውን፣ ነገር ግን በጽሕፈት ቤቱ የነበሩ ሰዎች አሁን ሌሊት ነው አንቀበልም ብለው መልሰዋቸዋል በማለት አቶ አሥራት አስረድተዋል፡፡ አቶ አሥራት ማብራሪያ አስተዳደሩ መደበኛ የሆነ ደብዳቤ መስጠት ከፈለገ ቅዳሜ ዕለት ሰዎቹ ተመልሰው መስጠት ይችሉ ነበር በማለት የሚሞግቱ ሲሆን፣ ‹‹ነገር ግን አካሄዱ ራሱ በመሠረቱ ሕገወጥ በመሆኑ ይህ ሊሆን አልቻለም፤›› በማለት ይተቻሉ፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ፓርቲው ጥቅምት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ ‹‹ሰላማዊ ትግሉን በጭፍጨፋና በውንብድና ለማቆም መሞከር ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው›› በማለት መግለጫ አውጥቷል፡፡ በመግለጫው ላይ እንደተጠቀሰው፣ ‹‹ሕጉ አስተዳደሩ በ12 ሰዓት ውስጥ መልስ መስጠት አለበት ቢልም፣ ከ72 ሰዓት በኋላ በሚዲያ ‹ሠልፉ ሕገወጥ ነው› የሚል መግለጫ ከማውጣት ውጪ በደብዳቤ የመለሱት ነገር አልነበረም፤›› በማለት የአስተዳደሩን ዕርምጃ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ተቃውመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲው በመግለጫው በመሠረቱ በስብሰባና በሠልፍ አዋጁ መሠረት አንድ ፓርቲ ሠልፍ እንደሚያደርግ ለአስተዳደሩ ማሳወቅ ነው ያለበት፡፡ አስተዳደሩ ደግሞ ሠልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ኃይል በመመደብ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንጂ፣ ሠልፍ መፍቀድም ሆነ መከልከል አይችልም ብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የአስተዳደሩ ውሳኔና አካሄድ ሕግን ያልተከተለ እንደሆነ የፓርቲው አመራሮች ይከራከራሉ፡፡ አቶ አሥራት በሠልፉ የተጎዱት የፓርቲው አመራሮችና አባላት ቁጥር 27 እንደሆነ ገልጸው፣ ነገር ግን ከረብሻው በኋላ ተጎድተው ዝም ብለው ወደ ቤታቸውና በግልም ወደ ሕክምና ተቋማት የሄዱ ሰዎች በመኖራቸው ምክንያት ይህ ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል ብለው እንደሚገምቱ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዚህም ምክንያት 40 ወይም 50 ያህል ግለሰቦች ሳይጎዱ አይቀሩም የሚል ግምት፤›› አለኝ በማለት አስረድተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ‹‹ሠልፍ እንዲያደርጉ ምንም ዓይነት ዕውቅና የላቸውም፡፡ ዕውቅና ከሌላቸው ደግሞ ድርጊታቸው በሙሉ ሕገወጥ ነው፡፡ ሕገወጥነትን ለመከላከል ፖሊስ ኃላፊነት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በተጨማሪም ፖሊስ ሕገ መንግሥቱንና ከሕገ መንግሥቱ አንፃር የሚወጡ ሕጎችን ያከብራል፣ ያስከብራል፡፡ በዕለቱም ከ50 የማይበልጡ ግለሰቦች ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው ሠልፍ ለማድረግ ነው የሞከሩት፡፡ በዚህ መሀል ፖሊስ ሠልፍ ለማድረግ ዕውቅና የላችሁም ስለዚህ በሕግ ያስጠይቃል አቁሙ የሚል ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ ፖሊስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ አንቀበልም ብለው ገፍተው ሄደዋል፤›› በማለት በዕለቱ በፖሊስ በኩል የነበረውን አጠቃላይ ሁኔታ አስረድተዋል፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩ ስለተፈጠረው ሁኔታ ይህን ቢሉም አቶ አሥራት ግን ይቃወማሉ፡፡ ‹‹ገና ከግቢያችን እንደወጣን የፀጥታ ኃይሎች ከበቡን እንጂ እንድንመለስ አልነገሩንም፡፡ ምንም አላሉንም፡፡ ወዲያው አዛዡ ጀምር የሚል ትዕዛዝ ሲያወርድ ያገኙትን በሙሉ ደበደቡ፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አሳዛኝም አስገራሚም ነገር ነው፤›› በማለት ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ከፖሊስ እንዳልደረሳቸው አስታውቀዋል፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩ በበኩላቸው፣ ‹‹እንዲህ ዓይነት ውንጀላ ሐሰት ነው፤›› በማለት ለዚህ በሚያቀርቡት መከራከሪያ ደግሞ፣ ‹‹ፖሊስ እየሰጠ የነበረውን ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ አንቀበልም ብለው እስከ 80 ሜትር ድረስ መጓዝ ነው የጀመሩት፡፡ በዚህ መሀል አሁንም ሕገወጥ ናችሁ ሠልፋችሁን አቁሙ ብለው ማሳሰቢያ እየሰጡ የነበራትን ፖሊሶች ሠልፈኞቹ መደብደብ ጀመሩ፤›› በማለት ፖሊስ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ይሞግታሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ እስጥ አገባ በኋላ ዕርምጃ መወሰዱን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ፖሊሶች ራሳቸውን ለመከላከል ተመጣጣኝ ዕርምጃ ወስደዋል፤›› ብለዋል፡፡ ማክሰኞ ዕለት አንድነት ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ በእሑድ ዕለቱ ረብሻ ጉዳት የደረሰባቸው የፓርቲው አባላትና አመራሮች በፓርቲው ጽሕፈት ቤት ተገኝተው የጉዳታቸውን መጠን ለጋዜጠኞች አሳይተዋል፡፡ የደረሰባቸውን ጉዳት ለጋዜጠኞች ካሳዩት የፓርቲው አባላት መካከል ወ/ሮ ልዕልና ጉግሳ የፓርቲው የብሔራዊ ምክር ቤት አባል ይጠቀሳሉ፡፡ በዕለቱ ክፉኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው የተለያዩ ሰንበሮችና ጠባሳዎችን አሳይተዋል፡፡ በተለይ ኩላሊታቸው አካባቢ የደረሰባቸው ዱላ ክፉኛ እንደነበር ገላቸው ላይ የቀረው ጠባሳ ምልክቱን ትቶ ማለፉ ታይቷል፡፡ ሌሎች የፓርቲው አባላትም የደረሰባቸውን ድብደባ ለጋዜጠኞች ከማሳየት ባለፈ፣ ‹‹ወደዚህ ትግል ስንገባ ይህ ብቻ ሳይሆን ሞትም ሊገጥመን እንደሚችል እያወቅን በመሆኑ፣ ይህ ድብደባ ያበረታናል እንጂ ከትግላችን ወደ ኋላ አይመልሰንም፤›› በማለት ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ ሁሉ በደል ቢፈጸምብንም ትግላችን ይቀጥላል፤›› ያሉት የፓርቲው አባላት ሲሆኑ፣ ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ደግሞ፣ ‹‹አሁንም ቢሆን አንድነት ይህን የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሴራና ውንብድና በመቃወም ለሚቀጥለው እሑድ ጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በሌሎች የተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ ሠልፍ ያደርጋል፤›› በማለት አስታውቋል፡፡ የመጪውን እሑድ ሠልፍ በተመለከተም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደብዳቤ ማስገባታቸውን የፓርቲው አመራር አባላት አስታውቀዋል፡፡ በዕለቱ የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባዔ እንዳለ እንደተነገራቸው ግን አቶ አሥራት ገልጸዋል፡፡ አቶ አሥራት ይህን በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ዝም ብሎ በደፈናው ሠልፍ አታደርጉም የሚባል ከሆነ አንቀበለውም፡፡ አሁንም ቢሆን ተጠናክረን እንወጣለን፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ አንፃር ቦርዱ አንድነት ፓርቲ በምርጫ ይሳተፍ ቢል ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ ለሚለው ጥያቄም ምላሽ የሰጡት አቶ አሥራት፣ ‹‹ፓርቲው በአሁኑ ጊዜ 450 የሚደርሱ ዕጩዎችን አዘጋጅቶ በተጠንቀቅ ቆሞ እየጠበቀ ነው፤›› በማለት ለምርጫው ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ማክሰኞ ዕለት በፓርቲው ጽሕፈት ቤት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማንኛውም የመንግሥት ሚዲያ እንዲሳተፍ ፓርቲው ባለመፍቀዱ፣ ጉዳዩ ለጥቂት ደቂቃዎች በጋዜጠኞችና በፓርቲው አመራሮች መካከል ንትርክ ፈጥሮ ነበር፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለአንድነትና ለመኢአድ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም. የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የቦርዱ ቀጣይ ውሳኔና የፓርቲዎች አጠቃላይ ምላሽ በመጪዎቹ ቀናት የሚጠበቅ ሌላው የምርጫ 2007 ክስተት ይሆናል፡፡