ኢትዮጵያን እየጎበኙ ያሉት የኖርዌይ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አልጋ ወራሽ ልዑል ሃኮን ማገኑስ፣ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በብሔራዊ ቤተመንግሥት ጥቅምት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. የክብር አቀባበል ባደረጉላቸው ጊዜ የተናገሩት፡፡
ፕሬዚዳቱና ልዑል አልጋ ወራሹ ሰባት አሠርታት ያስቆጠረው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከኖርዌይ ጋር ያላትን ግንኙነት በሁሉም ዘርፎች ለማሳደግ ዝግጁ መሆኗን ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በገነባቻቸውና በግንባታ ላይ ባሉ ሰፋፊና ምቹ የኢንዱስትሪ ዞኖች፥ የኖርዌይ ባለሃብቶች መጥተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑም ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ ከባለቤታቸው ልዕልት ሜቲ ማሪት ጋር የተገኙት ልዑል ሃኮን በበኩላቸው፣ ከ51 ዓመት በኋላ በንጉሣዊ ቤተሰብ ደረጃ የተደረገው ጉብኝታቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት የላቀ ግምት ማሳያ ነው ብለዋል። እንደ አየር ንብረት ለውጥና ዘላቂ የልማት ግቦች ያሉ ዓለም አቀፍ ትልሞች በጋራ ለመሥራት እድል እንደሚፈጥሩም ገልጸዋል።