Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ዘርፎች የግብይት ሥርዓት ሥጋት ፈጥረውብኛል አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ሕግ በመጣስ ለአገር ውስጥ ገበያ እያቀረቡ ነው ተብሏል

– ‹‹በአንደር ኢንቮይስ›› ተጠርጥረዋል

 በኤክስፖርት ገበያ ላይ አተኩረው የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲያሰፉ በተመረጡት የቆዳና ጨርቃ ጨርቅ የኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች፣ የገበያ ሥርዓት ሥጋት እንደፈጠሩበት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም. የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በተጠቀሱት ሁለት ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎች ከተፈቀደላቸው የግብይት ሥርዓት ውጪ በመሸጥ ላይ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሁለት ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎች እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ብቻ እንዲያቀርቡ ተዋውለው የገቡ ቢሆንም፣ የኤክስፖርት ገበያቸው ከፍተኛ የሥጋት ምንጭ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡ በተለይ በቆዳ ፋብሪካዎች ላይ ትኩረት ተደርጐ በተካሄደ ጥናት ያለቀለት ቆዳ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚገባቸው ስምንት ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለገበያ ሳይሆን፣ ለእናት ኩባንያቸው እንደሚያቀርቡ ሚኒስቴሩ ማረጋገጡን አቶ አህመድ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እዚህ አገር ለማምረት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ግዥ የሚፈጸመው በእናት ኩባንያዎቻቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህ የግብይት ሥርዓት በሁለት ምክንያቶች አገሪቱን ጉዳት ላይ ሊጥል ይችላል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹አንደኛው ለእናት ኩባንያዎቻቸው የሚሸጡት በዝቅተኛ ዋጋ በመሆኑ ኢትዮጵያ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ያሳጣል፤›› ብለዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የተረጋገጠው ያሉት ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ በተሰማሩበት ዘርፍ ለማምረት የሚያስፈልጉዋቸውን ግብዓቶች የሚገዙት በእናት ኩባንያቸው በኩል በመሆኑ፣ የግብዓት ወጪዎቻቸውን በማናር የሒሳብ ሪፖርታቸው ኪሳራን ወይም ዝቅተኛ ትርፍን እንዲያሳይ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ከማጣቷ በተጨማሪ፣ ኩባንያዎቹም ሪፖርት እያደረጉ ያሉት ኪሳራ ወይም ዝቅተኛ ሪፖርት በመሆኑ መገኘት የሚገባውን ታክስም ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ሚኒስቴሩ ያለቀለት ቆዳ የዓለም አማካይ ገበያን በማጤን ባረጋገጠው መሠረት፣ ከአማካይ ዋጋው በታች ለመሸጥ የተዋዋሉ ላኪዎች ምርታቸው ከአገር እንዳይወጣ ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ትዕዛዝ ማስተላለፉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በጥሬ ዕቃ ግብዓቶች ማለትም በቆዳና በጥጥ አቅርቦት እጥረት የተነሳ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ጥጥ ከውጭ ገዝቶ እያከፋፈለ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በዓለም ገበያ የአንድ ኪሎ ግራም ክር ዋጋ 38 ብር መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ 78 ብር በመሆኑ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ሕግ በመጣስ ለአገር ውስጥ ገበያ እያቀረቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኩባንያዎቹ ሕገወጥ ሥራ እየሠሩ መሆኑ ሲናገራቸውም ‹‹ከምንከስር ብለን ነው፡፡ የማምረቻ ዋጋችን በመናሩ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ያከስረናል፤›› የሚል ምላሽ እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡ የማምረቻ ወጪያቸው በተለይ በትራንስፖርትና በባንክ የኤልሲ (LC) የአገልግሎት ክፍያ መጠን ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ፣ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ያለው የትራንስፖርት ዋጋ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ብቻ ከ20 እስከ 30 በመቶ እንዲቀንስ በመንግሥት መወሰኑን፣ እንዲሁም የኤልሲ የአገልግሎት ክፍያ ከሦስት በመቶ ወደ 0.5 በመቶ ዝቅ እንዲል መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የጀመርነው ዕርምጃ አለ፡፡ ይህንን እስከሚያማቸው ድረስ እንቀጥልበታለን፡፡ ትግሉ እልህ አስጨራሽ እንደሚሆንም እንገምታለን፤›› ብለዋል፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ኤክስፖርት ዘርፍ በዕድገትና በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መጨረሻ ማለትም በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከዘርፉ 2.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል፡፡ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ከዘርፉ የተገኘው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ 397 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የሚኒስትሩ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ከተጠቀሰው ዘርፍ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት በሰፊው ታቅዷል፡፡ ይህም ማለት በስድስት ወራት ውስጥ 505 ሚሊዮን ዶላር ማግኘትን ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የተገኘው 191.5 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 38 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የግብዓት እጥረትና የተዛባ የግብይት ሥርዓት ለአፈጻጸሙ አነስተኛነት ምክንያቶች መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች