Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሚኒስትር ዴኤታው የንግድ ምክር ቤቱ ባላደራ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተሰየሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ሚኒስትሩ ባላደራ ቦርዱ በአስቸኳይ እንዲቋቋም ትዕዘዝ ሰጥተዋል

 የአዲስ አበባ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የባላደራ ቦርድ እንዲረከበው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ፣ የባላደራ ቦርዱን በሰብሳቢነት እንዲመሩ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አሊ ሲራጅ ተሾሙ፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ አዲስ ምርጫ እስኪያካሂድ ድረስ በባላደራ ቦርድ እንዲመራና ይህንንም ቦርድ እንዲያቋቁም ኃላፊነት የተሰጠው ንግድ ሚኒስቴር በመሆኑ፣ የአቶ አሊ ሹመት የተሰጠው በንግድ ሚኒስትሩ ነው፡፡ በንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጽፎ የወጣው ደብዳቤ ባላደራ ቦርዱን በሰብሳቢነት እንዲመሩ ከተሰየሙት አቶ አሊ ሲራጅ በተጨማሪ፣ የንግድ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ አየነው ፈረደ በባላደራ ቦርዱ ውስጥ ንግድ ሚኒስቴርን በመወከል በአባልነት እንዲሠሩ መወከላቸውን ይገልጻል፡፡ ይህም ደብዳቤ ጥር 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሁሉም የሚመለከታቸው አካላት እንደደረሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ባላደራ ቦርዱ በንግድ ሚኒስቴር እንዲቋቋም፣ ቦርዱም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮን በአባልነት እንዲያቅፍ የሚያዝ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በዚሁ መሠረት በባላደራ ቦርዱ ውስጥ እንዲካተቱ ንግድ ሚኒስቴር ከወከላቸው የሥራ ኃላፊዎች በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ሰብሳቢ ወይም ምክትል ሰብሳቢ፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የቢሮው ኃላፊ በቦርዱ ውስጥ እንዲወከሉና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንዲያስፈጽሙ የሚኒስትሩ ደብዳቤ ያሳስባል፡፡ ‹‹ንግድን፣ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የተደራጀው የልማት ተቋም ያለቦርድ አመራር ለብዙ ጊዜ ከቆየ በልማቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል የታመነ ነው፤›› የሚለው የሚኒስትሩ ደብዳቤ፣ ባላደራ ቦርዱ በተፋጠነ ሁኔታ ተቋቁሞ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣም በጥብቅ ያሳስባል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ በባላደራ ቦርድ እንዲመራ የተወሰነው የፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያና በንግድ ምክር ቤቱ መካከል በነበረው ክርክር ውሳኔ ከሰጠ በኋላ በወጣው አፈጻጸም ነው፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. የተካሄደው የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ፣ በጉባዔው የተላለፉ ውሳኔዎችና በዕለቱ የተመረጡ የቦርድ አባላት፣ ፕሬዚዳንቱና ምክትል ፕሬዚዳንቱ መሻራቸውንም የሚገልጽ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዘጠነኛው ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጠው ቦርድ ንግድ ምክር ቤቱን በመወከል የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተቋርጧል፡፡ ባላደራ ቦርዱም ዋነኛ ሥራው የተሻረውን ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባዔ እንደገና ጠርቶ አዲስ ምርጫ ማካሄድና ለሚመረጠው ቦርድ ኃላፊነቱን ማስረከብ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች