Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሰሎሞን ዴሬሳ!

ሰሎሞን ዴሬሳ!

ቀን:

በቅርቡ በ80 ዓመቱ ዜና ዕረፍቱ የተሰማው፣ በዘርፈ ብዙ ዕውቀቱ ተጠቃሽ የነበረው ዕውቁ ገጣሚና ጸሐፊ፣ ጋዜጠኛና የፍልስፍና መምህር ሰሎሞን ዴሬሳ ሥርዓተ ቀብሩ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚኔሶታ ከተማ በግብአተ እሳት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡ ነፍስ ኄር ሰሎሞን ዴሬሳ ከ19 ዓመታት በፊት (መስከረም 1991 ዓ.ም.) ከሪፖርተር መጽሔት ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር፡፡ በዚያ ቆይታው ስለትምህርቱ፣ ስለጓደኞቹ፣ ስለግጥሞቹ፣ ስለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፣ ስለመንፈሳዊነት፣ ስለኢትዮጵያውያንና ስለብሔረሰቦች፣ እንዲሁም ስለጋዜጠኝነት ሰፊ ሐተታ ሰጥቷል፡፡ ለዝክረ ነገር ይሆን ዘንድ በዚህ እትም የመጀመርያው ክፍል ሲቀርብ ቀሪው በእሑዱ እትም ይስተናገዳል፡፡

ዐውደ ሕይወት

በወለጋ ክፍለ አገር ጩታ በተባለች መንደር በ1929 ወይም በ1930 ዓ.ም. [1937] ተወለድኩ፡፡ በጣሊያን ጊዜ፡፡ አራት ዓመት ሲሞላኝ ዘመዶቼ ወደ አዲስ አበባ ይዘውኝ ስለመጡ አገሬ አዲስ አበባ ነው ማለት ይቀለኛል፡፡

ትምህርት አልገባ ብሎታል ተብዬ ያልገባሁበት ትምህርት ቤት የለም፡፡ በመጨረሻ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ16 ዓመቴ ገባሁ፡፡ እዚያም ከትምህርቱ ይልቅ ልጅ ሁሉ እንደሚያደርገው ጨዋታና መበጥበጥ ይበልጥብኝ ነበር፡፡ ክፍል ውስጥ የሚገኘውን ትምህርት አላጠናቅኩትም፡፡ ነገር ግን ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከሚገኙት ልጆች መጻሕፍት ቤቱን እንደኔ የተጠቀመበት ብዙ ተማሪ ያለ አይመስለኝም፡፡ ከዚያ ለሦስት ወራት የእንግሊዝኛ ዜና አንባቢ ሆኜ በአሁኑ ራዲዮ ኢትዮጵያ በቀድሞው ራዲዮ አዲስ አበባ ተቀጠርኩ፡፡ ከአለቃዩ ጋር በልጅነቴ የተነሳ አልተስማማንም፡፡ ወዲያው እንዳጋጣሚ ፈረንሣይ አገር ስኮላርሺፕ አገኘሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ በፈረንሣይኛ ቋንቋ ትምህርት የጅማሪ ክፍሎን ሦስት ጊዜ በተደጋጋሚ የወደቀ ቢኖር እኔ ብቻ ሳልሆን አልቀርም፡፡

ፈረንሣይኛ ይህን ያህል አላስቸገረኝም፡፡ ተማሪ ቤት ተመዘገብኩ፡፡ ፈረንሣይ አገር የዩኒቨርሲቲ ፈተና በዓመት አንድ ጊዜ ነው የምትፈተነው፡፡ የምማረው ቱሉዝ ነበርና እኔ አውሮፓ ውስጥ ስዞር ከርሜ አንድ ሦስት ወር ሲቀረው መጥቼ አጥንቼ አልፋለሁ፡፡ በኋላ ሰዓሊው እስክንድር በጎስያን ጥቁር አሜሪካዊት አላባማ ሊያገባ ስለነበር ለሱ ሚዜ ሆኜ አሜሪካ ሄድኩኝ፡፡ ሁለተኛ ወደ አውሮፓ አልተመለስኩም፡፡

ወደ ካሊፎርኒያ ሄጄ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አገኘሁ፡፡ በቴፕ እየቀረፁ ቋንቋ ማስተማር የመጀመሪያውን ክፍላቸውን ከጌታሁን አምባቸው ጋር እኔ ነበርኩ ያቋቋምኩት፡፡ ያላየሁት ገንዘብ እጄ ገባ፡፡ አማርኛ አስተምር ነበር፣ ይህን አሠራ ነበር፣ በኋላ ላይ ደግሞ ዎልፍ ሌስላው ‹‹ኢትዮጵያን ዲክሽነሪ›› ብሎ ያወጣትን አንድ አሥራ አንድ ኢትዮጵያውያን ሆነን ስንሠራ እሱ ሱፐርቫይዘር ነበር፤ በዚህ ሁሉ የማገኘው ገንዘብብ ኪሴን ሞላው፡፡

ከዚያ ወደ ኒዮርክ ሄድሁና ለአንድ ለሁለት ቀን ሉካንዳ ውስጥ ሥራ እሠራለሁ ብዬ ገባሁ፡፡ ገንዘቡ ጥሩ ነበር፤ ግን የሥጋው ሽታ ስለበዛ እሱን ጥዬ ወጣሁ፡፡ ግራና ቀኝ ስል በተባበሩት መንግሥታት ሥራ አገኘሁ፡፡ እዚያ እየሠራሁ አንድ ማስታወቂያ አየሁ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ ሠራተኛ ይፈልጋል›› የሚል ሲሆን፣ አሜሪካኖችም ሌሎችም ሲያመለክቱ እኔም አመለከትኩ፡፡ በቋንቋ ማወቅ ስለሆነ እኔ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ፈረንሣይኛ፣ እንግሊዝኛ እናገራለሁ፡፡ ትግርኛም ትንሽ ትንሽ እሰማ ነበር፡፡ በዚህ አሜሪካኖቹን አሸንፌ ተቀጥሬ መጣሁ፡፡

በእውነት ያደግሁት ራዲዮ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ ነፍሴን ያወቅሁት፡፡ ወደ መጨረሻ ከዚያ ስወጣ የራዲዮ የቴሌቪዥን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ነበርኩ፤ ለአዲስ ሪፖርተር እንግሊዝኛ መጽሔት እሠራ ነበር ግጥም እፃፅፍ ነበር፡፡

እውነቱን ለመናገር እኔ ገጣሚ ነኝ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ እንዲሁ በየቦታው እየተጻፈ (አሁንም እንዲሁ ነው) የጠፋው ጠፍቶ የተገኘውን ባለቤት ስብሰባ ካስቀመጣቸው ውስጥ ‹‹ልጅነት›› ወጣች፡፡ የቀሩትን እዚሁ ትቻቸው ሄድኩኝ፡፡ እንደ ሦስት ጅምር ተውኔቶች፣ የአጫጭር ልቦለድ ስብስቦችና ግጥሞች እዚሁ ቀረሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ጽሑፍ አስተምር ስነበር ለብዙ ጊዜ አልጽፍም ነበር፡፡ ለእኔ ሁለቱ አንድ ላይ አልሄደም፤ አስቸገረ፡፡

የማስተምረው Critical Thinking እና Creative Writing አንድ ላይ በማንኛውም አቅጣጫ ነው፡፡  Wrting for the sciences writng for literature writing for the fin arts writing for the social sciences አስተምር ነበር፡፡ ለማስተማር ኳሊፊኬሽን ኖሮኝ አያውቅም፡፡ ሳመለክት እንዳጋጣሚ እቀጠራለሁ ከዚያ ከተማሪዎቹ ጋር እየተማርኩ ነው የማስተምረው፡፡ የዛሬ አምስት ነው ስድስት ዓመት ገደማ ከዩኒቨርሲቲ ወጣሁ፡፡ ምክንያቱም የተማሪዎቼን ጽሑፍ ማረም ስለሰለቸኝ ነበር፡፡ ከዚያ training and consulting in communication ጀመርኩኝ፡፡ አሁንም የምሠራው ይህንኑ ነው፡፡ ከየትኛውም ተቋም ጋር ግንኙነት የለኝም፡፡ የማስተምረው በአንድ ቦታ ሳይሆን እየተዘዋወርኩ ነው፡፡ ተማሪዎቼን የማሰባስበው በአፍ ማስታወቂያና እርስ በርሱ እየተስማማ ከሚመጣው ነው፡፡

ያለኝ የባችለር ዲግሪ ነው የመጀመሪያ ዲግሪ ብቻ ነገር ግን የድህረ ምረቃ ተማሪዎችንም አስተምር ነበር፡፡ መጀመሪያ በዩኒቨርሲቲው ፕብሊክ ሄልዝ ኮሌጅ ውስጥ ከዚያ ደግሞ ገሽታልት ኢንስቲትዩት (የሳይኮሎጂ) ውስጥ በሳይኮሎጂ ለፒኤችዲ የሚሠሩትንም፣ ሶሻል ወርከሮችንም፣ ሳይካትሪስቶችንም አስተምር ነበር፡፡ አሁንም እንደዚህ ያሉ የግል ተሪማዎች አሉኝ፡፡

የባችለር ዲግሪዬን አዲስ አበባ ሳልጨርሰው ነው የሄድኩት፡፡ አሜሪካ ሄጄ የጨረስኩት Oriental Philosophy and American literature ነው፡፡ እዚህ ዩኒቨርሲቲ ሳልጨርሰው ሳይሆን ዲግሬዬን ሳላገኝ የወጣሁት Literature and western philosophy ነበረ፡፡ የምዕራባውያን ፍልስፍናን ክፍል ውስጥ በመማር ሳይሆን በማንበብ ምናልባት ኮሌጅ ለማስተርስ ከሚሠሩት ጋር እኩል ሳላነብ የቀረሁ አይመስለኝ፡፡ ስላልተፈተንኩበት ሳለማር ልል አልችልም፡፡ እዚያ ብሄድ አዲስ ነገር ካጋጠመኝ ብዬ በአንድ ስምንት ወር ውስጥ ጨረስኳት፡፡

ከሦስት ወር በኋላ እዚያው ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ መልሰው ለማስተማር ቀጠሩኝ፡፡ መጀመሪያ ስቀጠር ሳስተምረው የነበረ ኮርስ ‹‹ሥነ ጥበብና ቴክኖሎጂ›› የሚል የራስ ፈጠራ የሆነ ነበር፡፡ ቴክኖሎጂው እየተሻሻለ ሲሄድ ሥነ ጥበቡን ይለውጠዋል፡፡ ሥነ ጥበቡ ደግሞ እየተሻሻለ ሲሄድ ለቴክኖሎጂው አዲስ መንገድ ይከፍታል፡፡ እና በዓለም ታሪክ ውስጥ ሥነ ጥበብና ቴክኖሎጂ የት የት ቦታ ነው የተገናኙት የሚለውን ማስተማር ጀመርሁ፡፡

የፈረንሳይ ሥነጽሑፍና እኔ

የፈረንሳይን ሥነ ጽሑፍ አነብም አጠናም ነበር፡፡ የደረሱበትን አላውቅም እንጂ በፈረንሣይኛ የጻፍኳቸው፣ ታትመው የወጡም ግጥሞች ነበሩኝ፡፡ አሁን ፈረንሣይኛው እየጠፋ ሄዷል፡፡ የቀሩኝ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ ኦሮምኛ ናቸው፡፡ በኦሮምኛ እስካሁን አልጻፍኩም፡፡  

በኔ ላይ ተፅዕኖ ያሳደረብኝ የፈረንሳይ ሥነ ጽሑፍ ሳይሆን ፓሪስ መኖሬ ነው፡፡ ፓሪስ ስደርስ 20 ዓመቴ ነበር፡፡ ፓሪስ ነፃ ክፍት ከተማ ስለነበርና ልጅ ስለበርኩ ቁልፉን የከተማው ከንቲባ እንደሰጠኝ ነው ያየሁት፡፡ በኋላ ትልልቅ የሆኑ ጸሐፊዎች፣ የሙዚቃ ሰዎች ሠዓሊዎች ነበሩ፡፡ እንዲያውም ላንድ አቫን ጋርድ የፈረንሣይ ጋለሪ ማንም ሳይሾመኝ ሥዕል አውቃለሁ ብዬ ገብቼ አንድ አማካሪ ሆኜ ያኔ የመረጥኳቸው ሠዓሊዎች አሁን በዓለም የታወቁ አሉ፤ ኢትዮጵያውያን ማለቴ አይደለም፡፡ ዋናው ተፅዕኖ ከነሱ ጋር መዋል መቻሌ ነው፡፡ ከጥቁር አሜሪካዎች ጋርም በጣም በጣም ቅርብ ነበርኩኝ በተለይ ከጃዝ ሙዚቀኞች ጋር፡፡ አሁንም በብዛት የምሰማው ሙዚቃ የኢትዮጵያ፣ ጃዝና ክላሲካል ሙዚቃ ነው፡፡ ከፈረንሣይ ጸሐፊዎች ጋርም ያለ ዕድሜዬና ያለ ዕውቀቴ እኩል ገብቼ ዋልኩኝ፡፡ በማንበብ ሳይሆን አብሮ በመዋል እንዳባቶች ሆነው አሳድገውኛል፡፡ ከፈረንሣይ፣ ከእንግሊዝ ከአሜሪካን ጸሐፊዎች ውስጥ ሪቻርድ ሪይት ለትንሽ አመለጠኝ፡፡ ግን የእሱ ጓደኞች ከሚውሉበት ነበር የምውለው፡፡ እነ ቸስተር ሃየምስ፣ ጀምስ ቦልድዊንና ስማቸውን ከማላስታውሳቸው ጸሐፊዎች ጋር አብሮ መዋል እኔንም ጸሐፊ ያደረገኝ መስሎኝ ነበር፡፡ ያሳደጉኝ እነሱ እንጂ የፈረንሣይ ዩኒቨርሲቲ አይደለም፡፡ በተጨማሪም ፓሪስ ከተማ አለች ከኢትዮጵያውያን ጓደኞቼ ጋር እየዋልኩኝ ወደ ሙዚየም፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቲያትር ቤት፣ ኮንሰርት እሄድ ነበር፡፡ ገንዘብ ብዙ አልነበረበኝም፡፡ በተለይ መጨረሻው ላይ ምንም አልነበረኝም፡፡ ከትሬንታ ላይ ሌሊት ሌሊት አትክልት እያወረድኩ ነበረ የምኖረው፡፡ ግን አንድ ሳንቲም ኪሴ ሳይኖር እንደ ሚሊየነር ልጅ ነው ፓሪስን የኖርኩባት፡፡ ከአዲስ አበባ ቀጥላ የትውልድ ከተማዬ የምትመስለኝ ፓሪስ ነች፡፡

የሥነ ጽሑፍ አቋም

ከብዙ ወጣት ደራስያን ጋር ከዮሐንስ አድማሱ፣ ብርሃኑ ዘርይሁን ጋር የተለየ አቋም ነበረኝ፡፡ ከዮሐንስ ጋር ከሥነ ጽሑፍ ይልቅ የጓደኝነት ግንኙነት ነበረን፡፡ በጣም በጣም አደንቀው የነበረና አሁንም የማደንቀው የአማርኛ ባለቅኔ ብዬ የምገምተው ገብረክርስቶስ ደስታ ነው የተረሳ፡፡ የተረሳ ስል ግጥሞቹ ተሰብስበው በመጽሐፍ መልክ አልወጡም፡፡ ከአቶ መንግሥቱ ለማ ጋርም ጓደኞች ነን፡፡ አንዳንዶቹን ግጥሞቹን በጣም አደንቃቸው ነበር፡፡ እሱ እኔ ላይ ተፅዕኖ ሳይኖረው አይቀርም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም መጻፍ ሳልጀምር ነው የሱን ግጥም እሱ ሲያነብ መስማት የጀመርኩት፡፡ እንዲያውም ልጅነት ውስጥ ‹‹ቱሉዝ ገምቤላ›› የምትል አንድ ግጥም አለች፡፡ እሷ ያለጥርጥር የመንግሥቱ ተፅዕኖ አለባት፡፡

አንዳንድ ጸሐፊዎች ወይም ገጣሚዎች አካባቢያቸው ያለውን የሰው ሕይወት ሆነ፣ የማኅበራዊ ሆነ፣ የመሬት አቀማመጥ፣ ቅጠላ ቅጠሉን ይጽፋሉ፡፡ አንዳንድ ደግሞ ከሐሳብ ነው የሚጽፉት ግብ አላቸው፡፡ ወይ የማስተማር ወይ የመቀስቀስ (እንደ ፉከራ) ወይ ሕይወት ከበደኝ ብሎ እሮሮ የማሰማት ዓለማ አለው፡፡ ሌላው መንገድ የሰው ልጅ ውጪው ብቻ ሳይሆን ውስጡም ሕይወት አለውና የውስጡ ብዙ ጊዜ እውጪ አንፀባርቆ አይታይም፡፡ እኔን በተለይ የሚስበኝ ይኼ ነው፡፡ ነገር ግን ወስኜ ‹‹ጥበብ ለጥበብነቱ ሲባል›› ብዬ ተነስቼ አላውቅም፡፡ ልጅም ሆኜ ወደዚያ ይስበኝ ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ በልጅነቴ የመጀመሪያዬን ግጥም 10 ሳንቲም ነበር ሸጥኳት፡፡ ጎረቤታችን የነበረች አንድ ወጣት ሴት ከአንድ ወጣት ጋር ፍቅር ይዟት 10 ሳንቲም ከፍላ እሷ ናት ግጥም ያጻፈችኝ፡፡  የግጥሙም አለመወደድ ይሁን ወይም የሷ የትም አልደረሰም፡፡ እና እሱ ተፅዕኖ አሳደረብኝ፣ ግብ ለማጣት አይለም፡፡ ግብ መጀመሪያ ላይ ወስኜ እንዲህ ይሁን ብዬ አልነበረም የምጽፈው፡፡ ውስጤ ያለውን እንደመጣም ነበር የምጽፈው፡፡

አሁን ደግሞ ለኔ እንደሚመስለኝ ዛሬ የምጽፈው ግጥም ሳየው ግጥሙን አንብቤ የሚለው ሁሉ ዛሬ ካወቅሁት ባይታተም ግዴለኝም፡፡ አሜሪካ እንድ አሥራ ሦስት ግጥሞች አንድ የግጥም መድበል ውስጥ ወጥተዋል፡፡ እንግሊዝ አገርም አንድ ሁለት ወጥተዋል፡፡ ካናዳም ወጥተዋል፡፡ እና እንዳጋጣሚ ወዳጅ አግኝቷቸው ፎቶ ኮፒ ልኮልኝ ሳያቸው ያኔ ምን እንደሆኑ አላውቃቸውም ነበር፡፡ አሁን ነው የምረዳቸው፡፡ አንብቤው ግጥሙ በሙሉ ለራሴ ግልጽ ሆኖ ከታየኝ የትናንትናውን፣ ያለፈውን እንደማወራ መስሎ ስለሚሰማኝ አላስቀምጣቸውም፡፡ ግጥም እንደዚህ መጻፍ ጥሩ አይደለም ማለቴ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ አናፂ ሆነ ጸሐፊ የየራሱ ባህርይ ስላለው የኔ ባህርይ ወደ ውጭው አይደለም ማለቴ ነው፡፡ ግብ በሚመለከት ግን እኔ ባልወስነውም ያገኛል፡፡

ጓደኛሞች

ከስብሐት ገብረእግዚአብሔርና ከተስፋዬ ገሰሰ ጋር አብሮ አደጎች ነበርን፤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፡፡ ውጭ ሁላችንም የራስ የራሳችን ጓደኞች ነበርን፡፡ ሲመሽ ሁላችንም አንድ ሰፈር ነበር የምንሄደው ውቤ በረሃ፡፡ አንዳንዴ አብረን እንሄዳለን እንጂ የውቤ በረሃ ጓደኞቼ እነስብሐት አልነበሩም፡፡ ሦስታችን ስንገናኝ ሥነ ጽሑፍ በብዛት እናነብ ነበር፡፡ ስብሐት ያን ጊዜም ቢሆን ግጥም አልነበረም የሚጽፈው፣ አጫጭር ልቦለዶች ነው፡፡ ተስፋዬ ግጥምም ይሞካክር ነበር፡፡ እኔ ወደ ግጥም ነበር የማደላው፡፡

ስብሐት መጀመሪያ ጽፎ አስደንቆኝ ያየሁት ኤክስ አን ፕሮቫንስ ሆኖ የጻፈውን ነው፡፡ እኔ ፓሪስ ነበርኩ፡፡ ላየው ስለፈለኩ መንገድ ላይ መኪና እየለመንኩ ደረስኩ፡፡ ይች ትኩሳት ተብላ የወጣችው ያኔ ስትጻፍ ነበረች አጀማመሯን አየሁት፡፡ ከዚያ ደግሞ እዚህ መጥቼ በእጅ ተገልብጠው ቀበና በላይ እንግሊዝ ተማሪ ቤት በታች ሲኖር አስነበበኝ፡፡ የኔንም አብረን እናነብ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ እህቴን አገባ፤ ሃና ይልማን፡፡ ከመንገድ ወዲህና ከመንገድ ወዲያ ስለምንኖር ሁልጊዜ ማታ ማታ እንገናኝ ነበር፡፡ ስብሐትና ተስፋዬ በወንድምነትም በጓደኝነትም እንደ ወንድሞቼ የሚቀርቡኝ ናቸው፡፡

ከነገብረክርስቶስ ደስታ፣ መንግሥቱ ለማ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ዮሐንስ አድማሱ ጋር ያገናኘን ሥነ ጽሑፍ ነው፡፡ ከዚያ ተነስቶ ነው ጓደኞች የሆነው፡፡ ከዮሐንስ ጋር ትንሽ እንዳንቀራረብ ያደረገን የሥነ ሐሳብ መለያየት ሳይሆን ሐረር ሊያስተምር መሄዱ ነው፤ የምንገናኘው ሲመጣ ነበር፡፡ የሚገርመኝ ነገር እኔ የሱን ግጥም ሳነብ በሐሳብ ተለያየን ብዬ አልነበረም የማስበው፤ ‹‹ይኼ ዮሐንስ አድማሱ ነው›› ነው የምለው እሱም አንስቶት በዚህ ስንከራከር አላውቅም፡፡ ሲያነብ ግን ይኼ ሰሎሞን ነው ይላል፡፡ ሳናነብበት መለያየታችንን ተቀብለን የምንናበብ ይመስለኛል፡፡

ገብረክርስቶስ ዊንጌት አብረን ስንማር እሱ ሥዕል ነበር የሚሠራው፤ ጀርመን አገር ሲማርም ሄጄ ጎብኜቸዋለሁ፤ ከእስክንድር ጋር፡፡ መጀመሪያ ግጥም ያነበበልኝ እዚያ ነው፤ ኮለን አጠገብ ይኖር ነበር፡፡ ምንም እንኳ ሥዕሎቹ ቆንጆ ቢሆኑም የሚያስደንቁኝ የአማርኛ ግጥሞቹ ነበሩ፡፡ ከዚያ መጥተን እዚህ ቀጠልን፡፡

ያን ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምም ይጻጽፍ ነበር፤ አሁን ትቶ እንደሆነ አላውቅም፡፡ እሱም አንዱ ባለጠበል ነበር፡፡ ዳኛቸው አይመጣም፡፡ ተጎትቶ ካልሆነ ከሰው አይቀርብም ነበር፡፡ ከኔ ጋር ግን ውጭም ወዳጆች ነበርን፡፡

‹‹ልጅነት›› ታትማ ስትወጣ በመጠኑ ቁጣ ወረደባት፡፡ የኢትዮጵያን የግጥም አወራረድ አበላሽ፤ ከፈረንጅ ያመጣው ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ሱሪያሊስቶቹን ገልብጦ ነው ምናምን ይባል ነበር፡፡ የማስታውሰው የምስጋና ጽሑፍ ያገኙሁት ከዳኛቸው ወርቁ ብቻ ነው፡፡ የደረሰኝ የምስጋና ጽሑፍ የቄስ ጽሕፈት ይመስል ነበርና የሱ መሆኑን ያወቅሁት በኋላ ስንቀራረብ ነው፤ አልፈረመባትም ነበር፡፡ እንደ አጋጣሚ ደግሞ እኔ ‹‹አደፍርስ››ን አግኝቼ ሳነብ ‹‹ማነው ልጅነትን የጻፈው?›› ብሎ ሲፈልግ ነው የተገናኘነው፡፡ በጣም በጣም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም ቦታ ከማደንቃቸው ጸሐፊዎች ዳኛቸው አንዱ ነው፡፡ በሁሉም ሳይሆን በአደፍርስና በ The Thirteenth Sun:: በአጠቃላይ ግን አንድ ጸሐፊ አንደ ደህና ነገር ከጻፈ በኋላ ሕይወቱ ካልተለወጠ ድግግሞሽ ነው የሚጽፈው፡፡

እነ ዳኛቸው ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ያደረጉት አስተዋፅኦ ከሁሉ የበለጠ ስታይል (አማርኛ ምን እንደምለው አላውቅም) ይመስለኛል፡፡ ይኸውም የስብሐትን የአማርኛ አጻጻፍ የትም ባየውና ባይፈርምበትም የስብሐት መሆኑን አውቃለሁ፡፡ መጀመሪያ መቅለሏ፣ የአረፍተ ነገሩ ማጠር፣ ቁጭ ብለህ የምትነጋገር ነው የሚመስልህ፡፡ አማርኛ አሁንም ብሶበታል፤ ገመድ ሆኗል፡፡ የዳኛቸው ደግሞ የስብሐት ተቃራኒ የሆነ ነው፡፡ ግን ገመድ አለበትም፡፡ የመንግሥቱ ለማ ሌላው ቢቀር ‹‹ማን ያውቃል›› የምትል ግጥም አለች፡፡

የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ

ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ

                ማን ያውቃል?

የምትል፡፡

አንድ ጸሐፊ ሁልጊዜ ተነባ የምትታወስና የሰውን መንፈስ ፍላጎት የምትቀሰቅስ ከጻፈ ዕድለኛ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እና የመንግሥቱ ለማ ይኼ ግጥም አለ፤ ሌሎችም አሉት፡፡ ትያትሮችም አሉ፡፡ መንግሥቱ ለማ ፌዘኛና ተሰጥኦ ነበረው፡፡ ሌላ እንደሱ ተሰጥኦ የነበረውም አቶ ነጋሽ ገብረማርያም ነው፤ አሁንም ይጽፍ እንደሆነ አላውቅም፡፡ በጣም ለማሳቅ ስጦታ ያለው፡፡

እስክንድር አሁን በቅርብ ‹‹Ethiopian Birr›› በሚል መጽሔት አንድ ረዘም ያለ ድርሰት ስለሱ በእንግሊዝኛ ጽፌ ነበር፡፡ ያው እዚያ ያልኩትን ነው የምደግመው፡፡ እስክንድር በኢትዮጵያ ሥነ ሥዕል ውስጥ የተለየ ቦታ ያለው ይመስለኛል፡፡ የተለየ ቦታ ያለው ስል ከሌሎቹ ሁሉ ይልቃል ለማለት ሳይሆን ጨክኖ መንገድ ክፍቷል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ መንገድ ሲከፍት ደግሞ ፓሪስና ሎንደን አሥር ዓመት ከተማረ በኋላ (እውነቱን ለመናገር አልተማረም ከሠዓሊዎች ጋር በመዋል፤ ሙዚየሙም ውስጥ ጊዜ ከማሳለፍ፣ ከማጠንጠን ተነስቶ) ከፈረንጆቹ ተፈናቅሎ ወደ አፍሪካ ትራዲሽን በጠቅላላው፣ በተለይ ደግሞ የምዕራብ አፍሪካ ቅርፆች ተፅዕኖ አሳደሩበት፡፡ የነ ኤምስጋርቱቶላ ጽሑፍ ተፅዕኖ አሳደረበት፡፡ ከዚያ ተላቆ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1966 እንደገና መንገድ ለመለወጥ በጣም ዝግጁ ሆኖ መጣ፡፡ መጥቶ የአክሱምን፣ የጎንደርን፣ የላሊበላን፣ የወላይታ ቅርፃ ቅርፆችን፣ ኦሮሞ መቃብር ላይ የሚቆሙትን፣ ሐረር ዋሻ ውስጥ ያሉትን አየና አንድ ጊዜ ጭንቅላጹን በረገደው፡፡ ተመልሶ ያንን ሊሠራ ሲችል ተላቀቀና ወደዚህ ዞረ፡፡ አሁን የኢትዮጵያን ሥዕሎች ዞሬ አላሁም እንጂ ለብዙ ጊዜ ተፅዕኖው ይታ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ሰንፈው ነው፡፡ ባትሰንፍም የአንዳንድ ሰው ሥዕል አንድ ጊዜ ካየኸው አይለቅህም፡፡ የእስክንድር ሥዕሎች ሲታዩ አዲስ ነገር ይመስላሉ፤ ደግመህ ስታየው አብረኸው ያደግኸው ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያን ሥዕሎች ጥንት የነበሩት ጎንደር ደብረብረሃን ሥላሴ ያሉት ሥዕሎች የሚያስደንቁ ናቸው፡፡ ከዚያ ወዲህ ጨክኖ ዓይኑን ወደዚህ ዞር ያደረገና ታይቶት የሠራ ነው፡፡ በቅርብ ካሉት ውስጥ በጣም የማደንቀው ሠዓሊ እሱ ነው፡፡ ይልቃል አይደለም አደንቀዋለሁ ነው የምለው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...