Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለም‹‹ውስጠ ወይራ›› የተባለው የሳዑዲ ዓረቢያ ልዑላንና ባለሀብቶች እስር

‹‹ውስጠ ወይራ›› የተባለው የሳዑዲ ዓረቢያ ልዑላንና ባለሀብቶች እስር

ቀን:

ለሳዑዲ ዓረቢያ ልዑላን ቤተሰቦች፣ ጎምቱ ባለሀብቶች፣ እንዲሁም ሚኒስትሮች የቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት መልካም አልነበረም፡፡ አሥራ አንድ ልዑላን፣ በሥራ ላይ የነበሩ አራት ሚኒስትሮችና ቁጥራቸው ያልተገለጸ የቀድሞ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም ባለሀብቶች ቀድሞ የተቀነባበረ ነው በተባለ ሴራ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

የሳዑዲ መንግሥት ከሙስና ጋር በተያያዘ ከዚህ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ እንደሚችሉ ያስታወቀ ቢሆንም፣ ወጣቱ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን በሳዑዲ ዓረቢያ ፖለቲካና ንግድ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑትንና ተቀናቃኞቹን ለማፅዳት የከወነው ነውም ተብሏል፡፡

የሳዑዲው አል ዓረቢያ ጋዜጣ አሁን የተጀመረው ምርመራ እ.ኤ.አ. በ2009 በጅዳ ተከስቶ የነበረውን ጎርፍና በ2012 በሳዑዲ የተከሰተውን ሜርስ ቫይረስ ተከትሎ እንደሆነ ቢያስታውቅም፣ የፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ የ32 ዓመቱ አልጋ ወራሽ ልዑል ሰልማን የራሱን የፖለቲካ ምኅዳር ለማጠናከርና መሠረት ለመጣል የወሰደው ዕርምጃ ነው ብለዋል፡፡

- Advertisement -

የቢቢሲው የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ ፍራንክ ጋርድነርም አልጋ ወራሹ የፖለቲካውን፣ የንግዱንና የእስልምናውን አጠቃላይ ምኅዳር ለመቆጣጠር እንቅፋት ሊሆኑበት የሚችሉ ባለሀብቶችንና ሚኒስትሮችን ከፊቱ የማስወገድ ሥራ ይዟል ይላል፡፡

‹‹ውስጠ ወይራ›› የተባለው የሳዑዲ ዓረቢያ ልዑላንና ባለሀብቶች እስር

 

በሳዑዲ ዓረቢያ የተጀመረው ሚኒስትሮችንና ባለሀብቶችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ተግባር ለዓለም የተነገረው ‹‹የፀረ ሙስና ዘመቻ›› ተብሎ ቢሆንም፣ የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ጉዳዩ ውስጠ ወይራ ነው፡፡

ልዑል አልጋ ወራሽ ሰልማን መሐመድ ቢን አልጋ ወራሽነቱን ከተቆናጠጠ ወዲህ፣ በሳዑዲው ንጉሥ ሰልማን ቢን አብዱላዚዝ አል ሳዑድ አነሳሽነት ሳዑዲ በየመን እየተደረገ ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማርገብ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንድታደርግ፣ የሳዑዲ እ.ኤ.አ. የ2030 ራዕይ ማለትም በ2030 አመጣዋለሁ ብላ ያቀደችውን ዕድገት በምትታወቅበት የነዳጅ ምርት ብቻ ሳይሆን በሌሎች የተለያዩ ዘርፎች በመግባትም የጤና፣ የትምህርት፣ የመሠረተ ልማት፣ የመዝናኛና የቱሪዝም ዘርፎችን ለማጠናከር የተነደፈውን ዕቅድ ለማስፈጸም ያለው ተነሳሽነት በዕድሜ በበሰሉት የሳዑዲ ዜጎች ዘንድ ‹‹ፈጠን አለ›› የሚል አመለካከት ቢያሳድርም፣ በወጣቶቹ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡

ኢኮኖሚውን ማጠናከርና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ በነዳጅ ምርት ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስና ከዚህ ውጪ በሆኑ ንግዶች ላይ መሰማራት፣ ከአገሮች ጋር የሚኖሩ የንግድ ልውውጦች በነዳጅ ምርት ላይ ከሚያተኩሩ ይልቅ ለሸማቹ የዕለት ፍጆታ በሚሆኑ ሌሎች ምርቶች ላይ ትኩረት ማድረግ፣ መከላከያው የጦር መሣሪያና ቁሳቁሶች ለማምረት ተጨማሪ በጀት እንዲኖረው የሚሉትን ጨምሮ የተለያዩ ዓላማዎች ያሉትን የአገሪቱ የ2030 ዕቅድ፣ ልዑል አልጋ ወራሹ ‹‹ወደፊት›› ብሎ የተነሳበት ቢሆንም፣ ለወግ አጥባቂዎቹም ሆነ በነዳጅ ምርት ላይ ተሰማርተው ቱጃር ለሆኑት ባለሀብቶች እንዲህ በቀላሉ የሚዋጥ አልሆነም፡፡

ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ መፍቀድን ጨምሮ በተለይ ለምዕራቡ ዓለም የቀረቡ ልማዶችን ወደ ሳዑዲ በመሳብ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት የሚተጉት ንጉሡና አልጋ ወራሹ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ ዘመናዊነትንና አዲስ ዓይነት ምልከታ የማምጣቱ አካሄዳቸው በወጣቱ ይሁንታን ያስገኘላቸው ቢሆንም፣ በወግ አጥባቂዎቹና ለዓመታት ንግዳቸውን እየተቀባበሉ በቆዩት ልዑላውያን ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

‹‹ውስጠ ወይራ›› የተባለው የሳዑዲ ዓረቢያ ልዑላንና ባለሀብቶች እስር

 

የሰሞኑ የእስር ዕርምጃም ሳዑዲ ዓረቢያ እየተገበረች ያለችውን አዲስ አካሄድ የማይቀበሉትን ከማደን ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አል ዓረቢያ ጉዳዩን ከሙስና ጋር ቢያያይዘውም፣ ተግባራዊ ይደረጋሉ የተባሉ 80 አዳዲስ ፕሮጀክቶች ቀድመው ንግድን ርስት ላደረጉት የተወሰኑ ባለሀብቶችና ልዑላን ቤተሰቦች አስደንጋጭ እንደሆኑም ተነግሯል፡፡ ይህን መሰል ተቃርኖ ቢኖርም የሳዑዲ መንግሥት ‹‹በሙስና ላይ የጀመርኩት ዘመቻ ይቀጥላል፤›› ሲል ማክሰኞ ዕለት አስታውቋል፡፡

ቢቢሲ የሳዑዲ ዓረቢያን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሼክ ሳዑድ አል ሙጂብን ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ ሙሰኛ ተብለው በተጠረጠሩት ላይ የተጀመረው ዘመቻ በአገሪቱ ሙስና አለበት ተብሎ በሚጠረጠር ሥፍራ ሁሉ ከሥር መሠረቱ እስኪነቀል የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በልዑል አልጋ ወራሹ የሚመራውና አዲስ የተዋቀረው የፀረ ሙስና ኮሚቴ ልዑላንን፣ ነጋዴዎችን፣ የቀድሞና የአሁን ሚኒስትሮችን ያሰረ ሲሆን፣ የማሰርና የጉዞ ዕገዳ የመጣል ሥልጣንም ተሰጥቶታል፡፡ ንጉሡ ደግሞ በፊናቸው የብሔራዊ ዘቡንና የባህር ኃይሉን አዛዥ ቀይረዋል፡፡ ይህም ከንጉሡ ጀርባ የልዑል አልጋ ወራሹ ጡንቻ አለ አስብሏል፡፡

ቅዳሜ ማታ የተጀመረውና ይቀጥላል የተባለው የሳዑዲ ‹‹ፀረ ሙስና ዘመቻ›› የፖለቲካ ተቀናቃኞችን የማፅዳት ህቡዕ ተግባር አለው ያስባለው ተጨማሪ ምክንያት፣ በሳዑዲ የአሲር ግዛት ምክትል ገዢ ልዑል መንሱር ቢን ሙክሪን ከብዙ ባለሥልጣናት ጋር የቅኝት ሥራ ጨርሰው ወደ ሳዑዲ በመመለስ ላይ እያሉ ሔሊኮፕተራቸው በሳዑዲና በየመን ድንበር ተከስክሶ መሞታቸው ነው፡፡

አል ኢክቤሪያ ዜና አገልግሎት እንደሚለው፣ ሔሊኮፕተሩ የተከሰከሰበት ምክንያት አልታወቀም፡፡ ሆኖም በአጠቃላይ ከ40 የሚበልጡ ልዑላን ባለሀብቶችና ሚኒስትሮች በቁጥጥር ሥር በዋሉ ማግሥት ልዑል ሙክሪንና ቁጥራቸው ያልተገለጸ ባለሥልጣናት በሔሊኮፕተር መከስከስ አደጋ የመሞታቸው ዜና መሰማቱ፣ አልጋ ወራሹ ሥልጣኑን ለማራዘም የሚያደርገው ጥረት አንድ አካል ተደርጎ ተጠርጥሮበታል፡፡

‹‹ውስጠ ወይራ›› የተባለው የሳዑዲ ዓረቢያ ልዑላንና ባለሀብቶች እስር

 

ልዑል ሙክሪን የቀድሞው አልጋ ወራሽ ሙክሪን ቢን አብዱል አዚዝ ልጅ ሲሆን፣ አብዱልአዚዝም የንጉሥ ሰልማን የእንጀራ ወንድም ናቸው፡፡ ንጉሥ ሰልማን ንግሥናውን እ.ኤ.አ. በ2015 ካገኙ ከጥቂት ወራት በኋላ ባልተገመተ ሁኔታ ነበር ሙክሪን ቢን አብዱልአዚዝን ከአልጋ ወራሽነት ያነሱት፡፡

በምትኩም የ32 ዓመቱንና በሳዑዲ ሪያድ ኪንግ ሳዑድ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ያጠናውን ልጃቸውን መሐመድ ቢን ሰልማን አልጋ ወራሽ አድርገዋል፡፡ ንጉሡ 81 ዓመታቸው ሲሆን፣ የአሁኑ ዘመቻም ያላቸውን መንበር በአስተማማኝ ሁኔታ ከመተካት ጋር የተያያዘ አስመስሎታል፡፡

ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት አሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የሳዑዲ ባለሥልጣናት የወሰዱትን ዕርምጃ የሚደግፉ መሆኑን ያስታወቁ ሲሆን፣ ‹‹ንጉሥ ሰልማንና ልዑል አልጋ ወራሹ የሚያደርጉትን ያውቃሉ፣ በእነሱ ላይ ታላቅ እምነት አለኝ፤›› ሲሉም በትዊተራቸው ይፋ አድርገዋል፡፡  

በሳዑዲው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን የሚመራው የፀረ ሙስና ኮሚቴ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው መካከል ቢልየነሩ ልዑል አልዋሊድ ቢን ታላል፣ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር ኢብራሒም አል አሳፍ፣ የሳዑዲ ባህር ኃይል ኮማንደር አብዱላህ አል ሱልጣን፣ የኤምቢሲ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ባለቤት አልዋሊድ አል ኢብራሒም፣ ባለሀብቱ ሼክ መሐመድ ዓሊ አል አሙዲ፣ እንዲሁም የሳዑዲ ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን የቀድሞ ገዥ አሚር አል ዳባጋ እንደሚገኙበት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በተጨማሪም ቢሊየነሩ ልዑል አዋሊድ ቢን ታላል፣ የብሔራዊ ዘብ ሚኒስትሩ ልዑል ሚተብ ቢን አብዱላህ፣ የኢኮኖሚና ፕላኒንግ ሚኒስትሩ ልዑል አደል ፋኪ፣ የኦሳማ ቢን ላደን ወንድምና የቢን ላደን ግሩፕ ሊቀመንበር ባክር ቢን ላደን በሪያድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ሪትዝ ካርልተን በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

‹‹ውስጠ ወይራ›› የተባለው የሳዑዲ ዓረቢያ ልዑላንና ባለሀብቶች እስር

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...