• ከተሰበሰበው ገቢ 40 በመቶ ከቫት የተገኘ ነው
• የቀረጥ ነፃ መብት ያላቸው 30 ቢሊዮን ብር እንዳይከፍሉ ተደርጓል
• 904 ሠራተኞች ባለሥልጣኑን ለቀዋል
• ከአዲስ አበባ 9.4 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ባለፉት ስድስት ወራት ከተለያዩ የገቢ ዓይነቶች 64.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡ ባለሥልጣኑ በግማሽ ዓመቱ ለመሰብሰብ ያቀደው 66.09 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ ሰበሰብኩት ያለው የዕቅዱን 97.82 በመቶ ነው፡፡ ማዕከላዊው መንግሥት በ2007 በጀት ዓመት ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲሰበስብ ኃላፊነት የሰጠው 115.9 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣኑ በራሱ መንገድ ለመሰብሰበ ያቀደው ደግሞ 134.2 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ አሁን የሰበሰበው ግን በራሱ መንገድ ባስቀመጠው የተለጠጠ ዕቅድ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ታውቋል፡፡ ባለሥልጣኑ የሰበሰበው ገንዘብ ራሱ ካስቀመጠው አንፃር የ2.18 በመቶ ጉድለት ቢኖርበትም፣ ካለፈው ዓመት ግማሽ ዓመት ጋር ሲነፃፀር 21.24 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ ባለሥልጣኑ ከሰበሰበው ገቢ ውስጥ 36.5 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ፣ 28.0 ቢሊዮን ብር ከወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ፣ 63.5 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከብሔራዊ ሎተሪ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ባለሥልጣኑ ከአገር ውስጥ ከሰበሰበው ገቢ ውስጥ የተጨማሪ እሴት ታክስ 40 በመቶ ድርሻ እንዳለው ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አዲስ አበባ ከተማ የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ ከአስተዳደሩ ውክልና መውሰዱ ይታወቃል፡፡ በዚህ መሠረት በ2007 በጀት ዓመት ከአዲስ አበባ የገቢ ርዕሶች 21 ቢሊዮን ብር፣ በግማሽ ዓመቱ ደግሞ 12.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣኑ ካቀደው ውስጥ 9.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የቻለ ሲሆን፣ ይኼም ከዕቅዱ 76.07 በመቶ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢ ከዕቅዱ 2.9 ቢሊዮን ብር ወይም 23.9 በመቶ ጉድለት ቢኖረውም፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የታክስ ገቢው 76.7 በመቶ፣ ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ደግሞ በ59.5 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ተጠቁሟል፡፡ መንግሥት ትኩረት በሰጣቸው ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከቀረጥ ነፃ ማበረታቻ እንደሚሰጥ ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት በግማሽ ዓመቱ መሰብሰብ ይችል ከነበረው 30 ቢሊዮን ብር ለእነዚህ ባለሀብቶች መተው ተገልጿል፡፡ ይህ ገንዘብ በግማሽ ዓመቱ ከተሰበሰበው ጠቅላላ ገቢ 46.5 በመቶ ይሆናል ተብሏል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በአጠቃላይ ከ18,000 በላይ ሠራተኞች መያዝ የሚችል መዋቅር አለው፡፡ ነገር ግን በግማሽ ዓመቱ ብቻ 904 ሠራተኞች ተሰናብተዋል፡፡ የባለሥልጣኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳብራሩት፣ ከእነዚህ ሠራተኞች 787 የሚሆኑት በራሳቸው ፈቃድ፣ 28 በሥነ ምግባር ጉድለት፣ 89 ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ለቀዋል፡፡ ሠራተኞች የሚለቁት ባለሥልጣኑ በተሰጠው ሥልጣን ጫና ስለሚያድርባቸው ነው ወይ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ አቶ ኤፍሬም ሲመልሱ በፍፁም አይደለም ብለዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ በመምጣቱ በርካታ የግልና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተሻለ ክፍያ ይከፍላሉ፡፡ በሥነ ምግባር ጉድለት የተባረሩት ከጠቅላላው 28 ሠራተኞች ብቻ ናቸው በማለት አቶ ኤፍሬም ሠራተኞቹ የሚለቁት የተሻለ ፍለጋ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ሕገወጥ የንግድ ሥራዎችን ለመቆጣጠር ከዘረጋቸው አሠራሮች አንዱ ጠቋሚዎችን ማበረታት ነው፡፡ በዚህም በግማሽ ዓመቱ ባቀረቡት ጥቆማ ውጤታማ የተባለላቸው 147 ጠቋሚዎች 18.5 ሚሊዮን ብር ተንበሽብሸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕገወጦችን ተከታትለው ለያዙ 101 ሰዎች ደግሞ 10.75 ሚሊዮን ብር፣ በአጠቃላይ ባለሥልጣኑ ረድተውኛል ላላቸው ወገኖች 29.21 ሚሊዮን ብር ማንበሽበሹ ተገልጿል፡፡