Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተጨማሪ እሴትና የገቢ ግብር ሕጐች እንዲሻሻሉ ጥያቄ ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተጨማሪ እሴትና የገቢ ግብር ሕጐች ጥናትን መሠረት ያደረገ ማሻሻያ ሳይደረግባቸው ከአሥር ዓመታት በላይ ሥራ ላይ መዋላቸው፣ የታክስ መርህን የሚፃረር መሆኑ በጥናት ተመለከተ፡፡ ፎረም ፎር ሶቫል ስተዲስ (FSS) ጥር 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ባዘጋጀው መድረክ ላይ ‹‹የታክስ ሕጐችና ፖሊሲዎች በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ጥናታቸውን ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስና የአካውንቲንግ ትምህርት ክፍል መምህር ዶ/ር ወለላ አቤሆዴ እንዳብራሩት፣ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ለውጦች የተስተዋሉ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. በ2002 ሥራ ላይ የዋሉት እነዚህ የግብር ዓይነቶች ይህ ነው የሚባል ለውጥ ሳይደረግባቸው ለአሥራ ሦስት ዓመት መዝለቃቸው ችግር ነው፡፡ ‹‹ታክስ በባህሪው ለውጦች ከሥር ከሥር እየታዩ ሁኔታዎች እንዲጣጣሙ የሚጠይቅ ነው፡፡ ነገር ግን ሕጐቹ ብዙ ለውጥ ሳይደረግባቸው በሥራ ላይ ይገኛሉ፤›› ብለዋል የጥናቱ አቅራቢ፡፡ በእነዚህ የታክስ ሕጐች ላይ ለውጥ ሳይደረግ እስካሁን ሥራ ላይ መዋላቸው የፈጠረውን ተፅዕኖ የሚያመለክተው ጥናቱ፣ የገቢ ግብር ሕግን በመጥቀስ በሕጉ መሠረት የሠራተኛ ደመወዝ የመጀመሪያው 150 ብር ከታክስ ነፃ ቢሆንም በዛሬ ግሽበት የዚህ ገንዘብ መጠን ከግብር ነፃ መሆን ትርጉም የሚሰጥ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህ ከድህነት ወለል አንፃር ቢታይም ትርጉም የሌለው መሆኑን፣ የቢዝነሶች ከግብር ነፃ የሚሆንበት የመጀመሪያው 1,800 ብርም በተመሳሳይ ትርጉም አልባ አሠራር መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ በተመሳሳይ የገቢ ግብር የምጣኔ ወሰኖች ቢታዩ፣ ከፍተኛው የገቢ ግብር መጣል የሚጀምርበት 5,000 ብር አቅሙ የተሸረሸረ በመሆኑ የታክስ መጠኑን ማሻሻል የግድ እንደሆነ ጥናት አቅራቢዋ ገልጸዋል፡፡ የድርጅቶች ደረጃ የሚለካበት አንዱ መሥፈርት የዓመታዊ ሽያጭ ወሰን ሲሆን፣ ይህም በግሽበቱ እየተሸረሸረ በመሆኑ ደረጃ ‹‹ሀ›› ውስጥ የነበሩ ወደ ‹‹ለ›› እና ከዚያም በታች እየሆኑ እንዲገኙ በማድረግ ቢዝነሶች የማይሆን ምድብ ውስጥ እንደሚገቡ ከማድረጉ ባሻገር፣ በተለይ በአነስተኛ ቢዝነሶች ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ ጥናቱ በገቢና በሽያጭ የገቢ ግብሮች ግሽበትን ባገናዘበ መንገድ (Inflation Adjusted) የተጣሉ ባለመሆናቸው ገቢ በትክክል (In Real Terms) ሳይጨምር እንደጨመረ ታሳቢ ተደርጐ ግብር ከፋዩ ላይ እየተጣሉ ናቸው ይላል፡፡ ምንም እንኳ የተወሰኑ ጉልህ ችግሮች ቢኖሩም፣ የአገሪቱ የታክስ ሕግ መሠረታዊ ችግር አለበት የሚባል እንዳልሆነና ይልቁንም ለታክስ ሥርዓቱ ትልቅ ችግር እየሆነ ያለው የታክስ አስተዳደሩ አቅም ውስን መሆን እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል፡፡ ለዚህ እንደማሳያ የተጠቀሰው ከአገሪቱ 32 ዩኒቨርሲቲዎች በመቀሌና በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ የታክስ ፕሮግራም በድኅረ ምረቃ የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡ በአስተዳደሩ የሚቀጠሩት በአካውንቲንግ፣ በማኔጅመንት፣ በሕግና በመሰል ዘርፎች የሠለጠኑ ምሩቃን ጥቅል የሆነ የታክስ ዕውቀት ሊኖራቸው ቢችልም የታክስ አስተዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ብቃት እንደማይኖራቸው ዶ/ር ወለላ ገልጸዋል፡፡ የግብር መክፈል ባህል ደካማ መሆን የታክስ ከፋይና የታክስ ሰብሳቢ ውዝግብ አፈታት ሥርዓት ብቃት የሌለው በመሆኑ እንደሆነ በጥናቱ የተመለከቱ ሌሎች ችግሮች ናቸው፡፡ ውዝግብ በተፈጠረ በአሥር ቀናት ውስጥ አቤቱታ ማቅረብ ግዴታ መደረጉ አስፈላጊ ማስረጃዎችንና ሰነዶችን አሟልቶ ለማቅረብ ጊዜው አጭር ከመሆኑ አንፃር ሥርዓቱን ተወቃሽ እንደሚያደርግ ጥናቱ ያስረዳል፡፡ በአቤቱታ አቀራረብ ሒደት ውስጥ ይግባኝ ለማለት ግብር ከፋዮች ግማሽ በመቶ የተጣለባቸውን ግብር በቅድሚያ መክፈል ግድ መሆኑም ጥያቄ የሚነሳበት ሌላው ነጥብ ነው፡፡ ቀዳሚው ጥያቄ ግማሽ በመቶ መከፈል አለበት ሲባል የዚህ መሠረቱ ምንድነው? የሚለው እንደሆነ አጥኚዋ ያስረዳሉ፡፡ የውዝግብ ሒደቱ ረዥም ዓመታት የሚወስድ መሆኑ፣ አብዛኛውን ጊዜ ውሳኔዎች ወደ ታክስ አስተዳደሩ ያመዘኑ መሆናቸውም በግብር ከፋዮች ዘንድ በተደጋጋሚ እንደሚገለጽ ጥናቱ ያሳያል፡፡ ጥናቱ ካስቀመጣቸው ምክረ ሐሳቦች መካከል ረዥም ጊዜ ባስቆጠሩ ንብረቶች ላይ የተጣሉ ግብሮችን ማሻሻልና የአነስተኛ ቢዝነሶች የግብር ጫናን ማቅለል የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በአሁኑ የወቅት የገቢ ግብርን የሚመለከተው ሕግ በመሻሻል ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ በየጊዜው በሚያካሂዳቸው የውይይት መድረኮች ላይ እንደ ርዕሰ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶችና የሲቪል ማኅበራት ኃላፊዎች የሚገኙ ቢሆንም፣ በዚህ መድረክ ላይ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የተገኘ ተወካይ አልነበረም፡፡ ለሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ጥሪ የተላለፈ መሆኑን ግን ከፎረሙ ለመረዳት ተችቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች