Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ተግባራዊ ሳይንስ በአገራችን ገና አልዳበረም››

አቶ ኢዩኤል ኃይሉ፣ የስቴም ሲነርጂ የቴክኖሎጂ ኃላፊ

      ስቴም ሲነርጂ ከስምንት ዓመት በፊት የተቋቋመ የተራድኦ ድርጅት ነው፡፡ በምሕፃረ ቃል ስቴም የሚባለው ድርጅቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግና ማቴማቲክስ (ሒሳብ) የሚሠራ ሲሆን፣ 13 ማዕከሎች በተለያዩ አካባቢዎች አቋቁሟል፡፡ ታዳጊዎች በተግባር የተደገፈ የሳይንስ ሥልጠና እንዲያገኙ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ፣ የሳይንስ ሙዚየሞች በማቋቋምና ሳይንሳዊ ውድድሮች በማካሄድም ይታወቃል፡፡ ድርጅቱ ማኅበረሰብ አቀፍ ስቴምን በተመለከተ አዲስ ፕሮጀክት በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ ስለ ፕሮጀክቱና አጠቃላይ የተቋሙ እንቅስቃሴዎች የስቴም ሲነርጂ የቴክኖሎጂ ኃላፊ አቶ ኢዩኤል ኃይሉን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ስቴም ሲነርጂ የተቋቋመው እንዴትና ምን ዓላማ አንግቦ ነበር?

አቶ ኢዩኤል፡- ስቴም ሲነርጂ የተቋቋመው ጄኤፍሲቲ የተራድኦ ድርጅትን ተከትሎ ነው፡፡ ድርጅቱ በአንድ ሰው የሚደገፍ የቤተሰብ ድርጅት ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የሄዱ ቤተ እሥራኤላውያን ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ልጆችን ይደግፉ ነበር፡፡ ልጆቹ የሚረዳቸውን ሰው በሮቦቲክስ ውድድር እንዲያስገባቸው ይጠይቁታል፡፡ በሮቦቶቲክስ ውድድር ከሚሳተፉ ልጆች ጋር ያለውን ውድድር አትችሉትም አላቸው፡፡ ሆኖም ደጋግመው ሲጠይቁት ተቀበላቸው፡፡ በሚገርም ሁኔታ ልጆቹ ሦስተኛ ወጡ፡፡ በዚህ ወቅት የልጆቹ የትውልድ ቦታ ብሄድ ብዙ ታዳጊዎችን እደግፋለሁ ብሎ ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡፡ የመጀመርያውን ፎቃ ስቴም ማዕከል በቢሾፍቱ ከተማ አቋቋመ፡፡ በጄኤፍሲቲ የተጀመረው መልካም ነገር እንዲቀጥልና የሚደግፉ ተቋሞች እንዲሳተፉ አሜሪካ ላይ የተራድኦ ድርጅቱን አቋቋምን፡፡ ዓላማችን ስቴምን በ13ቱ ማዕከሎቻችን ማብቃት ነው

ሪፖርተር፡- የስቴም ሲነርጂ ዋና ዋና ተግባሮችን ቢገልጹልን?

አቶ ኢዩኤል፡- አንደኛው የስቴም ማዕከሎችን ማስፋፋት ነው፡፡ የስቴም ተደራሽነትን ለማስፋፋት በእያንዳንዱ ክልል ቢያንስ አንድ ማዕከል አለን፡፡ ማዕከሎቹ ከዩኒቨርሲቲዎች ተቀናጅተው መደበኛ ቅርፅ ይዘዋል፡፡ የስቴም ማዕከሎችን የማስፋፋት ሥራችን ስኬታማ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ሁለተኛው የሳይንስ ሙዚየም ነው፡፡ በአዲስ አበባ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ የሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም ከ40 በላይ አሳታፊ ኤግዚቢቶች አሉት፡፡ ማንኛውንም አደጋ መቋቋም የሚችሉ መሣሪያዎች አሏቸው፡፡ ልጆች እየተጫወቱ ሳይንስ የሚማሩባቸው ናቸው፡፡ ሦስተኛው ከእሥራኤል የወሰድነው ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ነው፡፡ የመጀመርያውን የከፈትነው ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ በየዓመቱ በአካባቢው ያሉ በሳይንስ ትምህርቶችና በሒሳብ የላቀ አቅም ያላቸው ተማሪዎችን ይቀበላል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ማስተርስና ፒኤችዲ እንዲሁም በሙያው ልምድ ያላቸው መምህራን ያስተምራሉ፡፡ ተማሪዎቹ የቀረውን የሳይንስ ትምህርት በመደበኛ ትምህርት ቤታቸው ያገኛሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- በማዕከሉ ትምህርት የሚሰጣቸው በየትኛው ዕድሜ ክልል ያሉ ናቸው? መመዘኛ መስፈርታችሁስ ምንድነው?

አቶ ኢዩኤል፡- በሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የምንቀበለው ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ ተማሪዎችን ነው፡፡ ተማሪዎቹን የምንቀበለው የስምንተኛ ክፍል የሚኒስትሪ ውጤታቸውን አይተን ሲሆን፣ ከትምህርት ቤት የሚሰጣቸው ትራንስክሪፕትም ይታያል፡፡ ተማሪዎቹ መግቢያ ፈተናም ይወስዳሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ተማሪዎቹ በሳይንስ ትምህርቶች ብቁ እንዲሆኑ ከማሠልጠን በተጨማሪ ተግባራዊ ሳይንስን ለማስገንዘብ ምን ዓይነት ስልቶች ትጠቀማላችሁ?

አቶ ኢዩኤል፡- ልጆቹ በመደበኛ ትምህርት ቤት ፊዚክስ ይማራሉ፡፡ የሚጎላቸው ተግባራዊ ዕውቀት ነው፡፡ እኛ ጋ ፊዚክስን በንድፈ ሐሳብ ሳይሆን በተግባር ይማራሉ፡፡ ሳይንስን በተግባር የሚያሳዩ መሳሪያዎች አሉን፡፡

ሪፖርተር፡- ውጤታማነታችሁን የምትመዝኑት በምን መንገድ ነው?

አቶ ኢዩኤል፡- ሥራ ከጀመርን ስምንት ዓመታችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተግባራዊ ሳይንስ ተደራሽነት ክፍተት ነበር፡፡ አሁንም አለ፡፡ እኛ ጋ ሥልጠና የጀመሩ ልጆች አሁን ዩኒቨርሲቲ ናቸው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ በምናገኘው ምላሽም ልጆቹ ጥሩ እንቅስቃሴ አላቸው፡፡ ልጆቹ በፈጠራ ሥራም የተካኑ ናቸው፡፡ መጀመርያ ስለ ደኅንነት ይማራሉ፡፡ ከዛ በሥራ ወቅት መቃጠል ያለበት ይቃጠላል፡፡ በሥራ ወቅት ለሚከሰተው ነገር በሙላ ኃላፊነቱን እንወስዳለን፡፡ ስለዚህ በነፃነት የፈጠራ ችሎታቸው ያድጋል፡፡ አንድ ችግርን እንዴት መፍታት እንደሚችሉ እናስተምራለን፡፡ በመጨረሻ ፕሮቶታይፕ (የፈጠራ ሥራ ሞዴል) እንዲያወጡ እናደርጋለን፡፡ ልጆቹ ለማኅበረሰባቸውም አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ቤታቸው ውስጥ የሚገጥማቸውን ችግር እንደ ችግር መቀበል ሳይሆን መፍትሔ መስጠት ይመርጣሉ፡፡ የኛ ውጤት ልጆቹ ችግሮችን እየፈቱ መቀጠላቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበረሰቡን ችግርን በመፍታት ከሚጠቀሱ የፈጠራ ውጤቶች ጥቂቱን ቢነግሩን?

አቶ ኢዩኤል፡- ትልቁና 12 ቤተ ሙከራ ያለው ማዕከላችን ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ፣ መቐለ፣ ጎንደር፣ ሐዋሳ፣ ቢሾፍቱ፣ አፋር፣ ጋምቤላና አሶሳም ማዕከል አለን፡፡ የኮተቤው ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ወደ 400 ተማሪዎች አሉት፡፡ በቅርቡ ባካሄድነው የሳይንስ ፌር ውድድር ላይ ከተሳተፉት አንጋፋው የቢሾፍቱ ፎቃ ማዕከል ይገኝበታል፡፡ አንድ ልጅ ለዓይነ ስውራን የሚሆን ዱላ (ስማርት ስቲክ) ፕሮቶታይፕ ሠርቷል፡፡ ዓይነ ስውራን ከፊታቸው አንዳች እንቅፋት ሲኖር ቫይብሬት በማድረግ (በመንቀጥቀጥ) የሚያሳውቅ በኪስ የሚያዝ ዱላ ነው፡፡ ስማርት ግሪን ሐውስ የሠሩ ልጆችም አሉ፡፡ መሳሪያው ለምሳሌ ለአበባ እርሻ ውኃ፣ ማዳበሪያና ንፋስ ሲያስፈልግ ያሳውቃል፡፡ በጎንደር ማዕከል በባዮጋዝ የሚሠራ ጄኔሬተር የሠራ ልጅም አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ፈጠራዎቹ መሬት ላይ ወርደው ካልተተገበሩ ሐሳብ ብቻ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ፕሮቶታይፖቹን ማኅበረሰቡን ወደሚጠቅም ፈጠራ ለማምጣት የምታደርጉት ጥረት አለ?

አቶ ኢዩኤል፡- ቀጣዩ ሥራችን እሱ ነው፡፡ ልጆቹ ችግርን እንዴት እንደሚፈቱ እያወቁ ነው፡፡ የፈጠራውን ፓተንት (የፈጠራ ሕጋዊ ባለቤትነት) ሒደት የሕግ ክፍላችን ያስጨርሰዋል፡፡ ፈጠራዎቹን ወደ ማኅበረሰቡ ለማምጣት በቀጣይ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች እንዲሳተፉ ግንዛቤ እንፈጥራለን፡፡ የሚፈጥሩት ልጆች ሕጋዊ የፈጠራ ባለቤትነት ተከብሮ ብዙኃኑ በሚጠቀሙበት መልኩ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች በብዛት የሚያመርቱበትን ሁኔታ በቅርቡ እናስተዋውቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- በስቴም የሚሳተፉት ወንዶች ቁጥር ከማመዘኑ አንፃር፣ ድርጅታችሁ ምን ያህል ሴቶችን ያሳትፋል?

አቶ ኢዩኤል፡- ለወንዶችም ለሴቶችም እኩል ዕድል አለን፡፡ ሴቶችን ለማበረታታት በአነስተኛ ውጤት መቀበል ጀምረን ነበር፡፡ ልጆቹ እንደሚችሉ እየነገሩን ተጨማሪ ድጋፍ ለመስጠት በመሞከራችን ቅሬታ አስነስቷል፡፡ ዕድሉን ከሰጣችሁን ተጨማሪ ድጋፍ አንፈልግም ተብለናል፡፡ ማንኛዋም ሴት መሥራት እስከቻለች ድረስ እንቀበላለን፡፡ ሆኖም የሴቶች ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ ከ30 እስከ 40 በመቶ ቢሆን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሳይንስ ሙዚየሞች በአገሪቱ በብዛት አይገኙምና የናንተ ሙዚየሞች ምን ዓይነት አገልግሎት እየሰጡ ነው?

አቶ ኢዩኤል፡- ሙዚየሞቹ የተለያዩ የፊዚክስ ማሳያ ኤግዚቢቶች አሏቸው፡፡ የኦፕቲክስ፣ የኤሌክትሮኒክስና ሌሎችም ኤግዚቢቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ስክሪብቷችንን ፀጉራችን ላይ አሽተን ወረቀት ወደ ላይ እናነሳለን፡፡ ይህ ስታሪክ ኤሌክትሪሲቲ ነው፡፡ ተማሪዎች ትምህርት ቤት የተማሩትን መሰል ንድፈ ሐሳብና ቀመር በተግባር ያያሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የሳይንስ ፌሮች ብዙ ባይሆኑም በመንግሥትና በግለሰቦች ተነሳሽነት አልፎ አልፎ ይካሄዳሉ፡፡ ከተመሳሳይ ሳይንስ ተኮር እንቅስቃሴዎች አንፃር ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶታል ማለት ይቻላል?

አቶ ኢዩኤል፡- ዘርፉ ብዙ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ሐሳቦች ሐሳብ ሆነው እንዳይቀሩና አገልግሎት እንዲሰጡ ይፈልጋል፡፡ ዘርፉ ግን ገና ነው፡፡ ቤተሰቦች ልጆቻቸው በማዕከሉ ለትምህርት የሚጠቅም ነገር የሚሠሩ አይመስላቸውም፡፡ ተማሪዎች አንድ ሳምንት ትምህርት ቤት በንድፈ ሐሳብ የሚማሩትን በኛ ማዕከል በአንድ ቀን በተግባር ይጨርሳሉ፡፡ ኅዳር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ሁለተኛውን የሳይንስ ፌር ከተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ)፣ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚና ሌሎችም ተቋሞች ጋር እናካሂዳለን፡፡ ልጆቹን ከየክልሉ ያሰባሰበልን ትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ውድድሮች በተደጋጋሚ ሲደረጉ የፈጠራ ሰዎችን ማፍራትና ችግሮችን መፍታት ይቻላል፡፡ ኢንቨስተሮች በነዚህ ሳይንስ ፌሮች ተገኝተው ሐሳብ አለባቸው፡፡ ያኔ ዘርፉ እያደገ ይሄዳል፡፡ እነ ሲልከን ቫሊ ዛሬ ያሉበት የደረሱት ባለሀብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆናቸው ነው፡፡ ጥሩ የፈጠራ ሥራ እስካቀረቡ ድረስ መሬት እንደማይወድቅ ያውቃሉ፡፡ በኛ አገር ከመዳደቀ ዕቃ መሥራት የሚባል ነገር አለ፡፡ ሁሌ ከወደቀ ዕቃ ፈጠራ መሠራት የለበትም፡፡ በማዕከላችን ልጆቹ ከወደቀ ነገር ብቻ ሳይሆን ከመሬት (ከዜሮ) ተነስተው መፍጠር እንደሚችሉ እናሳያቸዋልን፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት ስምንት ዓመታት ለድርጅቱ እንቅስቃሴ የሆኑ ነገሮች ነበሩ?

አቶ ኢዩኤል፡- አንደኛው ፈተና የግንዛቤ እጥረት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የምትሠሩት ምንድነው? እንባላለን፡፡ ትምህርት ቤታችን ውስጥ ቤተ ሙከራ ሥሩልን የሚሉን አሉ፡፡ ዓላማው ግን ትምህርት ቤት ውስጥ ቤተ ሙከራ ከመክፈት የዘለለ ነው፡፡ ስቴም የባዮሎጂ ወይም የኬሚስትሪ ቤተ ሙከራ ብቻ አይደለም፡፡ የግንዛቤ ክፍተቱን በተለያየ መንገድ ለመሙላት እየሞከርን ነው፡፡ ሌላው ችግር ዕቃ ወደ አገር ውስጥ ስናስገባ ያለው ቀረጥ ነው፡፡ በውድ የሚሸጡ ዕቃዎችን የሚሰጡን ዕርዳታ አድራጊዎች በነፃ ይህንን ሁሉ ዕቃ እየሰጠናችሁ እንዴት ስለ ቀረጥ ትጠይቁናላችሁ ይላሉ፡፡ በመንግሥት በኩል ቀረጥ ቢስተካከልልን ብዙ ነገር መሥራት እንችላለን፡፡ ሦስተኛው ችግር ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ወደኛ አለመላካቸው ነው፡፡ አንዳንዴም የማጠናከሪያ ትምህርት ይመስላቸዋል፡፡ ወላጆች ልጆች ማትሪክ አልፈው ዩኒቨርሲቲ ከገቡ ብቻ የሚሳካላቸው ስለሚመስላቸው አይፈረድባቸውም፡፡ ተግባራዊ ሳይንስ በአገራችን ገና አልዳበረም፡፡ አንስታይን ብዙ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ የተባረረ ሰው ነው፡፡ በተመሳሳይ ዓለም ላይ ብዙ ስኬታማ ሰዎች አሉ፡፡ ወላጆች ይህንን ቢገነዘቡ መልካም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ትምህርት ቤቶች የድርሻቸውን ይወጣሉ?

አቶ ኢዩኤል፡- ትምህርት ቤቶችስ ተባባሪ ናቸው፡፡ የፈረቃ ትምህርት ቤቶች ልጆች ከሰዓት እኛ ጋ እንዲመጡ ያመቻቹላቸዋል፡፡ ትምህርት ቤት ውስጥ የሳይንስ ክለብ ያቋቁሙና በንቃት የሚሳተፉት ይመረጣሉ፡፡ ክለቦቹን ትምህርት ቢሮ ያውቃቸዋል፡፡ ልጆቹም የሳይንስ ዝንባሌ ያላቸው ስለሆኑ ወደኛ ሲመጡ ምን እንደሚሠሩ ያውቃሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ለዚህ ዘርፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ ምንድነው?

አቶ ኢዩኤል፡- በኢትዮጵያ ስቴም የሚለው ሐሳብ መታወቁ የኛ አስተዋጽኦ ነው፡፡ አሁን ቲዲኤ የሚባል የልማት ድርጅት ሐሳቡን ገዝቶት ወደ 30 የሚሆኑ የስቴም ማዕከሎች መሥራት ጀምሯል፡፡ ይሄ የኛ ውጤት ነው ብዬ በኩራት የምናገረው ነው፡፡ ሌላው የሳይንስ ሙዚየሞቹ ናቸው፡፡ ልጅ ሆኜ በትምህርት ቤት ጉዞ ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ አንድ የሳይንስ ሙዚየም መጎብኘቴን አስታውሳለሁ፡፡ አሁን ያ ሙዚየም የለም፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው የሳይንስ ሙዚየም እንዲያዩ ቢወስዷቸው፣ ለዘለዓለም በህሊናቸው ተቀርጾ ይቀራል፡፡ በየትምህርት ቤቱ ቤተ ሙከራ ማቋቋም በጣም ውድ ስለሆነ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ማቋቋም ይመረጣል፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ 100 ቤተ ሙከራዎች ከሚሠሩ፣ ተማሪዎች በአንድ ትልቅ ቤተ ሙከራ በፕሮግራም በጥሩ ፕሮፌሰሮች ቢማሩ ይሻላል፡፡ ሌላው የኛ ውጤት ቨርቹዋል ኮምፒውቲንግ ነው፡፡ እስካሁን ወደ 70 ትምህርት ቤቶች አዳርሰናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ለኮምፒውተር ትምህርት ኮምፒውተሮች ያስፈልጋሉ፡፡ ዛሬ ዛሬ ያሉት ኮምፒዩተሮች በጣም ፈጣን ናቸው፡፡ ከፍጥነታቸው ጋር በተያያዘ የሚገዙበት ዋጋና ጥቅም ላይ ሲውሉ የሚያስወጡት (ራኒንግ ኮስት) በጣም ብዙ ነው፡፡ አገልግሎታቸው አልቆ ሲጣሉም መርዛማ ናቸው፡፡ በአንድ የኮምፒውተር ቤተ ሙከራ የሚሠሩ አዳዲስ ኮምፒውተሮች አንድ ሲስተም ኖሯቸው፣ ተርሚናል ብቻ ተገጥሞላቸው እንዲሠሩ እናደርጋለን፡፡ በዚህ መንገድ የኤሌክትሪክ ፍጆታን 90 በመቶ እንቆጥባለን፡፡ ሲወገዱም በዛው መጠን ጉዳቱ ይቀንሳል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የናንተ ዓይነት ድርጅቶችን በምን መንገድ መደገፍ አለበት?

አቶ ኢዩኤል፡- ትልቁ ችግራችን የቀረጥ ጉዳይ ነው፡፡ በተጨማሪ መንግሥት የስቴም ሐሳብን በገንዘብ መደገፍ አለበት፡፡ ዕርዳታ ፈልገን እያመጣን ሳይሆን መንግሥት በጀት መመደብ አለበት፡፡ ምክንያቱም ስቴም የአንድ አገር የጀርባ አጥንት ነው፡፡ እንደ እስራኤል ያለ ትንሽ አገር ዓለምን ቀጥ አድርገው የያዙት በቴክኖሎጂ ነው፡፡ በእርግጥ ከመንግሥት ጋር እጅና ጓንት ሆነን እንሠራለን፡፡ የክረምት ሥልጠና (ሰመር አውትሪች ፕሮግራም) ጀምረን ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ክረምት ሲዘጉ ቤተ ሙከራዎቹ ምንም ጥቅም አይሰጡም፡፡ መምህራንም አይሠሩም፡፡ ስለዚህ ክረምት ላይ ልጆችን ተቀብለው በቤተ ሙከራዎቹ መምህራኑ እንዲያስተምሯቸው እናደርጋለን፡፡ መንግሥት ጠቃሚነቱን ስላወቀ አሁን በጀት መድቦለት እየተካሄደ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ በቅርቡ ይፋ ስለሚያደርገው ኮምዩኒቲ ቤዝድ ቼንጅ ስሩ ስቴም (ማኅበረሰብን ያማከለ ለውጥ በስቴም) ቢያብራሩልን?

አቶ ኢዩኤል፡- ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ የፓናል ውይይት እናካሂዳለን፡፡ ውይይቱ ማኅበረሰባችንን በስቴም እንዴት እንደምንለውጥ ነው፡፡ ከተለያየ ሙያ የመጡ ተወያዮች ይኖራሉ፡፡ አገር በቀል የልማት ድርጅቶችና ጎረቤት አገሮችም ተጋብዘዋል፡፡ በስቴም እንዴት ማኅበረሰባዊ ለውጥ እንደሚመጣ ልምድ ያካፍሉናል፡፡ በትምህርት ዘርፍ የሚሠሩና አገራችንን የሚደግፉ የተለያዩ አገሮች ድርጅቶችንም የምናመሠግንበት መርሐ ግብር ነው፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች የሚደርሰው ወገን ፈንድ

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አገሮች ልገሳን ለማሰባሰብ ‹‹ወገን ፈንድ›› የሚባል የበይነ መረብ (ኦንላይን) የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ...

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...