Friday, February 23, 2024

የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦችን ያገናኘው መድረክ ለምን አስፈለገ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ለአምስት ቀናት የተካሄደው የኦሕዴድ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ በተጠናቀቀ ማግሥት በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ ባህር ዳር አቅንቶ ነበር፡፡ በዚህ የልዑካን ቡድን አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ፣ የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፣ ሌሎች የቢሮ ኃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ድምፃዊያን፣ ምሁራን፣ ደራሲያንና ሌሎች ግለሰቦች ወደ ባህር ዳር አቅንተው ነበር፡፡

የልዑካን ቡድኑ ወደ ባህር ዳር ያቀናበት ዋነኛ ምክንያትም በአማራና በኦሮሞ ወንድማማችና እህትማማች ሕዝቦች መካከል የቆየውን የአብሮ መኖር ባህል ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግና አዲስ የትስስር መንፈስ ለመፍጠር እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ከሁሉም አካባቢዎች የተውጣጣውና 250 ሰዎችን ያቀፈው የልዑካን ቡድን የዓባይን በረሃ ተሻግሮ የአማራ ክልልን መሬት ሲረግጥ ጀምሮ፣ በሁሉም አካባቢዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

በአሁኑ በወቅት ይህን መሰል የሕዝብ ለሕዝብ የትስስር መድረክ ማካሄድ ያስፈለገበት ምክንያት ምንድነው? ሲሉ ብዙዎቹ ይጠይቃሉ፡፡

ሁለቱ ክልሎች ሰፊ የሆነ አስተዳደራዊ ወሰን የሚጋሩ ናቸው፡፡ ብዛት ያለው የአማራ ክልል ብሔር ተወላጅ በኦሮሚያ ክልል፣ እንዲሁም የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ በአማራ ክልል እንደሚኖሩም ይታወቃል፡፡ ሕዝቦቹ በመከባበር ላይ በተመሠረተ የአንድነት መንፈስ በሰላምና በፍቅር አብረው ከመኖር ባሻገር በደም የተሳሰሩ እንደሆኑም ይነገራል፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁለቱን ወንድማማቾች ሕዝቦች የማጋጨት አዝማሚያ ያላቸው ድርጊቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ሳይቀር እየተለቀቁ መሆናቸውን የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ የሁለቱ ሕዝቦች የትስስር መድረክ ተካሂዶ በነበረበት ወቅትም ለውይይት መነሻነት ጽሑፎችን ያቀረቡ ምሁራን ይህን አረጋግጠዋል፡፡ ጽሑፎችን ያቀረቡ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተባባሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ለሜሳ (ዶ/ር) እና አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡

ዶ/ር ብርሃኑ በጽሑፋቸው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ የኦሮሞ ታሪክ መገንጠል ሆኖ በውሸት ተቀርጿል፤›› ብለዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በበኩላቸው፣ የኦሮሞና የአማራ የ19ኛውና የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታሪክ በትክክል አለመጻፍ የፈጠረው ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የአማራውን ገዥ መደብ እንደ ጨቋኝ መቁጠር፣ የሕዝብን መስተጋብር መሠረት ያላደረገ የልሂቃን ፖለቲካም የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት ሸርሽሮት ቆይቷል፡፡ ያለፈውን መሠረት አድርጎ የብሔር ጭቆና አለ ብሎ ማሰብ የሁለቱን ብሔሮች አንድነት አሳስቷል፤›› ብለዋል፡፡

ኦሮሞን ከኢትዮጵያ የመገንጠል ፍላጎት እንዳለና አማራን ደግሞ እንደ ገዥና ጨቋኝ በመቁጠር ሁለቱ ሕዝቦችን ሳይቀራረቡና መቆየታቸውን ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ የተገንጣይና የአማራን ሕዝብ የጨቋኝ ካባ በማልበስ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ልዩነት ሲፈጠርና አልፎ አልፎም ብሔር ተኮር ግጭት ሲካሄድ እንደነበር ጥናት አቅራቢዎች ገልጸዋል፡፡

ለሁለቱ ሕዝቦች የጠባብነትና የትምክህተኝነት ስያሜ በመስጠት ክፍተት ሲፈጠርና አንድነታቸው ሲሸረሸር መቆየቱንም ጽሑፍ አቅራቢዎች ተናግረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እነዚህን ክፍተቶችና ስያሜዎች በመጠቀም፣ ሁለቱ ሕዝቦች በዓይነ ቁራኛ እንዲተያዩና ዕርስ በራሳቸው ወደ ግጭት እንደሚያመሩ የሚያደርጉ አዝማሚያዎች መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡

የሕዝብ ለሕዝብ የትስስር መድረኩ መዘጋጀት ዋነኛ ዓላማም እነዚህን ክፍተቶች በመጠቀም፣ ሁለቱን ሕዝቦች ወደ ጦርነት ብሎም አገሪቱን ወደ ብተና እንዳይካታት የሚያደርግ የአንድነት መንፈስ ለመፍጠርና አዲሱ ትውልድ የአብሮ መኖር ስሜት ተላብሶ እንዲኖር ለማስቻል እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያችል አስተሳሰብ ለመፍጠር እንደሚረዳም በጥናት አቅራቢዎቹ ተመልክቷል፡፡

የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች የትስስር መድረክ ባለፉት 26 ዓመታት የተለመደ እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሁለቱ ሰፊ የቆዳ ስፋትና ብዙ ሕዝብ ያላቸው ክልሎች ከመሆናቸው አኳያ አንድ ሆነው ለአገራዊ ግንባታ የአንበሳውን ድርሻ እንዲወጡ ማድረግ ተገቢነቱ ላይ ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህን መሰል መድረክ ባለመኖሩ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ እንልተሠራ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡ ተመሳሳይ መድረኮች ከዚህ በፊት በሁለቱ መካከል ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ እስከ ዛሬ ድረስ አገሪቱ ከዚህ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጥቅም እንደነበረው ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በቅርቡ ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ 200 ወጣቶች በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለመከላከል ‹‹ጣና ኬኛ›› ወይም ‹‹ጣና የእኛ ነው›› በሚል መፈክር ወደ ባህር ዳር መሄዳቸው ይታወሳል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ የተካሄደው የሁለቱ ሕዝቦች የትስስር መድረክም መነሻ ሐሳቡ ያኔ እንደተጠነሰሰ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የወጣቶቹ ወደ ባህር ዳር መሄድ በአገሪቱ በተለይም በሁለቱ ክልሎች መካከል የነበረውን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዳደረገው የሁለቱ ክልሎች ኃላፊዎች ገልጸው ነበር፡፡

 በበደሌ ዞን ሦስት ወረዳዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት የተጎዱ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ለመከታተል ወደ ሥፍራው አቅንተው የነበሩት የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ ወደ ሥፍራው አቅንተው በነበረበት ጊዜ ይህ ጉዳይ መስመር እንደያዘና የትስስር መድረኩ ቀን እንደተቆረጠ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህ የትስስር መድረክ ላይ ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚሰብኩ ንግግሮች፣ ሙዚቃዎችና የሥነ ጥበብ ሥራዎች ቀርበው ነበር፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ‹‹ኢትጵያዊነት የራሱና የጋራ በሆኑ ባህሎች፣ ወጎች፣ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ትውፊቶችና ጠንካራ የአብሮነት እሴቶች  ጥምረት ድርና ማግ ሆኖ የተሠራ የከበረ ማንነት ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊነት የተገመደ አብሮነትና ውህደት ነው፡፡ እንደሚጠፋ እንፋሎት ቢነፍስ ተወዛውዞ የሚወድቅ ወይም የሚሰበር ሳይሆን ይበልጥ ሥር እየሰደደ፣ እየጠበቀና እየጠለቀ የሚሄዱ ታላቅ ኃይል ያለው ማንነት ነው፤›› ሲሉ አቶ ገዱ አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊነት የኅብረት፣ የአብሮነት፣ የአንድነትና የመከባበር ምልክት መሆኑን ያልተገነዘቡ የሩቅና የቅርብ ጠላቶቻችን ዛሬ ዛሬ የራሳችንን ድክመቶች መፈናጠጫ እርካብ እያደረጉ ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ፈልፍለው እየገቡ፣ ውሸቱንም ጭምር እየደራረቱ ሊለያዩን ሲታትሩ ይታያል፤›› በማለት እየተፈጠረ ነው ያሉትን አዝማሚያ ጠቁመዋል፡፡

የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ አንድነትን በተመለከተም ‹‹በባህል፣ በወግና በአኗኗር በእጅጉ ከመተሳሰራቸው ባሻገር በበርካታ አካባቢዎች በጋብቻ፣ በጉዲፈቻና በጡት ማጥባት ጭምር ተዋህደው እየኖሩ ያሉ ሕዝቦች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ የአማራ ተወላጅ ከአማራ ክልል ቀጥሎ በብዛት እየኖረ ያለው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች አልፎ፣ አልፎ ግጭቶች እንደሚከሰቱና ሲከሰቱም የኦሮሞ ሕዝብ አጥፊውን በመኮነንና ለሕግ በማቅረብ የአማራን ሕዝብ ሕይወትና ንብረት ሲታደግ እንደቆየ ጠቁመዋል፡፡

‹‹በዚህም የኦሮሞ ሕዝብ አንዳንዶች እንደሚሉት አግላይ ሳይሆን ሁሉንም አቃፊ የሆነ የተከበረ ባህል ባለቤት መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በአማራ ክልል ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ የኦሮሞ ተወላጅ እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የሚኖሩ የኦሮሞ ሕፃናትን በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር መብት ለማስጠበቅ ሲባልም፣ በአሁኑ ጊዜ በ257 ትምህርት ቤቶች አንድ መቶ ሺሕ የሚጠጉ ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በአፋን ኦሮሞ በመማር ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ታሪክን እንደ መነሻ በመውሰድ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ቅራኔ እንዲፈጠር የሚሠሩ አካላት እንዳሉ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ‹‹በአስተዋዩና ሰላም ወዳዱ በአገራችን ሕዝብ እንቢተኝነት የዕለተ ተዕለት ትንኮሳዎቻቸው እየመከነ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በሕዝቦች መካከል ያለው የአንድነት ገመድም በቀላሉ የማይበጠስ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ማናችንም ልንክደው የማንችል፣ ልንለውጠው የማንችል፣ ለዘመናት የተገነባ ማንነትና አንድነት አለን፡፡ በሆነ አጋጣሚ ሊፈርስ የማይችል ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ሰርገኛ ጤፍ ነው ብለናል፡፡ አብሮ የሚበጠር፣ አብሮ የሚፈጭ፣ አብሮ የሚበላ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን መኖርን ብቻ አይደለም አብረው የተጋሩት ሞትንም የተጋራን ሕዝቦች ነን፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹አጽማችን አንድ ላይ የተቀበረ፣ ደማችን አንድ ላይ የፈሰሰ ሕዝቦች ነን፤›› ብለዋል፡፡

 ኢትዮጵያዊያን ከውጭ የመጣን ጠላት ለመዋጋት ሲሉ አብረው እንደታገሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዓደዋ ላይ ሞትን ተጋርተናል፡፡ ደማችን አንድ ላይ ፈሷል፡፡ የማናችንም ደም ባድመ ላይ አለ፤›› በማለት በኢትዮጵያና በኤርትራ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያዊያን የከፈሉትን ዋጋ አስታውሰዋል፡፡

‹‹ቅጥረኞች ሆነን፣ ተከፍሎን አይደለም ደማችንን ያፈሰስነው፡፡ ለማን? ለዚች አገር ሉዓላዊነት፣ ለዚች አገር ክብር ሲባል ነው፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊውም ሕይወቱን የሰዋሰው ሕይወት ቀልድ ስለሆነ አይደለም፡፡ ለአገሩ ክቡር ሲል ነው ራሱን አሳልፎ የሰጠው፤›› ብለዋል፡፡ ያለፈውን ታሪክ ለዛሬና ለነገ መሠረት ቢሆንም የኋላውን በማንሳትና በመተረክ ጊዜ ማባከን ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች የትስስር መድረክ የተዛነፉ ታሪኮችን በማስተካከል፣ በሁለቱ ክልሎች የሚኖሩ ሕዝቦችን አብሮ የመኖር ባህልና ወግ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች ግን ጉዳዩ ከዚህም ገፋ ያለ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ከማኅበራዊ ጠቀሜታው ይልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳው ያመዘነ ነው ይላሉ፡፡

‹‹እኔ ስላለፈው ታሪክ አያስጨንቀኝም፡፡ ከማንም ጋር አያጣላኝም፡፡ እውነት ነው ያለፈው ታሪክ የሁላችንም ታሪክ ነው፡፡ በጎም ይሁን መጥፎ፡፡ የራሳችንን ታሪክ ነው፡፡ እንደ ታሪክነቱ መቀመጥ አለበት፡፡ የትናንቱ ታሪክ ለዛሬ ማስተማሪያ የሚሆን ካለ ደግሞ ወስደን ልንማርበት፣ የተበላሸ ታሪክ ካለ ዛሬ ለማስተከከል፣ ወደ ኋላ እያየን ወደ ፊት መሄድ አንችልም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የትናንቱ ትውልድ የራሱን ሠርቶ አልፏል፡፡ ዛሬ ሌላ ትውልድ ነው፡፡ ራሳችን በራሳችን ለራሳችን የሚጠቅመን ሞዴል ለምን አንሠራም? መሥራት እየቻልን ለምን?›› ብለዋል፡፡

ሁለቱ ትልልቅ ክልሎች በዚህ መንገድ ትስስር መፍጠራቸው፣ በአገሪቱ ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችንና ሥጋቶችን ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙ አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች የሁለቱን ሕዝቦች የቆየ የአብሮ መኖር  ባህልና እሴት አንስተው ለተሳታፊዎች አካፍለዋል፡፡

የሁለቱ ክልሎች የጋራ ትስስር መድረክ ግንኙነትን፣ ከሁለት ክልሎች አልፎ የሁለት አገሮች ግንኙነት እንደ መሰለ ጥያቄ ያነሱ አሉ፡፡ ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት ሁለቱ ሕዝቦች መገናኘታቸውና መወያየታቸው መልካም ነው ቢባልም፣ ከመጠን በላይ ፖለቲካዊ ጎኑ ተለጥጦ መራገቡ ጤነኝነት ይጎድለዋል ይላሉ፡፡ ከዚህ ይልቅ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ላይ ቢተኮር ይመረጣል ባይ ናቸው፡፡

በሁለቱ ክልሎች የተጀመረው የሕዝብ ለሕዝብ የትስሰር መድረክም ወደፊት ቀጣይ እንዲሆን አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ መድረኩ በቋሚነት እንዲቀጥል የሁለቱ የክልሎቹ አመራሮች የቤት ሥራ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በቀጣይም የትስስር መድረኩ በአዳማ ከተማ እንደሚካሄድ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

  

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -