Sunday, June 16, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ጥርሱ ያልረገፈው አልሸባብ ንክሻው መቼ ቆመ?!

በሒሩት ደበበ

በምሥራቃዊ ጎረቤት አገር ከ20 ዓመታት ለበለጠ ረጅም ጊዜ የአገሪቱ ዜጐች ብቻ ሳይሆኑ ቀጣናውንም ሲታመስ ከርሟል፡፡ ለዓመታት በአክራሪና በጽንፈኛ ኃይሎች ከፍተኛ በደል ደርሶበታል፡፡ የሶማሊያን የውስጥ ትርምስና ከዚያድ ባሬ አጉል የመስፋፋት ምኞት አንስቶ ያለውን ታሪክ እንመርምር ቢባል፣ የጋዜጣ ገጽ ካለመብቃቱ ባሻገር ለተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይም የሚጠቅም አይደለም፡፡

በሶማሊያ የነበረውን ግብረ ሽብር ከእስልምና ፍርድ ቤቶች ሸንጐ የተረከበው አልሸባብ እንደቀደሙት ሁሉ በጎረቤት አገሮች ላይ ጅሃድ በማወጅ ሶማሊያውያንን መፈናፈኛ ያሳጣ ሲሆን፣ እስከ 60 ሺሕ የሚደርሱ የታጠቁ ሸማቂዎች እንደነበሩትም ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህ አደገኛ ኃይል የሶማሊያን ወደቦች በመቆጣጠር የዓለም መንግሥታትን ትኩረት ስቧል፡፡ ይፋዊ ትስስር መኖሩ በመረጃ ባይገለጽም ከአልቃይዳ ጋር በነበረው የግብረ ሽብር መስተጋብር ምዕራባውያንን (በተለይም አሜሪካን) ዋነኛ ጠላት አድርጎ በመንቀሳቀስ በኬንያ፣ በታንዛኒያና በኡጋንዳ የሽብር ተግባራትን ፈጽሟል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት ዕውቅና ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ በማዝመት የሶማሊያውያንን ጣርና ስቃይ ከመነቀስ ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረውንም ሾተል ለመመለስ ተንቀሳቅሳለች፡፡ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ‹‹አሚሶም›› በተሰኘው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ ተቀላቅላ የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች ነው፡፡ ከወራት በፊት ጥምር ኃይሉ በተለይም ከሶማሊያ የሽግግር መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን በወሰዳቸው ዕርምጃ፣ አክራሪው የአልሸባብ ኃይል በርካታ ይዞታዎቹን ከመልቀቁም ባሻገር እንደተዳከመም ነው የሚታወቀው፡፡

ነሐሴ 26 ቀን 2006 ዓ.ም. (ሴፕቴምበር 1 ቀን 2014) በአሜሪካ የአየር ጥቃት ሶማሊያ ውስጥ ከተገደለው የአልሸባብ መሪ አህመድ አብዲ ጐዳኔ (የአልሸባብ ኦሶማ ቢላደን ይሉታል) በኋላ ደግሞ የአልሸባብ ወደ መቃብር የመውረድ ጉዞ ነበር ተደጋግሞ ሲነገር የነበረው፡፡ ባለፈው ሳምንት የቡድኑ ሁለተኛ ሰው የነበረው ዘካርያ አህመድ ሒልሳ ለሶማሊያ የሽግግር መንግሥት እጁን ሰጥቷል፡፡

መሪዎቹን ያጣው አልሸባብ ግን አመቺ ጊዜ እየጠበቀ በአገሩ ውስጥም በጎረቤት አገሮችም የሽብር ድርጊቱን ከመፈጸም አልታቀበም፡፡ ጎዳኔ በተገደለ በሳምንት ጊዜ ውስጥም በሞቃዲሾ ሁለት ሚኒባስ ሙሉ ንፁኃን ሰዎችን በአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ፈጅቷል፡፡ አንዳንድ የአገሪቱ ከተሞችንም በቦምብ አጋይቷል፡፡ ከዚያ ወዲህ በወሰዳቸው አሰቃቂ ዕርምጃዎች በኬንያ ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁኃንን ፈጅቷል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ለመፈጸም የሚያስበው ሽብር ባይሳካትም የዛቻ መዓት ሲያወርድ ሰንብቷል፡፡ በአሜሪካ የደኅንነት መዋቅር የተረጋገጡ የጥቃት ዓላማዎችን በአዲስ አበባ ከተማ ለመፈጸም አቅዶ ነበር፡፡ እነዚህ ምልክቶች አልሸባብ በአልሞትባይ ተጋዳይነትም ቢሆን እየተንፈራፈረ የምሥራቅ አፍሪካ የሽብር እጁን እንዳልሰበሰበ ነው፡፡

በቅርቡ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ምክር ቤታቸው በፀረ ሽብር ትግሉ ላይ አንድ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሕግ አውጥተዋል፡፡ የአገሪቱን የፖሊስና የደኅንነት ኃይል የሽብርተኛ ምርመራና የመከላከል ዕርምጃ ከማጠናከር ባሻገር፣ ዜጐችና አንዳንድ ሥነ ምግባር የጎደላቸው የመንግሥት አካላት የሕዝቡንና የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ በሚጥል አኳኋን ለሚያደርሱት አሻጥር ተገቢውን ቅጣት ለማሳለፍ የሚረዳ መሆኑም ተነግሮለታል፡፡

አልጄዚራ በሠራው ዜና የኡሁሩ ኬንያታን ንግግር ዘርዘር አድርጐ አቅርቧል፡፡ ‹‹ዓላማችን አንድና አንድ ነው፡፡ የኬንያን ሕዝብ ደኅንነት መጠበቅና ማስጠበቅ ለዚህ ደግሞ አልሸባብና ግብረአበሮቹ በተደጋጋሚ እያደረሱብን ያለውን ጥፋት ሳያዳግሙ መመከት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕጉ መውጣት አንድ ዕርምጃ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሕጉ ምንም ሆነ ምን በኬንያ ምክር ቤት (ፓርላማ) ውስጥ እስከ መደባደብ የደረሰ ውዝግብ ማስነሳቱ አልሸባብ አሁንም የአካባቢው አንድ አወዛጋቢ የሽብር ቡድን መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

በነገራችን ላይ የአልሸባብ ዓላማ ተጋሪ የሆኑት በእስልምና ሃይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነት ስም የጅሃድ፣ የአጥፍቶ መጥፋትና የሽብርተኝነት ፍልስፍና ተከታዮቹ አልቃይዳ፣ ታሊባንና ቦኮ ሐራም እያደረሱ ያሉትን ዕልቂት እየተመለከትን ነው፡፡ በቅርቡ ታሊባን በፓኪስታን አንድ መንደር የሚገኙ 145 የሚደርሱ ሕፃናት ተማሪዎች፣ መምህራንና ንፁኃን ዜጐችን በግፍ ፈጅቷል፡፡ ቦኮ ሐራምም በናይጄሪያ በአፍሪካ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ንፁኃንን እየፈጀ፣ ሕፃናትን እያገተና እያስጨነቀ፣ ሴቶችን እየደፈረና እያንገላታ አሰቃቂ ኃይልነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

አልሸባብ በቅርቡ በድረ ገጹ የመሪዎቹ በሚል የተለቀቀ ድምፅ የሽብር ድርጊቶቹ ትክክለኛ ዕርምጃዎች መሆናቸውን በማንቆለጳጰስ በቀጣናው ድርጊቱን አጠናክሮ እንደሚገፋበት ተናግሯል፡፡ እስካሁንም ድረስ የሶማሊያ ሁኔታ በአንቀልባ ከተያዘ ልጅ እምብዛም የተሻለ አለመሆኑና እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ አገሮች ጀርባ ላይ የተንጠላጠለ መሆኑም ለአልሸባብ መሞት ዋስትና አይሰጥም፡፡ አልሸባብ አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ ሞቶ ትንፋሹ ካልተቋረጠው ኦብነግና ብጥስጣሽ ርዝራዥ ጋር የዓላማ ተጋሪነት እንዳለው ይነገራል፡፡ የዕድልና የአቅም ማጣት ጉዳይ ሆኖ እንጂ ‹‹የሻዕቢያ ነጭ ለባሾች›› እና በቅርቡ የቤንሻንጉል ነፃ አውጭ ግንባርና በጋምቤላም ተከታታይ ጥፋት ከሚያደርሱ ኃይሎች ጋር ግንኙነት አይኖረውም ማለትም ያስቸግራል፡፡ ባለፈው ሰሞን የአልሸባብ ታጣቂዎች በሞቃዲሾ የአሚሶም ካምፕ ውስጥ አምስት ሰላም አስከባሪዎችን መግደሉ የትንፋሹ አለመቋረጥ ምልክት ነው፡፡

በእስልምና ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው ቁርአንና ነብዩ መሐመድን ስም እየጠቀሱ የሰው ልጅን ሰብዓዊ መብትና ነፃነት የሚገፉት እነአልሸባብ፣ ታሊባንም ሆኑ ቦኮ ሐራም ፍፁም ከሃይማኖቱ መርህ ውጭ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ለምሳሌ በእስልምና ሥነ ሕግ ‹‹የሕግ ፍልስፍና ውስጥ ቀደምቶች ሊቃውንቶች የሰብዓዊ ፍጡራን ንድፈ ሐሳባዊ ጥበቃ ያላቸው ፍላጐቶች›› (Protected Interests) አሉ፡፡ እነዚህም በአምስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያነጣጥራሉ፡፡ የሕይወት፣ የህሊና፣ የዘር ሐረግ ማፍራት፣ የገጽታና የንብረት ማፍራት መብቶች የሆኑት እነዚህ ዝርዝር ጉዳዮች ከሰዎች የሰብዓዊ መብቶች ጋር ያላቸው ቁርኝትም ቅርብ ነው፡፡ ይህ ሀቅ መሬት ላይ ያለ ሆኖ እያለ፣ ለምን ዘመናዊ ትምህርት ትማራላችሁ? መንግሥታዊ ሥርዓት እንዴት ይበጃል? የፊልም፣ የቴአትርና ዓለማዊ ተግባር ሁሉ ለምን ይኖራል? እያሉ ነው ንፁኃንን የሚፈጁት፡፡

ይህን ድርጊት በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን፣ በፓኪስታን፣ በሶሪያ አልፎም በሰሜን አፍሪካ በሊቢያ፣ በአልጄሪያ፣ በከፊል ግብፅ እንዲሁም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በናይጄሪያ፣ በማሊና በሴኔጋል እየተፈጸመ ያለው የሽብርተኝነት በትር ሁሉ መዘዙና አካሄዱ እነአልሸባብም የሚጓዙበት መንገድ መሆኑን መጠራጠር ያዳግታል፡፡ ስለሆነም የተለያዩ ተንታኞች እንደሚያስረዱት በአንድም በሌላም የዓለም ትስስር ያላቸውን በእስልምና ስም የተሳሰሩ ጽንፈኛ የሽብር ኃይሎች በአጭር ጊዜ ‹‹ደመሰስኩ!›› ብሎ ማረፍ አይቻልም፡፡ በተራዘመና በህቡዕ በተጠናከረ ሽብርተኝነት የተጠናከረው ኃይላቸው የዓለምን ብርቱ ርብርብና ትግሉ መፈለጉ አይቀርም፡፡

በመሠረቱ በእኛም አገር ቢሆን የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት ያረጋገጠው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በተለይ አንቀጽ 27 በሚገባ አጢኖ በተግባራዊነት ላይ የሚታዩ ችግሮች መፈተሽ አለባቸው፡፡ የትኛውም ዜጋ የማንኛውም ሃይማኖት ተከታይ ቢሆን የሕዝብ ደኅንነት፣ የሕዝብ ሰላም፣ የሕዝብ ጤና፣ የሕዝብ ትምህርት፣ የሕዝብ የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜጎች መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች እንዲሁም መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን በማረጋገጥ፣ በሃይማኖት ሽፋን የሚቃረን አካሄድ ገደብ ተጥሎበታል (በተለይ በንዑስ አንቀጽ 5)፡፡ አማኝ ጽንፈኛም እንበለው አክራሪ፣ ሽብርተኛም ሆነ የአልሸባብ ደጋፊ ሄዶ ሄዶ መንገዱ የጥፋት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የአገራችንና የአንድነታችን ፀር የሆኑትን እንደ አልሸባብ ያሉ ሽብርተኛ ኃይሎች ተጠናክረን ጥርስ ማርገፍ አለብን ሲባል፣ ትግሉ መጀመር ካለበት በውስጣችንም ከሚያቆጠቁጡ ጽንፈኛና አክራሪ ኃይሎች ጭምር መሆን አለበት፡፡

የውስጥ ትግል ሲነሳ የሃይማኖት አክራነት ጉዳይ ብቻ አይደለም ተነጥሎ መታየት አለበት፡፡ ከብሔር ጠባብነትና ‹‹ጥገኝነት›› አንፃር በአንዳንድ ክልሎች አንዴ እየጐመራ ሌላ ጊዜ እየከሰመ ያለውን ድርጊትም መመርመር ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በአልሸባብና በሻዕቢያ የሚደገፈው ኦብነግ ተመትቶ መውጣቱና ከፊሉ አመራርም ከመንግሥት ጋር ተደራድሮ ‹‹እጅ መስጠቱ›› ይነገራል፡፡ ነገር ግን አሁንም በክልሉ ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉና የፌዴራሉ ፀጥታ ኃይል ባይኖሩ በራሱ የሚቆም ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን የሚጠራጠሩ ብዙ ናቸው፡፡

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያስረዱት አሁንም ከአጎራባች የአፋር ወረዳዎች ጋር በሚደረግ የእርስ በርስ ግጭት የሰው ልጆች ይሞታሉ፣ ይፈናቀላሉ፣ የደሃ ሕዝብ ሀብትም ይወድማል፡፡ ይህን ችግር ለማብረድ በቅርቡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር የተሳተፉበት የሁለቱ ክልል ሕዝቦች የእርቅ ሥነ ሥርዓት በአዋሽ 40 ከተማ ሲካሄድ ታይቷል፡፡ ውስጥ አዋቂ መረጃዎች እንደሚያስረዱት በሁለቱ ክልሎች ድንበርኛ ሕዝቦችም ሆነ በሶማሌ ክልል በሚኖሩ የሌላ ብሔር ዜጎች ላይ ለሚደርሱ ግድያዎች፣ ከመንግሥት አንዳንድ ኃላፊዎች ጠባብነትና የግል ጥቅም ፍለጋ ባሻገር የአልሸባብና የኦብነግ የእጅ አዙር ድጋፍ አላቸው፡፡

በእርግጥ በቀጥታ የአልሸባብ ድጋፍ አለበት ባይባልም ውስጥን መፈተሽ ከተነሳ የጋምቤላና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ችግሮችም ተመሳሳይ ተግዳሮቶች ናቸው የተጫጫኗቸው፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች (በተለይ በጅማ ዞን፣ ባሌና አርሲ…)፣ በደቡብ ክልል ሥልጤ ዞንና ጉራጌ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በሌሎች የእምነት ተከታዮች ላይ የፍጅት ሾተል ለመምዘዝ የሞከሩና የመዘዙ ኃይሎችም ተጠራርገው አልተያዙም፡፡ ሌሎችን የሚያስተምር ፍርድ አላገኙም የሚሉ ወገኖች መኖራቸውንም መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ ለዚህ ሁኔታ መከሰት መንግሥት ‹‹የሽብርተኝነትና የአክራሪነት ዝንባሌው ተነቅቶበታል፡፡ አሁን ባለው ደረጃም ተዳክሟል፤›› ብሎ በመተው መሆኑም የሚያሰጋቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ስለዚህ አልሸባብን የመሰለ የሽብር ኃይል ሞቷል ወይም ትንፋሹ ቆሟል ለማለት ከውስጥ እስከ ውጭ ያለውን ተፃራሪ ኃይል አመለካከት መፈተሽና የተደፈነ የሚመስለውን የተዛባ አተያይ መመርመር ተገቢ ነው፡፡

የሰላም ሃይማኖት በሆነው ታላቁ እምነት እስልምና ስም እየማሉና እየተገዘቱ የሽብር ተግባር ውስጥ የተዘፈቁ ኃይሎች ሁሉ ለሕዝቦች ነፃነት እንደሚታገሉ ነው ራሳቸውን ያሳመኑት፡፡ በአጥፍቶ መጥፋት፣ በጅሃድም ሆነ ‹‹ካፊርን›› በማስወገድ ጨለምተኝነትና ጽንፈኝነት፣ እንዲሁም በኋላቀር ፍልስፍና የሚመሩ ከመሆናቸውም በላይ ለነፍሳቸው ሳይሳሱ እየሞቱ መግደላቸው ሲታይ፣ በተጨባጩ ዓለም ለምን ይኼ ድርጊት እየሰፋ ሄደ ብሎ መጠየቅ ተገቢነት አለው፡፡

አልሸባብ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይል በኢትዮጵያውያን ላይ ጀሃድ አውጇል፡፡ በውስጡ ‹‹የታላቋ ሶማሊያ ምሥረታ›› የዚያድ ባሬ መንፈስ እየተቀሰቀሰ የኢትዮጵያ ሶማሊያ ወገኖችን ጨፍልቆ ለመውሰድ ከመቋመጡም ባሻገር፣ ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት›› በሚለው ያረጀና ያፈጀ መፈክር አንግቦ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ‹‹ነፃ ማውጣት›› እንደ ግብ እንዳስቀመጠም የሚነገር እውነት ነው፡፡ ከእነዚህ ተቀባይነት የሌላቸው አስተሳሰቦች በላይ ደግሞ ሻዕቢያና አንዳንድ የኢትዮጵያን በጐ ዕድገት ማየት ከማይሹ የዓረቡ ዓለም አገሮች የሚደረግለት የእጅ አዙር ድጋፍና የሚሰጠው ተልዕኮም አለ፡፡

ይህን እኩይ ተግባር የተገነዘቡት የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በሶማሊያ የተጋረጠው ሽብርና አልሸባብን ለማንኮታኮት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የአፍሪካ ኅብረትና ኢጋድን ጨምሮ የጐረቤት አገሮችን እገዛ አጠናክሮ በተቀናጀ መንገድ አልሸባብ ላይ ተጠናክሮ መዝመት ያስፈልጋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ይህ ጽንፈኛና እኩይ የሽብር አቀንቃኝ ተሳክቶለት እንደፈለገው ኢትዮጵያን እያጠቃ አይደለም፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ግን የአልሸባብን ጥርስ ረግፏል ብሎ መዘናጋት አይቻልም፡፡ ማሸበሩ ባይሳካለትም የአክራሪነትና የጽንፈኛ አስተሳሰቡ ከሰላማዊ የሃይማኖት አስተሳሰቦች ጋር እየተቀላቀለ በመራገቡ ይህንና መሰል ኃይሎችን ነጥሎ ማጋለጥና በመንግሥትና በሕዝብ መሀል የሚታዩ ወልጋዳ አካሄዶችን አጥብቆ መጋፈጥ ያስፈልጋል፡፡ በሶማሊያ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ ከተገባደደም አገራችንና ሕዝባችን በሚጠበቅበት አኳኋን ወደ አገር ውስጥ የሚመለስበት መንገድም ሊታይ የግድ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

                    

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles