Tuesday, September 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ዕድገት በምን ዓይነት መስዋዕትነት ነው የሚገኘው?

በታመነ በእግዚአብሔር

አገራችን በትክክለኛው የዕድገት ጎዳና ላይ እየተጓዘች ነው፡፡ አንድ ወደ መዲናችን አዲስ አበባ የሚመጣ ጎብኚን ትኩረት የሚስቡ በርካታ ክስተቶች በከተማችን ይገኛሉ፡፡ ከፍተኛ የሕዝብ ሀብት የሚፈጁ የልማት ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ወደ አንድ ትልቅ  የግንባታ ሳይት እየተቀየረች ትመስላለች፡፡

በእርግጥ ማንኛውም እንደዚህ ዓይነት የሚሠሩ ሥራዎችን አስፈላጊነት  ለማወቅ ፍላጎት ያለው ሰው ይህንኑ ከበርካታ የታሪክ መጻሕፍትና ዓለም አቀፍ  ልማት ተግባራት ማግኘት ይችላል፡፡ እ.ኤ.አ በ1900ዎቹ የምዕራብ አገሮች አብዛኛዎቹ ዋና ዋና ከተሞች እንደዚህ ዓይነት መጠነ ሰፊ የግንባታ እንቅስቃሴን ለማየት ችለዋል፡፡ አሁን የምናያቸው ትላልቅ ሥነ ሕንፃ መዋቅሮች በዚህ ወቅት የተሠሩ ናቸው፡፡ ከፓሪስ እስከ ሮም ከሊዝበን እስከ ኒውዮርክ ያሉ ከተሞች አሁን ያላቸውን ገጽታ ሊያገኙ የቻሉት በዚያ ወቅት ነበር፡፡

እርግጥ ነው ይህ የግንባታ አባዜ እስከ እ.ኤ.አ የ1930ዎቹ ታላቁ የድህነት ዘመን (ግሬት ዲፕሬሽን) ቀጥሎ ነበር፡፡ ይህ ዘመን ከፍተኛ ዕዳ የተሸከመ የአገሮች ኢኮኖሚ መዳከምን ያሳየና በወቅቱ የፖሊቲካ ሰዎች ያሳለፉትን የተሳሳተ ውሳኔ ያመላከተ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ የኬኔሲያን የኢኖሚክ ጽንሰ ሐሳብ የሆነውን ሙሉ በሙሉ የኢኮኖሚ ዓላማ የያዘውን የሕዝብ መዋዕለ ንዋይን በማስታወቅ ዓለምን ሊታደግ ችሏል፡፡

 በተመሳሳይም የእስያ አኅጉር ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ ገብቶ ነበር፡፡ የአገር ውስጥ ጥቅል ምርትን (ጂዲፒ) የማሳደግ ዝንባሌ በነበረበት ወቅት፣ ከዚህ ጋር ተከትሎ በነበረው የፖሊቲካ ድጋፍ በመታገዝ ታይዋን፣ ኮሪያና ቻይናና የመሳሰሉ አገሮች የዕዳ ቋታቸውን አስፍተዋል፡፡ በውጭ አገር ብድር ለሚሠሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ቼክ ለመጻፍ ጊዜያቸውን አያባክኑም ነበር፡፡

ዓይኖቻቸው ትኩረት ያደረጉት ከፕሮጀክቶቹ የሚያገኙት የፖለቲካ ድጋፍ ላይ ብቻ በመሆኑ ምንም እንኳን የሚፈርሙት ብድር ከዚህ ጋር የተያያዙትን ዘርፈ ብዙ ሥጋቶችን በአንክሮ እንዲመለከቱ ግድ ይል የነበረ ቢሆንም፣ ይህንን በኃላፊነት ስሜት ለመወጣት ቸልተኛ ነበሩ፡፡ ለዚህ ድርጊታቸውም የደረሰው ቁጣ ጊዜም ሳይፈጅ የተከሰተ ነበር፡፡ ይህ በአንድ ጊዜ መንኮታኮት የጀመረ ኢኮኖሚ አብረቅራቂ የሆነውን የአገራቱን ሀብት በማሽመድመድ በአንድ ምሽት ባለፀጎችን ወደ ኪሳራ አፋፍ አድርሷቸው ነበር፡፡

እንደ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ባያደርጉ ኖሮ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት በታየበት ጊዜ ያካበቱት ሀብት በሙሉ ድራሹ ጠፍቶ የአገሪቱ ሕዝብ የሰቆቃ የብር ኖት ታቅፎ በቀረ ነበር፡፡ ነገር ግን ለዓለም አቀፉ ሥርዓት ምሥጋና ይግባውና ሁሉም ከዚህ መጥፎ ክስተት ሊድኑ ችለዋል፡፡ የተወሰነ ሀብታቸው ሊድን በመቻሉ እንደ አዲስ ያፈሩትን ሀብት በከፍተኛ ደረጃ መጠበቅ ችለዋል፡፡ ያም ሆኖ በወቅቱ የተከሰተው ቀውስ እጅግ ጠንካራ በመሆኑ አንዳንድ አገሮች ከዚህ ቀውስ ለመወጣት ትግላቸውን ቀጥለው ነበር፡፡

የዓለም ዙሪያ ልማት መዛግብትን ስናገላብጥ ልማት የሚያስከፍለው ዋጋ የኢኮኖሚ ውድቀት ላይ ብቻ የተገደበ እንዳልሆ ማየት እንችላለን፡፡ በአንፃሩ ይህ ዋጋ በአካባቢ፣ በማኅበረሰብና በባህል እንዲሁም በሕይወት ጭምር ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናል፡፡

ምንም እንኳን ቻይናዊያን ሊናገሩት ባይሹም የባህል አብዮት ተብሎ የሚጠራው ታሪካዊ የልማት ዕርምጃቸው በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ የአውሮፓ ልማትም እንዲሁ ረሃብን፣ ሞትን፣ የጎሳ ግጭትን፣ የመደብ ልዩነትንና የአካባቢ ብክለትን በጉያው አቅፎ ነበር፡፡ የሰሜን አሜሪካ የልማት ታሪክም ብዙ የተለየ ገጽታ ሳይኖረው በዘር ልዩነት፣ በባርነትና በጭቆና የጨቀየ ነበር፡፡

አሁን ጊዜው የአፍሪካ መስሎ ይታያል፡፡ ሁሉም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በአንድ ወቅት ተስፋ ቢስ ስለነበረችው ነገር ግን የረዥም ጊዜ ድህነትና ኃይል አልባ ቅርፊትን ተላብሳ ስለከረመችውና አሁን ከፍ እያለች ስለመጣችው አኅጉር እያወሩ ይገኛሉ፡፡ አፍሪካዊያን ታሪካዊ በሚባል ሁኔታ ከፍተኛ አቅምን እየተቀናጁ አብዛኞች ወደ ገቢ መሰላል እየተራመዱ መሆኑ በሰፊው ይነገራል፡፡ ምናልባት እዚህ ላይ የተዘነጋው ጉዳይ ዓለም እየኮራበት ያለው የአኅጉሪቱ ልማት የሚያስከፍለው ዋጋን ነው፡፡

 አፍሪካን ስንመለከት ይህ የሚከፈል ዋጋ ከአካባቢ ብክለት ጀምሮ ጭቆናና እኩልነት ማጣት ድረስ ሊሰፋ እንደሚችል ማየት እንችላለን፡፡ የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የበጀት መዛግብት ከፍተኛ በሆነ ዕዳ በተለይም ወደፊት ውድቀትን አብራ ልትቋደስ ከምትችለው ቻይና ጋር የተዘፈቁ ናቸው፡፡ ይህ የቀጣዩ ትውልድ ቀደምት አባቶች የወረሱትንና ገሸሽ ያደረጉትን ውድቀት የመሸከም ኃላፊነት እንዲኖርበት የሚያደርግ ነው፡፡ ማንኛውም በጉዳዩ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሰው በኢትዮጵያ መዲና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለውን ክስተት ማየት ይችላል፡፡ በዋና ከተማው የሚከናወኑ አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች ከቻይና በተገኘ ብድር የሚከናወኑ ናቸው፡፡ ሥራዎቹ የሚሠሩት በእነሱ ብድር ብቻ ሳይሆን በራሳቸውም የሰው ኃይል ጭምር ነው፡፡ ይህን ስናየው ከእያንዳንዱ ዶላር የሚገኘው የጥቅም ሥሌት በአግባቡ እንዳልታየ ነው፡፡

እያንዳንዱ በቀላል ባቡር ላይ የሚፈሰው ዶላር በኢኮኖሚው ላይ ምን ያህል ጥቅም ያስገኛል? ለምንድነው ተግባር ላይ የማይውልና ምንም ዓይነት ጥቅም ሳይሰጥ የሚባክን የምድር የኤሌክትሪክ ኃይል ላይ ይኼን ያህል ሚሊዮኖች ዶላር የሚፈሱት? ለምንድነው ሚሊዮኖች የፈሰሰባቸውን አውራ ጎዳናዎች ማፍረስ ቀላል የሆነው? ይህ የወቅቱ  አስቸጋሪ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ፖሊሲ አውጪዎች እነዚህን ጥያቄዎች መጠየቅ የሚፈልጉ አይመስሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ በአንፃሩ መልካም ሥራቸው ብቻ እንዲታይላቸው ይፈልጋሉ፡፡

ነገር ግን ጥያቄው እዚህ ላይ አያበቃም፡፡ ለምንድነው የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ መዘንጋት እየተለመደ የመጣው? እንደ ኢትዮ ቴሌኮም የመሳሰሉ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ኢንተርፕራይዞች ውድ ዋጋ ያላቸው ኮንትራቶችን፣ ምንም እንኳን ኮንትራቶቹ ውድና ለኢኮኖሚ ጠንቅ ቢሆኑም፣ ሕገወጥ በሆነ መንገድ እንደ ለአንዳንድ ኩባንያዎች የሚሰጡት ለምንድነው የመንግሥት ግዥ አሠራሮችን ወደ ጎን መተው እንደ ልማድ የተቆጠረው? ለምንድነው ሙስና በሰፊው የተንሰራፋው? ለምንድነው ተቆጣጣሪ አካላት ለሚደረጉት ውሳኔዎች ሥቃይ እየደረሰበት ያለውን ሕዝብ ቦታ ሊሰጡ ያልቻሉት? በእርግጥ ጥያቄዎቹ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

ነገር ግን ሁሉም ልማት ከሚያስከትለው ዋጋ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካ ከቀሪው ዓለም የኋላ ታሪክ ልምድ ነበረባቸው፡፡ መጨረሻ ላይ ከፍተኛ የሆነ ውድቀትን የሚያስከትሉና አሁን ቀድመን ልያናቸው የምንችላቸውን ውድቀቶች ለመታደግ እነዚህን ዋጋ አስከፋይ ሁኔታዎች ማስቀረት ነበረበት፡፡ ነገር ግን አሁንም አረፈደም፡፡ አሁንም ቢሆን ለአፍሪካዊያን ፖሊሲ አውጪዎች ፖሊሲያቸውን እንዲከልሱና ወደፊት የሚደርሱበትን ለመታደግ ጊዜ አለ፡፡ አስፈላጊው ነገር  ራስን መመርመር፣ ቅን መሆንና አርቆ ማሰብ ብቻ ነው፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles