Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊምስክር ሲጠፋ

ምስክር ሲጠፋ

ቀን:

ከዓመታት በፊት አሳዳጊ እናታቸውን በሞት ቢነጠቁም በውርስ ያገኙት መኖሪያ ቤት ለንግድ ዓይነተኛ ቦታ በመሆኑ ብዙ ረድቷቸዋል፡፡ ወጣቶቹን ያሳደጉት እናት ልጆቹን የወሰዱት እናት ከወንድምና ከእህታቸው ነበር፡፡ መሀንም ነበሩ፡፡  በመሆኑም ሕይወታቸው ሲያልፍ ያላቸውን ሀብት በሙሉ ላሳደጓቸው ልጆች ነበር የተናዘዙት፡፡

በውርስ ያገኙትን ቤት ለሁለት ከፍለዋል፡፡ ነገር ግን አንደኛውን አከራይተው፣ በአንደኛው ቤት መኖር በጀመሩ በጥቂት ወራት ውስጥ ነበር አንደኛው ልጅ በቤቱ ላይ ሙሉ መብት እንዳለው በመሆን ለሦስተኛ ወገን በድብቅ የሸጠው፡፡ ሁኔታውን የተረዳው ተበዳይም ‹‹አላግባብ መብቴ ተነክቷል›› ሲል ክስ ይመሠርታል፡፡ በወቅቱ በተበዳይ ላይ የደረሰውን ደባ የአካባቢው ነዋሪ ቢኮንንም የምስክርነት ቃላቸውን ‹‹ከቻልን በሽምግልና እንፈታዋለን እንጂ በመካከላችሁ ገብተን በአንደኛው ላይ በመመስከር ቂም አናተርፍም›› በማለት ፍርድ ቤት ተገኝተው ቃል እንደማይሰጡ ገለጹለት፡፡

ነገር ግን ፖሊስ ጉዳዩን በይበልጥ ያውቃሉ ለተባሉ ሁለት የመንደሩ ነዋሪዎች የግድ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ በማስጠንቀቅ ቀነ ቀጠሮ ቆረጠላቸው፡፡ ነገር ግን ምስክሮቹ ልዩ ልዩ ምክንያቶች በመደርደር ጣቢያ ቀርበው ቃላቸውን ሳይሰጡ ቀናት አሳለፉ፡፡ በዚህ መሀልም ተከሳሽ ድንገት ደብዛውን አጠፋ፡፡ በሁኔታዎች መደራረብ ተስፋ የቆረጠው ከሳሽም ውጣ ውረድ የበዛበትን ክስ እንደማያዋጣው በመገመት የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ደፋ ቀና ማለቱን ጀመረ፡፡ በጐረቤቶቹ ላይም ቅራኔ አድሮበታል፡፡

ሰዎች እርስ በርስ በሚኖራቸው መስተጋብር ግጭቶች ይፈጠራሉ፡፡ እነዚህን ግጭቶችም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የሕግ ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል፡፡ ሒደቱም ፍትሐዊነትን መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ ከሳሽ መበደሉን የሚያረጋግጥበት መረጃ ያሰባስባል፡፡ ተከሳሽም በበኩሉ አላጠፋሁም ካለ ንፅህናውን የሚያረጋግጡ መረጃዎች ያቀርባል፡፡ በእማኞች የሚሰጥ የምስክርነት ቃል፣ ልዩ ልዩ ዶክመንቶች፣ በቪዲዮ የተደገፉ መረጃዎችና ሌሎችም ፍትሕ ለማግኘት የሚሰበሰቡ መረጃዎች ናቸው፡፡

ነገር ግን በቪዲዮ የታገዙ መረጃዎችንና እንዲሁም ሌላ ዶክመንቶችን የመሰብሰቡ ባህል ዝቅተኛ በመሆኑ በብዛት ጥቅም ላይ ሲውል የሚታየው የመረጃ ዓይነት በእማኞች የሚሰጥ የምስክርነት ቃል እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይሁን እንጂ ፍርድ ቤት ቀርቦ የምስክርነት ቃል መስጠትን እንደ ከባድ ነገር በመቁጠር ሰበብ የሚያበዙ አልያም ደግሞ ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አሉ፡፡

ለዚህም ግጭቶች በተፈጠሩበት አጋጣሚ አንዱ ወገን ኃይል ከመጠቀም ይልቅ በሕግ ልዳኝ በማለት ‹‹ልብ አርጉልኝ›› በሚልበት ሰዓት ምስክር ሆነው እንዳይቆጠሩ አካባቢውን ለቀው የሚሰወሩ ሰዎችን መጥቀስ በቂ ነው፡፡ አልፎ አልፎም ከሳሽ ወይም ተከሳሽ ለምስክርነት ያጫቸውን  በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት ዕውቀት እንደሌላቸው በመግለጽ በምስክርነት ከጐን እንደማይቆሙ ያሳውቃሉ፡፡

በዚህ መልኩ ጥቂት የማይባሉ አቤቱታዎች ከፍርድ ቤት ሳይደርሱ ይቀራሉ፡፡ አንዳንዴ ግን የሚያውቁትን ከፍርድ ቤት ቀርቦ ማስረዳት እንደ መብት ሳይሆን ግዴታ መሆኑን የሚረዱ ለምስክርነት የታጩ ግለሰቦች እያቅማሙም ቢሆን ቃላቸውን ከመስጠት ወደኋላ አይሉም፡፡

ቢሆንም ግን ከሚመሰክሩበት ግለሰብ ጋር የሚፈጠረው ቅራኔ፣ አልፎ አልፎ ለመመስከር ፈቃደኛ የሆኑ ግለሰቦች ያላዩትን ጨማምረው ቃል እንዲሰጡ የሚገፉበት ሁኔታ፣ እና ከችሎት ፊት መቆም የሚያሳድርባቸው የሥነ ልቦና ጫና ምቾት ይነሳቸዋል፡፡ አልፎ አልፎም ከተከሳሾች ወገን የሚደርስባቸው ዛቻ እና ሌሎች ማስፈራሪያዎች ቃላቸውን እንዳይሰጡ ከሚያግዷቸው ክስተቶች አንዱ ነው፡፡

አቶ አብደላ ሳላህን ያገኘናቸው የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት በመጠባበቅ ላይ ሳሉ ነበር፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የሚመሰክሩበት ግለሰብ የቅርብ ጓደኛቸው ነው፡፡ አቶ አብደላ፣ አላግባብ መጠጥ በመውሰድ በስካር መንፈስ ብዙዎችን ሲበጠብጥ እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከብዙ ሰዎች ጋር አምባጓሮ ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ በመጨረሻ ግን አንድ ግለሰብ ላይ የወረወረው የቢራ ጠርሙስ ግለሰቡን ለከፍተኛ ጉዳት ዳርጐታል›› ይላሉ፡፡

ይህንንም ተከትሎ ተበዳይ በመሠረተው ክስ አቶ አብደላ ምስክር ሆነው ቀርበዋል፡፡ አቶ አብደላ እንደሚሉት፣ ፍርድ ቤት ቀርቦ ቃል መስጠት ከሚወስደው ጊዜ አንፃር ትዕግሥት ይፈትናል፡፡ በተጨማሪም በሰው ላይ መመስከር እርስ በርስ የሚፈጥረው ቅራኔ አለ ብለው ያምናሉ፡፡ በመሆኑም ግጭቶች በሽምግልና ቢታዩ ይመርጣሉ፡፡ እዚህ ከመምጣታቸውም በፊት በከሳሽና ተከሳሽ መካከል ያለውን ችግር በሽምግልና ለመፍታት ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ ጥረታቸው ባለመሳካቱ ቢያዝኑም ‹‹ያየሁትን የመናገር ግዴታ አለብኝ፡፡ እውነትን መደበቅም ሀጢያት ነው›› በማለት ቃላቸውን ለመስጠት ከፍርድ ቤቱ ተገኝተዋል፡፡

ገና ለገና ይፈጠራል ብለው ከሚሰጉባቸው ጉዳዮች ባሻገርም ከተከሳሽ በኩል ዛቻዎች እየደረሡባቸው እንደሆነም አልሸሸጉም፡፡ በተጨማሪም የተከሳሽና የእሳቸው ጓደኛ የነበሩ ግለሰቦች እንደቀልድ የሚሰነዝሩባቸው ሽሙጥ ቀላል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤት ቀርበው እንደሚያውቁ የሚናገሩት አቶ አብደላ በወቅቱ የተነጠቁትን ስልክ ለማስመለስ ነበር የዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው የቀረቡት፡፡ እንደእሳቸው ገለጻ ተከሳሽ ጥፋቱን አምኖ ዕቃውን ለመመለስ ፍቃደኛ ቢሆንም ‹‹የፍርድ ቤቱ ድባብ በጣም አስጨናቂ ነበር፡፡ እስክወጣ ድረስ ብቻ ነበር የቸኮልኩት››  በማለት አቤቱታ ያቀረቡበትን ዓላማ ረስተው ንብረታቸውን ሳይረከቡ መርሳታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ አሁንም ቢሆን የሥርዓቱ ጥብቅ መሆን ሊረብሻቸው እንደሚችል ይገምታሉ፡፡ ‹‹ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ነገሮችን በሽምግልና መፍታት ይሻላል›› ይላሉ፡፡

ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች ከሚሰሙትና መስክረው ከደረሰባቸው ማኅበራዊ ችግሮች አንፃር ምስክርነትን ይሸሹታል፡፡ አቶ ፀዳሉ ፍሥሐ ፍርድ ቤት ደጃፍ የረገጡት ገና የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ነበር፡፡ በጐረቤቶቻቸው መካከል የተነሳውን ግጭት አስመልክቶ ነበር ምስክር ሆነው የቀረቡት፡፡ ፍርድ ቤት እስኪቀርቡ ድረስም ከሳሽ ያልተባለውን እንዲሉ ይወተውቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹ቤታቸው ወስደውኝ ያስጠኑኝ ነበር›› ይላሉ፡፡

የመጨረሻው ሰዓት ደርሶ ቃላቸውን ለመስጠት ፍርድ ቤት በቀረቡበት ጊዜ ሁኔታዎች አስፈርቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ቢሆንም ያዩትንና ያጠኑትን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከተመሰከረባቸው ግለሰብ ጋር እስካሁን የዘለቀ ቅራኔ ሊፈጠር እንደቻለ ይናገራሉ፡፡ ‹‹መስክሮብኛል እኮ ይላሉ፡፡ እኔም ሳያቸው እሸማቀቃለሁ›› በማለት በመመስከራቸው የገጠማቸውን ችግር ይገልጻሉ፡፡

በመሆኑም የምስክርነት ጥያቄዎችን እንደሚሸሹ አልደበቁም፡፡ ‹‹የግድ መስክር የሚሉኝ ቢኖር እንኳን እንዳላየሁ ለማሳመን እሞክራለሁ›› በማለት አስገዳጅ ሁኔታ ካልተከሰተ ኃላፊነቱን እንደሚሸሹ ይጠቁማሉ፡፡

 በተለይም በወንጀል ጉዳይ ላይ ምስክር ሆኖ የመቅረብ ፍራቻ አለኝ የሚሉት አቶ ፀዳሉ፣ ወንጀል ነክ ነገሮች ላይ በመመስከራቸው ሊመጡ የሚችሉ ጉዳቶች ይበልጡን ያሳስቧቸዋል ‹‹ለአካላዊ ጉዳቶች ሕግ ከለላ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን አደጋው ከደረሰ በኋላ የሚሰጠኝ የሕግ ከለላ ትርጉም የለውም፡፡ በተጨማሪም ከዚያ ውጭ የሆኑ ሥነ ልቦናዊ ጫናን የሚፈጥሩ ክስተቶችን የምንጋፈጠው እኛው ነን›› በማለት ከሁለት ወገን የሚደርሰው ጫና እንደሚያሳስባቸው ይገልጻሉ፡፡

በሙሉ ፈቃድ ለግል ተበዳይ ምስክር በመሆን በሚቀርቡ አንዳንድ ግለሰቦች ላይም ‹‹ምን አገባህ›› በማለት በሰው ላይ መመስከር የኋላ ኋላ መዘዙ ከባድ እንደሆነ በመግለጽ ቃል እንዳይሰጡ የሚወተውቱ የምስክር የቅርብ ዘመዶች አልፎ አልፎ ይታያሉ፡፡

አቶ ደሳለኝ መልካሙ ይባላሉ፡፡ በአንድ ወቅት ለግብይት በወጡበት መገበያያ ሥፍራ አንድ ወጣት 15 ኪሎ ግራም የሚመዝን እህል ሲሰርቅ ያስተውላሉ፡፡ በነገሩ ተደናግጠው ‹‹ሌባ ሌባ›› በማለት ከባለቤቱና ከሌሎች ሰዎች ጋር ተባብረው ወጣቱን በመያዝ ወደ ሕግ ቦታ ወሰዱት፡፡ በአንደኛ ምስክርነት ተይዘውም በቀጠሮ ቀርበዋል፡፡ በወቅቱ ግን ቤተሰቦቻቸውና ሌሎችም ግለሰቦች ‹‹ምን አገባህ! ዝም ብለህ ኑሮህን አትኖርም እያሉኝ በሠራሁት ሥራ እንድሸማቀቅ ሲያደርጉኝ ነበር›› በማለት በወቅቱ የነበረው የሰዎች ተግሳጽ ቢረብሻቸውም መሠረተ ቢስ እንደሆነ አምነው ወደጐን እንደተውት ያስታውሳሉ፡፡

ፍርድ ቤት አካባቢ ያለውን እንቅስቃሴ በመፍራት ምስክር ላለመሆን የሚጥሩ ግለሰቦች በርካታ ናቸው፡፡ ብዙዎቹም ስለሕግ ሒደት በቂ ዕውቀት የሌላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን የምስክርነት ቃል በመስጠታቸው በማኅበራዊ ሕይወታቸው እና በሥነ ልቦናቸው ላይ ጫና እንደሚፈጥር በማመን ኃላፊነቱን የሚሸሹ አንዳንድ የሕግ ዕውቀት ያላቸው ሰዎችም አጋጥመውናል፡፡

አቶ አሸናፊ በኃይሉ (ስማቸው ተቀይሯል) ይባላሉ፡፡ ከዓመታት በፊት በሕግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሌላ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ቢሆንም በአንዱ የሕግ ክፍል በቅርቡ የድህረምረቃ ፕሮግራም ለመከታተል አቅደዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሚከታተሉበት ወቅት በተደጋጋሚ ጊዜ ፍርድ ቤቶችን የመጐብኘት አጋጣሚው ነበራቸው፡፡

ይሁን እንጂ ከወራት በፊት እሳቸው በሚያውቁት የውል ጉዳይ ላይ በተነሳ ግጭት የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ነበር፡፡ ‹‹ጉዳዩን ባውቀውም እንደማላውቅ ሆኜ ለማሳመን ሞከርኩኝ፡፡ ግን ሊሰሙኝ አልቻሉም፡፡ ምክንያት ፈጥሬ ከአካባቢው ጠፋሁኝ፡፡ ነገር ግን እስክመጣ ጠብቀውኝ ስለነበር እየፈራሁም ቢሆን፣ ቃሌን ሰጥቻለሁ›› ይላሉ፡፡

ፍርድ ቤት በቆሙበት ወቅት ሲያስጨንቃቸው የነበረው የፍርድ ቤት ጥብቅ ሥነ ሥርዓት መሆኑንና ያሳደረባቸው የሥነ ልቦና ጫና ከፍተኛ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ከመሰከሩበት ግለሰብ ጋር የነበራቸው ወዳጅነትም በዚያው ተቋጭቷል፡፡

እነዚህን የመሳሰሉት በምስክርነት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች የተበዳዮችን ፍትሕ የማግኘት ጥያቄ ማስተጓጐላቸው አያጠያይቅም፡፡ አብዛኛው ሰውም ምስክር ሆኖ የመቅረብ ፍራቻው ችግሩን እያባባሰው ይገኛል፡፡ ቃላቸውን መስጠት በፍላጐት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ የሚያምኑም ጥቂት አይደለም፡፡ ከመሠረተ ሐሳቡ ይልቅ ያስከትላል ብለው ስለሚያስቡት አሉታዊ ክስተት ይበልጥ የሚያስቡም አሉ፡፡

በሀሰት የሚሰጡ የምስክርነት ቃሎች፣ የምስክር መጥፋትና ሌሎችም መሰል ጉዳዮች በወንጀል ምርመራው ሥርዓት ምን ይመስላሉ በሚለው ዙሪያ ምክትል ሳጅን ዓለማየሁ ጐርፉ በቦሌ ክፍለ ከተማ ካራማራ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መርማሪ አነጋግረናል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ከሳሾች ወደ ጣቢያ በሚመጡበት ወቅት ብዙ ጊዜ የምስክር ችግር አያጋጥማቸውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ጣቢያ ለመገኘት የማይፈልጉ ምስክሮች አልያም ደግሞ ለከሳሽ ምስክር ሆነው ለመቅረብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ግለሰቦች ሲያጋጥሙ፣ ግለሰቡ በሚያደርገው ጥቆማ በመጥሪያ ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡ ይገደዳሉ፡፡

በዚህ ረገድ ግለሰቡ ሲበደል የተመለከቱ ሰዎችን እንደ ምስክር በማቅረብ በእምቢታቸው የተበዳይ የፍትሕ ጥያቄ እንዳይስተጓጐል ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ጣቢያ ላይ መዝገቡ ተጠናቅቆ ፍርድ ቤት ሲደርስ ‹‹ፍቃደኛ ሆነው የቀረቡ ምስክሮች ሳይቀሩ ይጠፉብናል›› ይላሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ መሰል ክስተቶች የሚፈጠሩት የግል ተበዳይና የተከሳሽ ቤተሰቦች በጉዳዩ በመደራደር ተስማምተው ሲቀሩ፣ በሌላ በኩልም ምስክሮች በሚኖርባቸው የደኅንነት ሥጋት፣ በሥራቸው ላይ የሚፈጠርን መጉላላት በማሰብ፣ እንደሚቀሩ ይናገራሉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ብዙ የክስ መዝገቦች እንደሚዘጉ የሚናገሩት ምክትል ሳጅን ዓለማየሁ ‹‹ምስክር አልቀረበም ተብሎ መዝገብ መዝጋት ተከሳሽን ማበረታታት ነው፡፡ ተመልሶ ሌላ ወንጀል እንዲፈጽም መንገድ መክፈት ነው፡፡ እኛም ብዙ ጥረት አድርገን የደረስንበት ውጤት መና በመቅረቱ ተስፋ ያስቆርጠናል፤›› ይላሉ፡፡

አልፎ አልፎም ምስክሮች በሀሰት የሚመሰክሩበት አጋጣሚ መኖሩን የሚናገሩት ምክትል ሳጅን ዓለማየሁ ‹‹ጣቢያ ላይ የሰጡትን ቃል ፍርድ ቤት ሲደርሱ የሚከዱበት አጋጣሚ ቀላል አይደለም›› ይላሉ፡፡ እኚህና መሰል ክስተቶች የፍርድ ሒደትን እንደሚያስተጓጉሉ በከፍተኛ ደረጃ እያስተጓጎሉ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

የሚያውቁትን መመስከር ግዴታ ወይስ መብት፣ በሀሰት መመስከርስ ምን ዓይነት ኃላፊነት ያስከትላል በሚለው ዙሪያ በፍትሕ ሚኒስቴር የቦሌ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አባቡን አነጋግረናል፡፡

‹‹አንድ ሰው ያየውንና የሰማውን የመመስከር ግዴታ አለበት›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ የምስክርነት ቃል መስጠት ግዴታ እንጂ የመብት ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡ አያይዘውም ፍትሕ እንዲሰፍንና ወንጀልን ለመከላከል የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነና ማንኛውም ዜጋ እንደ ግዴታ ሳይሆን በፈቃዱ ሊመሰክር እንደሚገባም ይናገራሉ፡፡

ሀሰተኛ ምስክርነትን በተመለከተም በፍርድ ሒደት ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚታይ ገጠመኝ መሆኑን ገልጸው ዓቃቢ ሕግ በሀሰተኛ ምስክርነት አልያም ደግሞ ግለሰብን በሀሰት በመወንጀል ክስ ምርመራ አጣርቶ ውሳኔ የሚተላለፍበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቁማሉ፡፡

ፍርድ ቤት ገብተው ከሚዘጉ ክሶች መካከል ምስክሮች አድራሻ ቀይረው መሰወራቸው ሲገኝበት፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በመቅረታቸው (ከሳሽ) የሚዘጉ ብዙ መዝገቦች አሉ ‹‹በዚህ 6 ወር ውስጥ ብዙ መዝገብ ተዘግቷል›› ይላሉ፡፡ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የምስክሮች የደኅንነት ሥጋትን በተመለከተም በምሥስክሮች ጥበቃ አዋጅ መሠረት ከለላ ይደረግላቸዋል፡፡ ‹‹ሥጋት አለብኝ ብሎ ምስክሩ የሚጠይቅ ከሆነ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡›› በብዛት ግን አጋጥሞን አያውቅም›› ይላሉ፡፡

         

    

 

 

     

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...