Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልባህላዊ ክሊፖች ፈር እንዲይዙ

ባህላዊ ክሊፖች ፈር እንዲይዙ

ቀን:

‹‹ኮንሶ›› የተሰኘው የሞላ ካሳ (ሙለር ኮንሶ) ባህላዊ ሙዚቃ ክሊፕ ቀረፃ መነሻውን ያደረገው የኮንሶ መንደር ውስጥ ነው፡፡ ክሊፑ የአካባቢው ተወላጆች ተሰብስበው ሲጨፍሩ ያሳያል፡፡ የአካባቢው የዕለት ከዕለት ኑሮም ተቀነጫጭቦ ክሊፑ ላይ ተካቷል፡፡ በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ተወላጆች የአካባቢውን ባህላዊ ልብስ ለብሰው ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን እየተጫወቱ ክሊፑን አድምቀውታል፡፡ ክሊፑ ከተወላጆቹ በተጨማሪ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› የተባለ የአዲስ አበባ የውዝዋዜ ቡድን አባላት በመንደር ውስጥ ሲወዛወዙ ያሳያል፡፡ ውሕደቱ ክሊፑን ተወዳጅ ያደረገው ሲሆን፣ በተመሳሳይ መልኩ በተለያዩ አካባቢዎች የሚሠሩ የባህላዊ ሙዚቃ ክሊፖች በጎ ምላሽ ሲሰጣቸው ይስተዋላል፡፡ ዘፈኑ ከሚያተኩርበት አካባቢ ውጪ ባሉ ቦታዎች ተቀርፀው የቀረቡና ተወዳጅነት ያተረፉ ክሊፖችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡

አንዳንድ ክሊፖች የተለያዩ አካባቢዎችን ባህል ለማንፀባረቅ በሚል ቢሠሩም ስህተት እንደሚበዛባቸው የሚናገሩ አሉ፡፡ በተለይ በአልባሳትና ውዝዋዜ መወከል ካለባቸው አካባቢ ባህል ውጪ እንደሚሠሩ ይተቻሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ ወጣቶቹ የ‹‹የኢትዮጵያዊነት›› አባላት አስተያየት ሰጥተውናል፡፡ በ‹‹ኮንሶ›› ክሊፕ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› የውዝዋዜ ቡድን ከተመሠረተ አምስተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ የውዝዋዜ ፍቅር ያላቸው ስምንት ታዳጊዎች ተሰባስበው ያቋቋሙት ሲሆን፣ አሁን ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን ያሠለጥናሉ፡፡ ሥራዎቻቸው ከሚታይበት መድረክ ዮድ አቢሲኒያ የባህል ምሽት ቤት ያላቸው  ትዕይንት ይጠቀሳል፡፡ የማንዲንጎ አፈወርቅ ‹‹በላይ›› እና ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ) ‹‹ክፉ አይንካብኝ›› ከሠሯቸው ክሊፖች ይጠቀሳሉ፡፡

ክሊፕ ሲሠሩ ድምፃውያን የሚያተኩሩበትን ብሔረሰብ ውዝዋዜ ከማዘጋጀታቸው አስቀድሞ ጥናት እንደሚያደርጉ የገለጸልን ከአባላቱ አንዱ ታምራት እሸቱ ነው፡፡ እሱ እንደሚለው፣ የቡድኑ ተወዛዋዦች ጥናት አድርገውና አልባሳት አዘጋጅተው ውዝዋዜውን በጥምረት የውዝዋዜ ቅንብር (ኬሮግራፍ) ያደርጋሉ፡፡ ቡድኑ አጠቃላይ የክሊፕ ሥራ አጠናቆ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ቢኖረውም በርካታ ድምፃውያን ቡድኑ የሚጠይቀውን ገንዘብ መክፈል ስለማይፈልጉ ከተወሰኑ ክሊፖች ማለፍ አልቻሉም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ተወዛዋዦችን በአነስተኛ ገንዘብ መቅጠር የተዋጣላቸው ክሊፖች እንዳይሠሩ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ ያምናል፡፡ ከፍተኛ ጉልበት ወጥቶበት የሚዘጋጅ የውዝዋዜ ቅንብር ተገቢው ዋጋ ሲከፈልበት ጥበብ ያድጋል፣ ሙያተኛውም ይከበራል  ይላል፡፡ የውዝዋዜው መሠረታዊ (ኦሪጅናል) አካባቢ ተገኝተው ልዩ ልዩ አኗኗር የሚያንፀባርቅ ጥናት አድርጎ ለመጻፍና ክሊፕ ለመሥራት እስከ 50,000 ብር ይጠይቃሉ፡፡ በአነስተኛ ዋጋ ያለ ጥናት የሚሠሩ ክሊፖች አንድ ውዝዋዜ ከሌላው የሚደባልቁና ፈር የለቀቁ መሆቸውን ይገልጻል፡፡

ሌላው የቡድኑ አባል አቤል ግዛው በበከሉ እንደሚለው፣ በዘርፉ የሚያሠለጥኑ  ትምህርት ቤቶች አለመኖራቸው ጠንካራ ሥራ እንዳይቀርብ አድርጓል፡፡ ሌላው ከተለመደው ወጣ ያለና ማራኪ አቀረራብ ያላቸው ክሊፖች በብዛት አለመታየታቸው ሲሆን፣ ክሊፖች ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የሚታይባቸው ለፈጠራ የሚገፋፋ ድባብ ባለመኖሩ ነው ይላል፡፡

ቡድኑ የሚማረው ከውዝዋዜ ድረ ገጾች እንደሆነ የሚናገረው አቤል፣ ከተለያዩ አገሮች የሚመለከቷቸውን ስልቶች እንደሚያጠኑ ያስረዳል፡፡ የሚያጠኑዋቸውን ስልቶች ከባህላዊ ውዝዋዜ ጋር ደባልቀው ያቀርባሉ፡፡ ባህላዊ ውዝዋዜ ያለ ምንም ተጨማሪ ስልት መቅረብ አለበት በሚለው ሐሳብ አይስማሙም፡፡ በእሱ እምነት፣ አሁን ያለውን ተመልካች ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ውዝዋዜ በሚስብ መልኩ መቅረብ አለበት፡፡

‹‹ባህላችንን ጠንቅቀን እናውቃለን፤ ውዝዋዜውም ትክክለኛ ባህልን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ሆኖም ከኛ ባህል ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ዘዬ አክለን ውዝዋዜ ማቅረብ እንዳለብን እናምናለን፤›› የሚለው ተወዛዋዡ፣ አካሄዳቸው ቀስ በቀስ ተቀባይነት ማግኘቱን ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ውድድሮች ላይ የሚቀርቡ ሥራዎች መሰል ውዝዋዜ እንዲለመድ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነት››ን የመሰሉ ቡድኖች ባህልን መሠረት አድርገው አዳዲስ ዘዬ እያሳዩ እንደሆነና ከዓመታት ጥረት በኋላ የተመልካችን ቀልብ እንደገዙ ይገልጻል፡፡

ለክሊፖች ወዝ የሚሰጡ እንቅስቃሴዎችን ከመጨመር ጎን ለጎን ልብሳቸው የተለያዩ ብሔረሰቦችን እንዲወክል ያደርጋሉ፡፡ በአንድ ትዕይንት የብዙ ብሔረሰቦችን ውዝዋዜ ስለሚያቀርቡ ልብሳቸውም እያንዳንዱን ብሔረሰብ የሚወክል አሠራር ካለው የጨርቅ ቀለም የተሠራ ነው፡፡

ታምራትና አቤል ባህላዊ ውዝዋዜን ከአዳዲስ እንቅስቃሴዎች ጋር አዋሕዶ መሥራት ተመራጭ እንደሆነ ይስማሙበታል፡፡ ክሊፖች የየብሔረሰቡን ውዝዋዜ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያንን አለባበስና አኗኗር የሚያንፀባርቁ መሆን እንደሚገባቸውና የዓለምን ትኩረት የሚስቡ መሆን እንዳለባቸው በአፅንኦት ይናገራሉ፡፡ እንደ ምሳሌ ዝነኛውን የጋና ‹‹አዞንቶ›› ዳንስ ጠቅሰዋል፡፡

ኬሮግራፈር ኪዳኔ ምስጋናው ለ14 ዓመታት በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ በተወዛዋዥነት ሠርቷል፡፡ በቴአትር ቤቱ ረዳት ውዝዋዜ አሠልጣኝ ሆኖ በየክፍለ ሀገሩ በመዘዋወር ልዩ ልዩ የውዝዋዜ ዓይነቶችን አጥንተው ያቀረቡበትን ጊዜ ያስታውሳል፡፡  ከቴአትር ቤቱ ውዝዋዜ ኬሮግራፊ በተጨማሪ ሙዚቃዊ ተውኔቶች አዘጋጅና ኬሮግራፈር ነው፡፡ በብሔር ብሔረሰቦች ቀን ከተዘጋጁ ሙዚቃዊ ድራማዎች ብዙዎቹንም ኬሮግራፍ አድርጓል፡፡ በፀሐይ ዮሐንስ ‹‹ወላይታ›› እና በማዲንጎ አፈወርቅ ‹‹ጎንደር›› ክሊፕ ኬሮግራፊ ይታወቃል፡፡

እንደ ኪዳኔ ገለጻ፣ ቀድሞ ወደተለያዩ አካባቢዎች እየሄዱ በመመልከት ባህላዊ ውዝዋዜ የማዘጋጀት ሐሳብ ተግባራዊ የሆነው ከባህል የሚጻረሩ ውዝዋዜዎች እየታዩ ነው የሚል ትችት ስለበዛ ነበር፡፡ በተለይ በቴአትርና ባህል አዳራሽ ያዘጋጃቸው ሥራዎች በየክልሉ እየተዘዋወሩ ባጠኑት ወዝዋዜ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ ከጥናት በተጨማሪ የየአካባቢው ተወላጆች እንዲሳተፉ ይደረግ ነበር፡፡

ዘፈን ያለ ምክንያት አይዘፈንም የሚለው ኪዳኔ፣ በየአካባቢው ስሜትን ለመግለጽ ወይም ለበዓላት የሚዘፈኑ ዘፈኖች የየራሳቸው አጨዋወት እንዳላቸው መታወቅ አለበት ይላል፡፡ ዛሬ ዛሬ የትኛው አለባበስና መጊያጊያጫ የቱን ብሔረሰብ እንደሚወክል ሳይታወቅ ክሊፕ ሲሠራ ይታያል፡፡ በየብሔረሰቡ ያሉ ቁሳቁሶችና አኗኗሩ መልዕክት ቢኖራቸውም ይህን ተረድተው በክሊፕ የሚያካትቷቸው ጥቂቶች ናቸው ይላል ባለሙያው፡፡

እንደ እሱ እምነት፣ ከአነስተኛ ቁሳቁሶች አንስቶ የአንድ ብሔረሰብ መገለጫ የሆኑ ግብዓቶች ተሟልተው ክሊፖች መሠራት ቢኖርባቸውም የሚያሠራው ሰው በትንሽ ወጪ ለመጨረስ ሲል እንዲካተቱ ጥረት አያደርግም፡፡ ከእውቀት ማነስ በተጨማሪ ለክሊፕ የሚወጣው በጀት አነስተኛ መሆን ችግሩን ያጎላዋል፡፡ ‹‹ቀድሞ ሁላችንም ስህተት ብንሠራም ተምረን አሁን ትክክለኛ መስመር ውስጥ ገብተናል፤ የአሁኑ ትውልድ ውበትና ገበያ መሳብ ላይ ያተኮረ ሥራ ይሠራል፤›› የሚለው ኪዳኔ፣ ውዝዋዜ ፈጽሞ መነሻውን መልቀቅ እንደሌለበትና ከምንም ዘዬ ጋር መቀየጥ እንደማይገባው በአጽንኦት ይናገራል፡፡

ውዝዋዜ ከሰውነት እንቅስቃሴ ባሻገር መልዕክት ማስተላለፊያ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በክሊፖች ውዝዋዜ አንዳች ስሜት በሚሰጥና መልዕክት በሚያስተላልፍ መልኩ መሰናዳት እንዳለበትም ያስረዳል፡፡ ባህል ለማሳየትና ለክሊፑ ትርጉም  ለመስጠት አስፈላጊው ወጪ ተመድቦ በጥንቃቄ እንዲሠራ ያሳስባል፡፡ ተወዛዋዦችና ኬሮግራፈሮች የሚከፈላቸውን አስበው ድምፃውያን የፈለጉት ዓይነት ውዝዋዜ ቢያቀርቡ እንጀራ ስለሆነ አይፈረድባቸውም ቢልም፣ ዘመናዊነት በሚል ከባህል ጋር የሚቀየጡ ውዝዋዜዎችና አልባሳት እንደሚቃወም ያስረግጣል፡፡ እሱ የእያንዳንዱ አካባቢ ባህል ምንም ሳይታከልበት ማራኪ እንደሆነ ይናገራል፡፡

ኪዳኔ ከሚያጣቅሳቸው አንዱ የካሳሁን ታዬ ‹‹ሶራ›› ላይ የሚታየውን ውዝዋዜና አለባበስ ነው፡፡ በሰቆጣ ተወላጆች የተሠራው ክሊፕ ባህሉ ላይ ምንም ሳይጨመር በአጭር ጊዜ ተወዷል፡፡ ‹‹ቢፍቱ ኦሮሚያ›› የተባለ የውዝዋዜ ቡድን የተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎችን የሚገልጽ ውዝዋዜና አልባሳት እንደሚያሳይም ይጠቅሳል፡፡ በዚህ ረገድ ለገበያ ሲባል ብቻ አካባቢን የማይወክሉ ሥራዎች ከሚሠሩ፣ በባለቤትነት የሚያሠሩ ድምፃውያን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያሳስባል፡፡ ክሊፖች የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በአንዳንድ ግለሰቦች አለባበስ ላይ መታየቱን በቅሬታ ይናገራል፡፡ ባህል እንዲጠበቅ የማድረግ ኃላፊነት ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አንስቶ የእያንዳንዱ ሰው እንደሆነና ክሊፖች በጥናት እንዲመረኮዙ ያሳስባል፡፡

ባህላዊ ክሊፖች ዘመናዊነትን ማሳየት ቢፈልጉ በዘፈቀደ ማደበላለቅ ሳይሆን ትክክለኛውን ባህላዊ ውዝዋዜ አቅርቦ ዘመናዊ የሚባለውን ለብቻው ማሳየት አለባቸው ይላል፡፡ አንደ ምሳሌ የጠቀሰው ክሊፕ ከፊሉ ኮንሶ የተቀረው አዲስ አበባ ላይ ተቀርጿል፡፡ ክሊፑ የኮንሶን ባህል በአካባቢውና ተጨማሪውን በአዲስ አበባ ማሳየቱ እንዳስደሰተው ይናገራል፡፡

ክሊፖችን በማዘጋጀት ከሚታወቁት ፕሮዳክሽን ካምፖኒዎች አንዱ ምዕራፍ ፕሮሞሽን በስድስት ዓመት ዕድሜው ከ130 በላይ ክሊፖች መሥራቱን የድርጅቱ ባለቤትና የፊልም ባለሙያ ወልደሩፋኤል ዓለሙ (ቢኒ ምዕራፍ) ይናገራል፡፡ ድርጅቱ በዋነኛነቱ የሚሠራው የባህላዊ ሙዚቃ ክሊፖችን ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ከሠሯቸው  የማሚላና ኪቺኒ ‹‹ኤሶ ኤሶ፣›› የንጉሡ ታምራት ‹‹ያኒኮ››፣ የታምራት ደስታ ‹‹ኤሃማ›› እና ‹‹አዲስ ዘመን››፣ የጃኪ ጎሲ ‹‹ሰላ በይልኝ›› እና የሚኪያስ ቸርነት ‹‹አወነይ›› ጥቂቱ ናቸው፡፡

ወልደሩፋኤል በክሊፖች ስክሪፕት ጽሑፍ፣ ዝግጅት፣ ቀረፃና አርትኦት ይሳተፋል፡፡ ክሊፕ ከማዘጋጀታቸው በፊት የሙዚቃውን የጥራት ደረጃ  እንደሚገመግሙ ይናገራል፡፡ ቀጥሎ ውዝዋዜውን የሚመራ ጽሑፍ ይሰናዳና ተወዛዋዦች ይመረጣሉ፡፡ ኬሮግራፈር የሚፈልጉት ከተጻፈው ስክሪፕት አንፃር ሲሆን፣ አልባሳትና የቀረጻ ቦታ መረጣም ይካሄዳል፡፡ እንደ እሱ ገለጻ፣ ከቀረፃ በፊት ነገሮች በአግባቡ መከናወናቸው ክሊፑ በመገናኛ ብዙኃን ከተለቀቀ በኋላ እንዳያስወቅስ ያደርጋል፡፡

ኬሮግራፈሮች ስለሚሠራው ውዝዋዜ ዓይነት ያላቸው እውቀት ከፍተኛ ግምት ሊሰጠው ይገባል ይላል፡፡ ክሊፖች ከተሠሩ በኋላ የሚነገርለት አካባቢ ተወላጆች ወይም ኦሪጅናሉን የሚያወቁ ቅሬታ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ፡፡  አልባሳቱና ውዝዋዜው ባህሉን እንደማይገልጹ የሚተቹበትም አጋጣሚም ጥቂት አይደለም፡፡ በቸልተኝነትና የእውቀት ማነስ የሚሠሩ ስህተቶች ቢኖሩም ትክክለኛው ሥፍራ ሄዶ ለመሥራት የሚያስችል አቅም ማጣትም መንስኤ እንደሆነ  ወልደሩፋኤል ያስረዳል፡፡

አቅም ያላቸውና የአንድ አካባቢን የዕለት ከዕለት ሕይወት በቅርብ ተከታትለው በክሊፖች ያካተቱ ባለሙያዎች ተደማጭነት ያገኛሉ ይላል፡፡ ከድርጅቱ ተሞክሮ በመነሳት ለክሊፕ ሥራ የየአካባቢው አስተዳደር አካላት ድጋፍ ቢሰጡ ጥሩ ሥራ ማቀረብ ይቻላል ይላል፡፡ እንደ ምሳሌ የጠቀሰውን የሞላ ካሳን ‹‹ኮንሶ›› ዘፈን ለመቅረጽ የአካባቢው አስተዳደር ባደረገላቸው ግብዣ ወደ ኮንሶ ሄደው ነበር፡፡

በክሊፑ ከአካባቢው ሰላምታ አሰጣጥ አንስቶ አመጋገቡና አኗኗሩ ባጠቃላይ ተካቷል፡፡ ክሊፑም ጥሩ ምላሽ እንዳገኘ ይናገራል፡፡ ሌላው ስለ አንድ የባህል ልብስ ነጋዴ የሚተርከው የዮሐንስ ሙሉጌታ ‹‹ሎምዬ›› ነው፡፡ የክሊፑ መነሻ ወላይታ ላይ ቀሪው ሽሮ ሜዳ ከሚገኙ ባህላዊ አልባሳት ሠሪዎች ተቀርጿል፡፡

ባለሙያው ክሊፕ የትም ይቀረፅ የትም ቦታው ለሚፈጠረው ስህተት ማስተባበያ እንደማይሆን ያሰምርበታል፡፡ ኦሪጅናሉ መቅረፅ ተመራጭ ቢሆንም መሄድ ካልተቻለ ስለ አካባቢው ባህል ጠይቆ መረዳት ይቻላል፡፡ ውዝዋዜውና አልባሳቱን እንዲሁም ክሊፑ የሚያሳያቸውን ክንውኖች ትክክለኛነት ማረጋገጥ የድምፃዊው፣ የኬሮግራፈሩ፣ የአዘጋጁና የተወዛዋዦቹም ኃላፊት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በተለይ ወጣት ድምጻውያን ለየት ያለ ባህላዊ ሥራ ሲያገኙ በስሜት ብቻ ለመገናኛ ብዙኃን ፍጆታ ለማዋል ይጣደፋሉ የሚለው ባለሙያው፣ ባህሉን ከሚያውቅ ሰው ጋር መመካከር መለመድ አለበት ይላል፡፡

ባጠቃላይ ዘርፉ ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቅ ነውና ጥንቃቄ ያስፈልጋል ይላል፡፡ ‹‹መቅረፅ ስለተቻለ ብቻ ድፍረት ተገቢ አይደለም፡፡ የባህላዊ ዘፈን ክሊፖች ብቻ ሳይሆን ሌላውም በስሜት ሳይሆን በእውቀት መሠራት አለበት፤›› ይላል፡፡ ወልደሩፋኤል ባህላዊ ውዝዋዜ እንዳለ ሆኖ በክሊፖች አዳዲስ ዘዬዎች ሲታከሉ የበለጠ ትኩረት ይስባል የሚል ዕምነት አለው፡፡ ባህል ዘመናዊ በሚል የሚቀርቡ ሥራዎች ባህልን እንደሚያሳድጉና ሁሉም ሰው እኩል እንዲወደው ለማድረግ ተመራጭ እንደሆኑ ይናገራል፡፡

ለ37 ዓመታት በተወዛዋዥነት፣ በውዝዋዜ አሠልጣኝነትና ኬሮግራፈርነት የሠሩት የሺዋስ ንግርቱ አስተያየታቸውን ከሰጡን አንዱ ናቸው፡፡ በ1970 ዓ.ም. ራስ ቴአትር በተወዛዋዥነት ከተቀጠሩ በኋላ ለ21 ዓመታት በአሠልጣኝነትና ኬሮግራፈርነት ሠርተዋል፡፡ ከሕዝብ ለሕዝብ ቡድን ጋር ተጉዘው ሲመለሱ በሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር፣ በቴአትርና ባሕል አዳራሽ ያገለገሉ ሲሆን፣ አሁን በሀገር ፍቅር እየሠሩ ነው፡፡ እሳቸው በዕድሜ ምክንያት ባይወዛወዙም የሚወዱትን ሙያ ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ ብርቱ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

ከቀደመው ጊዜ አንፃር አሁን ክሊፖች የሚያዘጋጁ ወጣቶች ፍላጎቱ ቢኖራቸውም በብዛት የሚጠቀሟቸው አልባሳት ትክክለኛውን ብሔረሰብ እንደማይገልጹ ይናገራሉ፡፡ ክሊፖች ለዕይታ ከመብቃታቸው አስቀድሞ መገምገምና መታረም አለባቸው፡፡ ክሊፖቹ  ለቀጣይ ትውልድ ባህል የሚያተላልፉና ለዓለም የሚያስተዋውቁ ከመሆናቸው አንፃር ጥንቃቄ ይጠይቃሉ ይላሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ በአማራ ክልል የጎጃም፣ ሰቆጣ፣ አገው፣ ጎንደር፣ ምንጃር፣ ከሚሴና ወሎ እየተባለ የተለያየ ጭፈራ አለ፡፡ አማራ ስለተባለ ብቻ አንድ ዓይነት አይሆንም፡፡ መጠነኛም ቢሆን ልዩነት ያላቸው እንቅስቃሴዎች ተነጣጥለው መቅረብ አለባቸው፤›› ይላሉ፡፡

በክሊፖች ከውዝዋዜ በተጨማሪ የተለያዩ አካባቢዎችን አኗኗር የሚያሳዩ ክንውኖች ማካተት አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ ስለ አፋር የተዘፈነ ክሊፕ ሲሠራ ግመልን የመሰሉ እንስሳት ወይም በአካባቢ ያለውን ልዩ አኗኗርና የሉሲን ቅሪተ አካል ማሳየት ይቻላል፡፡ ከተቻለ የአካባቢውን ተወላጆች ማሳተፍ ክሊፖቹን ከማሳመሩ በላይ ለቀጣይ ሥራዎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡

ባለሙያው የሽዋስ፣ ከወጣቶቹ የ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› አባላት የተለየ ሐሳብ አላቸው፡፡ በእሳቸው እምነት ባህላዊ ውዝዋዜ ከምንም ጋር መቀየጥ የለበትም፡፡ ከትውልድ ትውልድ  የሚተላለፉ ክሊፖች ትክክለኛ ባህል ማንፀባረቅ አለባቸው ይላሉ፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ሥራ እስከዛሬ ድረስ የሚወሳው ቱባ ባህልን መሠረት ስላደረገ ነው ይላሉ፡፡ የወቅቱ ሥራዎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኙ እንደሆኑም ይገልጻሉ፡፡

 እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ውዝዋዜን በትክክል ማሳየት የሰውነት እንቅስቃሴው የሚያስተላልፈውን መልዕክት ሳያዛባ ያደርሳል፡፡ የኩናማ ምት ለማስደንገጥና የጎጃም እንቅጥቅጥ ፍርኃትን ለማንፀባረቅ እንዲሁም ሌሎች ውዝዋዜዎችም መስመራቸውን ሳይለቁ ሲሠሩ ትርጉም ይሰጣሉ ይላሉ፡፡ በተያያዥ የትኛውም ዘፈን የሚያነሳው ርዕሰ ጉዳይ ለውዝዋዜው መሠረት መሆን አለበት፡፡ ስለ አገር፣ ፍቅር፣ ግብርና ወይም ሌላ ጽንሰ ሐሳብ ሲነሳ ክሊፑ ግጥሙን በሚገልጽ ውዝዋዜ መታጀብ አለበት ይላሉ፡፡

ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች የባህላዊ ሙዚቃ ክሊፖች በጥሩ አቅም እየተሠሩ ቢሆንም ስህተቶችም እንደሚስተዋሉ ይስማሙበታል፡፡ በሚዘፈንለት አካባቢ የሚቀረፁ ክሊፖች ተወዳጅ የመሆን ዕድላቸው ቢሰፋም ሁልጊዜ ላይሳካ ይችላል፡፡ ክሊፖቹ በማንኛውም ቦታ ቢሠሩ በጥናት ላይ የተመረኮዙና ትክክለኛውን ባህል የሚያንፀባርቁ መሆን እንደሚገባቸው ከባለሙያዎች ገለጻ መረዳት ይቻላል፡፡

በክሊፖች ዝግጅት ድምፃውያን፣ ኬሮግራፈሮች፣ ተወዛዋዦች እንዲሁም አዘጋጆች ኃላፊነት እንዳለባቸውም አመላክተዋል፡፡ የክሊፑ ግብዓቶች ባጠቃላይ የአንድ አካባቢን ትክክለኛ ባህል የሚያሳዩ መሆን እንዳለባቸው ባለሙያዎቹ ቢስማሙም፣ ባህሉን ዘመናዊ ከሚባል እንቅስቃሴ ጋር መቀየጥና ኦሪጂናሉን እንዳለ የማቅረብን ሐሳብ የሚደግፉም የሚቃወሙም አሉ፡፡ 

     

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...