Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሥነ ምግባር ጉድለቶችና ወንጀሎች በሕክምናው ዘርፍ

የሥነ ምግባር ጉድለቶችና ወንጀሎች በሕክምናው ዘርፍ

ቀን:

የመኪና አደጋ የደረሰበት ግለሰብ ወዲያው የተወሰደው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነበር፡፡ ታማሚውን ያየው ሐኪም ሌሊት ደም ሲሰጠው አድሮ በቀጣዩ ቀን የቀዶ ሕክምና እንደሚደረግለት ገለጸ፡፡ እንደተባለው ሌሊት ላይ ለተጐጂው ደም እየተሰጠ ስላልነበር ቤተሰብ አሁንም አሁንም ተረኛ ነርሶችን ይወተውት ገባ፡፡ ቢሆንም ለተጐጂው ደም ሳይሰጥ ይቀራል፡፡ ተጐጅም በማግስቱ ሕይወቱ ያልፋል፡፡

ቤተሰብ ለተጐጂው ሊደረግለት የሚገባ ነገር አልተደረገለትም በማለት ወደ ፖሊስ ይሔዳል፡፡ ነገር ግን ፖሊስ ጉዳዩን ሊያጣራ አልቻለም ያሉት የተጐጂ ቤተሰቦች ለዓቃቤ ሕግ አመለከቱ፡፡ ኋላ በዓቃቤ ሕግና በፖሊስ ንግግር መሠረት ጉዳዩ እንዲጣራ ሆኖ በሆስፓታሉ፣ በዶክተሩና በተረኛ ነርስ ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡ በዚህ 2003 ዓ.ም. ላይ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ይታይ በነበረ ክስ ሆስፒታሉና ዶክተሩ በመጨረሻ ነፃ ሲባሉ ተረኛ ነርሱ ላይ ሁለት ዓመት እስር ተፈርዷል፡፡

በተመሳሳይ የመኪና አደጋ አጥንቱ ክፉኛ የተጐዳ ታማሚ ከአንድ የግል ሆስፒታል ገብቶ የአጥንት ቀዶ ሕክምና ይደረግለታል፡፡ ቀናት ተቆጥረው ታካሚው እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲሞክር ሲደረግ እግሩ ፈጽሞ መንቀሳቀስ እንደማይችል ታየ፡፡ ጉዳዩ ሲመረመር በቀዶ ሕክምና ወቅት የበሽተኛው አጥንት መሆን እንደነበረበት ሳይሆን በተቃራኒ አቅጣጫ መገጠሙ ተረጋገጠ፡፡ ይሄ ኬዝ በኢትዮጵያ የምግብና የመድሃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ሥር በሚገኘው የሕክምና ሥነ ምግባር ኮሚቴ ታይቶ ቀዶ ሕክምናውን ያካሔደው ሐኪም የብቃት ችግር እንዳለበት በመታመኑ የሙያ ፍቃዱ ተነጥቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሚሠራበት ክሊኒክ ብቻም ሳይሆን በየካፍቴሪያውና በተለያዩ ቦታዎች እየተቀጣጠረ በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ያስገባቸውን መድሃኒቶች በቆዳ ሕመም ተቸገርን ለሚሉ ይሰጥ የነበረ የቆዳ ሐኪምም ፍቃዱ ተነጥቋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንዲት ሴት በተሰጣት መድኃኒት ጉበቷ ተመርዞ ሕይወቷ በማለፉ ነበር፡፡   

በተለያየ መልኩ ከሚሰሙ የሕክምና ሙያ ሥነ ምግባር ችግሮችና የወንጀል ኬዞች የተጠቀሱት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የሥነ ምግባር ጉድለቶች ታካሚን ካለማክበርና ከማመናጨቅ በመጀመር ከሥነ ምግባር ጉድለትነት አልፈው ወንጀል እስከመሆን ይደርሳሉም፡፡ ካነጋገርናቸው ባለሙያዎች ለመረዳት እንደቻልነው የሥነ ምግባር ጉድለቶች ከትምህርት፣ ከሙያዊ ብቃት፣ ከታካሚዎች መረጃ ምስጥራዊነት፣ ከታካሚዎች የሕክምና ይሁኝታ ከኮሙኒኬሽንና ከሌሎችም ጉዳዮች ጋር ሊያያዙ ይችላሉ፡፡

በየጊዜው በመገናኛ ብዙኃንም የተለያዩ ቅሬታዎች ይቀርባሉ፡፡ ተገቢውን አገልግሎት አለማግኘት፣ የሚገባው ሳይሆን መሆን የሌለበት ዓይነት ምርመራና መድሃኒት መታዘዝ፣ ተአማኒነት የሚጐድላቸው የላብራቶሪ ምርመራ ውጤቶች፣ የተጋነነና አላግባብ ክፍያ በተደጋጋሚ የሚነሱ ቅሬታዎች መሆናቸውን ያነጋገርናቸው ገልጸውልናል፡፡

በአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጤናና የሕክምና ትምህርት ማበልፀጊያ ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ፀደቀ አሳምነው እንደሚሉት ችግሮች ቢኖሩም ቅሬታዎች ስላሉ ብቻ የሚባለው ዓይነት ችግር በሚባለው መጠን አለ ማለት አይቻልም፡፡ ከታች እስከላይ የተቀናጀ ሲስተም ባለመኖሩ ተቀባይነት ያላቸው የሌላቸውም ቅሬታዎች የሕክምናና የሕግ ባለሙያዎች ላሉበት፣ የሕክምና ሙያ ማኅበራትና የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ከተወከሉበት የሥነምግባር ኮሚቴ ይቀርባሉ፡፡ ተቀባይነት የሌላቸው ቅሬታዎች የሚሏቸው ከሥነምግባር ጉድለት ወይም ከምርመራ ግድፈት ሳይሆን ከታካሚዎች ግንዛቤ እጥረት ወይም አለመረዳት የሚነሱትን ኬዞች ነው፡፡ ይህን ያስረዳ ዘንድ በመገናኛ ብዙኃን ቀርቦ የሰሙትን ኬዝ አስታውሰዋል፡፡

ታካሚው ምንም እንኳ ጥርሱን አምሞት ሕክምና ለማግኘት ወደ ጤና ተቋም ቢሔድም ሜትሮኒዳዞል የተባለ ለአሜባ የሚሰጥ መድሃኒት በዶ/ር እንደታዘዘለት ይናገራል፡፡ በዚህ ባለሙያዎች እንዴት በግዴለሽነትና በስህተት ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ ለማስረዳትም ይሞክር እንደነበር፣ መድሃኒቱ ግን ለጥርስ ሕመምም እንደሚሰጥ ዶ/ር ፀደቀ ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ያሉ በግንዛቤ ችግር የሚቀርቡ ቅሬታዎች ብዙ ቢሆኑም የሥነምግባር ችግሮች መኖራቸውን ግን ያምናሉ፡፡

አንድ የሕክምና ባለሙያ ምን ዓይነት ምርመራዎችን ማካሔድ፣ ኬዞችን ማየት አለበት የለበትም የሚለውን በተመለከተ ግልፅ የሆነ የተግባር ወሰን (Scope of practice) አለመኖር ችግር መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የዚህ በግልጽ መቀመጥ አንድ ስፔሻሊስት ምን ዓይነት ኬዞችን ለሰብ ስፔሻሊስቶች ማሳለፍ አለበት? ነርስ ሐኪም ሳታማክር በራሷ ብትወስን? የሚሉና መሰል ሁኔታዎች ላይ ግልጽ አቅጣጫ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ይህ በሌሎች በተለይም ባደጉ አገሮች ነገሮችን መስመር የሚያስይዝ ዕርምጃ ነው፡፡ የሕክምና መመሪያ (Treatment Guideline) አለመኖርም የፈጠረው ትልቅ ክፍተት አለ፡፡

ዛሬ ላይ በትምህርቱ ዘርፍ የተለያዩ ነገሮች ላይ ለውጥ በማድረግ ቁጥር ላይ ሳይሆን ጥራት ላይ ትኩረት እየተደረገ መሆኑን የሚገልጹት ዶ/ር ፀደቀ የተማሪ መብዛት በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ለሚያጋጥሙ የሥነምግባር ችግሮች ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ረገድ የተማሪ ቁጥር ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ተማሪና አስተማሪ ፊት ለፊት እየተያየ የተማሪ ፀባይ እየታየ እየታረመ ብቃትም በደንብ እየታየ እንዲሔድ ቁጥር ወሳኝነት አለው›› ይላሉ፡፡

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አምስተኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ወጣት ቴዎድሮስ ወርቁ የሕክምና አገልግሎት ሥነ ምግባርን በሚመለከት የሚሰጠው ኮርስ እንዲህ ነው የማባል እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡ መጀመሪያ የወሰደው የአንድ ሴሚስተር ኮርስ በአራት ቀናት መጠናቀቁን ያስታውሳል፡፡ ኮርሱ ተሰጥቷል ለማለት ያህል፣ በተማሪ በኩልም ውጤት እንጂ ዋናው ነገር ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ አይመስልም፡፡

 ‹‹ሕክምና የሚጠይቀው ትልቅ ልብና መካከለኛ አይኪው ነው›› የሚለው ቴዎድሮስ የሥነምግባር ኮርስን በጥሩ ሁኔታ የተማረው ሁለተኛውን ኮርስ ይሰጥ የነበረው መምህር ጥሩ ስለነበር ብቻ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ዶ/ር ፀደቀም የሕክምና ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት አንደገና ሊታይ ይገባል ይላሉ፡፡

ቴዎድሮስ እንደሚለው ታካሚዎችን ማመናጨቅ፣ ነገሮች ለታካሚዎች ግልጽ ይሆኑ ዘንድ አለማስረዳት፣ የአገልግሎት ፈላጊና የተቋማት አቅም ያልተመጣጠነ መሆን ለሥነምግባር ከዚህም ለሚያልፉ ጉድለቶች ምክንያት ነው፡፡ ታካሚዎችን ከልብ ለማዳመጥ አለመፍቀድ፣ ይህን መድሃኒት ውሰዱ እንጂ እንዲህ እንዲህ ውሰዱ ብሎ ያለማስረዳት ችግር ምናልባትም ብዙዎች የሕክምና አገልግሎት ፈልገው ወደ ጤና ተቋማት በሔዱ ቁጥር የሚያጋጥማቸው እውነት ነው፡፡

በሐኪሞች ችግሮች ይኖራሉ በሚል ጥርጣሬ ወደ ላብራቶሪ የሚላኩ ምርመራዎች ፖዘቲቭ (+v) የመሆን ዕድል ዝቅተኛ መሆን ላብራቶሪ ላይ የሚነሳ ተደጋጋሚ ቅሬታ መሆኑን የገለጹልንም አሉ፡፡ ምርመራው በሚገባ ስለማይካሔድ ይኖራል ተብሎ የተጠረጠረው ነገር አይታይም ስለዚህም ንፁህ ነው ተብሎ ይመለሳል፡፡

በውጩ ዓለም ታካሚዎች ሲሞቱ የተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች የተወከሉበት ቡድን (Panel of experts) ህልፈቱ ከበሽታው ወይስ ከተደረገለት ሕክምና ጉድለት የሚለውን ከተለያየ አቅጣጫ ይመረምራል፡፡ በዚህም የሕክምና ባለሙያዎች ለትልቅም ለትንሽም ነገር ተጠያቂ ሆነው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ይታያል፡፡ ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት ባለበት የአገሪቱ የሕክምና ዘርፍ ይህ ተግባራዊ ይሁን የሚባል ባይሆንም ባለሙያዎች ባንድም ይሁን በሌላ መንገድ ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያደርግ የሕግና የሥነምግባር ቁጥጥር ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ያምናል ቴዎድሮስ፡፡

በሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ታካሚዎች መረጃ ያላቸው እየሆኑ በመምጣታቸው የሕክምና አገልግሎት የሥነምግባር ጉድለት የግድ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ሆነ እንጂ የአገልግሎቱ ተደራሽነት ትልቅ ተግዳሮት በሆነበት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጉዳዩ ትኩረት የሚያገኝበት ትክክለኛ ጊዜ እንዳልሆነ የሚያምኑት ዶ/ር ፀደቀ የኮሙኒኬሽን ክፍተትን በተመለከተ የቴዎድሮስን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ ለምሳሌ ቀዶ ሕክምና ቢያስፈልግ ይህ ሕክምና ለምን እንደተመረጠና ሊኖር ስለሚችል አደጋና ሊገኝ ስለሚችል ጥቅም አውቀው እንዲወስኑ ነገሮችን ለታካሚዎች ማስረዳት እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ፀደቀ ይናገራሉ፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት ሐኪሞች ያሉትን የመስማትና የመቀበል ነገር ቢኖርም በዛሬ ኢንተርኔት ዘመን የተወሰነ መረጃ ያላቸው ታካሚዎች ጥያቄ ሲያነሱና ነገሮች እንዲብራሩላቸው ሲጠይቁ ይስተዋላል፡፡ በተቃራኒው ባለሙያዎች ወቅታዊ መረጃዎችን በማየት ዕርምጃቸውን ካላስተካከሉ ይህ መደረጉ ስህተት ነው ሲባል ‹‹በማውቀው ነው የሠራሁት›› የሚል መልስ ሊሰጥ ይችላል፡፡

ባለሙያዎችን ከሥነምግባር ደንብና ከሕግ አንፃር ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎቹን ተጠያቂ የማድረግ አግባብን ራሱ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርግ ሥርዓትን ከላይ እስከታች መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች የሚጋሩት ሀሳብ ነው፡፡

የብቃት ማረጋገጫ ፈተና፣ በየጊዜው የሚደረግ የፍቃድ እድሳት ዓይነት አሠራሮች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ወሳኝ ዕርምጃዎች መሆናቸውን ዶ/ር ፀደቀ ያስረዳሉ፡፡   

በ1994 ዓ.ም. የተቋቋመው የሕክምና ሙያ ሥነ ምግባር ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የነበረ ሲሆን፣ የ2002ቱን የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ተከትሎ የሥነምግባር ኮሚቴው በምግብ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ባለሥልጣን ሥር ሆኖ ተጠሪነቱም ለባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሆነ፡፡ በ2006 ዓ.ም. ደግሞ ኮሚቴው እንደ አዲስ መደራጀቱን ከባለሥልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኮሚቴው ዋና ሥራ ቅሬታዎች ሲቀርቡ ቅሬታዎቹን ከሥነምግባርና ከባለሙያ ከብቃት አንፃር ማጣራትና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን መውሰድ ነው፡፡ በባለሥልጣኑ የምግብ ጤናና ጤና ነክ ተቋማት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የሥነምግባር ኮሚቴው አባል አቶ መሳፍንት አበጀ እንደገለጹልን ይሔ አገልግሎት ሊሰጠን ሲገባ አልተሰጠንም የሚሉ፣ ሕልፈትን የተከተሉ ቅሬታዎች በተደጋጋሚ ይቀርባሉ፡፡ በብዛት የሚቀርቡ ቅሬታዎች ግን ከቀዶ ሕክምና ጋር የተያያዙ ሲሆኑ፣ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ደግሞ ከማዋለድ ጋር የተያያዘ ቀዶ ሕክምና ነው፡፡

የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የተወሳሰቡ በመሆናቸው እንደማንኛውም ወንጀል ሊታዩ እንደማይችሉ ዶ/ር ፀደቀ ይገልጻሉ፡፡ እንዲሁ በጥቅሉ ሲታይም ሁሉም የወንጀል ኬዞች የሥነምግባር ችግሮች ናቸው ሊባል ቢችልም ሁሉም የሥነ ምግባር ችግሮች ወንጀል ይሆናሉ አይባልም፡፡ በዚሁ መሠረት የሥነምግባር ኮሚቴው የተወሰኑ ነገሮችን አይቶ ወደ ፖሊስ፣ ፖሊስም በተመሳሳይ መልኩ ወደ ሥነ ምግባር ኮሚቴው የሚልካቸው ኬዞች አሉ፡፡ ከ2003 እስከ 2005 ዓ.ም. ከሙያዊ ሥነምግባር አንፃር እንዲታዩ ለኮሚቴው የቀረቡ 19 ኬዞች ተጣርተው ለፖሊስ መመለሳቸውን አቶ መሳፍንት ይገልጻሉ፡፡ በንፅፅር ኮሚቴው ለፖሊስ የላካቸው ኬዞች ቁጥር ግን ትንሽ ነው፡፡

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ተጣርተው በሥነምግባር ኮሚቴው ዕርምጃ የተወሰደባቸው ኬዞች ከሙያ አንፃር ሲታዩ የማህፀንና የፅንስ ሕክምና የመጀመሪያውን ቦታ ሲይዝ የጠቅላላና የአጥንት ቀዶ ሕክምና ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ይከተላሉ፡፡ በተቋም ደረጃ ሲታይ ከባድ የሥነ ምግባር ችግር ከታየባቸው 14 ኬዞች 10 የሚሆኑት የግል የሕክምና ተቋማት ላይ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ የ4 የግል ተቋማት ሐኪሞች (ሁለቱ የውጭ ዜጐች ናቸው) የሥራ ፍቃድ ሲነጠቅ በዘጠኝ የግልና መንግሥት ተቋማት ባለሙያዎች ላይ እገዳ መጣሉን አቶ መሳፍንት ጠቁመዋል፡፡ የሙያ ብቃታቸው ላይ ጥያቄ የተነሳባቸው ሦስት ባለሙያዎች (ሁለት ሐኪምና አንድ ነርስ) ብቃታቸው እንዲረጋገጥ እንደገና ልምምድ እንዲያደርጉ ተደርጓል፡፡

    

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...