Saturday, January 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየተጨዋቾች የዝውውር ረቂቅ መመሪያና ዕጣ ፈንታው

የተጨዋቾች የዝውውር ረቂቅ መመሪያና ዕጣ ፈንታው

ቀን:

ሰሞኑን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ ሲወሳ የሰነበተው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር ረቂቅ መመሪያ የጠራ መስመር ሳይያዝበት ከጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ተግባራዊነቱ እንደሚያመራ እየተነገረ ነው፡፡ ከወንድና ሴቶች እግር ኳስ ተጨዋቾች የተውጣጡ ተወካዮች ባለፈው ረቡዕ ‹‹ሐሳብን ስለመግለጽ›› በሚል ለፌዴሬሽኑ ቅሬታቸውን አስገብተዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ የተጨዋቾቹን ቅሬታ በግብዓትነቱ እንደሚጠቀምበት ገልጿል፡፡
‹‹ከከረመ የዘልማድ አሠራር ወጥቶ ወደሠለጠነና ሕጋዊ የዝውውር ፖሊሲ መግባት አለብን፣›› የሚለውን የክለቦችና የፌዴሬሽኑ አቋም ብዙዎች በመመሪያ ደረጃ እንደሚቀበሉት እየገለጹ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ሌሎች የእግር ኳስ ባለሙያዎችና ተጨዋቾች ደግሞ ‹‹የለም ይህ ረቂቅ ደንብ ብዙ ያልጠሩ ጉዳዮችን የያዘ በመሆኑ ጊዜ ተወስዶ ሊከለስ ይገባል፣›› ባይ ናቸው፡፡
በዚህ አጨቃጫቂ የተጫዋቾች ደረጃና የዝውውር ውል ላይ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ከሰጡ ባለሙያዎች መካከል የኢትዮ ስፖርት ጋዜጣ ባለቤትና የብስራት ስፖርት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ የረቂቅ መመሪያው መተግበር አስፈላጊ መሆኑንና ከፕሮፌሽናሊዝም ውጪ ይፈጸሙ የነበሩትን ዝውውሮች መስመር ከማስያዝ አንፃር ረቂቅ መመሪያውን እንደሚቀበለው ይገልጻል፡፡ ሆኖም የረቂቅ መመሪያውን ሙሉነት (አካቶነት) ግን ይጠራጠራል፡፡ እንደ ምክንያት የሚያነሳቸው ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ የአሳዳጊ ክለቦችን (የመንደር ማሠልጠኛዎችን) ካሳ የ‹‹ሶሊዳሪቲ ኮንትሪብውሽን›› አይመልስም የሚል ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የተጨዋቾች ፊርማ ክፍያ በደፈናው ሙሉ ለሙሉ መቅረት የለበትም፣ እንደየሁኔታው ከጠቅላላው የዝውውር ክፍያ የተወሰነ ፐርሰንት በፊርማ ወቅት ሊለቀቅ ይገባዋል ባይ ነው፡፡
ሌላው የልምምድ ዋጋ (ትሬይኒንግ ኮምፐንሴሽን) በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የግድ መሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ተጨዋች ወደ አንድ ክለብ ቢዘዋወር ተጨዋቹ ለዚያ ቦታ ለመድረስ ከመንገድ ዳር ጀምሮ እስከ ሙሉ ፕሮፌሽናል ያልሆኑ ክለቦች ድረስ ክህሎቱ እንዲጎለብት ድርሻ ስላላቸው ተጨዋቹን ካዘዋወረው ክለብ ሁለት በመቶው ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባ የፊፋ መመሪያ ይፈቅዳል፡፡ ሆኖም እነዚህ ነገሮች በረቂቅ መመሪያው አለመካተቱን ይገልጻል፡፡
እንደ መነሻ ረቂቅ መመሪያው ለአገሪቱ እግር ኳስ ዕድገት ሲባል መተግበር እንዳለበት ለብዙ ዓመታት ሲነገር መቆየቱን የሚናገረው መንሱር፣ አሁንም ከነጉድለቱ ወደ ተግባር እንዲቀየር መደረጉ ትክክለኛ አቅጣጫ አለመሆኑንም ያስረዳል፡፡ ‹‹እግር ኳስ ፍትሐዊ የንግድ ተቋም እስካልሆነ ድረስ በሌሎች አገሮች የምንመለከተውን ዓይነት ለውጥ ማምጣት አስቸጋሪ ነው፣›› የሚለው ጋዜጠኛው፣ ‹‹ረቂቅ መመሪያ መዘግየቱ ካልሆነ ተግባራዊ የመሆኑ ጉዳይ ሊያነጋግር አይገባም፡፡ ምክንያቱም አንድ ክለብ ኮንትራት ያስገባውን ተጨዋች ሊጠቀምበት ይገባዋል›› ይላል፡፡ ሆኖም ቀደም ሲል በተገለጸው መልኩ በዚህ ደረጃ ጉድለት እንዳለበት፣ ምክንያቱም አንድ ክለብ ኮንትራት ባስገባው ተጨዋች የመገልገል መብት እንዳለው ሁሉ፣ ተጨዋቹም ኮንትራት በፈረመበት ክለብ የማይመቸው ሁኔታ ቢኖር ኮንትራቱን ገዝቶ ወደፈለገው ክለብ የመዘዋዋር መብት እንደሚኖረው መካተት እንደነበረበት ያስረዳል፡፡
በረቂቅ መመሪያው ሊካተት እንደሚገባው፣ ሆኖም ሳይካተት የቀረው የአሠልጣኞች የተጨዋቾች ወኪል (ኤጀንት) አስመልክቶም፣ ምንም ያለው ነገር አለመኖሩ፣ ራሱ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ረቂቅ መመሪያው በሚፈቅደው የዝውውር ሥርዓት ስለሚያገኘው ጥቅም እንኳን እንዴት መሆን እንዳለበት አለመካተቱ የረቂቅ መመሪያውን ጎደሎነት እንደሚያመለክትም ጭምር ያስረዳል፡፡
ረቂቅ መመሪያውን የተቃረኑት ተጨዋቾች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባስገቡት የቅሬታ ደብዳቤ፣ ‹‹ረቂቅ መመሪያው ወደባርነት የሚወስድ ነው፣›› በሚል ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ ይገልጻሉ፡፡ የፊፋን መመሪያ በመጥቀስ ተጨዋቾች ከክፍያና ተያያዥ ጉዳዮች ከክለቦች ጋር በነፃነት የመደራደር መብትን እንደሚያሳጣም በደብዳቤው ተካቷል፡፡
የተጨዋቾቹ ደብዳቤ በዋናነትም በአገሪቱ ሕግ የግለሰብ መሠረታዊ መብት፣ አንድ ሠራተኛ በነፃነት ውል የመዋዋል፣ የመደራደር ሙሉ መብት እንዳለው ገልፆ፣ ከዚህ ሕግ በተፃረረ መልኩ ግን በደንብነት ሊፀድቅ የታሰበው ረቂቅ ደንብ በአንቀፅ 13.4.6 ላይ ‹‹አንድ ተጨዋችና ክለብ ቋሚ ክፍያን አስመልክቶ የሚደራደሩት በደመወዝ ብቻ ይሆናል›› በማለት የተቀመጠውን ተቃውመውታል፡፡ መመሪያውም ደንብ ሆኖ መድደቅ እንደማይችልም ይጠይቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፊፋ ባወጣው የእግር ኳስ ተጨዋቾች ደንብ ላይ ከዝውውር ሒደቱ በገንዘብ ደረጃ እንዲደራደሩ፣ ክለቦች ክፍያ እንዲፈጽሙ ያዛል፡፡ ለረቂቅ ደንቡ እንደ መነሻ የተመለከታቸው አገሮችም ይህንን ደንብ እንደሚተገብሩት፣ ከዚህ አኳያ ይህንኑ የፊፋን ደንብ ተከትሎ መሄድ ሲገባ ተጨዋችን ወደባርነት ሥርዓት የሚወሰድ ደንብ ማርቀቅ ተገቢ አለመሆኑንም ያስረዳል፡፡
በአንቀፅ 21.1.7 ክለቡ የፋይናንስ ችግር ውስጥ ቢወድቅ ተጨዋቾቹ የችግሩ ተጋሪ ሊሆኑ እንደማይገባ፣ የተጨዋችን ድርሻ በተመለከተም በሜዳ ላይ ክለቡ እንዲያሸንፉ ጠንክሮ መሠራት እንደሆነ፣ በአንቀፅ 22.1.6 ላይ ተጨዋቹና ክለቡ ‹‹ስለ ግብር አከፋፈል ሁኔታ በአገሪቱ ሕግ መሠረት መስማማት አለባቸው፣›› የሚለውን አስመልክቶ ታክስ መክፈል የዜግነት ግዴታ እንደሆነ፣ ይህም በቀጣሪዎችና በሠራተኞች መካከል በሚፈጸም ስምምነት ‹‹ሲያሻ የሚከፈል ወይም የሚተው አይደለም፣›› በሚል በቀጣሪዎቻቸው በኩል አስፈላጊውን የገቢ ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውን ይገልጻል፡፡ የተጨዋቾችን ወቅታዊ ብቃት አስመልክቶ፣ በዚህ ረቂቅ መመሪያ መካተት እንዳለበት በሌሎች አገሮች ተጨዋቾች በጨዋታ ወቅት ጉዳት ቢደርስባቸው በክለቦች ተገቢው ክትትልና የሕክምና ወጪያቸው እንደሚሸፈንላቸው፣ ሆኖም በአገራችን ግን የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑንና በአንቀፅ 22.1.8 ላይ ተጨዋቹ ‹‹ከክለቡ የእግር ኳስ ሥራዎች ውጪ በሌላ ተግባር ላይ መሰማራት አይችልም፣›› መባሉ ተገቢና ትክክል እንዳልሆነ ተጨዋቾች ለፌዴሬሽኑ ባስገቡት ደብዳቤ ተካቷል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ፣ ‹‹ፌዴሬሽኑ የተጨዋቾችን ሐሳብ እንደ ግብዓት ይጠቀምበታል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ይህ የተጨዋቹ የቅሬታ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ከመድረሱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ  ተጨዋቾቹ ጽሕፈት ቤት ድረስ መጥተው ረቂቅ መመሪያውን አስመልከቶ አንድ በአንድ ተነጋግረንበታል፡፡ በተጨማሪም ተጨዋቾቹ ረቂቅ መመሪያው እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበው ተሰጥቷቸው ሄደዋል፡፡ በወቅቱም የሚባለው ነገር ግልጽ አንዳልነበረላቸው አሁን ግን ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ግልጽ ሆኗል ብለው ሄደዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የሰጡንን ግብረ መልስ በግብዓትነት እንወስዳለን፤›› ብለው፣ ተጨዋቾቹ ጊዜ ተሰጥቷቸው እንዲመለከቱት ያቀረቡትን ጥያቄ አስመልክቶ ግን የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኃላፊነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ረቂቅ መመሪያውን ካዘጋጁት ባለሙያዎች አንዱ የሆኑትና የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ በበኩላቸው፣ ረቂቅ ሠነዱ ያለቀለት መመሪያ እንዳልሆነና ረቂቅ መመሪያውን የሚያጠናክርና የሚያሻሽሉ ግብዓቶች ከመጡ እንደሚካተቱት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ተጨዋቾች ላነሱላቸው ጥያቄዎች የገቢ ግብርና ተያያዥ ጥቅማጥቅሞችን በተመለከተ ተጨዋቾች ‹‹የገቢ ግብር እየከፈልን ነው፣›› የሚሉት በፊርማ ከሚያገኙት ውጭ በወር ከሚያገኙት ክፍያ ላይ መሆኑ፣ በረቂቅ መመሪያው በቀጣይ ስለሚከፈላቸው ወርኃዊ ክፍያ ካልሆነ አስከዛሬ በሚከፈላቸው ላይ ምንም ያለው ነገር እንደሌለ፣ ሆኖም የፊርማ የሚባለው የገንዘብ ዝውውር ሕጋዊ መስመር ከያዘ በኋላ ግን፣ ማንኛውም ተጨዋች ማግኘት ስለሚኖርበት የገንዘብ ጥቅም የመደራደር መብቱ በረቂቂ ደንቡ መካተቱን አስረድተዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁንም ሆነ ወደፊት ይህ ረቂቅ መመሪያ የማይሻሻልበት አንዳችም ምክንያት እንደሌለ ጭምር ተናግረዋል፡፡
የፊርማ የሚባለውን ገንዘብ አስመልክቶ ተጨዋቾቹ ያቀረቡት ቅሬታ የፊፋን መመሪያን ጨምሮ ማንኛውም አገር እንደማይሠራበት አቶ ገዛኸኝም ሆኑ ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ይናገራሉ፡፡
ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የሕግ ባለሙያ ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እየተነገረ የሚገኘውን የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር ጉዳይን እንደተከታተሉት ይናገራሉ፡፡ ባለሙያው እንደሚሉትም፣ ‹‹ለማንኛውም የሥራ ድርሻ አንድ ግለሰብ በአንድ ተቋም ለሥራ በሚፈለግበት ጊዜ ቀጣሪው አካል የአቀጣጠሩን መመሪያ መስፈርት ማውጣት መብቱ ነው፡፡ ሕገወጥ ሊያስብለው የሚችለው ቀጣሪው አካል የሚያወጣው የቅጥር መመርያ ከአገሪቱ አሠሪና ሠራተኛ ሕግ ውጪ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በተረፈ ግን ቀጣሪው የሚያወጣውንና የሚስማማውን መሥፈርት ማውጣት፣ ተቀጣሪው ደግሞ በመሥፈርትነት በተቀመጠው መመርያ መሠረት የመስማማትና ያለመስማማት መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ ቀጣሪው የሚቀጥረውን ሠራተኛ የኮንትራት ጊዜውን ጨምሮ የመወሰን መብትም አለው፡፡ ለወር፣ ለአንድ ዓመትና ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ የእግር ኳስ ተጨዋቾች የኮንትራት ሁኔታም ቢሆን ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደማይገባው ነው የምረዳው፣›› በማለት የእሰጣ ገባው መነሻ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ይናገራሉ፡፡
    በአብዛኛው በእግር ኳሱ ቤተሰብ ዘንድ ለአገሪቱ እግር ኳስ ዕድገት ፈር ቀዳጅ ሊሆን ይችላል ተብሎ በሚጠበቀው የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር ረቂቅ መመርያ ላይ፣ ይህን መሰሉ እሰጣ ገባ መስተዋሉና መነጋገሪያነቱም የቀጠለ ሲሆን፣ ለዚህም ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች የሚጠበቅባቸውን ያህል ጊዜ ወስደው ረቂቅ መመርያውን ሳያጠኑና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በበቂ ሁኔታ አልሠሩም የሚለው የብዙዎቹ አስተያየት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ረቂቅ መመርያ የአሳዳጊ ክለቦችና የማለማመጃ ሜዳዎችን (አማተር ክለቦችን) ጥቅም በማያማክል መንገድ ‹‹እኛ ብቻ እንደፈለግን እንጠቀም›› የሚል አቋም በአንዳንድ የዝውውር አስፈጻሚዎች ዘንድ መንፀባረቁንም በብርቱ ይተቻሉ፡፡ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ አሁንም የሚመክሩት ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች ረቂቅ መመርያው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ከተጨዋቾቹም ሆነ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በግልጽ ሊመክሩበትና በባለሙያዎች በስፋት ማስገምገም እንደሚያስፈልገው ነው፡፡  
 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...