Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርተጫዋቾችን የሚገዛው አዲሱ ረቂቅ ሕግ ይስተካከል

ተጫዋቾችን የሚገዛው አዲሱ ረቂቅ ሕግ ይስተካከል

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቦችንና መንግሥትን ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ዕድገታችንን ለማፋጠን በማለት 28 አንቀጾችን የያዘ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ደረጃና ዝውውር መመርያ ረቂቅ ደንብ በአጥኚዎች አማካይነት ማውጣቱን ሰምተናል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ተጨዋቾች የእግር ኳሱ ዋና ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላት መሆናችን እየታወቀ፣ ፌዴሬሽኑ እኛን አግልሎ ይህንን ሕግ ለማውጣትና ለማፅደቅ መሞከሩ አሳዝኖናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ረቂቅ ደንቡ መውጣቱን ከመገናኛ ብዙኃን ብንሰማም፣ እንደ ባለድርሻ አካል ጉዳዩ ስለሚመለከተን፣ በፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ተገኝተን በተወሰነ ደረጃ በማንበብ ተወያይተንበታል፡፡ ምንም እንኳ በተጣበበ ጊዜ ውስጥ ደንቡን በሙሉ ትኩረት አንብቦ አቋም ለመውሰድ ባይቻልም፤ ፌዴሬሽኑ፣ ክለቦችና ሌሎች የሚመለከተን አካላት በጥሞና እንድናየው ጊዜ እንዲሰጠን እየጠየቅን በነበረን ጊዜ ተጠቅመን ካነበብነው ረቂቅ ደንብ ውስጥ ያገኘነውን ጭብጥ በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የግለሰብ መሠረታዊ መብቶች ከሆኑት መካከል አንድ ሠራተኛ በነፃነት ውል የመዋዋል፣ የመደራደር ሙሉ መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ከዚህ ሕግ ጋር በተፃረረ መልኩ ግን በደንብነት ሊፀድቅ የታሰበው ረቂቅ ደንብ፣ አንቀጽ 13.4.6 ላይ «አንድ ተጨዋችና ክለብ ቋሚ ክፍያን አስመልክቶ የሚደራደሩት በደመወዝ ብቻ ይሆናል፤» በማለት አገራችን ከሰጠችን የግለሰብ መብት አኳያ ተፃራሪ አንቀጽ መያዙን ተመልክተናል፡፡ ከላይ በጠቀስነው ምክንያትም ይህ ደንብ ሕግ ሆኖ መፅደቅ አይችልም፡፡

      ከዚህ በተጨማሪም የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ባወጣው የእግር ኳስ ተጨዋቾች ደንብ ላይ ተጨዋቾች ከዝውውር ሒደቶች በገንዘብ ደረጃ እንዲደራደሩና ክለቦችም ክፍያ እንዲፈጽሙ ደንቡ ያዛል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ረቂቅ ደንብ ሲጻፍ መነሻ የተደረጉት አገሮችም ይህንን ደንብ ሲተገብሩት እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ እኛም የፊፋን ደንብ ተከትለን መሔድ ሲገባን፣ ተጨዋቾችን ወደ ባርነት ሥርዓት የሚወስድ ደንብ ማርቀቅ ተገቢ አይሆንም፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአንቀጽ 21.1.7 ላይ ‹‹ክለቡ የፋይናንስ ችግር  ውስጥ  በወደቀ ጊዜ ችግሩን እንደሚጋራ የኮንትራቱ አካል መሆን አለበት፤›› ይላል፡፡ የተጫዋች ሥራ መጫወትና በሜዳ ላይ ክለቡ እንዲያሸንፍ ጠንክሮ መሥራት ነው፡፡ ስለ ክለቡ ፋይናንስ ችግሮች የሚመለከተው የክለቡን አስተዳደርና ማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊዎች ነው፡፡ ስለዚህም አንድ ተጨዋች የክለቡን የፋይናንስ ችግር መካፈል አይገባውም፡፡ ከዚህም በላይ የተለያዩ ቁንፅል ምክንያቶችን በመደርደር የተጫዋቾችን ደመወዝ በመቁረጥ የራሳቸውን በጀት ማስተካከል በሚፈልጉ ክለቦች መጠቀሚያ እየሆነ መምጣቱን ከዚህ በፊት በነበሩን ልምዶች ተመልክተናል፡፡ ተጫዋች ኮንትራት እያለው ያለምንም ማስጠንቀቂያ ከክለብ ሲባረር፤ ከሚያገኘው ደመወዝ  ሰባና ሰማንያ ከመቶ ሲቆረጥ ማንም ባለድርሻ አካል ለተጫዋቹ ሲቆም አልተመለከትንም፡፡

በረቂቅ ደንቡ አንቀጽ 22.1.16 ላይ ‹‹ተጫዋቹና ክለቡ ስለ ግብር አከፋፈል ሁኔታ በአገሪቱ ሕግ መሠረት መስማማት አለባቸው፤›› ይላል፡፡ ታክስ መክፈል የዜግነት ግዴታ እንጂ በቀጣሪዎችና በሠራተኞች መካከል በሚፈጸም ስምምነት ሳቢያ፣ ሲያሻ የሚከፈል ወይም የሚተው አይደለም፡፡ እኛም ይህንን የዜግነት ግዴታችንን በማወቅና አገራችን የምትጠብቅብንን ግብር በቀጣሪያችን በኩል ስንከፍል ቆይተናል፡፡ አሁንም በመክፈል ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህም ረቂቅ ደንቡን ያወጣው አካል ይህንን አውቆ አንቀጹን ሙሉ በሙሉ እንዲሰርዝልን ካለሆነም እንዲያብራራልን እንጠይቃለን፡፡

      ረቂቅ ደንቡ አንቀጽ 13.4.1 ላይ ውል ያላቸው ተጨዋቾች እንዴት እንደሚዘዋወሩና ዝውውራቸው እንዴት እንደሚፈጸም ነጥቦችን ሲያስቀምጥ፣ ውላቸውን የጨረሱ ተጫዋቾች እንዴት እንደሚዘዋወሩ፣ ዝውውራቸውም እንዴት እንደሚፈጸም ግን ምንም ያስቀመጠው ነገር ባለመኖሩ፣ ይህ አንቀጽ ሰፊ ክፍተት እንዳለበት ተመልክተናል፡፡

ደንቡ በሚረቅበት ወቅት ደቡብ አፍሪካን ከመሰሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ልምድ እንደወሰደ ከመገናኛ ብዙኃን ተረድተናል፡፡ የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተጫዋቾችን በምድብ ሲከፍል አማተርና ፕሮፌሽናል ብሎ ያስቀምጣል፡፡ የእኛ ረቂቅ ደንብም ተጫዋቾችን አማተርና ፕሮፌሽናል በማለት በደረጃ እንደከፋፈለ ተመልክተናል፡፡ ይህ ደንብ ተጫዋቾችን ከመከፋፈሉም በላይ ክለቦችንና ተጫዋቾችን አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ውስጥ ይከታል ብለን እናምናለን፡፡ የረቂቅ ደንቡ አዘጋጅ አካል ይህንን ቀድሞ በመረዳቱ ይመስለናል ከዚህ አንቀጽ ቀጥሎ ባለው አንቀጽ ሥር የግልግል ፍርድ ቤት ያቋቋመው፡፡ ይህ ስህተት የተፈጠረው ከትርጉም ስህተት ወይም የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደንብን በትክክል ካለመረዳት ይመስለናል፡፡

በረቂቅ ደንቡ ክፍል ሦስት ላይ የተጫዋቾች ብቁነት የሚለው አንቀጽ ለምን በዚህ አንቀጽ ውስጥ እንደተካተተ ግልጽ አይደለም፡፡ የዚህ አንቀጽ ዋና ዓላማ ምዝገባና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን መመልከት ሲሆን፣ የተጨዋቾችን ብቁነት የሚለካው ማን እንደሆነ፣ ተጨዋቾችን ማን ብቁ ናቸው እንደሚል ካለመግለጹም በላይ በአገሪቱ ካሉት ክለቦች ውስጥ የተጫዋቾችን ብቃት መመዘን የሚችል አደረጃጀትና የሰው ኃይል ያሟሉ ክለቦች ስንት ናቸው የሚለውንም ያገናዘበ አይደለም፡፡ እነዚህ ነገሮች ባለተሟሉበት ሁኔታ በደንቡ ላይ ስለ ተጫዋቾች ብቃት ማውራት ትክክል አይመስለንም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተጫዋቹ ያለውን እምቅ ችሎታ እንዲያወጣ የሚያስችሉ ሜዳዎች፣ የሥልጠና መሣሪያዎች፣ ልብስ መቀየሪያ ያላቸው ስታዲየሞች እንዲሁም የሰው ኃይል ባለተሟላበት አኳኃን ሕጉን በተጨዋቾች ላይ ሆን ተብሎ ለመጫን የታሰበ አስመስሎታል፡፡

በውጭው ዓለም አንድ ተጫዋች ከእግር ኳስ የሚያገለው አስከፊ ጉዳት ቢደርስበትና ውሉ ቢያልቅ ተጫዋቹ ሲጫወትለት የነበረው ክለብ ውሉ ቢያልቅም እንኳ ሲያሳክመው እናያለን፡፡ በእኛ አገር ግን ተጫዋቾች በጉዳት ምክያትንም ሆነ ውላቸውን ሲጨርሱ የማያሳክማቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለመታከሚያ የሚሆናቸውን ገንዘብ ማግኘት ይችሉ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ይህ ሕግ ተጨዋቹ ራሱን የሚጠብቅበትም ሆነ የሚያሳክምበት መንገድ እንዳይኖረው የሚያደርግ ነው፡፡

የተጫዋቾችን እንዲሁም የቀጣሪ ክለቦች ግዴታዎችን በሚመለከት፣ ቀጣሪው ክለብ በሚያወጣው የክለብ ሥነ ምግባር ላይ በመመሥረት ውል ስንፈርም ቆይተናል፡፡ በሕግ አግባብም የሥነ ምግባር ደንብን የሚያወጣው ቀጣሪው አካል ሆኖ ሳለ፣ እዚህ ደንብ ውስጥ የመካተቱ ምስጢር አልገባንም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሠራተኞች ሕግ መሠረት ማንኛውም ሰው የፈለገውን ያህል ሥራ መሥራት ይችላል የሚል ሕግ መኖሩ እየታወቀ፣ በረቂቅ ሕጉ አንቀጽ 22.1.8. ላይ ግን ተጫዋቹ ከክለቡ የእግር ኳስ ሥራዎች ውጭ በሌላ ተግባር ላይ መሠማራት አይችልም ይላል፡፡ ይህ አባባል ማኅበረሰባችንን በበጎ ፈቃድኝነት ስናገለግል ለነበርነው፣ ራሳችንንና ቤተሰባችንን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ የተለያዩ ሥራዎችን ከክለቦቻችን ጋር በመስማማት ስንሠራ የቆየነውን ተጫዋቾች ያማከለ አይደለም፡፡ በውጭው ዓለም የምናያቸው ታላላቅ ተጫዋቾች ከአንድ ክለብ ወደ ሌላው ሲዘዋወሩ ከሚያገኙት የዝውውር ክፍያ በተጨማሪ ራሳቸውን በገቢ ያጠናክሩ ዘንድ የተለያዩ የማስታወቂያና የስፖንሰርሺፕ ሥራዎች ላይ ሲሳተፉ እናያለን፡፡ በተለይም የዝውውር ክፍያ የለም እየተባለና ተጨዋቾች ወር ጠብቀው ደመወዝ እንዲያገኙ መደረጉ ሳያንስ፣ ከዚህ ውጪ በሌላ ሥራ ላይ መሰማራት አይችሉም ማለት ተገቢ መስሎ አልታየንም፡፡

የምንመኘውንና የዓለም አገሮች በእግር ኳሱ የደረሱበት ደረጃ ላይ እንደርስ ዘንድ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ ነው፡፡ ተጫዋች ላይ ሁሉንም ነገር በመጫን የምንመኘው ደረጃ ላይ መድረስ አንችልም፡፡ ስለዚህም ከላይ ከጠቀስናቸው በተጨማሪ ደንቡን ካነበብን በኋላ ሌሎችም ጥያቄዎች ስለሚኖሩን የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ አካል የመወያያ መድረክ እንዲፈጥርልን እንጠይቃለን፡፡            

(የኢትዮጵያ ወንዶችና ሴቶች እግር ኳስ ተጫዋቾች)

የአሉሚኒየም ፋብሪካ ቀድመን ያቋቋምነው እኛ ነን

ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው ቅጽ 20 ቁጥር 1538 ሪፖርተር ገጽ 4 ላይ ‹‹ትራኮን ትሬዲንግ በሽርክና ያቋቋመው ኩባንያ 30 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት አገኘ›› በሚል ርዕስ አንድ ዜና ቀርቧል፡፡ በዚሁ ጽሑፍ ውስጥም የሚቋቋመው የአሉሚኒየም ፋብሪካ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው እንደሚሆን ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ኩባንያችን ቢ ኤንድ ሲ አሉሚኒየም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ጥራቱን የጠበቀና በአገራችን የኮንስትራክሽን ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኝ የአሉሚኒየም ፋብሪካ ከሦስት ዓመት በፊት አቋቁሞ በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ ፋብሪካው ‹‹ኢንተር አፍሪካ ኤክስትሩዥን›› በሚል ስያሜ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ቃሊቲ አካባቢ በከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የተቋቋመ ሲሆን የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን ቀጥሮ በማሠራት ላይ ይገኛል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ሥራውን ሙሉ በሙሉ እንዲረከቡት አቅደን ጠንክረን እየሠራን ነው፡፡

ኩባንያችን በአገራችን የአሉሚኒየም ፋብሪካ በማቋቋም ፈር ቀዳጅ ስለመሆኑ በተለያዩ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የተዘገበ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራትን በሚያረጋግጡ አካላትም በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ወክሎ የጥራት ተሸላሚ የሆነ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዓርብ ጥር 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በተላለፈው የቢዝነስ ዘገባ በኩባንያችን ሥር ስለተቋቋመው የአሉሚኒየም ፋብሪካ ሥራዎች በሰፊው ተዘግቧል፡፡

እውነታው ከፍ ብሎ የተገለጸው ሆኖ እያለ በሪፖርተር የአሉሚኒየም ፋብሪካ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ እንዳልተቋቋመ ተደርጎ መዘገቡ የኩባንያችንንና የአገራችንን በጎ ገጽታ የሚያደበዝዝ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በበኩላችን ጋዜጣው ከመረጃ እጦት እንጂ ሆን ብሎ እውነታውን ለመደበቅ ዘገባውን አውጥቷል ብለን አናምንም፡፡

ስለሆነም ከፍ ብሎ በተገለጸው ጋዜጣ ላይ የአሉሚኒየም ፋብሪካ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው ድርጅትን በተመለከተ የወጣው ዘገባ ታርሞና ፋብሪካው በኩባንያችን ቀድሞ መቋቋሙን የሚያስረዱ መረጃዎችን ለጋዜጣው በመላክ እውነታው እንዲጣራ የጠየቅን መሆኑን እናሳውቃለን፡፡

(ቢ ኤንድ ሲ አሉሚኒየም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...