ተሻለ /ስሙ የተቀየረ/ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለረዥም ጊዜ የቆየ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሥራው እያዋጣው እንዳልሆነ ለሁሉም ይናገራል፡፡ በየጊዜው ለሚያጋጥመው የገንዘብ እጥረት ከተለያዩ ሰዎች ብድር መውሰድ ልማዱ ሆኗል፡፡ የማኅበራዊ ትስስሩ መስፋቱና አማኝ መምሰሉ የብድር ምንጩ እንዳይነጥፍ ረድቶታል፡፡ ለብድር መከፈል ዋስትና እንዲሆን ስንቅ የሌለው ቼክ መቁረጥን ለምዶታል፡፡ አበዳሪዎቹ ቼኩን ሳያስመቱበት በፊት ቼኩ እንዳይከፈል በማገድ አበዳሪዎቹን ይሸሻል፡፡ በእርሱ ንግግር የባንኮቹ አሠራር የደረቀውን ቼክ ያለመልምልኛል ይላል፡፡ አበዳሪዎቹ ጠይቀው ሲታክታቸው፣ እንደማይከፍላቸውም እርግጠኛ ሲሆኑ፣ ፍርድ ቤት ክስ ይመሠርታሉ፡፡ ጉዳያቸውን የሚይዙላቸው ጠበቆቹ ጉዳዩ በአጭር ሥርዓት እንደሚታይና በቶሎ እልባት እንደሚያገኝ ቢመክሯቸውም በተጨባጭ ያለው የፍርድ ቤት ጉዳይ ከሰሙት የራቀ ነው፡፡ ተሻለ ክስ ከቀረበበት በኋላ ፍርድ ቤቶቹ ቀጠሮ እንዴት ሊያበዙለት እንደሚችሉ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ የመከላከያ ማስፈቀጃውን ዳኞቹ ለወትሮው እንዲፈቅዱ በሚችሉበት ሁኔታ ያቀርባል፣ እንዲከላከል ሲፈቀድለት የተለያዩ ምክንያቶችና ማስረጃዎች በማቅረብ መልስ ሳይሰጥ ቀጠሮ እንዲራዘምለት ይጠይቃል፣ ከዚያም የመከላከያ መልሱን ረዥምና ውስብስብ በማስመሰል ያቀርበዋል፡፡ ይህንም መሠረት አድርጎ ፍርድ ቤቱ የቀጠሮ ጋጋታ ይሰጠዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ለምርመራ፣ ማስረጃ ለመስማት፣ ለብይን፣ ለውሳኔ እያለ እንደሚቀጥርለት ስለሚያውቅ ፍርድ ቤት ሲመላለስ ይኖራል፡፡ ከተፈረደበትም በተመሳሳይ መልኩ ይግባኝ በማቅረብ ብዙው ጊዜውን በፍርድ ቤት ቅጥር በማሳለፍ በጎ ለሠሩለት አበዳሪዎቹ በክፉ ዋጋቸውን ይመልስላቸዋል፡፡ ክፋቱን በቅርቡ የሚያውቁ ጓደኞቹ ይህን ለምን እንደሚያደርግ ሲጠይቁት ‹‹ጊዜ ለመግዛት›› በሚል በድፍረት ይናገራል፡፡ ለእርሱ የቼክ የክፍያን ጊዜ ለማራዘም አዋጩ መንገድ ጉዳዩ ፍርድ ቤት መድረሱ እንደሆነ ይናገራል፡፡
የሥነ ሥርዓት ደንቦቹ ዓላማና አፈጻጸም
ለአብነት ያነሳነው ይህ ጉዳይ የፍትሕ ተቋማት ሕጉ ከሙያው በሚጠይቀው መልኩ የሚቀርብላቸውን /ክርክር/ ካላስተናገዱ ፍትሕ ለተጓደለባቸው ሰዎች ትክክለኛ ቦታ ላይሆኑ እንደሚችሉ ነው፡፡ የማንኛውም አገር ሕግ በይዘቱ በተቻለ መጠን ፍትኃዊ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙም እንደ ሕጉ ፍትኃዊ እንዳይሆን ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ የፍትሕ ተቋማቱ ወይም የፍርድ ቤቶች ጉዳዮችን የማየት ብቃት፣ ቅልጥፍና ትጋት ነው፡፡ እነዚህን መርሆች መሠረት አድርገው ፍትሕ በተጨባጭ ለተከራካሪዎች እንዲደርስ የሚረዱት፣ ለዳኞችም ጉዳዮችን እንዲመሩበት የተዘጋጁ ሕግጋት የሥነ ሥርዓት ደንቦች ናቸው፡፡ የሥነ ሥርዓት ደንቦች ዓላማ ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ ክርክሮች በፍጥነት፣ ፍትኃዊ በሆነ መልኩና ወጪ ቆጣቢ ሆነው እልባት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ጉዳዮች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የዳኛው ግዴታ ሕጉ በግልጽ ያስቀመጣቸውን የክርክር ደረጃዎች ሊወስዳቸው ከሚገባው ምክንያታዊ ጊዜ ውጭ ጉዳዩን በማየት አለማራዘም ነው፡፡ መጠበቅ ያለበትን ሥነ ሥርዓትም አለመጠበቅ፣ ሥነ ሥርዓቱ ተፈጽሞም በየጊዜው ያለበቂ ምክንያት ውሳኔ ሳይሰጡ መቆየት ፍትሕ ማጓደል ነው፡፡ በምሳሌ ብንመለከተው በመደበኛ የፍትሐ ብሔር ሙግት ክስ ሲቀርብ የሚያልፍባቸው ሒደቶች አሉ፡፡ ከሳሽ ክስ ይመሠርታል፣ ተከሳሽ የመከላከያ መልስ ይሰጣል፣ ፍርድ ቤቱ ክሱን ይሰማል፣ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ካለ ብይን ይሰጣል፣ ጭብጥ ይመሠርታል፣ ማስረጃ ይሰማል፣ ፍርድ ይሰጣል፡፡ እነዚህ ሒደቶች ሕጉ ዳኛው እንዲከተላቸው ያስቀመጣቸው በመሆኑ ዳኛው ሊያልፋቸው፣ ሊተዋቸው ወይም ሊያሳጥራቸው አይችልም፡፡ እነዚህን ሒደቶች ዳኛው ሲከተል የሚወስደው ጊዜ ጉዳዩ በፍጥነት እልባት እንዳያገኝ አድርጓል አያስብለውም፡፡ ፍጥነቱ የሚጓደለው ለእያንዳንዱ ሒደት ዳኛው ምክንያታዊ ያልሆነ ጊዜ ለተከራካሪዎች በመስጠቱ፣ በራሱ ምክንያት (ባለመዘጋጀቱ፣ መዝገብ በመብዛቱ፣ ጉዳዩን ባለመረዳቱ ወዘተ.) ሒደቱ እንዲራዘም በመፍቀዱ ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ መነሻ ያደረግነውን የቼክ ጉዳይ ብንመለከት ሕጉ በአጭር ሥርዓት እንዲታዩ ከደነገጋቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ በአጭር ሥርዓት በሚታዩ ጉዳዮች (ቼክ፣ ብድር፣ ኪራይ፣ እቁብ) ተከሳሹ ሊያቀርበው የሚችለው መከላከያ አሳማኝ ካልሆነ በቀር ሙሉ የመሰማት መብት አይኖረውም፡፡ ክሱ እንደቀረበ ዳኛው ተከሳሹ የመከላከያ ማስፈቀጃ ካለው እንዲያቀርብ መጥሪያ ይልክለታል፡፡ ተከሳሹ በአሥር ቀናት መከላከያውን ካላስፈቀደ ወይም በአሥር ቀናት ውስጥ ያቀረበው ማስፈቀጃና ዝርዝር ማስረጃ የቀረበበትን ክስ ለመከላከል የሚያበቃ አሳማኝ ምክንያት ካላቀረበ፣ ዳኛው የከሳሽን ክስ መርምሮ ውሳኔ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ የመከላከያ ማስፈቀጃውን በአግባቡ አለመመርመርና እንደተጠየቀ ተከሳሽ እንዲከላከል መፍቀድ ጉዳዮች ሕጉ ባስቀመጠው መንገድና ፍጥነት እንዳይጠናቀቁ ማድረግ ነው፡፡
ዳኞች የቀረቡላቸውን ጉዳዮች በተገቢው ፍጥነት ማስተናገዳቸው የሚሰጡት ፍርድ ፍትኃዊውና ወጪ ቆጣቢም እንዲሆን ይረዳቸዋል፡፡ አንድ የፍርድ ሒደት ፍትኃዊ ነው የምንለው ሕጉን መሠረት አድርጎ ለተከራካሪዎች የመሰማት መብታቸውን ጠብቆና ማስረጃ በአግባቡ ተመርምሮ ፍርድ ሲሰጥ ነው፡፡ ጉዳዩን አፈጥናለሁ ብሎ ፍትሕ መንፈግም፤ ፍትኃዊ እሆናለሁ በማለትም ያለአግባብ ጊዜ ማራዘምን ሕጉ አይፈቅድም፡፡ ተከራካሪ ወገኖች ጉዳያቸው በፍጥነት የሚታይላቸውና እልባት የሚያገኝ ከሆነም በሒደቱ የሚያወጡት ወጪ ይቀንሳል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጉዳይ ይዞ የሚመጣም፣ ለቀረበበት ክስም መልስ ሰጥቶ የሚሟገትም በፍርዱ ሒደት የሚያወጣው ወጪ አለ፡፡ ጊዜው ይባክናል፣ ለተለያዩ ጉዳዮች የገንዘብ ወጪ (ለትራንስፖርት፣ ለነዳጅ፣ ለጠበቃ፣ ለኮፒ ወዘተ.) ያወጣል፡፡ ጉዳዮች በፍጥነት በታዩ መጠን ተሟጋቾች የሚያወጡአቸው እነዚህ ወጪዎች ይቀንሳሉ፡፡ ፍርድ ቤቶች ጉዳዮች ባረዘሙት መጠን ግን ተሟጋቾች የሚያወጡት ወጪ እንደሚጨምር ነጋሪም አይፈልግም፡፡
ለምሳሌ በመነሻችን በተመለከትነው የቼክ ጉዳይ የፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ያለአግባብ ተለጥጦ አንድ ዓመት ወሰደ ብንልና በሁለት ወራት ልዩነት ፍርድ ቤቱ ሦስት ቀጠሮዎችን ቢሰጥ፣ በዓመት ተሟጋቾቹ በሚቀርቡባቸው 18 ቀጠሮዎች የሚያወጡአቸው ወጪዎች ከሚጠይቁት የዳኝነት መጠንም ሊያልፍ ይችላል፡፡ ጉዳዩ በፍጥነት ቢጠናቀቅ ኖሮ ለግል ጉዳያቸው፣ ለተሰማሩበት ሥራ ቢያውሉ አገሪቱ በተሻለ በተጠቀመች ነበር፡፡
ፍትሕ ከዘገየም ውጤቱ አደገኛ ነው
ፍርድ ቤቶች የሥነ ሥርዓት ሕጉን ዓላማ በዘነጉት መጠን በአገራችን የሚፈጠረው ባህል፣ ለፍርድ ቤት ያለው አመለካከትና የፍትሕ እሳቤ የተዛባ ይሆናል፡፡ ‹‹ከሳሽ ከመሆን ተከሳሽ መሆን ይሻላል›› የሚለው ልማዳዊ አባባል ፍትሕ ለማግኘት ረዥም ጊዜያትን በፍርድ ቤት ለሚያሳልፉ መብት ጠያቂዎች ሲነገር የምንሰማው ነው፡፡ ሕዝቡም ጉዳዮች ምክንያታዊ ያልሆኑ ጊዜያትን እየወሰዱ ተከሳሾች በፍርድ ቤቶች አሠራር ክፈተት ጊዜ የሚገዙባቸው ተቋማት በሆኑ መጠን ፍርድ ቤት መብቴን ከምጠይቅ፣ እምባዬን በእጄ ወደ ሰማይ ብረጭ ይቀላል በሚል ዜጋው ምድራዊ መፍትሔ ለመፈለግ ወደ ኋላ ይላል፡፡ ጉልበተኛውም ፍርድ ቤት ከመመላለስ በጉልበቴ፣ በዛቻና በማስፈራራት መብቴን አስከብራለሁ በማለት ፍርድ ቤቶች ላይ ሕዝቡ ያለው መተማመን በጊዜ ሒደት ይጠፋል፡፡
ቀጠሮ የሚበዛ፣ ጉዳዮች በተገማች ጊዜ የማይጠናቀቁ ከሆነ የጠበቃስ ደመወዝ ከወዴት አለ? ፈጣንና ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት መኖሩ ጠበቆችም የደንበኞቻቸውን ጉዳይ በተገቢው ጊዜ እንዲያጠናቅቁ ይረዳቸዋል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ጠበቆች ቀጠሮ ጠባቂ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ባለጉዳይም የፍርድ ቤቱን ነባራዊ ሁኔታ ባለመረዳት ጠበቆቹን የሚጨቀጭቅ ይሆናል፡፡
ፍትሕ ለምን ይዘገያል?
ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ለመስጠት ወጥና ሁሉን አቀፍ ጥናት ያስፈልጋል፡፡ ይህ በሌለበት ሁኔታ ሁሉም ከዕለት ተዕለት ተሞክሮ የሚያስተውለውን ከመናገር፣ ተቋማትም የራሳቸውን እይታ ከማንፀባረቅ ውጭ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስልም፡፡ ተቋማቱ ብዙ ጊዜ ከሚያነሷቸው ምክንያቶች ብንጀምር የተወሰነ ነገር ማለት እንችላለን፡፡ ፍርድ ቤቶች ያሏቸው መዛግብትና የዳኞች ቁጥር ስለማይመጣጠን፣ የዳኞች የሥራ መልቀቅ መብዛት፣ የዳኞች ብቃትና ተከታታይ ሥልጠና ማነስ፣ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ የማይውሉበት ሁኔታ መኖር የተወሰኑት ናቸው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች በፍርድ ቤቶች መዛግብት ለረጅም ጊዜያት እየተቀጠሩ ባለጉዳዮች ሲመላለሱ እንደሚስተዋል ባለድርሻ አካላት የሚያስተውሉት ጉዳይ ነው፡፡ ተቋማቱ ባያነሱትም ዳኞች ሕጉን በጥብቅ የመከተልና ጉዳዮችን በፍጥነት ለማስተናገድ ያላቸው ዝንባሌ አነስተኛ መሆን ሊታለፍ የማይገባው ፍትሕን ከሚያዘገዩ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ ማንም ባለጉዳይ ፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ ሲገኝ የሚጠብቀው ዳኛው የመንግሥት ሠራተኛ የመሆኑን ያህል የተቀጠረውን መዝገብ መርምሮ ባለጉዳዮቹን እንደሚያስተናግድ ነው፡፡ ያለምክንያት ቀጠሮ የሚሰጥ ከሆነ ግን ሥልጣኑን ያለተጠያቂነት የያዘው ያስመስለዋል፡፡
ከፍትሕ ተቋማቱ ውጭ ያሉ ባለድርሻ አካላትም ለፍትሕ መዘግየት የራሳቸው አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ከላይ በመነሻችን የተመለከትነው ጉዳይ ለዚህ ዓብይ አስረጅ ነው፡፡ አቶ ተሻለ ለቆረጡት ቼክ ኃላፊ መሆናቸውን አጥተውት ሳይሆን የፍርድ ቤቶችን ልማድ ጠንቅቆ በመረዳት ጊዜ ለመግዛት የሚያስችላቸው መሆኑን በመረዳታቸው ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች በፍርድ ቤቶች ያልተስተካከሉ አሠራሮችንና ፍትሕ የሚያዘገዩ ልማዶችን ለተንኮላቸው መሸፈኛ ያደርጉታል፡፡ በዚህ ረገድ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎችም አቤቱታዎችን በመዘብዘብ፣ የአቤቱታ ማሻሻል ጥያቄዎችን ያለአግባብ በማቅረብ፣ ጊዜያዊ ውጤት ያላቸውን (እግድ፣ ቀጠሮ ይራዘምልን፣ መዝገብ ተደረበብኝ ወዘተ) ዓይነት አቤቱታዎችን በማብዛት ፍትሕ እንዲዘገይ ሊያደርጉ ስለመቻላቸው የዕለት ተዕለት ተሞክሯችን አሳይቶናል፡፡
ፍትሕ እንዳይዘገይ ምን ይደረግ?
ፍትሕ በተሻለ ፍጥነት በፍርድ ቤቶች እንዲሠራ ዋና አስተዋጽኦ ያላቸው ፍርድ ቤቶች ራሳቸው ናቸው፡፡ ለዚህ መነሻ ባደረግነው ጉዳይ ለመገንዘብ እንደሚቻለው ዳኞች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ፍትሕ ለማዘግየት ለሚፈልጉ ወገኖች መደበቂያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የዚህ ዋና መፍትሔ ዳኞች ሕጉንና ማስረጃ ብቻ መሠረት አድርገው ጉዳዮችን እንዲያስተናግዱ ማድረግ ነው፡፡ ተከራካሪ ወገኖች የተለያዩ አቤቱታዎችን በማቅረብ ፍትሕ እንዲያዘገዩ፣ የአቤቱታዎቻቸው ይዘት ዋና ጠቃሚ ፍሬ ነገርን ብቻ እዲይዙ፣ ቀጠሮ እንዲቀየር የሚያቀርቡት ምክንያት አሳማኝ ስለመሆን አለመሆኑ በአግባቡ መመርመር ተገቢ ነው፡፡ እያንዳንዱን ጉዳይ በነጠላ ልብ ብለው መርምረው ቀጠሮ የሚቀጥሩ ካልሆነ በቀጠሮው ቀንም ከፍርድ ቤቱ የሚጠበቀውን ሥራ ማጠናቀቅ ካልቻሉ ፍትሕ መዘግየቱ አይቀርም፡፡ በልማድ ብቻ መዝገብን ሳይመረምሩ፣ ተገቢውን ሳይሠሩ ዝም ብሎ መቅጠር ሕጉም አይፈቅደውም፡፡ በኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጥረው አመለካከት አሉታዊ መሆኑ አይቀርም፡፡ እንደ ማንኛውም የመንግሥት ባለጉዳይ የፍርድ ቤቶች ባለጉዳይ የሆኑ ወገኖችም ተገቢው ሥራ በተገቢው ጊዜ እንዲፈጸምላቸው የመጠየቅ መብት ያላቸው መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በሕጉ ቀጠሮ የሚለወጥበትን ሁኔታዎች የሚገዙ ደንቦች ያሉ በመሆኑ እነዚሁ ደንቦች ተፈጻሚ ሊሆኑ ይገባል፡፡
በሌላ በኩል ዳኞች እንደ ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ለሚሠሩት ሥራና ለሚያስከትለው ኃላፊነት ተጠያቂነት እንዳለባቸው መዘንጋት አይገባም፡፡ ግልጽ ሕግጋትን ባልተገበሩና ያለተገቢ ምክንያት ቀጠሮ በመቀያየር ፍትሕ በሚያዘገዩበት መጠን ተጠያቂነታቸውን የሚያረጋግጠው ሥርዓት ተፈጻሚ ሊሆን ይገባል፡፡ የዳኞች የሥነ ምግባር ደንብ ዓላማውም፣ ግቡም ከዚሁ የዘለለ አይደለም፡፡ የመገናኛ ብዙኃን አራተኛ የመንግሥት አካል ናቸው የሚባሉትን ያህል ዳኞችና ፍርድ ቤቶች ላይ እውነትን መሠረት አድርጐ የሚሰጡት ትችት አለመኖሩ የፍትሕ መዘግየት ቸል እንዲባል አድርጐታል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን የገለልተኝነትና የነፃነት መብት በማይጥስ መልኩ የፍትሕ መዘግየት እንዳይኖር፣ ወደ ከፋም ደረጃ እንዳይደርስ ሚዲያዎች ፍርድ ቤቶች ላይ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ የተመለከትነው የአቶ ተሻለ ጉዳይ ፍትሕ ለሚዘገይባቸው ፍትሐ ብሔራዊ ጉዳይ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡