Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየምርጫ ሥነ ምግባር ቢኖርም ተግባራዊነቱ ላይ ጉድለቶች እየታዩ ነው

የምርጫ ሥነ ምግባር ቢኖርም ተግባራዊነቱ ላይ ጉድለቶች እየታዩ ነው

ቀን:

በአሳምነው ጐርፉ

የኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ሰማንያ ሦስት ዓመት ሞልቶታል፡፡ (ከ1923 ዓ.ም. የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግሥት አንስቶ) ነበር ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡ ልክ አሜሪካኖች ሕገ መንግሥታዊ ምርጫ የጀመርነው እ.ኤ.አ. በ1790 ነው እንደሚሉት፡፡ አሜሪካኖቹ ይህን ይበሉ እንጂ ያን ጊዜ የነበራቸው ምርጫ ጥቁሮቹንና ሴቶችን የማያሳትፍ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከነጮቹም በምጣኔ ሀብታዊ ክፍፍል ሀብታሞቹን ብቻ ያቀፈ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ በንጉሡ ዘመን የእንደራሴዎች ምርጫም ሆነ በደርግ ጊዜ የተሞከረው የሸንጐ አባላት ምርጫ ከዴሞክራሲያዊ ምርጫ ባህሪ አኳያ ሲመዘኑ በርካታ ችግሮች ነበሩባቸው፡፡ አንደኛው በአገሪቱ ያሉ በርካታ ብሔሮችን እንደ ሕዝብ ከመቁጠር ይልቅ የገዥ መደቡ ታማኝነት፣ ባለርስትነትና ባለሀብትነት በኋላም የደርግ ኢሠፓ አባልና ደጋፊነት ብቻ ብቸኛው ለመመረጥ የሚያስችል መሥፈርት ሆኖ መታየቱ ነው፡፡ ሕዝቡ የሥልጣን ባለቤት መሆን ሲገባው የመምረጥም ሆነ የመወሰን ዕድሉ በገዥዎቹ የተቀነበበ፣ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲና አስተሳሰብም የሚስተናገድበት ዕድል የተዘጋ ሆኖ አልፏል፡፡

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣም ሆነ በሽግግሩ መንግሥት ዘመን የተሻለ የዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ ምርጫ ሙከራ መታየት ጀምሯል፡፡ ለዚህ አባባል ማሳያ የሚሆኑ ጥቂት ነጥቦችን ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በቀዳሚነት በሕገ መንግሥቱ የዜጐች በነፃነት የመደራጀት፣ የፈለጉቱን ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ የመመሥረትና ለሥልጣን የመፎካከር መብት ያጎናፀፋቸው መሆኑ ነው፡፡ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ማናቸውም የአገሪቱ ዜጐች (በሕግ ከታገዱት በስተቀር) የመምረጥም ሆነ የመመመረጥ መብታቸው ተረጋግጧል፡፡

ሌላው ለዜጎች ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ ጉዞ ወሳኝ የሚባለው የሐሳብና የመረጃ ነፃነት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና አግኝቷል፡፡ በዚህም የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን ያረጋገጠው ቅድመ ምርመራም ተወግዷል፡፡ አፈጻጸም ላይ እንደ ታዳጊ ማኅበረሰብ የሚታዩ የተለያዩ ክፍተቶች ቢኖሩም በሕግና ሥርዓት የተበጁ መርሆዎችና ድንጋጌዎች እንደ ቀላል የሚታዩ አይደሉም፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ግን ባለፉት 24 ዓመታት ሕዝቡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ላይ እያሳየ የመጣውን የሠለጠነ ግንዛቤ ያህል የፖለቲከኞቹ ብቃት፣ ጥንካሬና ዴሞክራሲያዊነት አልጎለበተም፡፡ የተቃዋሚው ጎራ በውስጡ የዴሞክራሲያዊነት ባህሪ እያጣ፣ በፕሮግራምም ሆነ በፖሊሲ እየጠነከረ መምጣት ባለመቻል፣ መቀናጀት፣ መዋሀድና መተባበር እየተሳነው የመጣ ነው፡፡ ሁለትና ሦስት ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ ቃና ያላቸው መሠረተ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸው ፓርቲዎች ከመታየታቸው ይልቅ፣ በየትም አገር ባልታየ ሁኔታ 70 እና 80 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩበት ምርጫ ለማየትም ተገደናል፡፡

በገዥው ፓርቲና በመንግሥት በኩል ከሕገ መንግሥቱ አንስቶ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን በመንደፉ በጥንካሬ የሚጠቀሱ ተግባራት አሉ፡፡ አፈጻጸሙ ላይ ግን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይበጁ የተለያዩ እንቅፋቶች መደቀናቸው አልቀረም፡፡ አንደኛው መንግሥትና ገዥው ፓርቲ የሚለያዩበት መስመር እየቀጠነ መምጣቱ ነው፡፡ ከላይ እስከ ታች በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያሉ የገዥው ፓርቲ አባላት፣ መንግሥታዊ መዋቅሩና የመንግሥት ሀብትና የሰው ኃይል ለፓርቲው ሥራና ጥቅም የሚውልበት ጊዜ እየበዛ መጥቷል፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይም በምርጫ ወቅት አደጋው ከፍተኛ ነው፡፡

በሌላ በኩል የፍትሕ አካላት፣ የፖሊስና የፀጥታ እንዲሁም አስተዳደሮች ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድን ተከትለው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በገለልተኝነት ዓይን ከማየት ይልቅ፣ ከሕጉ በተፃራሪ ቆመው ይታያሉ፡፡ ይልቁንም በጠላትነትና በወንጀለኝነት በማየት ሕግና ሥርዓትን በመጣስ ጭምር ግልጽና የእጅ አዙር ጫናዎችን የሚያሳድሩ አካላት አሉ፡፡ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃንም ቢሆኑ ነፃ፣ ገለልተኛና ሚዛናዊ ሆነው በተለይ በምርጫ ወቅት መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡ ይህ ድርጊታቸው ሕገወጥነት ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ጉዞውን የሚያሰናክል ነው፡፡

ከእነዚህ እውነታዎች አንፃር ሲመዘን ነው ምርጫን በፖለቲካ ፓርቲዎች ሥነ ምግባር መርህ መምራት አስፈላጊነቱ አያጠራጥርም፡፡ በዚህ ረገድ የተለያዩ የአውሮፓ፣ የእስያና የአፍሪካ አገሮች ተሞክሮ ሲታይ የቀደመ ሆኖ ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር ተረቅቆ የፀደቀው በ2002 ዓ.ም. በአራተኛው ብሔራዊ ምርጫ ወቅት ነበር፡፡ በወቅቱ ኢሕአዴግ፣ መኢአድ፣ ኢዴፓና በአቶ አየለ ሜሚሶ የሚመራው ቅንጅት ተስማምተው የተፈራረሙት የምርጫ ሥነ ምግባር፣ በአሁኑ ወቅት ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደፈረሙበት ይታወቃል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ሌሎች አምስት ፓርቲዎች አሉ ማለት ነው፡፡

አገራችን በ1997 ዓ.ም. በምርጫ ምክንያት የገባችበት ውዝግብ፣ ሁከትና ብጥብጥ ገጽታዋን አጠልሽቶት ነበር፡፡ ሊደገሙ የማይገባቸው ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች የሰው ልጆች ሕይወት አስገብረዋል፡፡ በተለይ ከዘረኝነትና ከአጥፊ ጠባብነት ጋር የተቆላለፉ ፀያፍ ተግባራት መቻቻል፣ አብሮነትና መከባበርን ሁሉ በሚያፈርሱበት መንገድ በከተሞች ተከስተዋል፡፡ የምርጫ ኮሮጆ ተሰረቀና ምርጫ ተጭበረበረ የሚለው መረጃም ጣሪያ የሚሰነጥቅ ነበር፡፡

እንደዚያ ያሉ አለመተማመኖችና ውዝግቦች እንዳይደገሙ ብሎም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ነው የምርጫ ሥነ ምግባር ሕግ የተዘጋጀው፡፡ መርሆዎችን በዝርዝር እንመልከት፡፡

አንድ ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊ የሚባለው እንደ ምርጫ ሥነ ምግባር ያሉ የጋራ ጉዳዮች ፀድቀው ተግባራዊ ሲሆኑ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ቀዳሚው ‹‹መራጮች በነፃነት በድምፃቸው የፖለቲካ ውሳኔ ሲያሳልፉ›› የሚለው ነው፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ዜጐች በከተማም ይኑሩ በገጠር፣ ወንዶችም ሴቶችም እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመታት በላይ የሆኑ ዜጐች በያሉበት እንዲመርጡ መደረግ አለበት፡፡ የፈለጉትን እንዲመርጡም ድምፃቸውን ያለምንም ዓይነት ተፅዕኖ ጫና በራሳቸው ውሳኔ እንዲሰጡ መደረግ አለበት፡፡ እዚህ ላይ ባለፉት ምርጫዎች ከገዥው ፓርቲም ሆነ ከአንዳንድ ተቃዋሚዎች ይሰነዘሩ የነበሩ ጫናዎች እንደነበሩ ግን መካድ አይቻልም፡፡ ስለሆነም ዘንድሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላትና መራጮች ለቀዳሚው የምርጫ ሥነ ምግባር መርሆ ሊገዙ ይገባል፡፡

ሁለተኛው ‹‹መራጮች ስለተፎካካሪዎች በበቂ ሁኔታ መረጃ ካገኙ›› የሚል ነው፡፡ ይህ ማለት በአገሪቱ በሰላማዊ፣ በሕጋዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በምርጫ የሚፎካከሩ ፓርቲዎች ፍትሐዊና ተመጣጣኝ መብትን ይመለከታል፡፡ ፓርቲዎቹ ያላቸውን ፖሊሲ፣ ስትራቴጂም ሆነ ፕሮግራም ለሕዝቡ ለማስተዋወቅ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃንን በፍትሐዊነት ሊጠቀሙ ይገባል፡፡ ከግልና ከሌሎች ሚዲያዎችም ገለልተኛና ሚዛናዊ አገልግሎትን አግኝተው ወደ ሕዝቡ ሊደርሱ ይገባል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በሕዝባዊ ስብሰባ፣ በሰላማዊ ሠልፍም ሆነ በቤት ለቤት ቅስቀሳ ፓርቲዎች ይመርጡናል ብለው የሚያስቧቸውን ደጋፊዎቻቸውን መቀስቀስና ማሳመን ይችላሉ፡፡

ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ዜጐች (መራጮች) ስለተወዳዳሪዎች በቂ መረጃ ለማግኘት ይችላሉ ማለት ነው፡፡ በአገራችን ከታዩት ያለፉት አራት ምርጫዎች አንፃር ስናይ ዜጐች የፓርቲዎችን አቋምና ፖሊሲ የሚገነዘቡበት ዕድል ዝግ ነበር ሊባል አይችልም፡፡ ምንም እንኳን በሒደቱ ውስጥ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች መኖራቸው ባይካድምና የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድክመት ቢኖርም ሕዝቡ የሚመዘንበት ዕድል ነበረው፡፡ በዘንድሮው ምርጫ እየተስተዋለ ያለው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውዝግብ፣ የውስጠ ዴሞክራሲ ማጣትም ሆነ ወደ መቀናጀትና ኅብረት ያዘነበለ አካሄድ አለመታየት፣ ሕዝቡ ተፎካካሪዎችን አመዛዝኖ ለመምረጥ እያስቸገረው ይመስላል፡፡ ፓርቲዎቹ ሕጋዊነታቸውን ለማስቀጠል ፈተና የተደቀነባቸውም መስሏል፡፡

ሦስተኛው መርሆ ‹‹ግልጽና ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚ መመደብ›› የሚለው ነው፡፡ ባለፉት ጊዜያት ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ለገዥው ፓርቲ የሚያደሉ አስፈጻሚዎችና የቦርድ አባላት ያሉበት ስለሆነ ገለልተኛ አይደለም የሚሉ ወገኖች ነበሩ፡፡ አሁንም አሉ፡፡ በእርግጥ በመረጃ ላይ ተመሥርቶ ውኃ የሚቋጥር መከራከሪያ ማቅረብም ላይ ችግር ነበር፡፡ ዘንድሮ ቦርዱ በሰው ኃይል፣ በግብዓትና ሎጂስቲክስ አቅርቦት እንዲሁም በምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ምርጫ ያሳየው ጥረት ችግሮች ቢኖሩ እንኳን፣ ቀደም ሲል ከነበረው ሐሜት አኳያ የሚያስወቅሰው ነው ብዬ አላምንም፡፡

በዘንድሮው ምርጫ ከወትሮው ለየት ባለ አኳኋን በተለይ አንድነትና መኢአድ የተሰኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ጭቅጭቅና ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ወገኖች ታዲያ ከፓርቲዎቹ የውስጥ ቀውስ ጀርባ ምርጫ ቦርድና ገዥው ፓርቲ እንዳሉበት አድርገው መቀስቀሳቸው ይታያል፡፡

በምርጫ ሥነ ምግባርም ሆነ በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ ከተደነገገው ‹‹ምርጫ ቦርድን ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ላይ መጣል ክልክል ነው›› መርህ አንፃር ድርጊቱ ሊታይም የሚገባው ነው፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኝነትና የማስፈጸም አቅም ጉድለት ከገጠመ ግን በሒደቱ ውስጥ በመቼውም ጊዜና ቦታ ቢሆን በመረጃ ላይ ተመሥርቶ በማጋለጥ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር ውስጥ በአራተኛ ደረጃ የተጠቀሰው መሠረታዊ ሥነ ምግባር የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትና በኃላፊነት ስሜት እንዲሠሩ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ተግባር ላይ ትልቁ ባለድርሻ አካል መንግሥት ቢሆንም፣ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሚናቸው ትንሽ አይደለም፡፡ እንደማንኛውም ታዳጊ አገር አገራችን ለጋ የሚባል የዴሞክራሲ ደረጃ ላይ የምትገኝ ነች፡፡ ስለሆነም የግልም ሆኑ የመንግሥት (አንዳንዶች የሕዝብ ይሉታል) መገናኛ ብዙኃን ለገለልተኝነት፣ ለሚዛናዊነትና ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጡ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ጋዜጠኞች (የመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶችና ብሮድካስተሮች) በፖለቲካ ፍላጐት ጫና ውስጥ በመግባት የሕግና የህሊና ጥሰት ሊፈጽሙ አይገባም፡፡

በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ውስጥ ምርጫ አንዱ የማኅበረሰባዊና ተቋማዊ ዕድገት ማሳያ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ ሲመጣ በአንዳንድ አገሮች የሰላም እጦት፣ የማኅበረሰብ ግጭትና አለመተማመን ይከሰታል፡፡ ችግሩ ከፍ ሲልም ወዳልተፈለገ ቀውስና ግጭት ያድጋል፡፡ የሕይወት ሕልፈትና የንብረት ውድመት ይከሰታል፡፡ ይህን ድርጊት በወሬ ብቻ ሳይሆን በእኛም አገር በተለይ በ1997 ዓ.ም. ተሞክሮ ዓይተነዋል፡፡ ስለሆነም በእንዲህ ያሉ የምርጫ ቀውስ ወቅቶች መገናኛ ብዙኃን በሕግና ሥርዓት፣ በሥነ ምግባርና መርሆ መመራትና በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይገባቸዋል፡፡

በዚህ ላይ በመጨረሻ የሚነሳው ብዙኃን ማኅበራት በምርጫው ሒደት የማስተማርና የመታዘብ መብት እንዲኖራቸው መደረጉ ላይ ነው፡፡ የቅርብ ጊዜ የአገሪቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ17 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሏቸው የብዙኃንና የሙያ ማኅበራት አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ስለዴሞክራሲያዊ ምርጫ እሴቶች፣ መርሆዎችና ሕጋዊ ማዕቀፎች ግንዛቤ የሚያስጨብጡ አሉ፡፡ በምርጫ 2007 ከ45 ሺሕ በላይ ታዛቢዎችን በመላው አገሪቱ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በታዛቢነት በመመደብ የሒደቱን ተዓማኒነት ለማረጋገጥም እንደሚንቀሳቀሱ ከሰሞኑ የብዙኃን ጥምረት መሪዎች አስታወቀዋል፡፡ ነገር ግን በእርግጥ እነዚህ ወገኖች በነፃነት የሚንቀሳቀሱ ናቸው? አጠራጣሪ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ የብዙኃን ማኅበራትና አገር በቀል የሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ታዛቢዎች ላይ የተስተዋሉ ጉድለቶች እንዳይደገሙ ግን ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ አንደኛው ታዛቢ ተቋማት (ማኅበራት) ወይም ግለሰቦች የገለልተኝነት ጥያቄ የሚነሳባቸው መሆናቸው ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. በገለልተኛ ታዛቢነት ስም የተፎካካሪ ፓርቲ ምልክት ይዘው ሲቀሰቅሱ ከነበሩ የአንዳንድ ማኅበራት መሪዎች አንስቶ፣ በገዥው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የተሞሉ ማኅበራትም በዝተው እንደሚስተዋሉ ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚያም አልፎ ‹‹ኮሮጆ እስኪሰረቅና ካርድ እስኪቀየር›› ድረስ ነገሮችን ዓይቶ እንዳለየ በማለፋቸው ታሪክና ሕዝብ ሚፈርድባቸው የህሊና ተወቃሾችም ‹‹ታዛቢ›› ተብለው መክረማቸው አይዘነጋም፡፡

ከእነዚህ እውነታዎች በመነሳት ዘንድሮ የምርጫ መታዘብ ሒደቱን በሥነ ምግባር መርሆ የታገዘና ያማረ እንዲሆን ማድረግ ያሻል፡፡ ምንም እንኳን በሕዝቡ በመንግሥትም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የውጭ ታዛቢ መምጣትን እንደ ትልቅ ዕርምጃ የመቁጠር አመለካከት እየተቀየረ ቢመጣም፣ በአገር ውስጥ ያሉ የማኅበራትና የሕዝብ ተወካይ ታዛቢዎችን ተሳትፎ ማሳደግ ግን ያስፈልጋል፡፡ ይህ የተሳትፎ ማደግ ግን ነፃነትና ገለልተኝነትን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት፡፡

ማጠቃለያ

በምርጫ 2007 ዋዜማ እያየን ያለነው እውነታ እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው፡፡ ከፍተኛ የሕዝብ መነሳሳትና የዴሞክራሲ ግንባታ ፍላጐት በአንድ በኩል ሲታይ፣ በሌላ በኩል የተፎካካሪ ፓርቲዎች መባላትና ነገሮችን ወደ ኢሕጋዊነት የመግፋት አካሄድ አለ፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምርጫ ቦርድ፣ አንድነትና መኢአድ የመሰሉት ፓርቲዎች የጀመሩት እሰጥ አገባ ብዙዎችን እያስገረመ ነው፡፡ በተለይ የተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በውስጥ ዴሞክራሲ ባህል መንጠፍ፣ የሥልጣን ፍላጐትም እንበለው የገንዘብ ምኞት ከሕዝብ ጥቅምና አገራዊ ኃላፊነት በልጦ መታየቱ እጅግ የሚያሳፍር ተግባር ነው፡፡ በፓርቲዎች ውስጥ የተከሰቱ ችግሮችን በማስፋትና በመለጠጥ የራሳቸውን ትርፍ አስልተው የሚገቡ ኃይሎች ተግባርም ያሳፍራል፡፡ ኢዴሞክራሲያዊ ከመሆኑም በላይ ነውር ነው፡፡

‹‹የፖለቲካ ምኅዳር ጠቧል፣ መንቀሳቀስ አልቻልንም፣ ገዥው ፓርቲ ኢዴሞክራሲያዊ አካሄድ እየመረጠ ነው፤›› ሲሉ የከረሙ ፓርቲዎች ዛሬ ችግር ሲያጋጥማቸው የችግር አፈታትን ካላወቁበት አደጋ ነው፡፡ ሕዝባዊ ስብሰባና ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ የሚችሉበትን ሕጋዊ መሠረትም ከማጣታቸውም በላይ፣ ከዚያም አልፎ የምርጫ ምልክት ወስደው በምርጫው ስለመሳተፋቸው እርግጠኛ የሚያደርጋቸው ቁመና ላይ አለመሆናቸው ያሳስባል፡፡ ይህ ችግር በቶሎ ካልተፈታ እንደ አገር ያሳስባል፡፡

እነዚህ እውነታዎች ባሉበት ወሳኝ ወቅት ደግሞ ከሕግና ከሥርዓት ውጪ የሚከናወኑ የኃይል ተግባሮች እየታዩ ነው፡፡ እልህ የተሞላበት ግብግብ ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ የብዙኃኑን ሕዝብ ፍላጐትና ጥቅም የሚጎዳ ተግባርም ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያ ገባውን መርምረው፣ ሒደቱን በጥሞና ፈትሸው ራሳቸውን ማስተካከል አለባቸው፡፡ መንግሥትና ምርጫ ቦርድም የዴሞክራሲ ሒደቱ እንዳይደናቀፍ እስከ መጨረሻው ፓርቲዎቹ ወደ ውድድር ሜዳው እንዲገቡ ማድረግ አለባቸው፡፡ ከሁሉም ክስተት ጀርባ ያለው ሕዝብ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሕጋዊና ፍትሐዊ ምርጫ ብቻ እንደሚፈልግ መዘንጋት ግን ሞኝነትና ተላላነት ነው፡፡ ሕዝብ የሥልጣን ምንጭ ባለቤት ነው ሲባል የይስሙላ መሆን እንደሌለበት ሁሉም ወገን ማወቅ ይኖርበታል፡፡      

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

       

  

      

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...