በበቀለ ሹሜ
ብሔራዊ ልማታችን ከክፍለ አኅጉራዊ አካባቢያችን ጋር ተያያዥነት እንዳለው ማየት፣ ቤትን ለልማት እንዲሆን አድርጐ ከማሰናዳት ተግባር ጋር በጣም የተቆራኘ ነው፡፡ ስኬት ከውድቀት የሚለይበት ዋነኛው ሥራ ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ቤታችንን የሚያተራምሰውን የልግመት፣ የብክነትና የአይጥ መዓት ስናስብ፣ የደቡብ እስያ አገሮች ዓይነት እገዛ ብናገኝስ ዕድገትን እናመጣ ነበር? ብለን ራሳችንን ስንጠይቅ ያለብን አቀበት እጅግ ከባድ መሆኑ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡
የኢሕአዴግ መንግሥት የብሔር/ብሔረሰቦች ሌጣ መብት ብቻውን ያለ ሐሳብ ለመግዛት እንዳላበቃውና በውድቀት ዳር ላይ መሆኑን፣ ብቸኛ መዳኛውም ልማት መሆኑን በስተመጨረሻ ተረድቶ መንደፋደፍ ጀምሯል፡፡ ‹‹የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የልማት መስመሮችና ስትራቴጂዎች›› (ነሐሴ 1992) በተሰኘ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸውም በዛሬው ዓለማዊ ሁኔታ መልማት ከባድ ተግባር እንደሆነ አጢኗል (ገጽ 93)፡፡ ይህ ከባድ የልማት ተግባርም ‹‹ለልማት የቆመና የታለመውን በተግባር ማዋል የሚያስችል ባህሪና አቅም ያለው መንግሥት፣ የገበያ ጉድለቶችን በብቃት መሸፈን የሚችል ግልጽና የጠራ ፖሊሲና ሰፊ የኅብረተሰብ ርብርብ›› የሚጠይቅ መሆኑን በደንብ አስቀምጧል፡፡ በጣም ጥሩ፡፡ በጣም ትክክል፡፡
ወዲያውኑ ግን የሚናገረውን አይረዳውም ወይም ዓይን ካወጣ የማስመሰል ጨዋታ አልወጣም በሚያሰኝ ደረጃ ቆራጥና ብቁ የልማት መንግሥትና የተፈተኑ ብቁ ፖሊሲዎች ጉዳይ ‹‹በተለየ ታሪካዊ ሒደትና አጋጣሚ በመሠረቱ ተሟልቷል፤›› ይለናል (ገጽ 98)፡፡
የዕድገት፣ የሹመት፣ የጭማሪ፣ የዝውውር፣ የትምህርትና የሥልጠና ዕድሎችንና የመሳሰሉትን በፖለቲካ መጥቀሚያነት እየተጠቀመ፣ የሥራ ጠልና ሥራ ግራው እበላ ባዮችን እየለቃቀመ ሊያሽሞነሙን፣ የታታሪዎችንና የባለ ችሎታዎችን የሥራ ስሜት እየገደለ ልሽቀትን ሲያራባ የነበረ፣ የሙስና ጥሩ ወኪልም (ኤጀንት) ሆኖ ስንትና ስንት ዓመት የሠራ መንግሥት፣ ከፌዴራል ዋና ከተማ እስከ ገጠር ድረስ የከተማ ቦታ ባትጋሩኝ እየተባለ የሚያዝበትን፣ የባለሥልጣን ፊርማና ማህተም በጉቦ የሚገዛበትን፣ ደንና ፓርክ የሚጨፈጨፍበትንና ወደ ማሳ የሚለወጥበትን፣ የመንግሥትና የፕሮጀክት ገንዘብ የሚታለብበትን ተግባር ሁሉ እንደ እንሶስላ ሲሞቅ የኖረ መንግሥት፣ ‹‹ለልማት የቆመና የተለመውን በተግባር ማዋል የሚያስችል ባህርይና አቅም ያለው መንግሥት›› በእኔ አምሳል ተገኝቷል፡፡ ይህ ሁኔታ በእኔ አማካይነት ተሟልቷል፡፡ እኔ የልማት መንግሥት ነኝ ሲል ይህ ጭንቅላት አስይዞ ያስጮሃል፡፡
ኢትዮጵያ በልማት የሚመራት መንግሥት ሲበዛ ትፈልጋለች፡፡ ይህ ግን ሕዝብንም ባለሀብቱንም በማስተባበር የምመራ እኔ ነኝ ብሎ ራስን በቃላት የመሾም ጉዳይ አይደለም፡፡ በተግባር ሆኖ መገኘት ነው፡፡ የመንግሥትን መሪነት ሕዝብና ባለሀብት ሲጠይቀው ቆይቷል፡፡ መንግሥት ኢኮኖሚውን ወደፊት ሊወስዱና ሊያራምዱ በሚችሉ ወሳኝ ኢንቨስትመንቶች ውስጥ ሁሉ ሚና መጫወት አለበት፡፡ ‹‹ጊዜው የነፃ ገበያ ነው፡፡ የጨዋታው ሕግ ተወዳደርና አሸንፍ ነው፡፡ መንግሥት ሥራው የጨዋታውን ሕግ ማስከበር ነው፤›› ሲል የነበረው ኢሕአዴግ፣ የመንግሥት ሚና ከአጫዋችነት ያለፈ መሆኑን መረዳቱ አንድ ነገር ነው፡፡
ይህ ዓይነቱ የመንግሥት ሚና ጊዜው ያለፈበት ሳይሆን በባለፀጐቹ አገሮች ታሪክ ውስጥ የነበረና ዛሬም ያለ ነው፡፡ የመንግሥትንና የግል ባለሀብቶችን አጋርነት (አብዮታዊ ዲሞክራሲ እንጂ) ሊበራሊዝም አይቀበለውም የሚለው አስተሳሰብም (ገጽ 101) የዛሬው ጊዜ ዓለምአቀፍ ካፒታሊዝም የሌላውን ቤት ለማስበርገድ የሚጠቀምበትን ዘዴ ከእውነታው ጋር ማምታታት ነው፡፡ ድጐማ፣ የታሪፍ ጥበቃ፣ ባንዱ ወይም በሌላ ምክንያት በውጭ ሸቀጥ ላይ እገዳ መጣል ዛሬም እንደሚሠራበት፣ የሲአይኤ አንድ ሁነኛ ሥራም የአሜሪካን የኢኮኖሚ ጦርነት ማሳካት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
ኢሕአዴግ ‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ወገናዊነቱ ለልማት ለቆሙት ባለሀብቶች እንደሆነ በግልጽ አውጆ ይሠራል፤›› ባይ ነው፡፡ (ገጽ 34) ‹‹የልማት ባለሀብቶች›› ሲልም አዲስ ሀብት በመፍጠር ላይ የተሰማሩትን መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይህ ዓይነቱ አከፋፈል አሳሳችና ከአምራቹ ባለሀብት ውጪ ያለውንና በአገልግሎት መስክ የተሰማራውን ለልማት ያልቆመ የሚል ዓይን ውስጥ የሚከት ነው፡፡ በጤና፣ በትምህርት፣ በሆቴል አገልግሎት፣ ወዘተ መስክ ሁሉ የተሰማራውን ባለሀብት ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ›› (ከነባር ሀብት ተካፋይ) መሆኑ እውነት ነው፡፡ በጥቅሉ ልማታዊ ከመሆን ጋር አቃርኖ ማየት ግን ፖለቲካዊ ጅልነት ከመሆኑም በላይ የአገልግሎት ኪራይ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ያለውን ድርሻ ከማየት ይጋርዳል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በምርትም ይሁን በአገልግሎት መስክ ላይ ተሰማርተው በጉቦና በጉርሻ የሚሠሩትን አንቃዣችና ተጣቢዎችን ለይቶ ‹‹ለመዋጋት›› እንቅፋት ይሆናል፡፡ ኢልማታዊ መባል ያለባቸው እነዚህ ናቸው፡፡ እነዚህን ለማዳከምም ከሕገወጡ ይበልጥ ሕጋዊውን መንገድ ተመራጭ ወይም ቀላል የሚያደርግ የፖለቲካ የባህልና የአሠራር ሁኔታ ማልማት ነው፡፡ በኪራይ ስብሰባ ላይ ያለውን መጨናነነቅ ወደ ምርታማ መስክ የማንሸራሸር ነገርም አጋር የማድረግ ጉዳይ ሳይሆን በማበረታቻ የመሳብና የማስተባበር ብልኃት ነው፡፡
በተረፈ ባለሀብቱ በሙሉ (ከበርቴው) በጥቅሉ አጋር ነው፡፡ የሚገነባው ሥርዓትም የራሱ የከበርቴው ነው፡፡ የከበርቴው የራሱ ነው፡፡ ዋናው ትግልም በማኅበራዊ ቀውሶችና በካፒታል ድርቀት ካፒታሊዝም ጭንጋፊ ሆኖ እንዳይቀር የአጠቃላይ ኅብረተሰቡን ኑሮ በሚያነሳ አኳኋን ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገር ለማስቻል ነው፡፡ ይህ የገባው የልማት መንግሥት በአጠቃላይ የአገሩን ባለሀብት መንከባከብ፣ መግራትና የባህል ደረጃውን ማንሳት ይጠበቅበታል፡፡ የአገሩን ባለሀብት ንቆና ረስቶ የውጭ ባለሀብትን መሳብ የማይሆን ነው፡፡ የውጭው ባለሀብት ከመንግሥት የማባበያ ጉብኝትና ቃለ መጠይቃዊ መግለጫ ይበልጥ የሚያምነው ከቢጤው (ከባለሀብቱ) የሚያገኘውን መረጃ ነው፡፡ ማለትም የውጭ ባለሀብትን የመሳብ ስኬት ለአገር ልጆች ከመመቸትና የአገር ውስጥ ባለሀብትን ልብ ከመርታት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡
የውስጥ አቅምን በአግባቡ ለመጠቀም ቆርጫለሁ የሚል መንግሥት እንደ መንገድ ዓይነት (ዕዳቸውን በራሳቸው የማይከፍሉ) መሠረተ ልማቶችን በከፍተኛ የውጭ ብድርና በውጭ ኮንትራት ወደ ማሠራት አያዘነብልም፡፡ የአገር ውስጥ የሥራ ተቋራጮችንም ንቆ አይተውም፡፡ የውስጥ ሥራ ተቋራጮች በቴክኖሎጂ፣ በሥነ ምግባርና በካፒታል ዕርምጃ የሚያሳዩበትን መፍትሔ ከእነሱ ጋር ሆኖ መፈለግ፣ ከጉልበት ሠራተኛ እስከ አናት ድረስ ያለባቸውን ብልሹ አሠራር ታግለው እንዲያስወግዱና ታማኝነት ለማዳበር እንዲችሉ መታገል የማይቀር የልማት ጥያቄ ነው፡፡ እነሱን ትቶ ንቅዘትን ሙስናን ማሸነፍ አይቻልም፡፡ የንቅዘትና የሙስና ችግር በመንግሥት ቤት ገና እየዋኘ ሳለ እነሱን በንቀት ለማየትስ እንደምን ይቻላል? ከሕዝብ የሚሰበሰበው ታክስና ግብር የጥቂቶች መቅለጥለጫ እንዳይሆን፣ የሚመጣው የውጭ ብድርም ትርፉ ዕዳ ብቻ እንዳይሆን የሚካሄደው ትግል ገና ብዙ ፈተና አለበት፡፡ ይህን ያጤነና የሚበደረውን ገንዘብ ከቀርጣፊ አድኖ በሚብስ ሥፍራ ላይ ማዋል ያልተሳካለት መንግሥት ተቆርቋሪ አዕምሮ ካለው የውጭ ብድርን ከመሳብ ይልቅ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ወደመሳብ ያጋድላል፡፡ የሕዝብን ውዴታ የሙያ፣ የመሣሪያ የገንዘብና የጉልበት ትግግዝ ይዞ ድንቅ የልማት ዕርምጃ ማሳየት ከተፈለገም የግል ዘርፉ ድርሻ የማይቀር ነው፡፡
ሀቅ ከመሸፋፈንና ራስን ከማታለል ተላቆ የተሳካ ነገር መሥራቱን መመዘን የፈለገ መንግሥትም የሰው ነገር ቢሰማና ከቀድሞው በስንት በለጥኩ እያሉ ቁጥር ከማስላት ወጥቶ ኢንቨስትመንትን የሚስብ፣ ለሥራ የሚያነሳሳ ምን ያህል ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ? የሥራ አጥነትን በማዳከምና የሥራ ከፈታን በማበራከት ረገድ ምን ያህል ዕርምጃ ታየ? የሚሉትን ጥያቆዎች ቢጠይቅ ይሻለዋል፡፡ ኅብረተሰቡን አስተባብሬ ለልማትና ለለውጥ አነቃንቄያለሁ የሚል መንግሥት ደግሞ ከዚህ የበለጡ ጥያቄዎች አሉበት፡፡
ለልማት የቆረጡ በውስጥና በውጭ ያሉ የአገሪቱን ውድ ልጆች በዙሪያዬ አሰባስቤያለሁ?
ምሁራኑ ከዝምታና ከሐሜት፣ ለይምሰል በአቋም መግለጫ ከማጨብጨብ ወጥተው በልማት አነቃናቂነት እየተዋደቁ ነው?
ባለሀብቱና ሕዝቡ አለኝታዬ እያለ ነው? ነቀዞችና አንቃዠች ሽፋን እያጡ ሕዝብ፣ ጋዜጠኛው፣ ሠራተኛውና ባለሀብቱ ሁሉ መደበቂያ እያሳጣቸው ነው?
አድራጊ ፈጣሪነት ሕዝብን መፍራት ጀመረ? በፖሊሲና በፍርድ ቤት ላይ ሕዝብ እምነት መጣለ ቻለ? ወይስ አሁንም እምነት የለውም? ፍትሕ አገኛለሁ ብሎ አምኖ በየቦታው የሚደርስበትን በደል ያጋልጣል? ይከሳል? ይፋረዳል? ወይስ ነፃ ማኅበር እንኳ ለማቋቋም ተስኖታል?
የሕዝብን ነፃ የልማት እንቅስቃሴዎች የማያያዝና የማስተናገድ ሥራ መንግሥትን እያዋከበው ነው? ወይስ ሕዝብን ማነቃነቅ መከራ ሆኖበታል?
ለእነዚህ ጥያቄዎች እውነተኛ መልስ መስጠት የወደፊት አካሄድንም ለማረም ያስችላል፡፡
ወደ ልማት ቅያሱ እንምጣ፡፡ ከገጠር መር የልማት ስትራቴጂው ጀርባ ያለው አስተሳሰብ ‹‹በአሁኑ ወቅት የሚኖረው አማራጭ ዓለም አቀፉን የሥራ ክፍፍል እንደ ቅቡል (Given) ሁኔታ ወስዶ በዚያው ክልል ቦታህን ለማሻሻልና ከተስፈኝነት ለመውጣት በሒደት ደግሞ ከዚያ በላይ ለመሻገር መሥራት፤›› የሚል ነው፡፡ (ገጽ 93)
በቅድሚያ ወደ ኢንዱስትሪ ያልገቡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ‹‹ተስፈኛ›› በመባል መለየታቸው ከተፈጥሮ ጥገኝነት አለመውጣታቸውንና ጉርስን ለማሸነፍ አለመቻላቸውን አጉልቶ ለመግለጽ ታስቦ ይመስላል፡፡ ሆኖም ተስፈኝነት ከአምራችነት ጋር እየተነፃፀረ (በውጭ ጉዳይ ሰነዱ ጭምር) ተደጋግሞ ሲቀርብ ላስተዋለ አሳሳችነቱን ለመጠቆም ያስገድዳል፡፡ ተስፈኝነትን ከአምራችነት ጋር ማቃረን ስህተት ነው፡፡ ተስፈኝነት (ምፅዋተኛነት) አቅምን አለመቻልን እንጂ በዓለማዊው የሥራ ክፍፍል ውስጥ ያለንን ድርሻ አይናገርም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ያላቸው የሥራ ድርሻ ጥሬ ምርት አምርቶ ማቅረብ ነው፡፡ በሌላ በኩል አምራችነትን ከተስፈኝነት ጋር ማነፃፀር ሳናመርት ምፅዋት የምንጠብቅ የሚያስመስል፣ ምፅዋቱንም የለጋሾቻችን ንፁህ ውለታ አድርጐ የሚያጭበረብርና (ከየአካባቢው ከሚመጣ ካፒታሊስታዊ መጠጣ ላይ የሚጣልልን መሆኑ የሚጋርድ) ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የኢኮኖሚያችን መሠረት የሆነውን ግብርናን ከማዳበር መነሳት ትክክል ቢሆንም በጥሬ ዕቃ አቅራቢነት የሥራ ድርሻ ውስጥ የተዋጣለት አምራች ለመሆን መሥራት፣ ከዚያ ደግሞ እንዲህ እንዲህ እያሉ ለማዝገም፣ ሊያናጭ ለደረሰው ድቀታችን ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ የውጭ ገበያን ብቻ የተማመኑ ጥሬ ምርቶች ጥሩ አምራችና ጥሩ ሻጭ መሆን፣ ገዢዎች ዘወር ሲሉ ብክትክቱ ሊወጣ ከሚችል ኢኮኖሚ ጋር መጓዝ ነው፡፡ የልማት ጥያቄያችን በጥሬ ዕቃ አቅራቢነት ውስጥ ከመርመጥመጥና ከተፈጥሮ ጥገኝነት ጋር ከተጠበቀ ከመኖርና ያለመኖር ዕጣ የወጣ አስተማማኝ የኑሮ አብራክ መፍጠር ነው፡፡ ይህም በቴክኖሎጂና በሳይንስ ላይ የተመረኮዘ ህልውና ከመገንባት ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ በሌላ ስሙ ግብርናና ፋብሪካ የተላላሱበት ኢንዱስትሪያዊ ኢኮኖሚ ማደራጀት ነው፡፡
የግል ባለሀብቱ እንደ ዕዳ ሲታይ ቆይቷል፡፡ ‹‹ልማታዊ ባለሀብት›› የሚለው መለያም ከዚያው ተፈላቆ የወጣ ነው፡፡ ሰፋፊ እርሻዎች ገበሬውን ከገበያ የሚያወጡና የማይፈለጉ ተደርገው ሲታዩ ቆይተዋል፡፡ ለግል አልሚዎች የነበረው አቀባበልም ቀዝቃዛ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የገጠር ልማትን በተመለከተ በተካሄደ የ‹‹አገራዊ መግባባት›› ውይይት ላይ ‹‹የልማት ኃይል ሊሆን የሚችል መካከለኛ መደብ (ሚድል ክላስ) አለ ማለት አይቻልም፡፡ ይህ መደብ ገና መፈጠር አለበት፡፡ ገበሬው በገጠር ልማት እየበለፀገ ሄዶ በሚከተል መፈላቀቅ ወደ ከበርቴና ወዛደር እየተቀየረ ኢንዱስትሪና ሰፋፊ እርሻ እየተስፋፋ ይመጣል፤›› የሚል ትንታኔ ትላልቅ በሚባሉ የኢሕአዴግ ካድሬዎች ሲሰጥም ተሰምቷል፡፡
መጀመርያ ተይዞ የነበረው የግብርና ‹‹ኤክስቴንሽን›› መርሐ ግብር አጀብ የሚያሰኝ የግብርና ምርት መትረፍረፍ ፈጥሮ ሕዝብን በማስጨብጨብ ጉጉት የተነዳ፣ የምርጥ ዘር ጥራትና ከአፈርና ከአየር ንብረት ጋር የተሳሰረ የሥምሪት ጉድለት የነበረበት ነበር፡፡ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ውድነት በገበሬው ላይ ይዞት የሚመጣው አደጋ እንኳ ልብ አልተባለም ነበር፡፡ በ1994-95 ዓ.ም. ድርቅ ከ14 እስከ 15 ሚሊዮን ሕዝብ በረሃብ አደጋ ውስጥ መግባት የግብርና ልማቱን መርሐ ግብር ድክመት አሳጣ፡፡ ዝናብን ብቻ በማመን የትም እንደማይደረስ አምርሮ አሳየ፡፡ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ውድ አመራረት እንዴት በዕዳ ሊዘፍቅ እንደሚችል መሰከረ፡፡ የውኃ ማቆር ዘዴ ከፍ ብሎ ተነሳ፡፡ የግብርና ልማት መርሐ ግብሩ ብዙ አማራጭ አዘል እንዲሆን ታቀደ፡፡ ድርቅ ከደጋገማቸው ሥፍራዎች እያነሱ ወደተሻሉ አካባቢዎች ማስፈርን መላዬ እስከማለት ተደረሰ፡፡
ያም ሆነ ይህ በድህነትና በከፊል ረሃብ ውስጥ የምንገኝ እንደመሆናችን፣ በእጅ ያለ መትረፊያችንም፣ የካፒታል ምንጫችንም ያው ግብርና እንደመሆኑ መጠን፣ በአሁኑ ጊዜ አጣዳፊው ርብርባችን በዚሁ መስክ ላይ መሆኑ ፈጽሞ የሚያከራከር አይደለም፡፡ ግድም ነው፡፡
- የገበሬውን አመራረት በተሻሻሉና በቀላል ዋጋ በሚገኙ መሣሪያዎች ማንሳት፣
- በአመዛኙ ከእርሻ ወይም ከእርባታ ጋር የተጣበቀውን የባላገሩን ህልውና የኑሮ ለውጥ ሊያመጡ ከሚችሉ ዓይነተ-ብዙ የግብርና ሥራዎች ጋር ማያያዝ፣
- የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤንና የግብርና ልማትን ማግባባት፣
- የማምረቻ ወጪ ጫናን የሚያቃልሉ የምርጥ ዘር አበዛዝና የማዳበሪያ ዘዴዎችን መጠቀም፣
- የውኃ እጥረትን የሚያቃልሉ መፍትሔዎችን ከትናንሽ ክትሮች አንስቶ ወንዞችን ገድቦ ለብዙ ዓይነት አገልግሎት እስከማዋስ ድረስ ማሳካት፣
- አሳ የማጥመድ ተግባርን ከአሳ ልማት ጋር ማስተሳሰር፣ ሥጋና ከብትን ለውጭ ገበያ ማቅረብንም ከእርባታ ልማት ጋር ማመጋገብ፣
- ከአንድ የሰብል ዘር/ተክል ወይም ወተት ጋር ይበልጥ የተጣበቀውን የባላገር አመጋገብ ከተለያዩ አማራጮች ጋር ማዛመድ፣
- የክፉ ቀን መጠባበቂያ የሚፈጠርበትን ሥርዓት ማበጀት ይቆይ የማይባል ተግባር ነው፡፡
ሰፈራ ያልተበላ መሬትን እያዳረሱ በመጨረስ የአደጋ መስመር ውስጥ የሚገኝ ጊዜያዊ መዳኛ ስለሆነ በረሃማነትን የመከላከል፣ ያለቀለት መሬት የማደስና ደህነኛውን የመንከባከብ ሰፊና የረዥም ጊዜ መርሐ ግብር መዘርጋት የማይታለፍ ነው፡፡ የመሬት መራቆት ጉዳይ ሲነሳ ቶሎ የሚታወሰው ሰሜን ኢትዮጵያ ነው፡፡ ግን በአስፈሪ ፍጥነት እየተራቆተ ያለው ደቡባዊና ምዕራባዊ ክፍል በጊዜ ሊደረስበት ይገባል፡፡ የአፈር እጥበቱ ችግር በደን መጨፍጨፍና በመሬቱ ተዳፋት ብቻ የሚብራራ አይደለም፡፡ የአውራ ጐዳናዎች የግራ ቀኝ ቦዮች ማስተንፈሻዎች ምን ያህል ተረተሮችና ሸለቆዎች ከዓመት ወደ ዓመት ሲፈጥሩ እንደኖሩ ለመገንዘብ ትንሽ ልብ ማለት ብቻ በቂ ነው፡፡ ወንዞችም የከተማ ነዋሪዎችንና የፋብሪካዎችን ቆሻሻ ከማስወገድ ሥራ መላቀቅ አለባቸው፡፡ የውበትና የፅዳት ኤጀንሲ ባለበትና የግል ቆሻሻ አንሺዎች በተስፋፉበት አዲስ አበባ ውስጥ ከፍለው ማስነሳት ለማይችሉት ጭምር ዘላቂ ሥርዓት ማበጀት ተስኖ ወንዞች በቆሻሻ ሲሞሉ የሚያስተዛዝብ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ለልማት የሚሆን የአዲስ ሀብት ዋና ምንጫችን ባላገሩ መሆኑ የግድ የሀብቱን ከፍተኛ ባለድርሻም አብሮ የሚያሳየን አይደለም፡፡ ‹‹ሕዝቡ በጉልበቱና በመሬቱ በመጠቀም ከሚያመርተው ምርት ከፍተኛው ድርሻ የራሱ የአምራቹ ስለሚሆን›› (ገጽ 13) ብሎ ማሰብ ስህተት ላይ ይጥላል፡፡ የገበሬው ምርት መውጫ ቀዳዳዎች ብዙ ናቸው፡፡ ወለድ፣ ግብርና መዋጮ አለበት፡፡ ከሁሉም ደግሞ ዋጋ መስበርና ማዋከብ በሞላበት መልቲ ገበያ ጉልበቱን የሚነጠቅበትና ዋና አትራፊው ነጋዴው የሚሆንበት ሁኔታ ዛሬም አለ፡፡ ስለዚህም ከግብርና የሚገኘውን ሀብት ለልማት የማዋል ጉዳይ ገበሬውን ብቻ ሳይሆን፣ ከገበሬው ውጪ ያለውን የትርፍ ሀብት ተካፋዩን ሁሉ እንድናይ ሊያስችለን ይገባል፡፡
ኢሕአዴግ እንዳጤነው በአሁኑ ደረጃ በገበሬው ዘንድ ጉልበትን በሰፊው የሚጠቀምና የሚያሠራ ቴክኖሎጂ የሚመረጠው በመኪና ማረስ ተጠልቶ ሳይሆን፣ ካፒታል ስለሌለና በመኪና የሚተካው ሰው ሌላ የሥምሪት አማራጭ ገና የሌለው በመሆኑ ነው፡፡ የግል አልሚው ግን የሰው ጉልበትን በሰፊው የሚያሰማራ አመራረትን የሚመርጠውና የሚጠቀመው፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ይበልጥ እስካተረፈው እንጂ በመድኃኒትነት ስለታዘዘለት አይደለም፡፡
የግብርናው ልማት ከኢንዱስትሪ ጋር በተለያየ አቅጣጫ ተያያዥነት አለው፡፡ ለውጭ ገበያ የሚሆኑ የግብርና ውጤቶችን የማምረት ጥረት በገበያው መኖር ምክንያት ብቻ የሚራወጡበት አይደለም፡፡ የውጭ ገዥ ሲታጣ ኪሳራን ታቅፎ ላለመቅረት ከአገር ውስጥ ሕዝብ የኢንዱስትሪ ፍጆታ ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በአበባ ልማት በኩል እየታየ ያለው የቅርብ ጊዜ ስኬት አስደሳች ቢሆንም፣ ተቀባዮቹ በትንሽ ምክንያት አንወስድም ቢሉ ሌላ አንሺ የሌለው ምርት ታቅፎ ሊቀር የሚችልበት አደጋ እንዳለው መረሳት የለበትም፡፡ በሌላ በኩል በተበጣጠሰ መሬት ላይ ያለው የአርሶ አደር ክምችት የሚቃለልበት ሌላ ልማት መኖሩ ግድ ነው፡፡ ይህም ከጥቃቅን እስከ ትላልቅ የኢንዱስትሪ ልማት የሰፋ ነው፡፡
የግብርና ምርታማነትን የማሳደግ ጉዳይም የተሻሻሉ መሣሪያዎችንና ሌሎች የፋብሪካ ውጤቶችን ይጠይቀናል፡፡ እነዚህን በተሻለ ዋጋ በአገር ውስጥ የማምረት ፍላጐት፣ ያለንን የማዕድን ሀብት ወደማወቅና ወደማልማት አቅጣጫ ያመለክተናል፡፡ የግብርና ውጤቶችም ተቀባይ ኢንዱስትሪን ይጠራሉ፡፡ ይህም ካፒታል ገና ከግብርናው እስኪከማች ይቆይ የሚባል ሳይሆን ጐን ለጐን ተቀናብሮ ሊመጣም ይችላል፡፡ በዚህ የግብርና-ፋብሪካ፣ ፋብሪካ-ግብርና፣ ፋብሪካ-ፋብሪካ ሰንሰለት ውስጥ ሊገባ የሚችል ካፒታል በአገር ውስጥ ይብዛም ይነስ አለ፡፡ ያለውን በአግባቡ እያሰማሩ የውጭ ካፒታል ለመሳብ ብርቱ ትግል ማድረግ ግድ ነው፡፡ የግድ ከጥቃቅንና ካነስተኛ ጀምረን እየዳህን ካልተጓዝን አይባልም፡፡ አቅም ያለው ከተገኘም ትልቁ ውስጥ ይገባል፡፡ መንግሥት ለዚህ ዓይነት መስተንግዶ ዕይታውን አስተካክሎ የኢኮኖሚውን የማዕድን-ግብርና-ኢንዱስትሪ ትስስር እንቆቅልሽ (Jigsaw) ከወዲሁ መፍታት ማለትም የቱ ከየቱ ጋር እንደሚገጣጠም ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡
ኢንዱስትሪው በወጪ ምርት (Export) ይመራ ሲባልም መታሰብ ያለበት በበለፀጉት አገሮች ገበያ ላይ መጋደል ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ ምርት ይዘው የሚራወጡትን የእኛን ቢጤዎች ገበያ አጢኖ፣ በተሻለ ዋጋ ልናቀርበው የምንችለውን የኢንዱስትሪ ምርት ማጥናትና ለዚያ መሥራት አንድ ብልጠት ነው፡፡ በጥራት፣ በደረጃና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን በማቅረብ ዓላማ ውስጥ መግባት ጠቃሚ የሚሆነው በዓለም ገበያ ተወዳድሮ በመሸጥ ረገድ ብቻ አይደለም፡፡ የአገር ውስጥ ገበያችንን ከአታላይ ሸቀጦች ለማዳንም ይበጀናል፡፡ የራሳችን ሸቀጦች የውጭ ሥራዎችን በተመራጭነት ብልጫ ሊያባርሩና ሊሻገሩም ይችላሉ፡፡
ይህ ግን የውስጥ ገበያውን በውጭ ሸቀጥ አስወርሮ፣ መንግሥታዊና የግል ማምረቻዎች በሞትና በሕይወት ውስጥ ሲቃትቱ በማየት፣ ወይም ችግርና ውድቀት ተወዳዳሪነትን ያስተምራቸው በማለት የሚጨበጥ አይደለም፡፡ መንግሥት ወደ ውጭ ተልካ ዶላር ለምታስገኝ ነገር እንደሚጨነቅ ሁሉ በአገር ውስጥ ገበያውም ውስጥ የውጭ ሸቀጦችን መጋተር የሚችሉ የአገር ውስጥ ምርቶች እንዲታዩ መልፋት ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ የአገራችንን የጨርቃ ጨርቅና የስፌት ፋብሪካዎች የከተማውን ዘመናይ ፍላጐት በማርካት ረገድ የውጭ አልባሌ ምርቶችን (በውድድር) መጠጋት ያቃታቸው ለምንድነው? በጥንካሬም በውበትም የተዋጣላቸው ጫማዎችን ለመሥራት የሚያስችል ክህሎት አነሰም በዛ እያለን ዕድሜ የለሽ የውጭ ቆዳ መሰል ላስቲክ ጫማዎች እንደምን ገበያውን አላስቀምስ አሉ? የአገራችን አምራቾች አትራፊ ዲዛይኖችን ፈጥኖ የማሽተትና የመተጣጠፍ ችግር ስላለባቸው? ከእያንዳንዱ ነገር ብዙ ካላተረፍን የሚል ጅልነት ስለሚጐትታቸው? ወጪ የሚቀንስ የሀብት አጠቃቀምና ምርታማነትን የሚጨምር ቴክኖሎጂ ስለሚጐላቸው? ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ የታክስ ጫና ስላላነቃቸው? ወይስ የደረጃና የጥራት ቁጥጥር የተሟላበት የውጭ ሸቀጦች ፍሰት ስለሌለ?
ችግሮቻቸው ይነሱም ይብዙ መንግሥት ቀርቦ ማስተዋልና ማዋየት አቋም እንዲያበጁ በምክር በመረጃና በሥልጠና መደገፍ፣ እንዲሁም በኢኮኖሚ ግንኙነቱ ውስጥ የሚገኘውን ተገቢ ያልሆነ ውድድርና ጥቃትን የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን ማስተካከል ይጠበቅበታል፡፡ በተለይ የጥራትና ደረጃ አጠባበቅ አውታሩ በሚያስተማምን ደረጃ መጠናከር ለውስጥና ለውጭ ንግዱ ለሸማቹም ደኅንነት ወሳኝ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ከድኅነት አዘቅት የማውጣት ጥያቄ በየትኛውም መልኩ ከሚገለጽ የሥልጣን ጥማትና ግብግብ በላይ ነው፡፡ የዛሬ ቡትቷምነት አኩሪ ታሪክና ባህል አለኝ በማለት አይጠገንም፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ አያሠራም›› በሚል አሸዋ ውስጥ ለመደበቅ መሞከርም አንዲት ጋት ፈቀቅ አያደርግም፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበት እውነታ የሠራበትንም ሆነ ተበድሮ ያመጣውን ገንዘብ በስካር፣ በማስመንተፍና በትርኪ ምርኪ እያባከነ ኑሮው የቆረቆዘ፣ በዕዳና በንትርክ በተጠመደ ቤተሰብ ሊመስል ይችላል፡፡ ይህ ቤተሰብ ከውድቀት ለመውጣት ከቆረጠ፣ አድፋፊነቱንና ጭቅጭቁን አሸንፎ፣ ጥሬ እየቆረጠመም ቢሆን ገንዘብ ማዳንና በሚብስና ፍሬያማ በሆነ ሥራ ላይ መልፋት መጀመር አለበት፡፡ አኗኗሩን በዚህ መንገድ ሲቀይርና ውጤት ማሳየት ሲችል ጀርባ የሰጠ ወዳጅና ዘመድም ይጠጋል፡፡
ምሳሌውን ወደ አገር ብንመልሰው ልማትን የሚጣሉ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎችን፣ አመለካከቶችንና ዘልማዶችን ተቆጣጥሮ እያስተካከሉ፣ ያለውንና ሊገኝ የሚችለውን የቁሳቁስ፣ የገንዘብ፣ የጥበብ፣ የሙያና የሥራ ሀብት ከውጤት ወደ ውጤት በሚያረማምድ ቅንብርና አቅጣጫ ማንቀሳቀስ ነው፡፡ ይህ ተሳካ ማለት በዓላማዊና በአካባቢያዊው የልማት ትግሉ ውስጥ ይበልጥ ለመሯሯጥ የሚያስችል አቅም ተዘማመደ ማለት ነው፡፡
የኢሕአዴግ መንግሥት የሕዝቡን አመለካከት ለመቀየር ‹‹ብሔራዊ መግባባት›› ለመፍጠር ጀምሬያለሁ ካለ ብዙ ጊዜው ነው፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ፣ ቢፒአር፣ ወዘተ በመሳሰሉ ‹‹በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል›› ዓይነት የከሸፈባቸው ሥልቶች የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጦች እያካሄደ ሠራተኛውን ከላይ ወደታችና ከታች ወደላይ እያገላበጠና እያባረረ የተያያዘው ‹‹የለውጥ›› ጉዞ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ደርግ ላለማው ሌብነት፣ ብቃት የለሽነትና ትርፍ የሠራተኛ ክምችት ሠራተኛው ከፋይ የተደረገበት ቁስል ሳይሽር፣ እንደገና በኢሕአዴግ አገዛዝ ከሥራ ብቃት ይልቅ በፖለቲካ ታማኝነት፣ በወንዝና በጐሳ መጓተት ለደረሰ ጭምልቅልቆሽ ሠራተኛው ሒሳብ ማወራረጃ እንዲሆን ተደረገ፡፡ ዝብርቅርቅ ሒደቱ ገና አላበቃም፡፡ ሆኖም ‹‹ሙሰኝነት››፣ ‹‹የለውጥ ዝግጁነት ማነስ››፣ ብቃት የለሽነት በሹምሽርና በፕወዛና በመባረር አይፀዳም፡፡ ሠሪተኛውን በመባረር ሥጋት ውስጥ ከትቶ ማንደባለልም የለውጥ ተቀባይነት ማረጋገጫ አይሆንም፡፡
ልማትን የሚቃረን፣ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ችግሮች መላ ያላለና የፖለቲካ ኃይሎችን ለማስተባበር ያልሞከረ ስብሰባ በማዥጐድጐድም አገራዊ መግባባት አይፈጠርም፡፡ የተካሄዱትና የሚካሄዱት ስብሰባዎች ለኢሕአዴግ አዲስ አባላት መመልመያ መድረክ ከመሆን ያለፈ የፈየዱት ነገር የለም፡፡ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች መጀመርያ ላይ ያሳዩት ቀልጣፋ አሠራር በኢሕአዴግና በአለቃ ክትትል ወይም ሥልት ስለተለወጠ ብቻ የሚረጋ አለመሆኑን ይኸው ዛሬ አይተናል፡፡ አለቃም የአለቃው መሪ ድርጅትም እስከ ላይ ሲነቅዝ እነዚያ ተለውጠው የነበሩ አሠራሮችም ሲፈዙ ወደነበሩበት ሲመለሱ አይተናል፡፡
ስርቆት፣ ብክነትና ‹‹ወሬ ወዳድነት›› በኢትዮጵያ ሥር የሰደደ ኅብረተሰቡንም አገዛዙንም የጀቦነ አጠቃላይ ችግር ነው፡፡ ‹‹ብላ እንብላው›› በየቦታው የሚንቀባረር የኑሮ ፈሊጥ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ሆ ብሎ በተግባራዊ ለውጥ፣ በዓይን፣ በጆሮ፣ በአንደበትና በብዕር እያሳደደ መድረሻ የሚያሳጣበት እንቅስቃሴ ካልተቀጣጠለ በቀር ላይ ላዩን መከርከም የትም አያደርስም፡፡
ስለሺ ደምሴ (‹‹ጋሼ አበራ ሞላ››) የጫረውና ከክልል ክልል እየተዘመተ ከባለፀጋ እስከ ጐዳና አዳሪ ያለውን ሁሉ አሠልፎ የነበረው የፅዳትና ከተማን የማስዋብ ዘመቻ ትልቅ አብነት አለው፡፡ ሕዝቡ ልቡን ለረታ ተልዕኮ ምን ያህል ሊነቃነቅ እንደሚችል በትንሹ አሳይቷል፡፡ የእብድ ያህል ተቆጥሮ የነበረ አንድ ግለሰብ ይህን ያህል ልዩነት መፍጠር ከቻለ፣ የአገሬ ድቀት ቆጠቆጠኝ የሚል በውስጥና በውጭ የሚገኝ ፖለቲከኛና ምሁር አንድ ላይ ቢገጥም ሕዝብ ተዓምር መሥራት ይችላል፡፡ በተረጋጋ ፖለቲካ ውስጥ ከአገር ገበሬ እስከ ግል ባለሀብት (ባለወረት)፣ የውጭ ካፒታል ከመሳብ አንስቶ የተሰደደ የአገር ልጅ እስከሚጥላት ጠብታ ድረስ የተነባበረበትና የተረባረበበት የልማት ትግል ውስጥ መግባት ከቻልን የተሻለ ተስፋ አለን፡፡ ጐስቋላዋ ኢትዮጵያ ይህን ዓይነቱን የኅብረተሰብ ንቅናቄ በጣም ተርባለች፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡