Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

​​​​​​​‹‹እንዲህ ዓይነት ትልልቅ የመንገድና የባቡር ፕሮጀክቶች አለቁ ማለት ብዙ ነገሮችን ይቀይራሉ››

ኢንጂነር ተሾመ ወርቁ፣ የኮር ኮንሰልቲንግና ኢንጂነርስ ኩባንያ የዓለም አቀፍ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ

ከአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ጋር ተያይዘው የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገዶች እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡ ወደ 2.5 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት የተያዘለት ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ከባቡር መስመሩ ዝርጋታ ጎን ለጎን እየተከናወነ ነው፡፡ በተለይ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ከሚዘረጋው የባቡር መስመር ጋር ተያይዞ እንዲሠራ የተደረገውንና ትላልቅ የማሳለጫ አደባባዮችን የያዘውን መንገድ ዲዛይን ለመሥራት ዕድሉን ያገኘው አገር በቀሉ ኮር ኮንሰልቲንግና ኢንጂነርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የባቡር መስመሩ እየተጠናቀቀ ሲሆን፣ በተዛማጅነት የሚሠሩት የመንገድ ግንባታዎች መጠናቀቂያ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ሆኖም ከተያዘላቸው የጊዜ ገደብ በላይ ወስደዋል፡፡ በዚህ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ያለውን የባቡር መስመር በመከተል በተሠሩት ሥራዎች ዙሪያ የዲዛይኑ ባለቤትና የፕሮጀክቱ አማካሪ ከሆነው የኮር ኮንሰልቲግና ኢንጂነርስ ኩባንያ የዓለም አቀፍ ፕሮጅክት ሥራ አስኪያጅ  ኢንጂነር ተሾመ ወርቁን ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ከሚዘረጋው የባቡር መስመር ጋር ተያይዞ የተሠራው የተሽከርካሪና የእግረኞች መንገድ ዲዛይንን የሠራችሁት እናንተ ናችሁ፡፡ የማማከሩንም ሥራ እየሠራችሁ ነው፡፡ የዚህ መንገድ ግንባታ በትክክል በዲዛይኑ መሠረት የተከናወነ ነው? የተለወጠ ነገር የለም?

ኢንጂነር ተሾመ፡- ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ከተዘረጋው የባቡር መንገድ ጋር ተያይዞ የተገነባው መንገድ ከጥቂት የዲዛይን ለውጦች በስተቀር 99 በመቶው የተከናወነው በዲዛይኑ መሠረት ነው፡፡ መጠነኛ ለውጥ የተደረገው በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ነው፡፡ መነሳት የሌለባቸው ናቸው ከተባሉ ሕንፃዎች ጋር በተያያዘ ቀላል ለውጦች ተደርገዋል፡፡ ወይም ደግሞ መጋቢ መንገዶችን ርዝመታቸውን እያየን ከተያዘላቸው በጀት ጋር መጠነኛ ለውጥ ያደረግንባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ሌላው አጫጭር የመገናኛ መንገዶች እንዲረዝሙ ለማድረግ የተደረገ ጥቃቅን ለውጥ ካልሆነ በስተቀር፣ ቀደም ሲል የተሠራው ዲዛይን ሙሉ ለሙሉ ተተግብሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ከባቡር መስመሩ ጋር ተያይዞ የተገነባው መንገድ ግንባታ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ኢንጂነር ተሾመ፡- ከውኃ ልማት እስከ መገናኛ ያለው መንገድና ሲአርቢሲ የሚሠራው መንገድ 90 በመቶ ፊዚካል ሥራው ተጠናቋል፡፡ በትድሃር ኮንስትራክሽን የሚሠራውና ከመገናኛ ውኃ ልማት ድረስ ያለው መንገድ ደግሞ ወደ 60 በመቶ ተጠናቋል፡፡ በጥቅል ሲታይ የፕሮጀክቱ ሥራ 80 በመቶ ተጠናቋል ማለት ይቻላል፡፡ የቀሩት የመጨረሻ የአስፓልትና የእግረኛ መሄጃዎች ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ በማሳለጫ መንገዶቹ ላይ የተወሰነ የስትራክቸር ሥራ አለ፡፡ ከውኃ ልማት እስከ መገናኛ በሚሠራው መንገድ ላይ የተወሰኑ መሠረታዊ ሊባሉ የሚችሉ ሥራዎችም ይኖራሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህ ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ገደብ አልተጠናቀቀም፡፡ ለምን? ሙሉ ለሙሉ መቼ ሊያልቅ ይችላል?

ኢንጂነር ተሾመ፡- የፕሮጀክቱ ሥራ ያልቃል ተብሎ የታሰበው በ18 ወራት ነው፡፡ በጥቅምት 2007 ዓ.ም. ነበር መጠናቀቅ የሚገባው፡፡ ነገር ግን ብዙ ኮንትራክተሮች አንድ ቦታ ላይ ሲሠሩ አንዱ በሌላው ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ በሚሠራው መንገድ ላይ ሦስት ኮንትራክተሮች ነበሩ፡፡ መጀመሪያው ላይ የውኃ መስመሩን የሚሠራው ኮንትራክተር ነው፡፡ ይህ ኮንትራክተር ከመገናኛ ጀምሮ እስክ ሜክሲኮ አደባባይ ያለውን ትልቁን የውኃ መስመር የሚሠራው ኮንትራክተር በባቡሩና በመንገዱ ኮንትራክተሮች ሥራ ላይ ተፅዕኖ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የመንገዱና የባቡሩ ኮንትራክተሮች ደግሞ ተቀናጅተው ሠርተዋል፡፡ ይህንን ቅንጅት ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት ባይደረግ ኖሮ ፕሮጀክቱ ረዥም ጊዜ ሊወስድ ይችል ነበር፡፡ በአንድ ቦታ ላይ አንዱ ከአንዱ ቀድሞ ለመሥራት ፍላጎት ነበር፡፡ የባቡር መስመሩን ሥራ የተረከበውም ሥራውን ቀድሞ ለመሥራት ይፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን የሁለቱንም ፍላጎቶች እያቻቻልንና እያስታረቅን አንዱ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆይ፣ ሌላው ሠርቶ እንዲወጣ እየተደረገ በማቀናጀት ተሠርቷል፡፡ ይህም የተወሰነ ጊዜ ወስዷል፡፡ የመንገድ ሥራውን የተረከቡትን ኮንትራክተሮች ስድስት ወራት ያህል ወደኋላ እንዲቀሩ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ይህ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ሁኔታ ግንባታው መቼ ያልቃል ተብሎ ይታሰባል?

ኢንጂነር ተሾመ፡- ለፕሮጀክቱ አሁን እኛ ማረጋገጫ የሰጠንበት ወይም ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የሰጠነው ጊዜ ስድስት ወራት አካባቢ ነው፡፡ ለኮንትራክተሮቹ ስድስት ወራት አካባቢ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተለይ ሲአርቢሲ የሚሠራው መንገድ ላይ ከጥቃቅን ሥራዎች በስተቀር አልቋል ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ኮንትራክተሮቹ በዚህ በዚህ ምክንያት ግንባታው እንዲዘገይብን ሆኗል፣ በወቅቱ ልንሠራ የሚገባንን  እንዳንሠራ በባቡር መስመሩ ዝርጋታና በሌሎች ምክንያቶች ጊዜ ባክኖብናል ብለው ማካካሻ ጠይቀዋል፡፡ ለባከነብን ጊዜ ማካካሻ ይገባናል ብለው ያቀረቡት ጥያቄ ትክክል ስለመሆኑ ምርመራ እየተደረባቸው ያሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ በትክክልም ደግሞ ተፅዕኖ ፈጥሮባቸዋል ተብሎ የታመነባቸውም ጊዜያት አሉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ሲያልቁ ነው በዚህ ጊዜ የሚባለው፡፡ ግን ቢያንስ የከተማውን የትራፊክ ፍሰቶች የሚያስተጓጉሉ ነገሮች እያለቁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሁለቱም መስመሮች የተዘረጋው የባቡር መስመር ግንባታ የማቋረጫ መንገዶች ጉዳይ የታሰበበት አይመስልም፡፡

ኢንጂነር ተሾመ፡- ከመገናኛ እስከ ጦር ኃይሎች ባለው መስመር ዝግ የተደረጉ ዋና ዋና መተላለፊያ የነበሩ መንገዶች ጥቂት ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ቦታዎች ላይ ማሳለጫዎቹ አሉ፡፡ ዝግ ከተደረጉት ውስጥ ባምቢስ አካባቢና ኮካ ኮላ አካባቢ ያሉት መንገዶች ናቸው፡፡ የኮካ ኮላውም ማቋረጫ ቢሆን በተወሰነ ሁኔታ ትንንሽ መኪኖችንና እግረኞችን እንዲያስተላልፍ ተከፍቷል፡፡ በእኔ እምነት ትልቅ ችግር አለ ብዬ የማስበው ከመገናኛ እስከ አያትና ከጎተራ እስከ ቃሊቲ ባለው መንገድ ላይ ነው፡፡ እኛ ከምንሠራበት ከጦር ኃይሎች እስከ መገናኛ ባለው መስመር ላይ በአብዛኛው በፊት የነበረውን የከተማዋን እንቅስቃሴ የማያውክ መንገድ ነው የተሠራው፡፡ ባቡሩ በረዥም ርቀት በአየር ላይ እንዲሄድ ነው የተደረገው፡፡ ከማሳለጫዎቹ ውስጥ በኡራኤል፣ በውኃ ልማት፣ በሃያ ሁለት፣ በለም ሆቴልና በመገናኛ አካባቢ ያሉት ማሳለጫዎች በጣም ተቀራርበው ነው የተሠሩት፡፡ በእነዚህ ቦታዎች በሙሉ ሰዎች በቀላሉ ከአንዱ ወደ ሌላው አቅጣጫ የሚዞሩባቸው ነፃ የሆኑ መተላለፊያዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ከአያት ወደ ጦር ኃይሎች ባለው መስመር ላይ የመሸጋገሪያ ችግር አይኖርም ነው የሚሉኝ?

ኢንጂነር ተሾመ፡- በዚህ ረገድ እዚህ መስመር ላይ ያለው ችግር በጣም አነስተኛ ነው፡፡ መንገድ ለሁለት ዓላማ ነው የሚሠራው፡፡ አንዱ ለፍጥነት ነው፡፡ ሁለተኛው ለተደራሽነት  ነው፡፡ አንድን የከተማ ቦታ በቀላሉ ለመድረስ ነው የሚሠራው፡፡ አንዱ ሌላውን እንዲያውክ ያደርጋል፡፡ መንገዶች በጣም እንዲታለፍባቸው ሲፈለግ ዝግ ይሆናሉ፡፡ ዝግ ይሆኑና እንቅስቃሴውን ለማሟላት ያዘነበሉ፣ ወደዚያ በይበልጥ የሄዱ መንገዶች ተደራሽነት ላይ ተፅዕኖ ያደርጋሉ፡፡ ተደራሽ አይሆኑም፡፡ በቀላሉ ማቋረጥ አይቻልም፡፡ መኪና በቀላሉ ከቀኝ ወደግራ፣ ከግራ ወደቀኝ ማንቀሳቀስ አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም ቦታ ክፍት ይሁን መኪና እንደፈለገ ይዟዟር ከተባለ ደግሞ ፍጥነት አይኖርም፡፡ ስለዚህ ይህንን የሚያቻችል ዲዛይን ነው እኛ የሠራነው፡፡ በተወሰነ ደረጃ ግን ለማሳለጫዎቹ ሲባል በሁሉም ቦታዎች እግረኛም መኪኖችም የማይዞሩባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ደግሞ ያንን የሚፈቅድ ነውና ይህንን ማቻቻል ሲችል ነው ዲዛይን የሚመረጠው፡፡ ሁለቱንም በእኩልነት ማስተናገድ ሲችል ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሜን ወደ ደቡብ የተዘረጋውን የባቡር መስመር ተከትሎ ባለው መንገድ ላይ ግን ብዙም መሸጋገሪያዎች የሉም፡፡ ማቋረጫዎች አሉት ከተባለ እንኳን በጣም ብዙ ተራርቆ የተሠራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ችግር ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል፡፡ ይህ እንደ ሥጋት እየታየ ያለ ጉዳይ መፍትሔ የሚኖረው እንዴት ነው? ሰሞኑን እንደታየው እግረኞች በማቋረጫ እጦት አጥር ዘለው ለመሻገር እየሞከሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አደጋ አለው፡፡

ኢንጂነር ተሾመ፡- እኔ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የባቡር መንገዱ ካለቀ በኋላ ይህንን ችግር የሚያቃልል ነገር ይሠራል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ይህንንም ሊያደርግ እንደሚችል የሰማሁት መረጃ አለ፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመሸጋገሪያ መንገዶች ዲዛይን ተደርገው እየተሠሩ ያሉ አሉ፡፡ ለምሳሌ ጐተራ ከመደረሱ በፊት የሚሠራው አንዱ ነው፡፡ የአያት መንገድ ላይ የሚሠሩና የጨረታ ዶክመንታቸው የተዘጋጀላቸው ሥራዎችም አሉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን የሚደፍኑ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን ትልቁና ከዚህ ፕሮጀክት መወሰድ አለበት ብዬ የማስበው ትምህርት ከመገናኛ እስከ ጦር ኃይሎች እየተሠራ ባለው መንገድና  የባቡሩ ሥራ ተቀናጅቶ የሚሠራበት ሁኔታ መኖር እንዳለበት ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ከዚህ በፊትም ጠቅሼው ነበር፡፡ በቅንጅት ሲሠራ ለምሳሌ ለመንገድ ሥራ አስቸጋሪ በሆነበት አካባቢ የባቡር መስመሩ ወደ ላይ ተነስቶ የሚሄድበት፣ ባቡሩ ደግሞ አስቸጋሪ ሲሆን ለመንገዱ ሌላ መፍትሔ የሚሰጥበት ሁኔታ እየተጠና መሠራቱ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ግን ካለው ጊዜ አንፃር ከመገናኛ እስከ አያትና ከመስቀል አደባባይ ቃሊቲ ያሉት መንገዶች ቀድመው በመሠራታቸው ይህንን ማድረግ አልተቻለም፡፡ ግን የባቡርና የመንገድ ግንባታው አዲስ ቦታ ላይ (ልክ ከመገናኛ ጦር ሃይሎች ያለው መንገድ ረዥም ዕድሜ የነበረውና ፈርሶ መሠራት ስለነበረበት) ሁለቱን አቀናጅቶ የመሥራት ዕድል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ባምቢስ አካባቢ ያለው ማቋረጫ ላይ መተላለፊያ ይሠራል ተብሎ ነበር፡፡ አሁን ሲታይ ግን መተላለፊያ መንገዱ የለም፡፡ ለምን?

ኢንጂነር ተሾመ፡- የመጀመሪያው ዲዛይን ላይ ብዙ አማራጮች ታይተዋል፡፡ ግን የመጨረሻው ዲዛይን ላይ የባምቢስ ማቋረጫው ዝግ እንዲሆን ተወስኗል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን ዝግ እንዲሆን ተወሰነ?

ኢንጂነር ተሾመ፡- አንዱ ምክንያት ቦታው ስለማይመች ነው፡፡ ወደ ኦሎምፒያ የሚወርደው መንገድ ላይ ድልድይ አለ፡፡ ከዚያ በአጭር ርቀት ተነስቶ ወደ ካዛንቺስ መንገድ መሸጋገሪያ መሥራትና ማገናኘት በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ ነው፡፡ ቦታው ይህንን ለመሥራት አይፈቅድም፡፡ ከዚህ ይልቅ የባቡር መስመሩ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ መሬት ላይ ከሚያርፍ ይልቅ የባምቢስን ማቋረጫ አልፎ መሬት ቢወርድ ይሻላል የሚል ሐሳብ አቅርበን ነበር፡፡ ይህ ተቀባይነት አላገኘም፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያቱ ምንድነው? ከወጪ አንፃር ታስቦ ነው?

ኢንጂነር ተሾመ፡- ብዙ ምክንያቶች ይኖሩታል፡፡ አየር ላይ ለሚሄደው ሥራ የነበረው ስምምነት ከመጠን በላይ ከሄደ ወጪም ይጠይቃል፡፡ ሌሎችም ቴክኒካዊ ምክንያቶች ሊኖሯቸው ይችላሉ፡፡ እኛ ግን እንደ መንገድ ኮንሰልታንት ሐሳቡን አቅርበን ነበር፡፡ ሌላው ከባምቢስ ማቋረጫ በተወሰነ ርቀት ላይ የተሠራው የኡራኤል መተላለፊያ ስላለ ወደዚያ መተላለፊያ ሄዶ ማቋረጡ ብዙም አይቸግርም ከሚል ነው፡፡ ሁለቱም ዘንድ ትልልቅ ሥራዎች መሥራት ከወጪም አንፃር ያልተመረጠ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የባቡር መስመሩ በሚያልፍባቸው በሁለቱም መስመሮች የተዘረጋው ግንባታ ከተማዋን ለሁለት ከፍሏል፡፡ በየአካባቢው ያለውንም ቢዝነስ አቀዛቅዟል፡፡ በተለይ በቂ ማቋረጫ አለመሠራቱ ትልቅ ችግር አይፈጥርም?

ኢንጂነር ተሾመ፡- በእያንዳንዱ ባቡሩ በሚያልፍበት ፌርማታዎች ሁሉ የእግረኛ ማቋረጫዎች አሉ፡፡ ከጦር ኃይሎች እስከ መገናኛ ባለው መስመር ላይ እኛ ከከፈትነው የእግረኞች መንቀሳቀሻ በተጨማሪ የባቡር መስመሩ ፌርማታዎች ባሉበት ሥፍራ እግረኞች ማቋረጥ ይችላሉ፡፡ እንዳየነው ፌርማታዎቹ በአማካይ በ600 ሜትር  ርቀት ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ከዚህ ሌላ እኛ የሠራናቸው ማቋረጫዎች ላይ እግረኞች ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ በተለይ ከመገናኛ እስከ ጦር ኃይሎች ባለው መንገድ ለእግረኛ በጣም ነፃ ማቋረጫዎች አሉ፡፡ ከኡራኤል በኋላ ግን የመሸጋገሪያዎች ቁጥር በተወሰነ ደረጃ ይቀንሳል፡፡ ይህ እንግዲህ በእኛ ዕምነት ለፍጥነት ሲባል የተደረገ ነው፡፡ አንድ ነገር ስታገኝ ሌላ ነገር ታጣለህ፡፡ እነዚህን ማቻቻል ደግሞ ግዴታ ነው፡፡ ሁለቱን ማስታረቅ ላይ በደንብ ጊዜ ሰጥቶ የሚመጣውን አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖ በደንብ አውቆ የመሥራት ነገር ቢኖርና ዕቅድ ላይ ረጅም ጊዜ ቢወሰድ የሚመጡት ነገሮች ይታወቃሉ፡፡ መፍትሔውም ይታወቃል፡፡ ሌላ ነገር ለማግኘት ሲባል የተወሰኑትን እንቀበላቸዋለን ተብሎም ሁሉንም የማግባባት ደረጃ ላይ ተደርሶ ሥራ ቢሠራ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ መታወቅ ያለበት ነገር ግን እንዲህ ያሉ መንገዶች ሲሠሩ የሚፈጠር ነገር ይኖራል፡፡ ቢዝነሶቹ ቦታቸውን ይለቃሉ፡፡ የተሻለ ቦታ ይሄዳሉ፡፡ እንዲህ ባለው ሥራ ወቅት መልቀቅ አለ፡፡ ይህንን ቀድሞ የማወቅ ጉዳይ ዕቅድ ላይ በደንብ ቢሠራ የተሻለ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በባቡር ፕሮጀክቱ ምክንያት ጥቂት የማይባሉ የቢዝነስ ተቋማት ተጐጂ ሆነዋል፡፡ ይህ ከታወቀ እናንተ በሠራችሁት ዲዛይን እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉና መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን አመላክታችኋል?

ኢንጂነር ተሾመ፡- ይህ የሚታወቅ እውነት ነው፡፡ መንገድ ዝግ በሆነበት ቦታ ላይ ሁሌም የቢዝነስ ተቋማት መነካታቸው አይቀርም፡፡ ለምሳሌ ቀለበት መንገድ ላይ የመሬት ዋጋ ከፍተኛ ነው ተብሎ በሚታመንበት ቦሌ አካባቢ እንኳን በቀለበት መንገዱ ምክንያት ተፅዕኖ ደርሷል፡፡ ከኢምፔሪያል ሆቴል ወይም ወደ ቦሌ ሚካኤል በሚወስደው መንገድ ላይ የቢዝነስ እንቅስቃሴ የለም፡፡ ስለዚህ መንገድ ሲዘጋ ውድ የተባለ ቦታ ላይ ሳይቀር የመሬት ዋጋው ይቀንሳል፡፡ የንግድ እንቅስቃሴውም ይወርዳል፡፡

 በሌላ በኩል ደግሞ መንገዱ በዚህ ሁኔታ መሠራቱና መኪኖች በፍጥነት በመሄዳቸው የሚያስገኘው ከፍተኛ ጠቀሜታ አለ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች የሚታወቁ እውነታዎች ናቸው፡፡ አጋጣሚው በሚፈጥረው ነገር እነዚያ ቢዝነሶች ወይ ፊታቸውን ያዞራሉ፡፡ ወይም ሌላ መንገድ ይፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹ዳውን ታውን›› ያላቸው አገሮች ‹‹ዳውን ታውን›› ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ መንገድ አይሠራም፡፡ የፍጥነት መንገዶች ዝግጁ በመሆናቸው ብቻ አይደለም ቢዝነሶች የሚቀንሱት፤ ምቹ ባለመሆናቸው ምክንያት ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ የቦሌ መንገድ ዝግ አይደለም፡፡ ግን ተሽከርካሪዎች በፍጥነት ስለሚያልፉበት ሰዎች እንደ ልብ ወዲህና ወዲያ ብለው የመግዛት ፍላጐታቸው ስለሚቀንስና ስለማይመቻቸው፣ በዚያ አካባቢ የመገልገል ፍላጎታቸው ይቀንሳል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ፕሮጀክት ምን ተማራችሁ? ምንስ አያችሁ?

ኢንጂነር ተሾመ፡- ትልቁ ትምህርት መሆን ያለበት ሁለቱ የመንገድና የባቡር ተጣምረው መሠራት እንዳለባቸው ነው፡፡ ባቡር አንድ መስመር ነው፡፡ ይህንን የባቡር መስመር የሚያቋርጥ የመንገድ ኔትወርክ ግን ውስብስብ ነው፡፡ ስለዚህ የባቡር ፕሮጀክት የሚከናወን ከሆነ ብቻውን ለምሳሌ ከመገናኛ ጦር ኃይሎች ድረስ ያለው የባቡር መስመር መሬት ላይ ተለጥፎ ቢሠራ ኖሮ ከተማው ውስጥ ትልቅ ችግር ይፈጥር ነበር፡፡ ሆኖም በአጋጣሚ ይህንን መንገድ እኛ ዲዛይን እንድናደርግ ሲሰጠን የባቡር ግንባታ ሥራውም ለኮንትራክተሩ የተሰጠበት ወቅት ስለነበር፣ ማቀናጀት ስለተቻለ ችግሩ በተወሰነ ደረጃ ቀንሷል፡፡ ስለዚህ ሌላ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ሲሠሩ ተመሳሳይ ቅንጅቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ካልተቀናጀ ግን የመንገዱ ሥራ በባቡሩ፣ የባቡሩ ሥራ ደግሞ በመንገዱ ላይ ጫና ያሳድራል፡፡ ይህም በሁለቱም ሥራ ኮንትራክተሮች እንዲህ ስለሆንን ልንሠራበት የምንችለው ጊዜ በዚህን ያህል ተወሰደብን፣ ይህንን ያህል ከሰርን ብለው ማካካሻ ይጠይቃሉ፡፡ ይህም ተጨማሪ ወጪ ያስወጣል፡፡ ስለዚህ ግንባታው ሳይቀር መቀናጀት አለበት፡፡ በእኛ በኩል ግን ተቀናጅቶ መሥራቱ ጠቅሞናል፡፡ ልዩነቱም ይታያል፡፡ በሁለቱ መንገዶች ላይ ባቡሩና የመንገዱ ሥራ ተቀናጅቶ የተሠራበትና ቀድሞ በተለያዩ ጊዜያት በተሠሩ ቦታዎች ላይ ያለው ልዩነት ታይቷል፡፡ ይህ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የተሽከርካሪ መንገዶችን ከባቡር መስመሩ ጋር በማቀናጀት ዲዛይን ለመሥራት ችላችኋል፡፡ ይህ የመጀመሪያ ተሞክሮ ነው፡፡ ወደ ተግባር ከተገባ በኋላ ግን ችግሮች አላጋጠሙዋችሁም?

ኢንጂነር ተሾመ፡- በጣም በብዙ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

ኢንጂነር ተሾመ፡- ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ትልቅ ተግዳሮቶች ነበሩ፡፡ በዲዛይን ሥራውም ወቅት በትልልቅ ሕንፃዎች መሀል የማለፍ፤ ሕንፃዎቹ ትልልቅ በመሆናቸው ይህ ሕንፃ ፈርሶ ይህን ላድን ልትል የምትችልበት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሃያ ሁለት አካባቢ የጎላጐል ሕንፃና ከፊት ለፊቱ ደግሞ አዲሱ የትራፊክ ጽሕፈት ቤት ሕንፃ ጉዳይ ትልቅ ችግር ነበር፡፡ በሁለቱ ሕንፃዎች መካከል ያለውን ቦታ ለመጠቀም በየዕለቱ ቦታውን እየለካን ነበር፡፡ ሁለቱም ሕንፃዎች መንገዱ በጣም ስለተጠጋቸው እንዳያውካቸው ለማድረግ ብዙ ችግር ነበር፡፡ የሕንፃዎቹ አጥርና ደረጃዎች ተነካክተዋል፡፡ የነበረው ቦታ በቂ ስላልነበረም የባቡሩ መስመር 11 ሜትር ይዞ መሠራት ሲኖርበት፣ በዚህ አካባቢ ግን በ9.60 ሜትር ነው እንዲሠራ የተደረገው፡፡ ስለዚህ ለባቡሩ በጭንቀት ነው የተሠራው፡፡ በ3.5 ሜትር ሊሠራ ይገባ የነበረም መንገድ ወደ ሦስት ሜትር አንሷል፡፡ ለእግረኛ ተብሎ የተሠራው መንገድ ከአራት ሜትር በላይ ቢሆንም፣ በዚህ አካባቢ ግን መሥራት የተቻለው በሦስት ሜትር ነው፡፡ ስለዚህ ሕንፃዎቹን ላለማፍረስ በጭንቀት ነው የተሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ አካባቢ ያሉት ሕንፃዎች መጀመሪያም ሲሆን ከማስተር ፕላን ውጪ የተሠሩ ናቸው ይባላል፡፡

ኢንጂነር ተሾመ፡- በተወሰነ ማስተር ፕላን ውስጥ ገብተዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ስለሆኑ ማድረግ የሚቻለውን ያህል ቴክኒካዊ መፍትሔ ትሰጣለህ፡፡

ሪፖርተር፡-  ግንባታውን ለማከናወን የሚያስችል መፍትሔ ተሰጠው ቢባልም የባቡሩ መስመር ወደ ሕንፃዎቹ መጠጋቱ ችግር አይኖረውም? ምክንያቱም ባቡሩ ንቅናቄ (ቫይብሬሽን) ስለሚኖረው ሕንፃዎቹ ላይ አደጋ አይኖረውም?

ኢንጂነር ተሾመ፡- ባቡሩ መሀል ላይ ነው ያለው፡፡ መንገዱም ቢሆን ትልልቅ ተሽከርካሪዎች ሲሄዱ ንቅናቄ አለው፡፡ የሕንፃ ሕጉ ላይ የተቀመጡ ነገሮች አሉ፡፡ ግንባታዎች ከመንገድ ገባ ብለው መከናወን አለባቸው፡፡ ነገር ግን መሬትን በጣም ውድ አድርጎ የማየት ነገር አለ፡፡ ትርፍ ቦታም ቢኖር ከኋላ ያስተርፋሉ እንጂ ከፊት በጣም ተጠግቶ የመሥራት ልማድ አለ፡፡ ይህ ብዙ ችግር ይፈጥራል፡፡ ችግሩ በራሳቸውም ላይ ጉዳት ያመጣል፡፡ ለምሳሌ እግረኛ በፍጥነት የሚሄድበት ቦታ ላይ በመስታወት ውስጥ የተቀመጠ ነገር ቆሞ ለማየት አይመችም፡፡ ስለዚህ ገባ ብለው ቢሠሩ ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግንባታውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለመጨረስ የገጠሙዋችሁ ችግሮች አልነበሩም?

ኢንጂነር ተሾመ፡- ግንባታውን ለማከናወን ከተቀመጠው ጊዜ አንፃር የመንገዱም ሆነ የባቡሩ መስመር ግንባታ በተያዘው ጊዜ እንዲያልቅ ለማድረግ ሁለቱን የማቀናጀቱ ሥራ ትልቅ ተግዳሮት ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ይጽፉልሃል፡፡ ለምሳሌ ከሜክሲኮ እስከ ልደታ ድረስ ያለው መስመር ለረዥም ጊዜ ታጥሮ ነበር፡፡ ይህንን ያጠረው የባቡር መስመሩን የሚሠራው ነው፡፡ መንገዱን የሚሠሩት ኮንትራክተሮች ደግሞ የባቡሩ ኮንትራክተር መንገዱን ይልቀቅልን አላሠራ አለን የሚል ተደጋጋሚ ደብዳቤዎች ጽፈዋል፡፡ ነገሩን የባቡሩን መስመር በሚገነባው ኮንትራክተር ቦታ ሆነህ ስታስበው ደግሞ ቦታው ትልቅ መታጠፊያ ያለበት ስለሆነ፣ የሚያቆሙዋቸው ምሰሶዎች ረዣዥም ስለነበሩና ይህን ድልድይ ጭምር የሚገነባበት በመሆኑ እነዚህን ሥራዎች  ለመሥራት ጊዜ ወስዶባቸዋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ማስታረቅ ትልቅ ተግዳሮት ነበር፡፡ ሌላው ትልቅ ተግዳሮት የነበረው ከውኃ መስመሩ ጋር የተያያዘው ነው፡፡ የውኃ መስመሩ ቀድሞ ነው የተሠራው፡፡ ቀድሞ መሠራቱ አስፈላጊ ነው፡፡ በመሀሉ ላይ ባቡር ስለሚሄድ ለባቡር ሥራው ቦታውን ለመልቀቅ ሲባል ወደ ዳር እንዲወጣ ተፈልጎ ነበር፡፡ ነገር ግን በኋላ ማሳለጫዎችን ስንሠራ ለምሳሌ ኡራኤል ላይ እስከ መፈንዳት ደርሶ ነበር፡፡ ይህም የመሬቱ ባህሪ ድንገት መቀያየር ያመጣው ነገር ነው፡፡

በመገናኛ አካባቢ ደግሞ በጣም ከባድ የነበረው ነገር ከቦሌ የሚመጣው ድልድይ በሥሩ እንዲያልፍ የማድረጉ ሥራ ነበር፡፡ ቮሪንግ ፓይል ቀብረንና አፈር ውስጥ አስረን ነበር ቆፍረን የምንሠራው፡፡ ይህንን በድፍረት የገባንበት ነው፡፡ ይኼ ሥራ በበጋ ወቅት ቢሠራ ያለብዙ ችግር ይከናወን ነበር፡፡ ኮንትራክተሩ ሥራውን ማጠናቀቅ ያለበት ጊዜ እየተገፋ ሄዶ ሥራውን ሳይጨርስ፣ ክረምት መጣበትና በዚህ ምክንያት ድልድዩ አደጋ ውስጥ ይወድቃል የሚል ሥጋት ውስጥ እንድንገባ አድርጎን ነበር፡፡ ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ የግንባታ ጊዜውን አስተካክለን፣ ሌሎች ዕርምጃዎችን ወስደን ልንሠራው ችለናል፡፡ በዚህ አካባቢ ለትራፊክ ዝግ የሆነውም ተሽከርካሪዎች በድልድዩ ላይ ሲሄዱ ተጨማሪ ንቅናቄ ስለሚኖረው ክረምቱ እስኪወጣ ድረስ ተዘግቶ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ድልድይ አሁን ምንም ችግር የለውም?

ኢንጂነር ተሾመ፡- ምንም ችግር የለውም፡፡ ችግሩ እንዳይገጥምም ቀድመን መንገዱን ማዘጋት ስለነበረብን አዘጋነው፡፡ ቀድሞም ቢሆን ሥራው በክረምት እንዲሠራ አልነበረም በዕቅድ ተይዞ የነበረው፡፡ ምክንያቱም ክረምት ላይ ብትሠራ አፈሩ የመናድ ዕድሉ ይጨምራል፡፡ አፈሩ ተናደ ማለት ቀድሞ የነበረው ድልድይ ምሰሶዎች ለአደጋ ይጋለጣሉ የሚል ሥጋት ስለነበር ሥራው በክረምት እንዲቆም አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- የመንገድ ግንባታው ፕሮጀክት በስድስት ወራት እንዲራዘም ሲደረግ የሚያስከትለው ተጨማሪ ወጪ የለም?

ኢንጂነር ተሾመ፡- እስካሁን ባለው ሒደት ፕሮጀክቱ በተያዘለት በጀት መሠረት የሚጠናቀቅ መሆኑ ነው፡፡ ተጨማሪ ወጪ ሊያስከትሉ የሚችሉ ውሳኔዎች አልተከሰቱም፡፡ ነገር ግን ኮንትራክተሮቹ ከተያዘላቸው የጊዜ ገደብ በላይ የወሰደባቸው  ከእነርሱ ቁጥጥር ውጪ በመሆኑ ምክንያት ከሆነ፣ ይህ ታይቶ የተወሰነ ማካካሻ ይችላል፡፡ ነገር ግን እስካሁን በዚህ ላይ የተወሰነ ነገር የለም፡፡ ይህ እየተመረመረ ነው፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ግን ሥራው በተያዘለት በጀት ይጠናቀቃል የሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  የዚህ ፕሮጀክት መጠናቀቅ የሚያስገኘው ጠቀሜታ እንዴት ይገለጻል?

ኢንጂነር ተሾመ፡- እንዲህ ዓይነት ትልልቅ የመንገድና የባቡር ፕሮጀክቶች አለቁ ማለት ብዙ ነገሮችን ይቀይራሉ፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውም ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆነ ማለት አይደለም፡፡ ተጨማሪ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ አንዱ ሲያልቅ አስፈላጊ ነው የሚባል ሌላ ሥራ ይመጣል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ስላለቀ የትራፊክ ፍሰቱ ሙሉ ለሙሉ ተወገደ ማለት አይደለም፡፡ ኅብረተሰቡ ይኼንን መገንዘብ አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነት ሥራዎች እያደገ ባለ አገር ውስጥ ይኖራሉ፡፡ አንድ ፕሮጀክት ሲያልቅ ሌላ ፕሮጀክት እንዲቀጥል የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ ፖሊሲ አውጪዎች ራሳቸው ይህን መገንዘብ አለባቸው፡፡ እፎይ የሚባልበት አይደለም፡፡ ይህ በማደግ ላይ ባለ አገር ሁሌም የሚኖር ነው፡፡ ይኼ ሥራ ስላለቀ ተብሎ ዝም የሚባልበት አይደለም፡፡ ተጨማሪ ሥራዎች ሲታከሉና ከትልልቅ ፕሮጀክቶች ጋር ሊተሳሰሩ የሚችሉ መንገዶች ሲገነቡ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የበለጠ እየሆነ ይሄዳል፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...