Tuesday, April 23, 2024

ጊዜ ያልገደበው የሰላማዊ ሠልፍ ንትርክ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣ ገባ ከሚሉባቸው የመንግሥት ቢሮዎች መካከል የአዲስ አበባ አስተዳደር የፈቃድና የማስታወቂያ ክፍል ዋነኛው ነው፡፡ ዓመቱ ጠቅላላ ምርጫ የሚደረግበት እንደመሆኑ ፓርቲዎቹ ቢሮውን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይበልጥ አዘውትረው እንደሚጎበኙት ይጠበቃል፡፡ በከንቲባው ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኘው ክፍል ዋነኛ ዓላማ ስለሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት የሚደነግገውን አዋጅ ቁጥር 3/1983 በአዲስ አበባ ማስፈጸም ነው፡፡

የክፍሉ መጠሪያ በራሱ ባለፉት 24 ዓመታት ሰላማዊ ሠልፍንና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባን አስመልክቶ ገዥው ፓርቲና መንግሥት በአንድ ወገን፣ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ በሌላ ወገን የሚያደርጉትን ክርክር የሚያሳይ ነው፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጁ ፈቃድ ሳይሆን ማስታወቅን ብቻ እንደሚያስቀምጥ ይጠቁማሉ፡፡ መንግሥት በበኩሉ በግልጽ ፈቃድ ያስፈልጋል ብሎ አይከራከር እንጂ፣ በተለያዩ መግለጫዎቹ ‘ያለፈቃድ የተደረጉ ሰላማዊ ሠልፎች’ ሲል ይጠቅሳል፡፡ ይበልጥ አተኩሮ የሚከራከረው ሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የማድረግ መብት እንደሌሎች መብቶች ሁሉ ገደብ የሚደረግበት መሆኑን ነው፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ባለፈው እሑድ ለማድረግ አስቦት የነበረውና በመንግሥት እንዳይካሄድ የተከለከለው ሰላማዊ ሠልፍ፣ እንዲሁም ጥር 24 ቀን 2007 ዓ.ም. አደርገዋለሁ ያለው ሰላማዊ ሠልፍ በፓርቲውና በመንግሥት መካከል የፈጠረው አለመግባባት የዚህ ችግር አንድ ማሳያ ነው፡፡ ባለፈው ሐሙስ ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ አመራር እንዳልሆነ ውሳኔ የሰጠበት ቡድን ውስጥ የተካተቱት የአንድነት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሥራት አብርሃም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፓርቲው ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ አቅዶ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ፈቃድና ማሳወቂያ ክፍል በሕጉ መሠረት ለማስታወቅ ደብዳቤ ይዘው ቢሄዱም የቢሮው ሠራተኞች አልተቀበሏቸውም፡፡ ደብዳቤውን በቢሮው ጥለው ቢሄዱም በድጋሚ በፖስታ ቤት ልከው መድረሱን እንዳረጋገጡም ይገልጻሉ፡፡ በማመልከቻቸው መሠረት መልስ ሳይሰጥ የቆየው ቢሮ ከ72 ሰዓት በኋላ ሰላማዊ ሠልፉ መከልከሉን እንደገለጸላቸው አቶ አሥራት አመልክተዋል፡፡

አቶ አሥራት ይኼ ዓይነት አሠራርን በመቃወም ሰላማዊ ሠልፍን ለማድረግ መሞከራቸውን ያስረዳሉ፡፡ ችግሩ በአዲስ አበባ የተባባሰ ቢሆንም በተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ መሰናክሎች እንዳሉም

ከሳምንት በፊት ሊደረግ የነበረው ሰላማዊ ሠልፍ ‘ሕገወጥ ነው’ በሚል መንግሥት በወሰደው ውሳኔ በሠልፈኞቹና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት መከሰቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ፓርቲው ግን በሳምንቱ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተመሳሳይ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ እየተዘጋጀ ነው፡፡ በአማራ ክልል በደሴ ከተማ ለሚደረገው ሰላማዊ ሠልፍ ፈቃድ ማግኘቱን የገለጸው አንድነት፣ ለአዲስ አበባው ግን በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ምክንያት ማካሄድ አትችልም መባሉን አስታውቋል፡፡ ‹‹ጥር 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ደብዳቤ አስገብተናል፡፡ በማግሥቱ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ስላለ አትችሉም የሚል መልስ ተሰጥቶናል፡፡ እኛም የመከልከል ሥልጣን እንደሌላቸው ገልጸን ጥር 20 ቀን ደብደቤ ጽፈናል፤›› ያሉት አቶ አሥራት፣ ሰላማዊ ሠልፉን በዕቅዱ መሠረት እንደሚገፉበት ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ከብሔራዊ ቦርድ ውሳኔ በኋላ ይህ የሚቻል አይመስልም፡፡ ሠልፉን የጠራው ‘ሕገወጥ’ የተባለው አመራር ነው፡፡

ይህንን መሰል ክርክር በሌሎች ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና በመንግሥት መካከል በተደጋጋሚ ተደርገዋል፡፡ ለአብነትም መድረክ፣ ሰማያዊና ኢዴፓን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ግጭቶቹና አለመግባባቶቹ የተከሰቱት በሕጉ መንፈስና በመንግሥት አተረጓጎም መካከል ልዩነት በመከሰቱ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ ሌሎች ግን በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ያለው ችግር ምንጭ በሕጉ ላይ ባለው አለመግባባትና የአተረጓጎም ልዩነት የተገደበ እንዳልሆነ ያብራራሉ፡፡

የሕጉ ግልጽነት ጥያቄ

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 30 ላይ ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም ከቤት ውጪ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሠልፎች በሚደረጉባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ፣ ወይም በመካሄድ ላይ ያለ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሠልፍ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥስ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡ ሆኖም ሕገ መንግሥቱ የወጣቶችን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስምን ለማስጠበቅ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነት በሚወጡ ሕጎች ሊገደብ እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡

ሕገ መንግሥቱ በሥራ ላይ ከዋለ 20 ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ በእነዚህ ጊዜያት ሰላማዊ ሠልፍንና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባን የተመለከተ ዝርዝር ድንጋጌ አልወጣም፡፡ ይሁንና ከሕገ መንግሥቱ መውጣት አስቀድሞ በሽግግሩ መንግሥት የወጣው የሰላማዊ ሠልፍና የሕዝባዊ ፖለቲካዊ ስብሰባዎች ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 3/1983 አሁንም በሥራ ላይ ይገኛል፡፡ አዋጁ ማንኛውም ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ድርጅት ሰላማዊ ሠልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ሲያዘጋጅ ሊያሟላቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ይዘረዝራል፡፡

በአዋጁ ከተዘረዘሩት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የሆነው የማሳወቅ ግዴታ ከላይ ለተገለጹት ዓይነት የተለያዩ አተረጓጎሞች በር የከፈተ ነው፡፡ አዋጁ የታሰበው ሰላማዊ ሠልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ከሚካሄድበት ጊዜ ቢያንስ ከ48 ሰዓታት በፊት በጽሑፍ የማሳወቅ ግዴታ ይጥላል፡፡ የማሳወቂያው ጽሑፍ ሰላማዊ ሠልፉ ወይም ሕዝባዊ ስብሰባው በከተማ ከሆነ የሚደረገው ለከተማው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት (ወይም ለተተኪው)፣ ከከተማ ውጪም ከሆነ ለአውራጃው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት (ወይም ለተተኪው) እንደሚሆንም ተደንግጓል፡፡

ለሚመለከተው አካል የሚቀርበው ጽሑፍ ሊያካትታቸው ከሚገቡ ነጥቦች መካከልም የሰላማዊ ሠልፉ ወይም የሕዝባዊ ፖለቲካ ስብሰባው ዓላማ፣ የሚደረግበት ቦታ፤ የሚደረግበት ቀንና ሰዓት፣ የሚወሰደው ጊዜ ግምትና የተሳታፊው ሕዝብ ብዛትና ማንነት ግምት፣ ከመንግሥት የሚፈለገው ዕርዳታና የአደራጁ ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ድርጅት አድራሻ ይጠቀሳሉ፡፡

የማስታወቂያ ደብዳቤ የሚጻፍለት አካል ሰላማዊ ሠልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው በሌላ ጊዜ ወይም በሌላ ሥፍራ ቢደረግ ይሻላል የሚል አስተያየት ካለው ምክንያቱን በመግለጽ ይህንኑ ጥያቄው በደረሰው በ12 ሰዓት ውስጥ በጽሑፍ ለአዘጋጁ የማሳወቅ ኃላፊነት እንዳለበት ሕጉ ይደነግጋል፡፡ ሆኖም ሰላማዊ ሠልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው ምንጊዜም በየትኛውም ቦታ ሊካሄድ አይችልም ማለት እንደማይችል በግልጽ ያስቀምጣል፡፡

አዋጁ ሰላማዊ ሠልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ወይም ምክንያቶችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስቀምጣል፡፡ በአዋጁ መግቢያ ላይ ሕጉን ለማውጣት መነሻ ከሆኑ ነጥቦች መካከል ሠልፍና ስብሰባ በሚያካሂዱ ግለሰቦችና በሌሎች ግለሰቦች መካከል ሊነሳ የሚችል አምባጓሮን ለመቆጣጠር፣ የሕዝብ ሰላምና ፀጥታ የሚያውክን ሁኔታ ለማስወገድ፣ በግለሰቦችና በንብረት ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳትና ጥፋትን ለመቆጣጠር የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨማሪም ይህን መብት ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው የሌሎችን ሕጋዊ መብቶች በማይጋፉበት አኳኋን እንደሆነም ሕጉ ይገልጻል፡፡

ሕጉ ማንኛውም ሰላማዊ ሠልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የዘር፣ የቀለም፣ የሃይማኖት፣ የፆታና የመሳሰሉትን የእኩልነት መብቶችን የሚፃረር ልዩነቶች በማድረግ ላይ የተመሠረተ ዓላማን፣ በብሔር፣ ብሔረሰቦችና በሕዝቦች ላይ በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ የጥላቻ አሉባልታንና ዘረኛ ጥርጣሬን ለማራመድና ለማነሳሳት እንደማይፈቀድለትም ያስቀምጣል፡፡

በመጨረሻው ሌላው በሕጉ ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ማንኛውም ሰላማዊ ሠልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ እንደ ኤምባሲዎች፣ ቤተ ክርስቲያኖች፣ መስጊዶች፣ ሆስፒታሎች፣ ግድቦችና የገበያ ቦታዎች ካሉ ሥፍራዎች በ100 ሜትር ርቀት ውስጥ ሊደረግ እንደማይችል ነው፡፡ በተመሳሳይ በጦር ኃይሎች፣ በጥበቃና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በሚቆጣጠሩ የመንግሥት የሥራ ክፍሎች አካባቢ በ500 ሜትር ርቀት ውስጥ ሊደረግ እንደማይችል ይደነግጋል፡፡

የማሳወቂያ ጽሑፍ የሚቀርብለት አካልም እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ወይም የክልከላ መሠረቶች አገናዝቦ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ ይሁንና በእነዚህ ነጥቦች ላይ ያሉት አለመግባባቶች ሕጉ በሥራ ላይ በዋለባቸው ጊዜያት ሁሉ አብረው የዘለቁ ናቸው፡፡

በተደጋጋሚ ከሚቀርብበት ቅሬታና ወቀሳ በተቃራኒ መንግሥት ሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባዎችን በተመለከተ በተደነገጉት ሕጎችና በተግባር መካከል መፋለስ እንደሌለ ይገልጻል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል፣ ሕገ መንግሥቱም ሆነ አዋጁ ግልጽነት የሚጎድላቸው እንዳልሆኑ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የማድረግ መብት ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና የተሰጠው በማንም የማይሰጥና የማይነፈግ መብት ነው፡፡ ፈቃድን የሚጠይቅ የሕግ ማዕቀፍ የለንም፤›› በማለት ለሪፖርተር የመንግሥትን አቋም ገልጸዋል፡፡ ይሁንና አቶ ሽመልስ በመብቱ ላይ እንደማንኛውም ሌላ መብት ገደብ የሚጣል መሆኑን አመልክተዋል፡፡ መንግሥት ለሰላማዊ ሠልፉ ዕውቅና ለመስጠት የሌሎች ግለሰቦች መብት የማይጣስ ስለመሆኑና በሕዝቡ ጥቅም ላይ ጉዳት የማይደርስ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የጥንቃቄ ዕርምጃዎች እንደሚወሰድ አቶ ሽመልስ አስረድተዋል፡፡

መንግሥት የሚወስዳቸው የጥንቃቄ ዕርምጃዎች በአብዛኛው ከጊዜና ከቦታ ጋር የተገናኙ ክልከላዎች ፈቃድ ተብለው ሊተረጎሙ እንደማይችሉም አቶ ሽመልስ ያስገነዝባሉ፡፡ የጥንቃቄ ዕርምጃዎች ሌሎች የተረጋገጡ መብቶች እንዳይጣሱና አስቀድመው እየተከናወኑ ካሉ ፕሮግራሞች ወይም ተቃራኒ አቋም ካላቸው ጋር ግጭት እንዳይፈጥሩ አስቀድሞ ማስተካከያ ለማድረግ አስፈላጊ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡ ፈቃድ የማይጠየቅ ከሆነ የፈቃድና የማሳወቂያ ክፍል በአስተዳደሩ መቋቋሙን እንዴት ያዩታል በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ሽመልስ ሲመልሱ፣ ‹‹እሱ የቃል አጠቃቀም ጉዳይ ነው፡፡ ምዝገባ በሚለው ስሜት ብንረዳው ጥሩ ነው፡፡ ጥንቃቄ ለማድረግ ነው የተቋቋመው፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ በመዝጋቢው አካል ፈቃድ አይከለከልም፡፡ ገደብ የሚደረገው ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ዮናታን ተስፋዬ የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሲሆኑ፣ የመንግሥት ክልከላዎች የገዥውን ፓርቲ ፍላጎት እንጂ የሕዝብ ጥቅምን መሠረት ስለማያደርጉ በአብዛኛው አሳማኝ እንዳልሆኑ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ‹‹በሕጉ መሠረት ማሳወቅ ያለብንን ነገሮች እናሳውቃለን፡፡ ምክንያቱ ካላሳመነን ግን በስብሰባው እንቀጥላለን፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ የመንግሥት አካላት ቀደም ብሎ ከሕጉ በተቃራኒ የማስፈራሪያ ቃላት እየተጠቀሙ የክልከላ ደብዳቤ የሚጽፉ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በአዋጁ የተቀመጡ የክልከላ ነጥቦችን ለመጥቀስ እንደሚሞክሩ ጥቂት ማሳያዎች እንዳሉ አቶ ዮናታን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ዋጋ እየተከፈለበትም ቢሆን በሕጉ መሠረት ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እንጥራለን፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ግን ሕጉ ክፍተት እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ ፓርቲያቸው ሐሳቡን ለመግለጽ እንደሚጥር የገለጹት ዶ/ር ጫኔ፣ ስለሰላማዊ ሠልፍ አስቀድሞ ማሳወቅ ለፀጥታና ለተለያዩ ጉዳዮች ሲባል ተገቢ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ይሁንና በአፈጻጸም ረገድ የሕግ ክፍተት መኖሩን መገንዘባቸውን ጠቁመዋል፡፡ ኢዴፓ ባለፈው ዓመት ሊያካሂድ ላሰበውና ዕውቅና ተሰጥቶት ለነበረው ስብሰባ ሕዝቡን ለመጥራት ማይክራፎን በመጠቀም ሲቀሰቅሱ የነበሩ የፓርቲው አባላት መታሰር ለዚህ አንድ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በእኛ እምነት ይህ ድርጊት [ቅስቀሳው] የስብሰባው አንድ አካል ነው፡፡ በተናጠል ሌላ ዕውቅና የምንጠይቅበት ምክንያት የለም፡፡ በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጉዳዩን አንስተን የሕግ ክፍተት እንዳለ ታምኖ እንዲታይ ውሳኔ ተላልፏል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

አቶ ሽመልስ የአስተዳደሩ ውሳኔ ያላሳመነው አካል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ መፍትሔ መሻት ቢኖርበትም፣ አላሳመነኝም በማለት በሠልፍ ወይም በስብሰባ መግፋት ሕገወጥ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በአዋጁ መሠረት ሊያሟሉ የሚገባቸውን ነገሮች ካላሟሉና ካላሳወቁ ድርጊታቸው ሕገወጥ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በታቃራኒ አቶ ዮናታን የአስተዳደሩ ምክንያት ባያሳምን ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ የውሳኔው ምክንያታዊነት ላይ ቅሬታ ለማቅረብ አመቺ ሁኔታዎች ስለሌሉ፣ በዕቅዳቸው መሠረት ለመቀጠል እንደሚገደዱ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹አስተዳደሩ የገዥውን ፓርቲ ሐሳብ ነው የሚያንፀባርቀው፡፡ ፍርድ ቤቱም ላይ ተመሳሳይ የገለልተኝነት ጥያቄ እናነሳለን፡፡ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ጊዜ ተፈትኖ ወድቋል፡፡ ስለዚህ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ጊዜ ማባከን ነው፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የሕገ መንግሥት ኤክስፐርትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እነዚህን አለመግባባቶች ለመፍታት ፍርድ ቤቶች የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ ይተቻሉ፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፍርድ ቤቶችን ባለመፈተን የፍትሕ ሥርዓት እንዲከበር የሚጠበቅባቸውን እየፈጸሙ አለመሆናቸው ድክመታቸው እንደሆነ የጠቆሙት ዶ/ር ጌዲዮን፣ ፍርድ ቤቶችን ያለመጠቀም ቸልተኝነታቸው ግን ምክንያት አልባ እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ፍርድ ቤቶታችን ላይ እምነት መኖሩ ያጠራጥራል፡፡ በተለይ ለሲቪልና ለፖለቲካ መብቶች ዘብ ቋሚዎች ሆነው እያገለገሉ አይደለም፡፡ ገለልተኝነት ይጎላቸዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በአብዛኛው አሳማኝ የሆነና መብትን የሚያስከብር ውሳኔ ሲሰጡ አይታይም፡፡ መብቱን ያላግባብ ከሚጠቀምበት አካል ለመጠበቅ ለመብቶች ቅርብ የሆኑ ፍርድ ቤቶች ያስፈልጋሉ፤›› በማለትም ያስረዳሉ፡፡

ዶ/ር ጌዲዮን አዋጁ እንደ ገደብ የሚቆጠሩ ሁኔታዎችን ማስቀመጡን አስታውሰው፣ ምንም እንኳን የወጣበት ጊዜ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን የቀደመ ቢሆንም፣ ሐሳብን የመግለጽ መብትን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 (6) ላይ የተቀመጡት ገደቦች አዋጁንም ቢሆን ሊገዙ እንደሚገባ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ስብሰባ ሰላማዊና አመፅን የሚያስወግድ መሆኑን ማረጋገጣቸው ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን አዳራሽ ተከራይተው ለሚያደርጉት ስብሰባ ማስታወቅ ያለባቸው ነገሮች የይዘት ክልከላን የሚጋብዙ ናቸው፡፡ መንግሥት ወይም ገዥው ፓርቲ ያላግባብ ክትትል እንዲያደርግ የሚጋብዝ ነው፡፡ ይዘትን መሠረት ያደረገ ክልከላ አይፈቀድም፡፡ የተከለከሉ ነገሮች በሕገ መንግሥቱ ተቀምጠዋል፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ‹ልማታዊ አይደለም› ወይም ‹ኪራይ ሰብሳቢነትን ያስፋፋል› ብለህ ልትገድበው አትችልም፡፡ ባደጉ አገሮች እንዲያውም ሕዝቡ ይወደዋል ባሉትና እንደ ቂልነት በሚያስወስድ ጉዳይ ላይ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ የተለመደ ነው፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

አዋጁ የተጠቀሱትና ሌሎች መጠነኛ ክፍተቶች ቢኖሩበትም ማሻሻያ ከማድረግ ይልቅ አፈጻጸሙን ማሻሻል የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ዶ/ር ጌዲዮን ይመክራሉ፡፡ ‹‹የትኛውም ሕግ ከክፍተት የፀዳ አይደለም፡፡ ክፍተቱን የሚሞላ ሥርዓት ከሌለ የተሻለ ሕግ ቢወጣም ለውጥ አይኖርም፤›› ሲሉም  ያክላሉ፡፡

መንግሥት በአሠራር ያደርግ የነበረውን ክልከላ ዘርዘር አድርጎ በመመርያ ሊያወጣ እንዳሰበና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በረቂቁ መመርያ መሠረት ውሳኔዎች እየተሰጡ ስለመሆኑ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ አንዳንዶች ይህን እንደ ሕግ ማሻሻያ ወስደው የውይይት አጀንዳ አድርገውታል፡፡ የሕግ ክፍተት ስለሌለ ሕጉን ማሻሻል እንደማያስፈልግ የሚከራከሩት አቶ ሽመልስ፣ ሕጉ ጠቅለል ተደርጎ ለቀጣይ ትውልድም ጭምር እንዲያገለግል እንደወጣ ያመለክታሉ፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ ሕግ ዝርዝር ጉዳዩን ለዝርዝር መመርያ አስፈጻሚው አካል መወሰኑ የተፈቀደ እንደሆነና ዋናው ቅድመ ሁኔታ የሕጉን መንፈስ ሳይለቅ መውጣቱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለመመርያው ከሚዲያ ቢሰሙም ስለመኖርና አለመኖሩ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ገልጸዋል፡፡ መመርያውን አውጥቶታል የተባለውን የአዲስ አበባ አስተዳደር የካቢኔ ጉዳዮችና የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ሪፖርተር ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡

ተግባራዊ ተግዳሮቶች

ሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ማድረግ ከፓርቲዎች ተፈጥሯዊ ባህርይ ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ መድረኮች ፓርቲዎቹ ከሕዝብ ጋር እንዲገናኙ፣ የቆሙለትን ዓላማ በማስረዳት አዳዲስ አባላትን እንዲመለምሉ፣ ገዥው ፓርቲ ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ ተቃውሞውን እንዲገልጽ ለማድረግና አማራጭ ፓርቲ መሆናቸውን ለማሳየት፣ ገዥው ፓርቲ የአካሄድ ለውጥ እንዲያደርግ ለማስገደድ ጠቃሚ እንደሆኑም ያመለክታሉ፡፡

በኢትዮጵያ ከአወዛጋቢው ምርጫ 97 በኋላ በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. በሰማያዊ ፓርቲ እስከ ተደረገው ሰላማዊ ሠልፍ ድረስ መብቱን የመጠቀም አዝማመሚያ ተቀዛቅዞ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ቢሆን የታቀዱ ሰላማዊ ሠልፎች ያለ ለውጥ የተደረጉበትን ቀን ማስታወስ ይከብዳል፡፡ ፓርቲዎቹ ተሳክቶላቸው ባደረጓቸው ሰላማዊ ሠልፎች የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ እንዲሰረዝ፣ የታሰሩ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ አመራሮች እንዲፈቱ፣ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም፣ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ይወክላሉ የሚባሉት እንዲፈቱ፣ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ የፖለቲካ መረጋጋት እንዲሰፍን፣ ሙስና እንዲገታ፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዲቆም፣ ፍርድ ቤቶች ነፃ እንዲሆኑ፣ ለብሔራዊ መግባባት ገዥው ፓርቲ እንዲሠራና የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ጥሪ አድርገዋል፡፡

ገዥው ፓርቲና መንግሥት ሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የማድረግ መብትን ተግባራዊ ለማድረግ ቢሞክሩም ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች ላይ ከሚፈጥሩት ጫና አንፃር ከሕጉ የበለጠ የፖለቲካ አካሄዱ ተግዳሮት መፍጠሩን በመጥቀስ የሚከራከሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ዶ/ር ጌዲዮን የአዋጁ መሠረታዊ ችግር ይዘቱ ሳይሆን፣ አፈጻጸሙ መሆኑን በመጥቀስ ይህንኑ አቋም ያጠናክራሉ፡፡ ‹‹ውሳኔ ሰጪ የመንግሥት አካላት ይህን መብት ተግባራዊ ሲያደርጉ ገዳቢ፣ በዘፈቀደ አሠራር የታጀቡና ምክንያታዊ ያልሆኑ ውሳኔዎችን ነው የሚሰጡት፡፡ ምክንያታቸው ለእነሱ ብቻ የሚገባ ነው የሚመስለው፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

ይህ አሳማኝ ያልሆነ የውሳኔ አሰጣጥ ከበርካታ ዓመታት በኋላ የመብቱ አፈጻጸም ለውጥ እንዳይኖረው ማድረጉንም ዶ/ር ጌዲዮን ያመለክታሉ፡፡ ለዚህ ችግር ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወቃሽ ቢሆኑም ትልቁ ድርሻ ግን በመንግሥት ላይ እንደሚወድቅ ዶ/ር ጌዲዮን ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹ፈቃዱ ካለው የመለወጥ ሥልጣን ያለው ገዥው ፓርቲ ወይም መንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በሆነ ባልሆነው እንቅፋት መፍጠሩ ማቆም አለበት፡፡ ለህልውናው ወሳኝ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም ጠቃሚ መሆኑን ማጤን መቻል አለበት፡፡ ከንግግር አልፎ ቁርጠኝነቱን በተግባር ማሳየት አለበት፤›› ሲሉም መንግሥት አስተዳደራዊ ጫናዎችንና እንቅፋቶችን እንዲያስወግድ ጠይቀዋል፡፡

ዶ/ር ጌዲዮን የመብቱ አፈጻጸም ከዚህ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የገዥው ፓርቲ ወይም መንግሥት ምልልስ ወጥቶ የሕዝቡ ጥያቄ ካልሆነ በቅርብ ጊዜ ለውጥ ማየት እንደማይቻልም አመልክተዋል፡፡ ‹‹ባህላችንና የኋላ ታሪካችን ከዴሞክራሲ ጋር የተሳሰረ ሳይሆን ለፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ድጋፍ የሚሰጥ ነው የነበረው፡፡ ይህን በመለወጥ ሥር የሰደደ የዴሞክራሲ ባህል እንዲያብብ ከተፅዕኖ ፈጣሪ መሪዎች፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከምሁራን፣ ከጋዜጠኞች ብዙ ይጠበቃል፤›› ያሉት ዶ/ር ጌዲዮን፣ ያን ጊዜ ብቻ መንግሥት ሕጉን ብቻ መሠረት አድርጎ እንዲሠራ ማስገደድ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ አቶ ዮናታን የችግሩ ምንጭ የገለልተኛ ተቋማት አገልግሎት አለመኖር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ተቋማቱን በመተባበር መንፈስ ሳይሆን በጥርጣሬ እንደሚያዩዋቸውም ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹አስተዳደሩ አንዱ የሚያቀርበው ምክንያት በቂ የፀጥታ ኃይል የለንም የሚል ነው፡፡ ለሠልፍ ከወጣን በኋላ እሱን ለመበተን የሚወስደውን ኃይል ብዛት ስታይ ምክንያታቸው አሳማኝ እንዳልሆነ ትረዳለህ፤›› በማለትም ምሳሌ ሰጥተዋል፡፡ መንግሥት ከፍተኛ ሥጋት ያለበት መሆኑና ለአማራጭ አስተሳሰቦች ቦታ የማይሰጥ ርዕዮተ ዓለም የሚከተል መሆኑ ምክንያታዊ ላልሆኑ ውሳኔዎች እንደዳረገውም አቶ ዮናታን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹መሠረተ ልማት እየተደረገበት ስለሆነ በስታዲየም ሠልፍ ማድረግ አይቻልም ብሎ የመለሰልን አካል፣ በሁለት ሳምንት ውስጥ እዚያው ቦታ መንግሥት ስብሰባ እንዲያደርግ ከፈቀደ ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም፤›› ሲሉም ሌላ አብነት አንስተዋል፡፡

አቶ ሽመልስና ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን ሰላማዊ ሠልፎችንና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባዎችን የሚፈራ መንግሥት በኢትዮጵያ እንደሌለ ይከራከራሉ፡፡ አቶ ሽመልስ ሰላማዊ ሠልፍ ተደረገ ለማለት ድርጊቱ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መደረጉን መጥቀስ አግባብ አለመሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ሕግን ከማክበር በዘለለና እነዚህ መብቶች ተግባራዊ እንዳይሆኑ የመገደብ አዝማሚያ የለውም፡፡ በርካታ ሠልፎችና ስብሰባዎች ተደርገዋል፡፡ በመንግሥት፣ በተለያዩ ማኅበራትና ቡድኖች እንዲሁም በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እየተደረጉ እየታየ መንግሥት ሠልፍና ስብሰባዎች እንዲደረጉ አይፈልግም ማለት ክህደት ነው፤›› ሲሉ የመንግሥትን አቋም ተከላክለዋል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ገለልተኛ ወገኖች ግን ከአቶ ሽመልስ በተቃራኒ ቆመዋል፡፡ ብዙዎች ግን ስለሠልፍ ማድረግና ፖለቲካዊ ስብሰባ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተመሳሳይ አቋም የሚይዙበትን ቀን መናፈቃቸውን ይናገራሉ፡፡

(ለዚህ ዘገባ ሚኪያስ ሰብስቤ አስተዋፅኦ አድርጓል)  

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -