ታማኝ የተባሉ አምስት ኩባንያዎች የጉምሩክ ፍተሻ ሳይካሄድባቸው ከውጭ ዕቃ እንዲያስገቡ ተፈቀደ፡፡ ኩባንያዎቹ ኒያላ ሞተርስ፣ ብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት፣ ኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ፣ አለ በጅምላና መላቅ ትሬዲንግ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንደገለጸው፣ በጉምሩክ ፈጣን አገልግሎት ፕሮግራም ለመታቀፍ ያመለከቱት የእነዚህ አምስት ድርጅቶች የአሠራር ኦዲት ከተካሄደ በኋላ ብቁ ሆነው በመገኘታቸው በፕሮግራሙ እንዲታቀፉ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም በዚህ ፕሮግራም የታቀፉት 16 ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ ከ16 ኩባንያዎች መካከል ሞኤንኮ፣ አይካ አዲስ፣ ድሬ ኢንዱስትሪስ፣ ካዲስኮ ቀለም፣ ሑጂያን ኢንተርናሽናል፣ አምባሳል ትሬዲንግና ዜኒት ገብስ እሸት ይገኙበታል፡፡
አምስቱ አዳዲስ ኩባንያዎች በመጨመራቸው የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ቁጥር በአጠቃላይ 21 እንደሚሆን የገለጸው ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ እነዚህ ኩባንያዎች የሚያስመጧቸው ዕቃዎች ምንም ፍተሻ ሳይደረግ በቀጥታ እንዲገቡላቸው ይደረጋል፡፡
ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሥጋት ደረጃን መነሻ በማድረግ አራት ደረጃዎች አውጥቷል፡፡ ደረጃዎቹ ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴና ሰማያዊ ይሰኛሉ፡፡ በእነዚህ ደረጃዎች መሠረት ብዛት ያላቸው ዲክላራሲዮኖች በከፍተኛ የሥጋት ደረጃ መጋለጫ በሆነው ‹‹ቀይ›› ሥር ሆነው ተስተናግደዋል፡፡ የዲክላራሲዮኖቹ ብዛትም 32,174 ነው፡፡
በአረንጓዴ ሥር ደግሞ 6,656 ዲክላራሲዮኖች ተስተናግደዋል፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኮሙዩኒኬሽንና ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን እንደገለጹት፣ በአረንጓዴ ደረጃ የተስተናገዱ አስመጪዎች ታማኞች ናቸው፡፡
ይህ አሠራር ሕጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱትን የሚጠቅም ነው በማለት የሚናገሩት አቶ ኤፍሬም፣ የሥጋት ቀጣና ናቸው ተብለው በተለዩት ላይ ጥብቅ ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡