Sunday, June 23, 2024

የግብፅ ፕሬዚዳንት የአዲስ አበባ ቆይታቸውን አቋርጠው ተመለሱ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

 የግቡፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ባለፈው ሐሙስ ለአፍሪካን ኅብረት ጉባዔ አዲስ አበባ ቢገቡም፣ በግብፅ አማፂያን ሲናይ ውስጥ በደረሰው ጥቃት ምክንያት የሦስት ቀን ቆይታቸውን ሰርዘው ተመለሱ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ዓርብ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ብቻ ተገኝተው፣ ቀሪ ኃላፊነቶችን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ሳሜህ ሽኩሪ ወክለው ሄደዋል፡፡

በ1987 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ መጥተው የነበሩት የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ አሸባሪዎች  ካደረጉት የግድያ ሙከራ በኋላ፣ ለመሪዎች ጉባዔ ግብፃውያን በፕሬዚዳንት ደረጃ ተገኘተው አያውቁም፡፡ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ ግብፅ ከአፍሪካውያን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስ እየጣሩ እንደሚገኙ በርካቶች የሚናገሩትና ሰሞኑንም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተወደሰ ጉዳይ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት አልሲሲ ወደ አዲስ አበባ ለመሪዎቹ ጉባዔ ሲመጡ ሌላ የጎንዮሽ ጉዳይም አንግበው እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ይህም በታላቁ የህዳሴ ግድብና በኢትዮጵያና በግብፅ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ለመምከር ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ ይህ የፕሬዚዳንቱ የአዲስ አበባ ጉብኝት ታሪካዊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከ120 በላይ የግብፅ ጋዜጠኞች ፕሬዚዳንቱን ተከትለው አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የፕሬዚዳንት አልሲሲ ጥረት እንደታሰበው አልሆነም፡፡ ባለፈው ሐሙስ ማምሻውን የአይኤስአይኤስ የግብፅ ክንፍ ነኝ የሚለው አንሳር ባያት አል መቃዲስ በሰሜን ሲናይ በፈጸመው የሽብር ጥቃት ምክንያት ዓርብ ረፋዱ ላይ ወደ ግብፅ ተመልሰዋል፡፡

አማፂያኑ በሲናይ በሚገኙ የግብፅ ወታደራዊ ይዞታዎችና የፀጥታ ተቋማት በድምሩ አራት ቦታዎች በሰነዘሩት ጥቃት 30 ሰዎች ሲገደሉ፣ 36 የሚሆኑ መቁሰላቸው ተዘግቧል፡፡

ፕሬዚዳንት አልሲሲ በተፈጸመው የሽብር ጥቃት ወደ አገራቸው ቢመለሱም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ከአፍሪካ ኅብረትና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚኖረውን ውይይት ፕሬዚዳንቱን በመወከል ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -