Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊብሔራዊ የጤና ፖሊሲ ማሻሻያ እየተደረገለት ነው

ብሔራዊ የጤና ፖሊሲ ማሻሻያ እየተደረገለት ነው

ቀን:

በሽግግሩ መንግሥት ወቅት ማለትም በ1985 ዓ.ም. ወጥቶ እስከዛሬ ድረስ እየተሠራበት ያለው ብሔራዊ የጤና ፖሊሲ ማሻሻያ እየተደረገለት ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ወራት ውስጥ ማሻሻያው ከተዘጋጀ በኋላ ለሚያፀድቀው አካል ይመራል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፖሊሲና ፕላን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኖህ ኤልያስ ከሪፖርተር ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ አሁን በሥራ ላይ ያለውን ፖሊሲ ማሻሻል ያስፈለገው ችግር ስላለበት፣ መጥፎ ስለሆነና አላሠራ ስላለ አይደለም፡፡ ፖሊሲው መከላከል ላይ መሠረት ያደረገ፣ እስከ ኅብረተሰቡ ድረስ የዘለቀና ኅብረተሰቡም በራሱ ጤናውን መጠበቅ የሚችልበትን አካሄድ ወይም አቅጣጫ ያስቀመጠ ነው፡፡

ይህ ዓይነቱን ፖሊሲ ለማሻሻል ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ከወቅቱ ሁኔታ ጋር እያሻሻሉ መሄድ ተገቢ መሆኑን በመረዳትና የበሽታዎችን ሒደታዊ ወይም ባህሪያዊ ለውጥ (ኢፒዲዩሞሎጂካል ትራንስፎርሜሽን) በመገንዘብ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ይህም ማለት በፊት ያልነበሩና አሁን እየመጡ ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ወይም ከኢኮኖሚ፣ ከዕድገትና ከተለያዩ ክስተቶች ጋር አብረው የሚመጡ የተለያዩ የጤና ችግሮች መኖራቸውን በማገናዘብ ነው፡፡

‹‹ሌላው ምክንያት አገሪቱ በየጊዜው ከፍተኛ የሆነ ዕድገት እያስመዘገበች ነው፡፡ በዚህም የተነሳ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ መቀላቀሏ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ የተለየ የጤና አገልግሎት ሊኖራት ይገባል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ከወዲሁ በፖሊሲ መልክ ማስቀመጥ ይገባታል፤›› ሲሉ ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

ከዚህም ሌላ አሁን እየተሠራበት ባለው ፖሊሲ ላይ የሚታዩት አንዳንድ የአፈጻጸም ክፍተችንም በመገምገም ፖሊሲውን ማሻሻል ተገቢ ሆኖ መገኘቱን፣ ከአቶ ኖህ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ፖሊሲውን ለማሻሻል የሚረዱ አንዳንድ የተለያዩ የምክክር ሥራዎች ከዚህ በፊት መከናወናቸው ተገልጿል፡፡ ከተከናወኑትም ሥራዎች መካከል አንደኛው ድሬዳዋ የተካሄደው 16ኛው ዓመታዊ የጤና ጉባዔ ነው፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት በዚህ ጉባዔ ላይ የጤና ፖሊሲው መሻሻል እንዳለበት የሚጠቁሙ ገንቢ ሐሳቦች እንደተንፀባረቁ አቶ ኖህ ገልጸዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አማካይነት ይህንን የማሻሻያ ሥራ የሚያካሂድ ቡድን እንደተቋቋመ፣ ቡድኑም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለውን ሥራ ማከናወን ከጀመረ ከአንድ ሳምንት በላይ እንደሆነው ተናግረዋል፡፡

ፖሊሲው በዝርዝር ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከል በየትኞቹ ላይ ነው የማሻሻያው ሥራ ያተኮረው? የየትኞቹ አገሮችስ ተሞክሮ ታይቷል? ተብሎ በሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ኖህ ሲመልሱ፣ ‹‹የማሻሻያው ሥራ የተጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የትኞቹ ቦታዎች ላይ ነው ትኩረት የሚሰጠው፣ ወዘተ የሚለውን አሁን ለመናገር ይከብዳል፡፡ በተረፈ አንድ የጤና ፖሊሲ ሲሻሻል የራሱ የሆነ አካሄድ እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን አካሄድ በመከተል የተለያዩ መረጃዎችንና መነሻዎችን (ቤንችማርክ) ልንጠቀምና ተሞክሮዎችን ልናይ እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ያለ አድልዎና ያለምንም ልዩነት የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ የመሆንና የአገልግሎቱን ደረጃ የማሳደግ መብት እንዳለው ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ መንግሥት ደግሞ ይህንን መብት የማስጠበቅ ቁርጠኛ የሆነ አቋም እንዳለው፣ በዚህም የተነሳ ፖሊሲው መንግሥት ቁርጠኝነቱን ወይም አቋሙን የሚገልጽበት ሰነድ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ