Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የነዳጅ ኩባንያዎችንና ማደያዎችን የትርፍ ህዳግ ሊያሻሽል ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንግድ ሚኒስቴር አክሲዮን ማኅበራትን እየተከታተልኩ ነው አለ

የነዳጅ ኩባንያዎችና ማደያዎች ከስምንት ዓመት በላይ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡት የነበረውን በነዳጅ ላይ የተጣለ ዝቅተኛ የትርፍ ህዳግ ይሻሻልልን ጥያቄ፣ በቅርቡ በአገሪቱ ተከስቶ ከነበረው የነዳጅ አቅርቦት ችግር በኋላ የመንግሥትን ጆሮ አግኝቶ የማሻሻያ ሥራ በመሠራት ላይ መሆኑ ታወቀ፡፡

የትርፍ ህዳጉን መንግሥት ለማሻሻል የወሰነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ በማሽቆልቆሉ ምክንያት መሆኑን፣ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ የ2007 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ጥር 21 ቀን 2007 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው ይህንን የተናገሩት፡፡

የፓርላማው የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ቀንሶ ሳለ፣ በቅርቡ በአዲስ አበባና በዋና ዋና የክልል ከተሞች የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለምን እንደተፈጠረና ችግሩ ወደፊት እንዳይደገም ንግድ ሚኒስቴር ምን እያደረገ እንደሆነ ማብራሪያ ጠይቆ ነበር፡፡

ሚኒስትሩ ለጥያቄው ማብራሪያ መስጠት የጀመሩት በነዳጅ የንግድ ዘርፍ በመንግሥትና በነዳጅ ኩባንያዎችና ማደያዎች መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት በማብራራት ነበር፡፡ በመንግሥትና በነዳጅ ንግድ ተዋናዮች መካከል በነበረው የንግድ ስምምነት መሠረት የዓለም የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር መንግሥት ድጐማ ሊያደርግና ሸክሙን ሊቀበል፣ የነዳጅ ዋጋ ሲቀንስ ደግሞ የነዳጅ ኩባንያዎች የሚገጥማቸውን የትርፍ መቀነስ ሊሸከሙት መሆኑንና በዚህም መሠረት ከአምስት ዓመታት በላይ ሲሠራ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ ላለፉት ዓመታት የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ ባለመስተዋሉ ችግሩ የነዳጅ ኩባንያዎችን እንዳልነካ፣ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ ኩባንያዎቹ በገጠማቸው የትርፍ ቅናሽ ደስተኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የትርፍ ህዳጋቸው በመንግሥት የሚወሰንና ከድሮም ጀምሮ ዝቅተኛ እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ነዳጅ አቅራቢው የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት በሊትር የሚያገኘው ትርፍ ስምንት ሳንቲም መሆኑን፣ የነዳጅ ኩባንያዎች ደግሞ በተመሳሳይ በሊትር ስድስት ሳንቲም እንዲሁም ነዳጅ ማደያዎች አራት ሳንቲም የትርፍ ህዳግ ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ኩባንያዎች ዋነኛ ትርፋቸውን የሚያገኙት ከነዳጅ ሳይሆን ከኢንዱስትሪ ዘይቶችና ቅባቶች መሆኑን፣ እስከቅርብ ጊዜ ድረስም በብቸኛ አስመጪነት በመንግሥት በተወሰነ 32 በመቶ የትርፍ ህዳግ መሠረት ሲያተርፉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ሁለት ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ ዘይት በአገር ውስጥ ማምረት በመጀመራቸውና ሌሎች አምስት ኩባንያዎችም በሒደት ውስጥ በመሆናቸው፣ የኢንዱስትሪ ዘይቶች ትርፍ በውድድሩ የተነሳ መቀነሱን ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ብቻ ከዚህ ምርት የነዳጅ ኩባንያዎች ያገኙት የነበረው 32 በመቶ ትርፍ ከ20 በመቶ በታች በመውረዱና በተመሳሳይ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ መደናገጣቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በነዳጅ ላይ የሚገጥማቸውን ኪሳራ ለማስወገድ ነዳጅ ከጂቡቲ ከማምጣታቸው በፊት የመንግሥትን የችርቻሮ ዋጋ ተመን በማዳመጥ፣ ተሽከርካሪዎችን ወደ ጂቡቲ እንደሚያሰማሩ መንግሥት መረዳቱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ እንዲታቀቡ ከመንገር በተጨማሪ በሥራ ላይ ያለውን ዝቅተኛ የትርፍ ህዳግ ማስተካከል አሁን ካለው የዓለም ገበያ ዋጋ አንፃር ተገቢ መሆኑን መንግሥት መገንዘቡን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ጥናት ተካሂዶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡንና በቅርቡም እንደሚወሰን ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ የትርፍ ህዳጉ በምን ያህል ከፍ ሊል እንደሚችልና ይህ በገበያው ላይ የሚኖረውን አንድምታ አልተናገሩም፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የነዳጅ ኩባንያዎችም ምን ያህል የትርፍ ህዳግ ሊያገኙ እንደሚችሉ አያውቁም፡፡ መንግሥት በጉዳዩ ላይ እየመከረ መሆኑን ግን መረጃው አላቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ የነዳጅ ሥርጭት እክል እንዳይኖርበት የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ቁጥር መጨመር እንደሚኖርበትና ማደያዎችም መስፋፋት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎት ከ15 እስከ 20 በመቶ በማደግ ላይ መሆኑንና ዋና ከተሞች በመስፋፋት ላይ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ነዳጅ ማደያዎች አንድ አካባቢ ላይ አተኩረው ከመሰባሰብ ይልቅ የከተሞችን መስፋፋት ማገናዘብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ያሉት ማደያዎች በቂ ባለመሆናቸውም፣ መንግሥት 40 የማደያዎች ግንባታ በዚህ ዓመት እንዲጀመር እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የአክሲዮን ማኅበሮች ሚና ጉልህ ቢሆንም፣ የአመራሮች ኪራይ ሰብሳቢነት ባለአክሲዮኖችን እያወዛገበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ችግር በኢትዮጵያ የአክሲዮን ማኅበራት ልማት ላይ መጥፎ አሻራ እንዳይጥል ሚኒስቴሩ የአክሲዮን ማኅበራትን የሚከታተል ዳይሬክቶሬት አቋቁሞ እየተከታተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ችግር ነበረባቸው ያሏቸው አክሲዮን ማኅበራት አራት ሲሆኑ ህብር ስኳር አክሲዮን ማኅበር፣ ጃካራንዳ አግሮ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር፣ ንብ ትራንስፖርትና አልፋ የትምህርትና ሥልጠና አክሲዮን ማኅበር ናቸው፡፡ የሁሉም አክሲዮን ማኅበራት ችግር በአመራሮቻቸው ላይ በሚሰነዘር የኪራይ ሰብሳቢነትና የግልጽነት ችግር መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ በማድረግና አመራሮቹን በጠቅላላ ጉባዔ በማስገምገምና በአዲስ እንዲተኩ በማድረግ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በመፍታት ወደ ሥራቸው እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ገና ለውጥ ያላመጣውና በርካታ የመንግሥት ኃላፊዎችን ጥረት እየጠየቀ ያለው የአክሰስ ሪል ስቴት ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአክሰስ ሪል ስቴት ላይ በአንድ በኩል ቤት ገዢዎች የሚያቀርቡት ገንዘባችን ይመለስልን ወይም ቤቱን አስረክቡን የሚል ጥያቄ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የባለአክሲዮኖች የሀብት ጥያቄ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የገዢ ተወካዮችን በአንድ በኩል በማደራጀት፣ የአክሲዮን አባላትንም እንደዚሁ በሌላ በኩል በማደራጀት በመንግሥት በኩል ከተደራጀው ቡድን ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እንደማስበው ችግሩን እንፈታዋለን፡፡ ይህ ካልሆነ በአገራችን የአክሲዮን ማኅበራት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ጉዳት ላይ ሊጥል ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች