Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየብሔራዊ ስታዲየም ዲዛይን ጨረታ የይገባኛል ክርክር ሰበር ሰሚ ችሎት ደረሰ

የብሔራዊ ስታዲየም ዲዛይን ጨረታ የይገባኛል ክርክር ሰበር ሰሚ ችሎት ደረሰ

ቀን:

የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ ለማስገንባት ላቀደው ብሔራዊ ስታዲየም የዲዛይን ጨረታ በ2006 ዓ.ም. የተጀመረው የሕግ ክርክር ሰበር ሰሚ ችሎት ደረሰ፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ተከሳሽ የሆነውን የስፖርት ኮሚሽንን ምላሽ ጠይቋል፡፡

ክርክሩ የተነሳው በጄዳው አማካሪ አርክቴክቶችና መሐንዲሶችና በፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን መካከል በፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ጄዳው አማካሪ አክርቴክቶችና መሐንዲሶች የስፖርት ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ ለማስገንባት ያቀደውን ብሔራዊ ስታዲየምና ስፖርት መንደር አርክቴክቸራል ዲዛይን ለመምረጥ፣ ዝርዝር ንድፍ እንዲዘጋጅና የውል አስተዳደርና ቁጥጥር ሥራዎችን ለማሠራት ፈልጎ ያወጣውን ጨረታ አሸንፎ የነበረ መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡

ይሁን እንጂ ተከሳሹ ስፖርት ኮሚሽን የካቲት 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ያወጣውን ጨረታ ወደ ጎን በመተው ከሳሽ አሸናፊ በሆነበት ጨረታ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በወጡ ተጫራቾች መካከል እንደገና ሁለተኛ ዙር ጨረታ መጥራቱ አግባብ አለመሆኑን ገልጾ፣ ለመንግሥት የግዥና ንብረት አስተዳደር ቅሬታ ሰሚ ቦርድ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት ማግኘቱንና ሁለተኛው ጨረታም እንዲቋረጥ መወሰኑን ይገልጻል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ቦርድ ውሳኔን ባለማክበር መጋቢት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. አውጥቶ በነበረው የጨረታ ሰነድ እንደ አዲስ ተጫራቾች የጨረታ ሰነድ ሞልቶ እንዲያቀርብ እንደጠየቀው በክሱ ገልጿል፡፡

አዲስ እንዲሞላ የተጠየቀው የጨረታ ሰነድ ውስጥ የተመለከቱት በሙሉ ከአዲስ ተጫራቾች ውስጥ አሸናፊን ለመምረጥ እንጂ ውድድሩን አሸንፎ ቴክኒካልና ፋይናንሺያል ፕሮፖዛል እንዲያቀርብ ለሚጠይቅ አማካሪ ድርጅት የሚቀርብ ሰነድ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ለይግባኝ ሰሚ ቦርዱ አቤቱታ ማቅረቡን የክስ ሰነዱ ያስረዳል፡፡ ይሁንና ከሳሽ ለቀረበው አዲስ ጨረታ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የቅሬታ ቦርዱ የስፖርት ኮሚሽንን ምላሽ ከመረመረ በኋላ ቅሬታ አቅራቢ ያሸነፈበትን ውድድር ወደ ጎን ብሎ በአዲስ ጨረታ መሳተፉ ሕገወጥ መሆኑን በመጥቀስ፣ የስፖርት ኮሚሽኑን አካሄድ እንዳፀናው ይገልጻል፡፡ በመሆኑም ስፖርት ኮሚሽን የፈጸመው ድርጊት ሕገወጥ መሆኑ በቅሬታ ሰሚ ቦርድ የተረጋገጠ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ሕገወጥ ድርጊቱን እንዲሽርለት ጠይቋል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስፖርት ኮሚሽንን ምላሽ እንዲሰጥ በጠየቀው መሠረት ኮሚሽኑ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በሰጠውም ምላሽ ከሳሽ አሸንፌያለሁ የሚለው በሞዴል ዲዛይን ደረጃ ያለውን የንድፍ ሥራ እንደሆነ፣ በዚህ ደረጃም ቢሆን ያሸነፈው እጅግ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቦ ሳይሆን ከነበሩ ተወዳዳሪዎች የተሻለ ውጤት በማምጣቱ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ሆኖም በዲዛይን ውድድር ዝክረ ተግባር እንደተገለጸው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝርዝር የዲዛይን ጥናት ሥራ ለመግባት በግዥ መመርያ መሠረት የቴክኒካል ግምገማ ውድድር ተብሎ የተጠቀሰው የመነሻ ነጥብ ማለፉን ስለሚጠይቅ መሆኑን ይገልጻል፡፡

በዚህ ማወዳደሪያ መሥፈርትም ከሳሽ ማሟላት ከሚጠበቅበት አነስተኛ የመነሻ ነጥብ በታች በመሆኑ ሥራውን ለመሥራት ብቃት እንደሌለው መረጋገጡን ይጠቅሳል፡፡ በመሆኑም ሁለተኛ ተወዳዳሪን ለመጥቀም አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዲገነዘብለትና ሕግን የተከተለ ሥራ መሥራቱን፣ ፍርድ ቤቱ ይህንን መከራከሪያ ባይቀበል እንኳ ጉዳዩ መታየት ያለበት በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አለመሆኑን ጠቅሷል፡፡

በምክንያትነት ያቀረበውም የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን እንደ አዲስ ተቀብሎ ማየቱ ቦርዱ በአዋጅ የተሰጠውን የሚፃረር መሆኑን የሚያመላክት መሆኑን ነው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጥር 29 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ ክሱ የቀረበው ይግባኝ ሰሚ ቦርዱ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ በመሆኑ፣ ከሳሽ በክስ መልክ አቤቱታቸውን ለመደበኛ ፍርድ ቤት ማቅረባቸው በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 14 (2) ሥር ‹‹በሕግ ለሌሎች አካላት የተሰጠውን የዳኝነት ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ›› በሚል የተደነገገውን የጣሰ አቀራረብ አለመሆኑን ጠቅሷል፡፡

በፌዴራል መንግሥት የግዥ አፈጻጸም መመርያ አንቀጽ 50 ሥር በግልጽ እንደተደነገገው ቦርዱ በሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ዕጩ ተወዳዳሪ ጉዳዩን አግባብ ላለው ፍርድ ቤት ሊያቀርብ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም አግባብ ያለው ፍርድ ቤት ተብሎ የተገለጸው የትኛውን መደበኛ ፍርድ ቤት እንደሆነ በግልጽ ያልተመለከተ በመሆኑ፣ የመጀመርያ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የመመልከት ሥልጣን እንዳለው ወስኗል፡፡

የካቲት 20 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ፍርድም ስፖርት ኮሚሽን ሁለተኛ ከወጣው ተወዳዳሪ ጋር እያደረገ ያለውን ግንኙነት እንዲያቋርጥና በመጀመርያው ጨረታ ከከሳሽ ጋር ሁለተኛና ሦስተኛ የወጡትን ድርጅቶች ቴክኒካልና ፋይናንሻል ፕሮፖዛል እንዲያቀርቡ እንዲያደርግ ወስኗል፡፡

በተጨማሪም ተከሳሽ ከሳሽ ቴክኒካልና ፋይናንሺያል ፕሮፖዛል ካቀረበ በኋላ የመንግሥትን ጥቅም በማይጎዳና ከሌሎች ተጫራቾች አንፃር ፍትሐዊ ጥቅም ለከሳሽ በማይሰጥ መልኩ ድርድር እንዲያደርግና ከሳሽ የሚያቀርበው ቴክኒካልና ፋይናንሻል ፕሮፖዛል ጥራትን መሠረት ባደረገ ሥልት ገምግሞ የሚገባውን ውጤት እንዲሰጠው ፍርድ ሰጥቷል፡፡

ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ላይ ቅር የተሰኘው ስፖርት ኮሚሽን በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም. ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሏል፡፡ በይግባኙ የሚፈልገውን ውጤት ለማግኘት እንዲረዳውም የመንግሥትን ጥቅም ለማስጠበቅ በማለት ፍትሕ ሚኒስቴር የባለሙያ ድጋፍ እንዲያደርግለት ጠይቋል፡፡ በዚህም መሠረት ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ባለሙያ መድቦ ይግባኙ መቀጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህም መሠረት የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የሌለው በመሆኑ የሰጠው ውሳኔ እንዲሻርለት የከፍተኛውን ፍርድ ቤት 4ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ጠይቋል፡፡ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለቱን ወገኖች አከራክሮ የመጀመርያው ፍርድ ቤት ጉዳዩን የመመልከት ሥልጣን የለውም ሲል ወስኗል፡፡

ከሳሽ ጄዳው አማካሪ በበኩሉ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይንም ከሳሽ ጄዳው አማካሪ አርክቴክቶችና መሐንዲሶች ለፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታ በቦርዱ ውሳኔ ላይ ቅሬታ ኖሮት እንዲታረምለት ሳይሆን፣ የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን እንደ አዲስ ተቀብሎ እንዲያይለት መሆኑን በመጥቀስ፣ ፍርድ ቤቱ ማየት እንደማይችልና ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ የሚነቀፍ አለመሆኑን ገልጿል፡፡

ከሳሹ ግን ይህንን ውሳኔ በመቃወም ለሰበር ሰሚ ችሎት ታኅሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ይግባኝ ብሏል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱም አቤቱታው ለሰበር ሰሚ መቅረብ የሚችል መሆኑን ጠቅሶ የስፖርት ኮሚሽንና ፍትሕ ሚኒስቴር ምላሽ እንዲሰጡ አዟል፡፡ በትዕዛዙ መሠረትም ሁለቱም አካላት ምላሻቸውን ጥር 19 እና 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ያስገቡ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ለየካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ከፍተኛው ፍርድ ቤትና ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሳኔ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የማየት ሥልጣን አለው የለውም የሚለው ላይ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ የፍሬ ነገር ክርክር አልተደረገበትም፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...