Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአምስት ዓመቱ ዕቅድ ለኤክስፖርት ዘርፍ የተጣለው ግብ እንደማይሳካ የንግድ ሚኒስትሩ ገለጹ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መጨረሻ ዓመት ማለትም በ2007 የበጀት ዓመት መጨረሻ፣ ከኤክስፖርት ዘርፍ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው የውጭ ምንዛሪ እንደማይሳካ የንግድ ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ የ2007 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው፣ በአምስት ዓመቱ ዕቅድ በኤክስፖርት ዘርፍ ይገኛል ተብሎ የተቀጠመው የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ መድረስ እንደማይቻል የገለጹት፡፡

በዕቅዱ መሠረት ከሁሉም የወጪ ንግድ ምርቶች በዕቅዱ መገባደጃ ማለትም በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 10.4 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን፣ በዚህም ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 2.5 ቢሊዮን ዶላር፣ ከግብርና ምርቶችና ሆርቲካልቸር ዘርፍን ጨምሮ ወደ 6.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ከማዕድን ዘርፍ አንድ ቢሊዮን ዶላር በድምሩ 10.4 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ግብ መጣሉን ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ሲጠናቀቅ ማግኘት የሚቻለው በአማካይ 3.25 ቢሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን ይህም በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዚሁም መሠረት የኤክስፖርት ዘርፉ የውጥኑን 31.25 በመቶ ብቻ እንደሚያሳካ ይጠበቃል፡፡

ዕቅዱ እውን እንዳይሆን ምክንያት ሆነዋል ካሏቸው መካከል በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ይጠበቁ የነበሩት የስኳር ፋብሪካዎች ተጠናቀው ወደ ኤክስፖርት ንግድ አለመግባታቸው አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ይገኛል ተብሎ የታቀደውን በሚፈለገው ደረጃ ማሳካት አለመቻሉ ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የግብዓት እጥረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከግብርና ምርቶች ጋር በተያያዘም (ሆርቲካልቸርን ሳይጨምር) ይገኛል ተብሎ ይጠበቅ ከነበረው 4.5 ቢሊዮን ዶላር በአሁኑ ወቅት ማሳካት የተቻለው 2.15 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጸው፣ የዚህ ግብ አለመሳካት ምክንያቱ አንዳንዴ የምርት አቅርቦት በመሳሳቱና ምርቱ ሲኖር ደግሞ የዓለም ገበያ በመቀነሱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ በእነዚህ ምክንያቶች በተቀመጠው ዕቅድ ላይ መድረስ አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡

በ2007 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ 1.98 ቢሊዮን ዶላር ከሁሉም የኤክስፖርት ምርቶች ለማግኘት ቢታቀድም፣ ማግኘት የተቻለው ግን 1.37 ቢሊዮን ዶላር ወይም 69.9 በመቶውን ብቻ ነው፡፡

ከግብርና ምርቶች 976 ሚሊዮን ዶላር በስድስት ወራት ውስጥ ለማግኘት ታቅዶ 913 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱ 93.5 በመቶ፣ በሆርቲካልቸር ዘርፍ 152.4 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታስቦ 113.9 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን፣ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 554.74 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 134.1 ሚሊዮን ዶላር ወይም 33.2 በመቶ መገኘቱን ሪፖርታቸው ያስረዳል፡፡

   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች