Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበምርጫ ቦርድ ውሳኔ የተቀናቃኞች ምላሽ

በምርጫ ቦርድ ውሳኔ የተቀናቃኞች ምላሽ

ቀን:

‹‹ምርጫ ቦርድ እከሌ ፕሬዚዳንት ይሁን ብሎ የመወሰን መብትም ሥልጣንም የለውም›› አቶ ማሙሸት አማረ

‹‹መኢአድን በተመለከተ የተላለፈው እውነተኛ ውሳኔ ነው›› አቶ አበባው መሐሪ

‹‹በመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት ላይ ፖለቲካዊ ውሳኔ ተወስኗል›› አቶ አሥራት አብረሃ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ትክክለኛና ሕጉን ያገናዘበ ነው›› አቶ ትዕግሥቱ አወሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) እና በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ላይ የመጨረሻ ያለውን ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ቦርዱ ይህን ውሳኔ ያስታወቀው የዚያኑ ዕለት የቦርዱ ሰብሳቢ በሚኒስትር ማዕረግ ፕሮፌሰር መርጋ በቃናና የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፌሳ በሒልተን ሆቴል በሰጡት መግለጫ ነው፡፡

በዚህም መሠረት አንድነትን በተመለከተ የእነ አቶ ትዕግሥቱ አወሉ ቡድን፣ መኢአድን በተመለከተ ደግሞ የእነ አቶ አበባው መሐሪ ቡድን ፓርቲዎቹን በመምራት ወደ ምርጫ እንዲገቡ በአንድ ድምፅ ወስኗል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ቦርዱ አንድነትንና መኢአድን በመምራት ላይ የነበሩት አቶ በላይ ፍቃዱና አቶ ማሙሸት አማረ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና እንዳልሰጣቸው አስታውቋል፡፡

አቶ ማሙሸት አማረ፣ ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ ምርጫ ቦርዱ እከሌ ፕሬዚዳንት ይሁን ብሎ የመወሰን ሥልጣንም ሆነ መብት የለውም፡፡ ፓርቲውን ሊያስተዳድር ይችላል የሚለውን አካል የመምረጥና የመሾም ሥልጣን ያለው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ናቸው፤›› በማለት በምርጫ ቦርድ የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ለሪፖርተር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ የ2005 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ እንደማይቀበል ለአቶ አበባው መሐሪ ከአሥር ጊዜያት በላይ ደብዳቤ ጽፎ አሳውቆ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ማሙሸት፣ ‹‹ምልዓተ ጉባዔ ያልተሟላበት ምርጫ አድርገሃል ብሎ ያለውን ግለሰብ መልሶ ዛሬ ሊቀበል የሚችልበት ምን ዓይነት የሕግ አግባብ ተገኝቶ ነው?›› በማለት ውሳኔው አሳዛኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አቶ ማሙሸት የቦርዱ ውሳኔ እርስ በእርሱ የሚጋጭና የሚቃረን ነው ብለው፣ ለዚህም እንደመከራከሪያ የሚያቀርቡት ነጥብ፣ ‹‹ቦርዱ እያለ ያለው ሁለት የተምታታ ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል የጥቅምት 2007 ዓ.ም. የጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርትን አቶ አበባው አስገብቶልኛል ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የ2005 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ አፅድቄያለሁ ይላል፡፡ ስለዚህ የትኛውን እንዳፀደቀው የሚገርም ነው፤›› በማለት መገረማቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ አበባው መሐሪ በበኩላቸው ከምርጫ ቦርድ ውሳኔ በተቃራኒው ለሪፖርተር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ምንም እንኳን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ አቶ አበባው የተመረጡበት የ2005 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ውጤት ዕውቅና እንዲያገኝ ተወስኗል ቢልም የአቶ አበባው ግን፣ ‹‹መጀመሪያ ሐምሌ 14 ቀን 2005 ዓ.ም. የተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ምልዓተ ጉባዔ አልተሟላም የሚል የነበረ ሲሆን፣ ምልዓተ ጉባዔ አሟሉ የሚል ደብዳቤ ጽፎልን ነበር፡፡ ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. የተደረገው ጠቅላላ ጉባዔም ምልዓተ ጉባዔ ለማሟላት ነበር፡፡ ስለዚህ በዚያ ዕለት የቦርዱ ኃላፊዎች በተገኙበት 333 የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ተሰብስበው ሁሉንም ውሳኔ ያካሄዱበት ሪፖርት ለምርጫ ቦርድ ገብቷል፡፡ ስለዚህ ውሳኔው የተንተራሰው በጥቅምቱ ጠቅላላ ጉባዔ እንጂ በመጀመሪያው ላይ አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

አቶ አበባው፣ ‹‹ውሳኔው በእውነት እውነተኛ ነው›› በማለት ውሳኔውን መቀበላቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ለቦርዱ ውሳኔ እውነተኛነት የሚሰጡት ምክንያት ደግሞ፣ ‹‹ችግሩ ያፈጠጠና ሕግን የጣሰ ስለነበር ሕጉን ተጠቅመው የወሰኑት ውሳኔ ትክክል በመሆኑ ነው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አቶ አበባው፣ ‹‹ዋነኛው ነገር ፓርቲው በሕይወት መቆየቱ ነው፡፡ ፓርቲውን ለትውልድ ማስተላለፋችን ወሳኙ እርሱ ነው፡፡ ባልተፈለገ ሁኔታ ፓርቲው ይዘጋል ወይም መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ይወድቃል ብለን ሥጋት ውስጥ ነበርን፡፡ አሁን ግን ፓርቲው ተርፏል፤›› በማለት አክለው ገልጸዋል፡፡

አቶ ማሙሸት ግን የቦርዱ ውሳኔ ‹‹ምንም መረጃ ሳይኖረው፣ ፓርቲው ሁለት ጊዜ ያካሄዳቸውን ጠቅላላ ጉባዔዎች ውጤት ሳይመረምርና ሳያይ በአየር ላይ ተለጣፊ የሆነ አንድ ድርጅትና አንድ ግለሰብ መርጧል ማለት ነው፤›› በማለት ውሳኔው በፓርቲው ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ ተጠባባቂ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሥራት አብረሃ በበኩላቸው፣ ‹‹ውሳኔው በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ላይ የተወሰደ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከቦርዱ ውሳኔ በኋላ ባለፈው ዓርብ ከምሳ ሰዓት ጀምሮ የፓርቲው ጽሕፈት ቤት በፖሊስ መከበቡንም አቶ አስራት አስረድተዋል፡፡ ‹‹ምንም የተነገረን ነገር ሳይኖርና ደብዳቤም ሆነ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይኖር የፓርቲውን ጽሕፈት ቤት የፖሊስ ኃይል ተቆጣጥሮታል፤›› ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

የቦርዱን ውሳኔ በተመለከተ ፓርቲው ስብሰባ ማድረጉን አቶ አስራት አስታውቀው፣ ‹‹በዚህም መሠረት ፓርቲው በገዥው ፓርቲ ተዘጋጅቶ እየመጣ ያለውንና የአንድነት አመራር ነኝ የሚለውን አካል፣ ማንኛውም የአንድነት አባልና ደጋፊ ትብብር እንዲነፍገውና አሁን አመራር ነኝ ከሚለው አካል ጋር ምንም ዓይነት ትብብር እንዳያደርግ ተወስኗል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስደውና የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ምንም ይሁን የፓርቲው አባላት ባሉበት መዋቅር ፀንተው እንዲቆዩ መወሰኑንም አቶ አሥራት አስረድተዋል፡፡

‹‹አሁን በቦርዱ በተሰጠው ውሳኔ መሠረት አንድነት ሌላ አዲስ ፓርቲ ለመፍጠርም ሆነ ሌላ ፓርቲ ውስጥ መቀላቀል ትርጉም የሌለው ድካም ነው የሚሆነው በሚል ነው የዘጋው፡፡ ታሪካዊ በሆነ አካሄድ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዳይኖር ሥርዓቱ እየሠራ ነው፤›› ሲሉም ውሳኔው አጠቃላይ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ላይ ጥላ ማጥላቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹የቦርዱ ውሳኔ ትክክለኛና ሕጉን ያገናዘበ ነው›› በማለት አቶ ትዕግሥቱ አወሉ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ለቦርዱ ውሳኔ ትክክለኛነት የሚያቀርቡት ምክንያት ደግሞ የሁለቱንም ቡድኖች ሕጋዊ አግባብነት መርምሮ ውሳኔ መስጠቱን ነው፡፡ ‹‹ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ለእኛ መስጠቱ ወይም ደግሞ የእኔን ሊቀመንበርነት ዕውቅና መስጠቱ የሄድኩበት መንገድ ሕጋዊ መሆኑን የሚያሳይና ውሳኔውም ትክክለኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...