‹‹ኢትዮጵያ ሁሌም የአፍሪካ ባለውለታ ናት›› አዲሱ የኅብረቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ
በድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት የኢትዮ ኤርትራ ድንበር እንዲካለል በኤርትራ የቀረበው ጥያቄ፣ በአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ውድቅ ተደረገ፡፡
ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ሲካሄድ በሰነበተው የአፍሪካ ኅብረት 24ኛ መደበኛ የመሪዎች ጉባዔ መጠናቀቂያ ላይ የኤርትራ መንግሥት አጀንዳ አስይዞ ነበር፡፡ በኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር እንዲካለልና የኢትዮጵያ ወታደሮችም በኃይል ከያዙት የኤርትራ ግዛት እንዲለቁ ኤርትራ ጠይቃለች፡፡ በአፍሪካ ኅብረት የኤርትራ ተወካዮች ጥያቄውን በአምባሳደር አርዓያ ደስታና በአቶ ቢኒያም በርሄ አማካይነት ስታቀርብ፣ ከኢትዮጵያ ተወካዮች ምላሽ ተሰጥቶበት መጠነኛ ውይይት እንደተደረገበት፣ ስብሰባው ከተገኙት ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያን መንግሥት ወክለው በዚሁ በዝግ በተካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ማጠናቀቂያ ላይ የተገኙት ምንጮች እንዳስረዱት፣ ኤርትራ ቀድማ አጀንዳ አስይዛ ያነሳችው ጥያቄ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን ነው፡፡ በተጨማሪም ድንበሩ እንዲከለልና የኢትዮጵያ ወታደሮች የኤርትራን ግዛት ለቀው ኤርትራ በሕግ የተሰጣትን መሬት እንድታገኝ ኅብረቱ ጫና እንዲፈጥር ጠይቃለች፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አምባሳደር ብርሃነ የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም ያብራሩ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ‹‹የድንበር ችግሩን ለመፍታትና በሁለቱም አገሮች መካከል ሰላም ለመፍጠር አስመራም ድረስ በመሄድ ለመደራደር ዝግጁ ነኝ፤›› ማለታቸውን አስምረው፣ መንግሥታቸው ዓለም አቀፍ ሕግን ለማክበር ምን ጊዜም ዝግጁ ቢሆንም የድንበር ውሳኔው ግን በውይይትና በድርድር ለመቋጨት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ በመከራከሪያ ሐሳባቸው፣ ‹‹ችግሩ ዓለም አቀፍ ሕግን ያለማክበር ሳይሆን የኤርትራ ሰላም አለመፈለግ ነው፡፡ የአስመራ መንግሥት አካባቢውን ለማተራመስ የሽብር አጀንዳ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፤›› ማለታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ አምባሳደሩ በማከልም የአፍሪካ ኅብረት ቀደም ሲል በኤርትራ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ አለመነሳቱን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤትም ሁለት ጊዜ የጣለው ማዕቀብ ያልተነሳ መሆኑ፣ የኤርትራ መንግሥት ከአሸባሪነት ባህሪው ያልተላቀቀ መሆኑን እንደሚያሳይ ማስረዳታቸው ታውቋል፡፡
በዚሁ 24ኛ መደበኛ የኅብረቱ ጉባዔ ላይ የኅብረቱ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡ የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያን አቋም በመደገፍ ሁለቱም አገሮች ችግራቸው መፍታት ያለባቸው በውይይትና በመተሳሰብ መሆን እንዳለበት፣ እንዲሁም የነጮችን ይሁንታ መጠበቅ እንደሌለባቸው ገልጸው፣ ለኅብረቱ የቀረበው ጥያቄ አግባብነት የሌለው መሆኑን መናገራቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
‹‹ጉዳያችሁን ለሦስተኛ ወገን አሳልፋችሁ አትስጡ፡፡ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የሰላም ሐሳብ በአዎንታ እንቀበለዋለን፡፡ መፍትሔውም እሱ ብቻ ነው፤›› በማለት ያቀረቡት ሐሳብ በመሪዎች ሙሉ ድጋፍና ከፍተኛ ጭብጨባ ተቀባይነት አግኝቶ ጉዳዩ መቋጨቱንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ውዝግብ ይፈታል ተብሎ የተቋቋመው ዘሔግ የሚገኘው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ፍርደ ገምድል ነው በማለት በኢትዮጵያ ተቀባይነት ያላገኘ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቀረበው ባለአምስት ነጥብ የሰላም ሐሳብ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተቀባይነት አግኝቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ዜና በቅርቡ የኬንያ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎችንና አማፂያንን በዘር ማጥፋት ወንጀል እየከሰሰ ወደ ሕግ በማቅረብ ላይ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤትን (ICC) በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ በኅብረቱ የፀና አቋም እንዲወስድበት ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የሐሳቡ ይዘት ይኼው ዓለም አቀፍ ተቋም በአፍሪካ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት በጋራ እንዲወገዝ፣ ወንጀለኛ ሆነው የተገኙ የአፍሪካ መሪዎችም በአፍሪካ ምድር እንዲዳኙና አፍሪካዊ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም የሚል ነበር፡፡
አጀንዳውን በተመለከተ በኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ፍርድ ቤቱን በተመለከተ ዝርዝር ችግር የቀረበ ሲሆን፣ ኅብረቱ በአይሲሲ ላይ ጠንከር ያለ አቋም ለመያዝ በኢትዮጵያ የቀረበው ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝቶ መተላለፉን ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡
ይህንን ሐሳብ በተመለከተ አዲሱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ ‹‹ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የአፍሪካ ባለውለታ ናት፤›› በማለት እሳቸው ራሳቸውንና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ የነፃነት ታጋዮች የሠለጠኑትና ድጋፍ ያገኙት በኢትዮጵያ እንደነበር ምስክራቸውን ሰጥተው፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የምታደርገው ተጋድሎ ሁሌም መታወስ እንዳለበት አውስተዋል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የቀረበውን ሐሳብም በተመለከተ፣ ‹‹ወንጀለኛ ነጮችን የማይጠይቅ፣ ጥቁር አፍሪካውያን ብቻ እያሳሳደደ ለፍርድ ለሚያቀርብ ፍርድ ቤት ዕውቅና መስጠት የለብንም፡፡ አፍሪካውያን ቢያጠፉም በአፍሪካ ምድር ብቻ መዳኘት አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡ የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽና የእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር በኢራቅ ፈጽመውታል ላሉት ወንጀል በፍርድ ቤቱ አለመጠየቃቸውንም እንደማሳያ እንዳቀረቡ ምንጮች አክለው ገልጸዋል፡፡