የሞጆ ደረቅ ወደብ አሁን ከገጠመው መጋዘን የመሆን ሥጋት ለማውጣትና የሎጂስቲክስ ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራ የሎጂስቲክስ ካውንስል ተቋቋመ፡፡
ሚኒስትሩ የሚመሩት ምክር ቤት ውስጥ በአባልነት የሚገኙት የትራንስፖርት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋሙ ማለትም የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ብሔራዊ ባንክና ንግድ ሚኒስቴር መሆናቸውን የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ገልጸዋል፡፡
አቶ ወርቅነህ ይህንን የተናገሩት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ባለፈው ማክሰኞ ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡
የምክር ቤቱ አባላት የሞጆ ደረቅ ወደብ በአሁኑ ወቅት ወደ መጋዘንነት እየተቀየረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አስመጪ ባለሀብቶችም ሆኑ የመንግሥት ተቋማት ንብረቶቻቸውን ከደረቅ ወደብ አለማውጣታቸው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ምን እያደረገ እንደሆነ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
‹‹ያለውን ችግር ለዚህ ምክር ቤት ዘርዝሬ አልጨርሰውም፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹አንዳንዱ ባለሀብት ያስመጣው ዕቃ በወቅቱ በገበያው የማይፈለግ ከሆነ ደረቅ ወደብ ጥሎት ይሄዳል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ የባንክ ችግር አለበት፡፡ በእርግጥ የእኛ ተቋማት የሚፈጥሩትም ያለመቀናጀት ችግር አስተዋጽኦ አለው፤›› በማለት ምክንያት ከሚሉቸው ዝርዝሮች ውስጥ ጥቂቶቹን ጠቅሰዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሲባልም የሎጂስቲክስ ምክር ቤቱ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ ችግሩን ለመቅረፍ እንሠራለን፡፡ በእርግጠኝነትም ይሳካልናል፤›› ብለዋል ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ፡፡
ችግሮቹ ተቀርፈው አሁንም ንብረቶችን የማያነሱ ካሉ በጉምሩክ ሕግ መሠረት ለመውረስ እንደሚገደዱ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ1,500 በላይ ኮንቴይነሮች በወደቡ መቆየት ከሚችሉበት የ45 ቀናት ጊዜ በላይ ሁለት ዓመት ያህል የሞላቸው እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡